በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ከረፋዱ አሥር ሰዓት ጀምሮ በተፈጠረ ግጭት፣ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ 11 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ማረጋገጥ የቻለው በግጭቱ 12 ግለሰቦች መገደላቸውንና አራት ሰዎች በፅኑ መቁሰላቸውን ነው፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የተጎጂ ቤተሰቦች የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልና የቆሰሉትም 26 እንደሚደርሱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የግጭቱ መነሻ የቦዲ ብሔረሰብ አባል የሆነች ግለሰብ በተሽከርካሪ በመገጨቷ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በአካባቢው የነበሩና ሲያልፉ የነበሩ ሾፌሮች በበቀል ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የብሔረሰቡ አባላት ጥቃቱን በጠመንጃና በባህላዊ የጦር መሣሪያዎች ታግዘው ማከናወናቸውን፣ በመኪና አደጋው ተጎጂ የነበረችው የብሔረሰቡ አባልም ከሟቾቹ ውስጥ አንዷ መሆኗ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አካባቢውን የክልሉ ፖሊስና በቅርብ ከሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ የሄዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እያረጋጉ መሆኑን፣ የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የግጭቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል የአዲስ አበባ ነዋሪ የነበሩ ግለሰብ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሟቹ አቶ ተስፋ ዳኘው የተባሉ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት በአካባቢው በሎቤድ ሾፌርነት እንደነበር ከቤተሰቦቻቸው ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር ከቤተሰባቸው ባገኘው መረጃ መሠረት ሥርዓተ ቀብራቸው ረቡዕ ኅዳር 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በቱሉ ዲምቱ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተከናወነው አቶ ተስፋ፣ በአካባቢው በሾፌርነት ሲሠሩ የግጭቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ‹‹በምን ምክንያት የግጭቱ ሰለባ እንደሆኑ ያገኘነው መረጃ የለም፤›› ሲሉ የአቶ ተስፋ አማች አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ስለጉዳዩ ቀርቦ ያናገረን የመንግሥት አካል የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን በግጭቱ በመሳተፍ የተጠረጠሩ ተጨማሪ ግለሰቦችን ለመያዝ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አቶ ሲሳይ ለሪፖርተር ገልጸው፣ እስከ ዓርብ ድረስ 11 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አረጋግጠዋል፡፡

 

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

Source Reporter 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *