የፅዳት ሥራ ከግል አሠሪዎች ተወስዶ ለኢሕአዴጋዊ ወጣት አሠሪዎች ሲሰጥ፣ ኢሕአዴጋዊ ባለመሆናቸው ነባር (መሥራች) አሠሪዎች ከሥራ ውጪ ተደርገው ዕርዳታ እስከ መለመን የደረሱበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ቆሻሻ የማንሳቱን ቀጥተኛ ሥራ ፊትም አሁንም የሚሠሩት ግን የመጨረሻ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ከልታሞች ናቸው፡፡ ሒደቱንና አሠራሩ ብልጥ ለብልጥ የሚባልበት ዓይነት ነው፡፡ ተመልማይ አባልነቱን ለጥቅሙ መሣሪያ ማድረግ እንደሚሻ ሁሉ፣ መልማዩም ድርጅት ኢሕአዴጋዊነትን በተግባር አሳይ ይላል፡፡ በዚህም ተመልማይ ቢወድም ቢጠላም የፖለቲካ ሎሌነት ሥራው የሚያጋጭና የሚያስተዛዝብ ተግባር ውስጥ እየነከረው በዚያው እንዲቀልጥ ያደርገዋል፡፡ VIA- reporter Amharic

አንባቢ በሲሳይ ገላው

የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት ህልውና የየትኛውም ፓርቲ ይዞታ ያልሆነ ዓምደ መንግሥት ከማደራጀት ተነጥሎ አይታይም፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ መውጫ የሌለው ጎሬ ውስጥ የተቀረቀረው ገና ኢሕአዴግ የመናጆ ኮንፈረንስና ፓርላማ አደራጅቶ፣ የራሱን ሠራዊት የሽግግር መንግሥት የመከላከያ ኃይል ማድረግ በቻለ ጊዜ ነው፡፡

በነባሩ የጦርና የፀጥታ መዋቅር ላይ ኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት ሆኜ ልቀመጥ ቢል የቂል ሥራ ይሆንበት እንደነበር እውነት ነው፡፡ ይህ እውነት መሆኑ ግን ነባሩን አፍርሶ የራሱን ፀጥታና ሠራዊት መንግሥታዊ ማድረጉን ትክክል አያደርገውም፡፡ የሰኔው ኮንፈረንስና የተቋቋመው ፓርላማ ሁሉን ቡድኖች ያካተተ ሊሆን ይችል እንደነበር ሁሉ፣ የአገሪቱ የፀጥታና የመከላከያ ኃይል እንደ አዲስ መደራጀት ከአንድ ቡድን ፍላጎት የተላቀቀ አገራዊ አደራ ሆኖ ሊካሄድ ይችል ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን ጠንክሮ የሚታገል አልነበረም፡፡ የኢሕአዴግም ፍላጎት አልነበረም፡፡

በዚህ መነሻ ምክንያትና ከዚያ ወዲህ ባሉት የ27 ዓመታት መከላከያዊ ልማትና ዕድገት እንዳስመዘገቡት፣ ዛሬ ከቡድን ቁጥጥር ውጪ ስለሆነ ምንም ዓይነት መንግሥታዊ አውታር መናገር አይቻልም፡፡  

ከመከላከያና ከፀጥታ ውጪ ያሉት መንግሥታዊ አውታራትም በጠቅላላ በኢሕአዴግና ‹‹አጋር›› ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች የተዋጡ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በድርጅታዊ ሰንሰለት፣ በመንግሥታዊ ስብሰባና በሕዝብ መገናኛ የሚናኝ የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››ን (የኢሕአዴግን ገዥነት) መተኪያ የለሽ የሚያደርግ፣ ተቃዋሚዎችን ‹‹ቀልባሽ፣ ሕገ መንግሥት አፍራሽ››፣ የሰላምና የሕዝብ ፀር የሚደርግ አመለካከትና ፕሮፓጋንዳ አብሮ ተዘርግቷል፡፡ ይህም ሥራ የማግኘትና በሥራ የመቆየት፣ የዕድገትና የሹመት፣ እንዲሁም ሌሎች ጥቅሞችንና ዕድሎችን ከፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት ጋር ያጣጠበቀና ሁሉንም (ነባሩንም፣ አዲስ መጡንም፣ ገና በትምህርትና በሥልጠና ላይ ያለውን) በሚሊዮኖች ቁጥር እያጥለቀለቀ ያለ ክንዋኔ ነው፡፡ ይህ ክንዋኔ ከፅዳት ሥራ እስከ ሕዋ ሳይንስ ድረስ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፡፡

ለምሳሌ የአዲስ አበባ የፅዳት ሥራ ከግል አሠሪዎች ተወስዶ ለኢሕአዴጋዊ ወጣት አሠሪዎች ሲሰጥ፣ ኢሕአዴጋዊ ባለመሆናቸው ነባር (መሥራች) አሠሪዎች ከሥራ ውጪ ተደርገው ዕርዳታ እስከ መለመን የደረሱበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ቆሻሻ የማንሳቱን ቀጥተኛ ሥራ ፊትም አሁንም የሚሠሩት ግን የመጨረሻ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ከልታሞች ናቸው፡፡ ሒደቱንና አሠራሩ ብልጥ ለብልጥ የሚባልበት ዓይነት ነው፡፡ ተመልማይ አባልነቱን ለጥቅሙ መሣሪያ ማድረግ እንደሚሻ ሁሉ፣ መልማዩም ድርጅት ኢሕአዴጋዊነትን በተግባር አሳይ ይላል፡፡ በዚህም ተመልማይ ቢወድም ቢጠላም የፖለቲካ ሎሌነት ሥራው የሚያጋጭና የሚያስተዛዝብ ተግባር ውስጥ እየነከረው በዚያው እንዲቀልጥ ያደርገዋል፡፡

በዚህና በሌሎችም ምክንያት ኢሕአዴግ ከእነ ጭፍሮቹ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ መንግሥትነትን ‹‹የሚሾም››፣ ‹‹የሚሸለም›› ፓርቲ ከመሆን ባለፈ የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት (State) ሆኖ ተደራጅቷል፡፡ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግንም ከመውደቅ የሚጠብቅ ኢሕአዴጋዊ ሠራዊት ነው፡፡ የአገሪቱ የደኅንነት አውታርም የአገሪቱን ደኅንነት እንደሚጠብቅ ሁሉ፣ ለኢሕአዴግም ይሠራል፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ጠላት/ፀረ ሰላም›› የሚል ስም የሚሰጣቸውን ተቃዋሚዎችም ‹‹ይጠብቃል››፣ ይጠባበቃል፡፡

ኢሕአዴግ ፍትሕን አሰፍናለሁ፣ ዴሞክራሲን እገነባለሁ የሚለው ደግሞ በዚህ እውነታ ላይ ነው፡፡ በዚህ እውነት ላይ እንኳን ፍትሕና ዴሞክራሲ ሕግን ማስከበር እንኳን የማይቻል ነው፡፡ የማይችልባቸውን ምክንያቶች በምሳሌነት ሳሳይ፡፡

የኢሕአዴግ ገዥ ቡድን መንግሥታዊውን የጉልበት ኃይል (ወታደራዊና የፀጥታ አውታር) ታማኝ መሣሪያው አድርጎ በማነፁ በማንኛውም ባለሥልጣን ይሁን ተራ ሰው ላይ፣ በማንኛውም ሸሪክም ይሁን ተቃዋሚ ቡድን ላይና በየትኛውም አካባቢያዊ መንግሥት ላይ ከሕግ ውጪና ከሕግ በላይ አዛዥ ናዛዥ የመሆን ጉልበት ይሰጠዋል፡፡ ይህ ባለጉልበትነቱ ደግሞ በማናቸውም ወገን ላይ የሚያሳድረው ፍርኃት የሕግ የበላይነትን፣ ነፃ ዳኝነትና ዴሞክራሲን ይጣላል፡፡

ኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲዎችንና መንግሥታዊ ቢሮክራሲውን እስከ መጨረሻ የከተማና የገጠር ቀበሌ መዋቅር ድረስ፣ እንዲሁም (የወጣት የሴት የመምህራን፣ ወዘተ) የሲቪክ ማኅበራት ሥጋና ደም አድርጎ የተዘረጋ፣ ተማሪውን፣ ገበሬውን፣ ሴቱን፣ የመንግሥት ሠራተኛውን፣ ሥራ አጡን፣ ነጋዴውን ሁሉ የተበተበ ድርጅት ነው፡፡ ትብትቡ ተቃዋሚዎች እንደ ልብ ሕዝብ ዘንድ እንዳይደርሱ፣ ድምፃቸው እንዳይሰማና ማስፈራሪያ እንዲሆኑ በግልጽና በሥውር ይሠራል፡፡ መንግሥታዊ የሥራ ዕድገት፣ የምግብ ለሥራ፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ መብቶችን ሁሉ በመቀጣጫነትና በመደለያነት መጠቀም፣ የሐሰት መረጃ የማቀናበር ወይም ማሳበቢያ የሚሆን ጥፋት ፈልጎ ወይም ወደ ጥፋት መርቶና አጥምዶ መወንጀል/ማሰር፣ በሕግ ሽፋን ሊጠመድ ያልቻለውን ወይም የዚያ ዓይነት ልፋት የማያስፈልገውን በሥውር ሥራ ፀጥ እንዲል ወይም በርግጎ እንዲጠፋ የማድረጉ ሥራ ሁሉ የሚከናወነው በዚህ የአመለካከትና የመዋቅር መረብ ውስጥ ነው፡፡

የኢሕአዴግ አፋኝ አመለካከት (ለተገኘው ድል ሁሉ መሠረት እኔ ነኝ፣ ሕዝባዊና ልማታዊ እኔ ብቻ ነኝ፣ መካከለኛ መደብ እስኪበዛ የእኔ በሥልጣን መቆየት ግድ ነው፡፡ የእኔ መውረድ የአገሪቱ መበጥበጥና የድሮው ሥርዓት መመለስ ነው፣ ከተቃዋሚዎች ጋር የጋራ መግባባትና አብሮ መሥራት የማይቻል ነው ማለቱ)፣ ድርጅታዊ ሥራና የፍርኃት ጥላ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተዘርግቶ እያለ፣ ገለልተኛ የሆነ ፖሊስ፣ ዳኝነትና የምርጫ አስፈጻሚነት ይኖራል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚገፈፍበትን መንገድ በመፈለግ ለዚያ በመታገል ፈንታ የዳኛውን፣ የፖሊስን፣ የምርጫ አስፈጻሚውን የፓርቲ አባል በመሆንና ባለመሆን ላይ ገለልተኛነትን ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ ተሳስቶ ከማሳሳት በስተቀር ከንቱ ልፋት ነው፡፡ ገዥው ቡድን ከነጭፍራው በምርጫ አስፈጻሚዎች ውስጥ አንድም የፓርቲ አባል የለም ማስረጃ ማቅረብ የሚችል ካለ ወዲያውኑ ዕርማት ይካሄዳል ቢል፣ ከዚያም አልፎ ‹‹በሕግ የበላይነት፣ በዳኝነት ነፃነት፣ በፍርድ ቤትና በፖሊስ ሥራ፣ በምርጫ አስፈጻሚነት ላይ ያሉ ችግሮች በአመዛኙ የአመለካከት ናቸው›› እየተባለ እንከን የሌለው ሥልጠና ቢሰጥ፣ ከመልክ ሥራ በቀር የሚቀየር ነገር አይኖርም፡፡ ሥልጠና ሰጪውም ሆነ ተሰጪው ይህንን ያውቁታል፡፡ እውነት የመሰለው አዲስ ገብ ቢኖር ትንሽ ቆይቶ ከቅዠቱ ይወጣል፡፡

ዳኞች በሙያዊ ጥፋትና በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውሳኔ የሚወገዱ ካልሆነ በቀር በማንም ሊባረሩ አለመቻላቸው፣ የዳኝነት ነፃነትን ያረጋግጣል የሚባለውም ወግ ተበድሮ ማጭበርበር ነው፡፡ ይህ የሚሠራውና ዕውን የሚሆነው ገዥው ቡድን የመንግሥት ዓምድ ባልሆነበት (በምርጫ ወጪና ወራጅ በሆነበት) ሥርዓት ነው፡፡ እንደ ኢሕአዴግ ያለ ባለኃይልና ባለጉልበት ግን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ቀዳዳ አይጠበውም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እንደሆነውም፣ የወይዘሪት ብርቱካን ዓይነት ለማንም ፍላጎት አላጎበድድም ብላ በሕግና በህሊና ተመርታ ዳኝነት የማየትን ጀግንነት ደፍራ የሞከረች ‹‹ወፈፌ›› ዳኛ ካጋጠመውም ማሸነፊያ አያጣም፡፡ ሞልተውታል፡፡

የእንጀራ ገመድን ተመርኩዞ የተስፋፋውና እየተስፋፋ ያለው ኢሕአዴጋዊ የፖለቲካ ሎሌነት እንኳን መንግሥታዊ አውታሩን ተቃዋሚ የሚባሉትን ሁሉ በስርገት ተብትቦ የሚያምስ፣ በተለይም ምርጫ ዋዜማ ላይ መከፋፈልና ማስፈንገጥን የፖለቲካ ዕርባና ለማሳጣት ይጠቀምባቸዋል፡፡

ከፌዴራል እስከ ወረዳ ሥልጣን ድረስ ምንም ዓይነት የድምፅ ማጭበርበር ሳይደረግ ኢሕዴግና አጋሮቹ ቢያሸንፉ እንኳን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ማለትም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት ሆኖ በተደራጀበት፣ በየተቋማቱና በየማኅበራቱ በየ‹‹አምስት ለአንዱ››፣ በ‹‹የቤተሰብ ፖሊስ›› እንደ ሠርዶ ውስጥ ለውስጥ ተሠራጭቶ ሥርና ጅማት ሆኖ በተንሠራፋበት ሁኔታ ምርጫና የሕዝብ ፍላጎት እንደተለያዩ ይኖራሉ፡፡ የዚህ ምክንያት ኢሕአዴግ ተደጋግሞ እንደተጠቀሰው ጠቅላላ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የተቆጣጠረና ተቃዋሚዎችንም ለመናጆ እንደሚያገለግሉ ያህል ቀስፎ በመያዙ ነው፡፡ ሕዝብ ለኢሕአዴግ የሚሰጠው ድምፅ በአማራጮች ላይ ከተደረገ የፍላጎት ውድድር የፈለቀ ከመሆን ይልቅ የኑሮ ግዴታን የማሟላት ግዳጅ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም የሕዝቡን ድምፅ ነፃ ድምፅ ተብሎ ከመቆጠር ይከላከለዋል፡፡ ተመራጩንም ሕጋዊነት (Legitimacy) ይነፍገዋል፡፡

ከትጥቅ ትግል አንስቶ የኢትዮጵያን ትግል በትክክለኛው አቅጣጫ የመራሁት እኔ ነኝ የሚለው፣ አውራ ፓርቲ የሚባል ነገርንም ያስተዋወቀው ኢሕአዴግ ‹‹በምርጫ›› የሚያሸንፈው ለሁሉም እኩልና ነፃ ባልሆነ ሜዳ ላይ ‹‹እየተወዳደረ›› ነው፡፡ መሪነቱም፣ አውራነቱም፣ በምርጫ አሸናፊነቱም በመዋቅርና ‹‹በእኖር ብዬ›› ገመድ መያዝን እንጂ እውነተኛ የሕዝብ ድጋፍን የሚያሳይና የሚናገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሄደ ብሎ መከራከር ይቅርና ነፃና ፍትሐዊ የሚሉትን ቃላት ለአፍ ለመጠቀም የሚያበቃ ፍጥርጥር የለም፡፡ የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዳኛው ከኢሕአዴግ ሆኖ ገዥው ፓርቲ በሰፊው ሜዳ ሌሎች በቀጭን ገመድ ላይ ተሽቀዳደሙ የሚል ዓይነት ነው፡፡ በራሳቸው በፓርቲዎችም ውስጥ ቢሆን የተሻለ ሐሳብንና የተሻለ ችሎታን በክርክር የማንጠር ወይም በድምፅ የመለየት እስትንፋስ የፈጠረባቸው አይመስልም፡፡ ይህ ለገዥውም ለሌሎችም ፓርቲዎች ይሠራል፡፡

በየትኛውም ዴሞክራሲ በአንድ ፓርቲና በመስመሩ የመመራት ጉዳይ ከሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ የመርታትና ሰፊ ተቀባይነት የማግኘት፣ ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ የማረጋገጥ መሆን አለበት፡፡ የገዥው ፓርቲ የእያንዳንዱ አባል ድርጅቶች ችግርም ይኼው ነው፡፡

የዚህ ምክንያት ከሌላው መሠረታዊ የዴሞክራሲ ችግር በተጨማሪ አንድ ዓይናው የቡድን መብት ያነገሠው ‹‹ብሔርተኝነት›› ነው፡፡ በኢትዮጵያችን ውስጥ ብሔርተኝነት በ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ስም ተሹሞ በስፋት የሚገኝ እንደ መሆኑ አዳላጭነቱን ጠጋ ብሎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡

በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዕቅዶች (በፓርቲ ምሥረታም ጭምር) የብዙ ሰዎችን ጥቅም አቀራርቦ መያዝና ብዙዎችን ለመሳብ መብቃት ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ሲተያይ በብሔርተኝነት ተቧድኖ ድጋፍ መፈለግ ከሁሉም የቀለለ ነው፡፡ የፖለቲካ ትግል ልምምድ ትንሽም የሌላቸው፣ ይህ ይቅርና የፖለቲካ ንድፈ ሐሳባዊ አስተሳሰብ ያላበጁ፣ ሰዎች ፕሮግራም ልትባል የማትችል ወረቀት አዘጋጅተው ብሔርተኛ ብሶትን እያንጎራጎሩ የብሔር ድርጅት ነኝ ሲሉ አጋጥሟል፡፡ ከብሔርተኛ መንገድ የሚጋጩ አስተሳሰቦች ያላቸውን ሰዎች፣ ዴሞክራቶችን፣ ፀረ ዴሞክራቶችንና ፋሽስታዊ ዝንባሌ ያላቸውን ጭምር በብሔር ተቆርቋሪነታቸው ብቻ አብረው መንጋፈፍ እንዲችሉ የተመቸ ነው፡፡ ብሔርተኛ አስተሳሰብና አደረጃጀት በተዘረጋበት ሥርዓት ውስጥ ምርጫ ቢካሄድም፣ መራጩ ሕዝብ ፓርቲዎችን ባላቸው ፕሮግራም ከማማረጥ ፈንታ በአመዛኙ ብሔር ብሔረሰቡን ‹‹ይወክላል.. ለተባለ ቡድን ዕጩዎች ድምፁን የመስጠት ሁኔታ ውስጥ ይወድቃል፡፡

አመለካከቱ ሙሉ ለሙሉ በብሔርተኝነት ገደብ ውስጥ የገባ ሰው ብሔሩን ከሌላ ብሔር ጋር በእኩል ዓይን ለማየትና ለመመዘን ይሳነዋል፡፡ የብሔሩን ወግና ባህል በሒስ ዓይን ከማየት ይልቅ እንደ ወረደ መካብ ያጠቃዋል፡፡ የብሔሩን ባለታሪኮች ጥሩ ሥራቸውን የማብዛትና ድክመታቸውን የመከለል/የማሳነስ ፍላጎት ይስበዋል፡፡ የበላይ ከነበረ ብሔር ወይም ገዥ መደብ ጋር ብሔሩ የነበረውንና ያለውን ታሪክ በመረዳት ረገድም፣ በደልና ጥቃትን የማነፍነፍና ከዚያ አኳያ አዛብቶና አጡዞ የመተርጎም ፍላጎት የምልከታና የማሰብ ሚዛኑን እየታገለ ያስቸግረዋል፡፡ ብሔራችን ተበድሏል እነዚህና እነዚህ አልተሟሉለትም የሚባለው ነገር ብዙ አየር እየተሞላ፣ አንዳንዴም የትግሉ ሁለንተና ሆኖ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያገናኙ ዓበይት ጥቅሞች እንዳይጤኑ የሚሸፈነውም ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ያለው የአብሮነት፣ የእኩልነትና የልማት ትግል ምልከታ ውስጥ ሳይገባ የሚካሄድ የድሮና የዘንድሮ የበደል ድርደራ ወደ ቅያሜ የሚያንሸራትት ድጥ አለው፡፡ ከትምክህት ወገኖች ጋር መተራረብ ታክሎበት በፈላ ስሜት መታወር ሊከተል ይችላል፡፡ በአገራችን ተሞክሮ መሰል ችግር እንግዳ አይደሉም ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረቱ ቋሚ ባህርይ አካል ሆኗል፡፡

የብሔር ብሔረሰብ ካባ መጎናፀፍ የብሔር ወገንተኝነትን ያጠበቀ ስሜታዊ ድጋፍ የሚገኝበት ጥሩ መደበቂያ መሆን ስለሚችልና ስለቻለ፣ ሥልጣን ፈላጊዎችና ሙሰኞች ሽፋን አድርገው ይነግዱበታል፣ ነግደውበታል፡፡ እነሱ የፈጠሩት ድርጅት የያዘውን አቋም የብሔር ብሔረሰቡ አቋም ያደርጉታል፣ አድርገውታል፡፡ ድክመታቸው ሲተች በእነሱ ላይ የተወረወረውን ትችት ብሔር ብሔረሰባቸው ላይ እንደተወረወረ አድርገው ለማምታታት ይመቻቸዋል፣ ተመችቷቸዋልም፡፡ ‹‹ድሮም . . . እየተባልክ ትዘለፍና ትናቅ ነበር ዛሬም ይኼው . . ›› እያሉ ስሜት ውስጥ መክተት የተለመደ ዘዴያቸው ሆኗል፡፡ ለማምታታትም ጠቅሟቸዋል፡፡ ምክንያቱም ብሔርተኛ የተቧድኖ እንቅስቃሴ የቡድን ማንነትና ፍላጎትን ከብሔር ብሔረሰብ ማንነትና ፍላጎት ነጥሎ በማየትና በመረዳት በኩል የበኩሉን አሳሳችነት ስለሚፈጥር ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰብን በደፈናው ሥራዬ ብሎ የሚያወግዝና የሚሳደብ የከተማ እብድ በኢትዮጵያ ሊታይ የቻለው (ከደርግ ውድቀት በኃላ) ከዚህ አሳሳችነት የተነሳ ነው፡፡

ለቅስቀሳው የሚውለው በደል ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ የሚመለከት ሲሆን እንኳ የሁላችንም ችግርና ጥቅም ነው ከማለት ይልቅ፣ የብሔርተኛ ትግል የራሱን ብሔር ብቻ የሚመለከት አስመስሎ በተናጠል የመጮህ ፀባይ ያጠቃዋል፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ የተናጠል ብሔርተኛ ጩኸት ሲሆን፣ ሌላ ወገን የራሱ ብሔርተኛ ንቅናቄ ወይም ሌላ የትግል አማራጭ ከሌለው በስተቀር ድርሻው ተመልካችነት ይሆናል፡፡ የብሔርተኛ ንቅናቄ በተፈጠረበት አካባቢ ያለ ውሁድ ኅብረተሰብ በተለይ ገዥ የሚባል ብሔር አባላት በተመልካችነት ላይወስንና ምንም በደል ባይደርስባቸውም የብሔርተኛ እንቅስቃሴ መፈጠሩ ብቻውን ሥጋታቸው ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ዓይተናል፡፡ ብሔርተኛ እንቅስቃሴው ክልላዊ ሥልጣን ሲይዝም ሥጋታቸው ይቀጥላል፡፡ ትምክህትም ሰለባውን ያበዛል፡፡ የብሔርተኛ ትግሉ ተገንጥሎ የመውጣት ጥያቄ የጨመረ ከሆነ ደግሞ መገንጠልን ከማይደግፍ ወገን ጋር በሞላ መቃረን ይፈጠራል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች የትግል ኃይል ይከፋፈላል፡፡

የትኛውም ዓይነት የብሔር ብሔረሰብ ብሔረተኛነት በውስጤ ያለ ሀብትና ጥቅም ቅድሚያ ለብሔር ወገኔ ይሁን የማለት ቁልቁለት አብሮት ይኖራል፡፡ በዚህ ቁልቁለት ከተንደረደሩ ማረፊያው አድሎኝነት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ከተወደቀ ከሌላው በበለጠ ለብሔር ብሔረሰብ ወገን መታመንና ከሌላው አብልጦ የብሔር ብሔረሰብ ወገንን ማቅረብና መጥቀም ይመጣል፡፡ ጥቅቅሞሹ በግልጽና በድብቅ መንገድ ወደ ልዩ ልዩ የሥራ መስክ፣ ወደ ትምህርት ምዘና፣ ወደ ኢንቨስትመንትና የመሬት ምሪት ሲሻገር የፖሊስና የዳኝነት ሥራን ሊበክል ችላል፡፡ ሲበክልም ታይቷል፡፡ የአድሎኝነት ችግር መኖር ከ‹‹ሚዳላለት›› ብሔር ውጪ ያሉ የኅብተሰብ ክፍሎችን ቅሬታ ላይ ይጥላል፡፡ የእኩል ዜግነት እምነታቸውን ይሰብራል፡፡ ትምክህተኛና ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ መስመሮችን ያነሳሳል፡፡ አድልኦ ባልተፈጸመበት ሥፍራና ጊዜም በይሆን ይሆናል መጠራጠርና ሐሜት እንዲራባ ያደርጋል፡፡ ሐሜቱ ደግሞ በፈንታው የብሔርተኛ ሹምን እልህ እያጋባ ማናለብኝነትንና አድሏዊነትን ያባብሳል፡፡ ይህ ሁሉ የአካባቢውን ሰላማዊ ኑሮና ልማት ይበድላል፡፡ መላ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የተለያየ ልክና መልክ ይዞ የሚታየው ሁሉ የዚህ ውጤት ነው፡፡

በደሉ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ‹‹የሚዳላለት›› ብሔር የተጠቃሚነት ስም ይትረፈው እንጂ ተበዳይነቱ በእሱ ይብሳል፡፡ አድልኦን ፈቅዶ እስከተቀበለው ወይም እስካልተቃወመው ድረስ የነፃነትንና የእኩልነትን ጣፋጭነት ማጣጣም አይችልም፡፡ በራሱም ላይ አድልኦ ይጠራል፡፡ በብሔር የተጀመረው ማዳላት የዘመድ፣ የትውውቅና የሽርክና ድር እየሠራ ይስፋፋልና ‹‹የብሔር ወገኖች››ም የአድልኦ ተጠቂነት አይቀርላቸውም፡፡ እንዲያውም ‹‹የብሔር ወገኔ››፣ ‹‹ለብሔሬ የቆመ›› ባይነት ሚዛናዊ አስተውሎቱን እያደበዘዘበት የጥቅመኞች መነገጃ መሆኑን ለማጤን ከሌላው የበለጠ ጊዜ ሊወስድበትና ብዙ ሊጠቃ ይችላል፡፡

በአድሏዊነትና በጥበት ስሙ የጎደፈ ወይም የተነሳ የአስተዳደር አካባቢ ወደ ሥፍራው ሊመጣ የሚችለውን ተወላጅ ያልሆነ አልሚ የማስቀረት ጉዳትም ያስከትላል፡፡ የክልል ልማት በክልል ተወላጅ፣ የአገርም ልማት በአገር ተወላጅ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በዛሬው የግሎባላይዜሽን ዘመን ልማት እንዲሳካ ከተፈለገ ባለሀብትንና ባለቴክኖሎጂን ከየትም ይሁን ከየት እየሳቡ፣ ልማትን እንዲያስፋፋ አድርጎ የመንከባከብ ብልህነት ዋና መሣሪያ ነው፡፡ አገርነት ይቅርና አኅጉርነት ጠብቦ የብሔር፣ የአገርና የአኅጉር ድንበር ሳይገድባቸው በተያያዙ ጥቂት ግዙፍ ኩባንያዎች ሥር በምትመራ ዓለም ውስጥ ሆነን፣ የብሔር ብሔረሰብ ዕድልንና ልማትን በትንሽ ክልል ደረጃ ከማሰብና ‹‹የብሔር አባሎቻችን ክልላችሁን አልሙ›› ከሚል ጠባብ ማዕቀፍ ማለፍ አይበዛብንም፡፡ በዚህ አቅጣጫ ከታሰበ ሐዋሳ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ዋና ከተማ ስትሆን፣ ከሁሉም በበለጠ የልማት ማዕከል መሆናቸውን በማስተዋል ሲዳማዎች መደሰት ይገባቸዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ መልካም ውኃ እንዲጠጣ፣ የትኞቹም አካባቢዎችና ወንዞች ከብክለት እንዲፀዱ፣ ሁሉም ከተሞች ቆሻሻና ፍሳሻቸውን ለገጠሩም ሆነ ለከተማው ጤና ችግር በማይሆን ዘዴ እንዲያስወግዱ ከማሰብና ከመታገል ፈንታ፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ውስጥ መሆኗና የመጠጥ ውኃና የፍሳሽ አገልግሎቷ በኦሮሚያ ላይ የተደገፈ ስለሆነ ክፍያ ልትፈጽም ይገባል የሚል አስተሳሰብ ዘንድሮም ያላቸው ካሉ ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡ በፌዴራል መንግሥት የድጎማ ገንዘብ ድርሻ ሥሌት ላይ ከመብሰልሰል፣ በአጠቃላይ የልማት ሥርጭት ሚዛናዊነትና ዕድገትን የማጠጋጋጥ ጥረት ረገድ እየተሠራ ያለውን መመርመር ይበልጣል፡፡

የድርሻ ጉዳይ ሌላ ዓይነት መንፀባረቂያም አለው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ሀብት ክፍፍል ከብሔር ብሔረሰብ አኳያ የሚያሠሉና የአማራ፣ የጉራጌ፣ የትግሬ፣ ኦሮሞ፣ የሐረሪ፣ ወዘተ ምን ያህል ሀብታም አለ? ምን ያህል ካፒታልስ ደርሶታል? እያሉ ከሕዝብ ብዛት ጋር የሚያነፃፅሩ ተፈጥረዋል፡፡ የዚህ ዓይነት ሥሌት ኅብረተሰቡን ለማቃቃር የሚውልና መበላለጥን እየፈለጉ ከማቅረብ በስተቀር የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ሰንጠረዥና ቀመር ሠርቶ የዚህ ወገን ድርሻ በዝቷልና ከዚህ ወደዚህ ይቀነስ ወይም የዚህኛው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ቆሞ የዚህኛው ይስፋ ሊባል አይችልም፡፡ ያልተመጣጠነ ዕድገት አጠቃላይ የሰው ልጅ ታሪክ ባህርይ ነው፡፡ ማድረግ የሚቻለው አድሏዊነት መወገዱንና አቀራራቢ የልማት ፖሊሲ መኖሩን በተግባር ማረጋገጥና በዚያ ውስጥ መጣር ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ፖሊሲ ተይዞ ሲጣርም እንኳ ከአድልኦ ውጪ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች መበላለጥ መከሰቱ አይቀርም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲዘረጋና ምርጫም ዕውን እንዲሆን ከተፈለገ ፓርቲዎች እንዲኖሩ፣ ኖረውም በሕግና በተግባር እኩል እንዲሆኑ፣ በምርጫም እኩል ወጪና ወራጅ መሆን እንዲችሉ የሚከለክል ጎዶሏችን መወገድ አለበት፡፡ መንግሥታዊ ዓምዶች ከፓርቲ ወገናዊነት፣ ተቀጥላነትና ይዞታነት ውጪ ነፃ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲያችንን እግር ከወርች የቀፈደደው ሌላው ነገር በዚህ ጽሑፍ በሁለተኛው አጋማሽ ክፍል ላይ የተጠቀሰው የብሔርተኝነት ድጥ ነው፡፡ የብሔርተኝነት ድጥና የትምክህት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በከፋ ደረጃ እየተከሰተ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች ማስተናገድ በሚችሉ ስታዲዮም ባላቸው ከተሞችና የፌዴራል ዩኒቨርሲቲ ባለባቸው ክልሎች ውስጥ የሚታየው ይህ ችግር የጫረው እሳት ነው፡፡ ክልልተኞች፣ ወገንተኞችና ትምክህተኞች በሚፈጥሯቸው ቅራኔዎችና ፍርኃቶች ውስጥ መኖር የሚስማማው ሕዝብ የለም፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ጋር መኖርም ግድ አይደለም፡፡ መንግሥትም ከቦታ ቦታ እየሮጠ ሁከት በማብረድና በማስታረቅ ችግሮችን መጨረስ አይችልም፡፡ ይህ አገር አዲስ ራዕይ፣ አዲስ ቅኝትና መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ አዲሱ መፍትሔ ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መውጣትን፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ገለል ማድረግን በጭራሽ አይጠይቅም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል እንጂ በተገላቢጦሽ የሁሉ ነገር መፍቻ አይደለምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *