…በትዳር ውስጥ ከሚፈጸመውና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ባሻገር ሕፃናት በጎረቤት፣ በቤተሰብ አባላት፣ በመምህራቸው አልያም በሌሎች ግለሰቦች ተገደው የመደፈራቸው ዜና በየጊዜው ይሰማል፡፡ በዚህ ረገድ ጎረምሶች ለሰባት ተፈራርቀው የደፈሯትና ሕይወቷ ያለፈውን የሃና ሎላንጎን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ መሰል አጋጣሚዎች ሴቶች በተለየ ለአደጋ ተጋላጭ እንዲሆኑ፣ በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ እንቅስቃሴያቸው ሥጋት ውስጥ እንዲወድቅ እያደረገው ይገኛል…. ሪፖርተር አማርኛ 

ተፈጥሯዊና ሳይንሳዊ መሠረት ባይኖረውም ሴትን ከወንዶች ዝቅ አድርጎ መገመት ከጥንት ጀምሮ የነበረ አድሏዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወንድ ሲወለድ የደስታ መግለጫ ጠብመንጃ ሲተኩሶ ሴት ስትሆን ደግሞ በአመዛኙ መቼስ ምን ይደረግ በሚል ዓይነት ትሁን ተብሎ የሚታለፈው፡፡ የችግሩ ክብደት እንደየ ማህበረሰቡ የተለያየ ነው፡፡ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ሴት ልጅ ለወላጆቿም ሆነ ወደ ፊት ለሚያገባት ባሏ እንደ ሸክም ትቆጠራለች፡፡ ለዚህም ሴት ሆና በመፈጠሯ ብቻ ቤተሰቦቿ በአሰቃቂ ሁኔታ ሊገድሏት ይችላሉ፡፡ መሰል አሰቃቂ ወንጀል ከሚፈጸምባቸው የእስያ አገሮች መካከል ህንድ ግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡

በህንድ ሴት ልጅ ስትወለድ ጀምሮ ወንድ ሆና ባለመወለዷ ባለዕዳ ነች፡፡ ሴትነቷ ዕዳዋ ስለሚሆን እንደ ተወለደች ሊገድሏት ሁሉ ይችላሉ፡፡ ዕድለኛ ሆና ካልሞተች ደግሞ እየኖረች የምታወራርደው ዕዳዋን ትከፍላለች፡፡ ገና ለአቅመ ሔዋን ሳትደርስ በልጅነቷ ትዳለች፡፡ ለሚያገባት ግለሰብም ጥሎሽ መስጠት ግዴታዋ ነው፡፡ ባሏ የሚጠይቀው የጥሎሽም መጠንም ከቤተሰቦቿ የመክፈል አቅም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥሎሹን ወስዶ ከተጋቡ በኋላ ሌላ ተጨማሪ ጥሎሽ ባሏ ሊጠይቅ ይችላል፡፡   

ቤተሰቦቿ የተጠየቁትን ለመክፈል አቅማሙ ማለት በሴቷ ሕይወት ላይ እንደመፍረድ ነው፡፡ ምክንያቱም የጥሎሽ ግዴታዋን መወጣት ያቃታት ሴት መጨሻዋ በአሰቃቂ ሁኔታ መሞት ነው፡፡ ባል የጠየቀው ጥሎሽ ካልተሰጠው ከሌላ ዓለም እንደመጣ ፍጡር ሙሽራዋ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ እሳት ይለኩስባታል፡፡ ይህ ጥንትም የነበረ በአሁኑ ወቅትም እየተፈጸመ የሚገኝ አሰቃቂ ‹‹ዶውሪ ዴዝ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የግድያ ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥርም ከዓመት ወደ ዓመት እያሻቀበ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በህንድ 8391 ሞት ተመዝግቧል፡፡

በተለየዩ የዓለም ክፍሎች በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረው ጭቆና በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ የሴቶች መብት ተከራካሪነን ባዮቹ ምዕራባውያንም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭቆናና ጥቃት ከዚህ ብዙ የተለየ አልነበረም፡፡ ባል በሚስቱ ላይ ማንኛውንም ነገር የማድረግ መብቱ ገደብ አልነበረውም፡፡ ሚስቱን መግረፍም ሆነ መግደል ይችላል፡፡ ታዲያ ይህንን ሲያደርግ የሚጠየቅበት አግባብ አልነበረም፡፡ ሚስቱን በንብረትነቷ እንጂ በሰውነቷ አይመዝናትም፡፡ ይህ በጊዜ ሒደት መቀየር ችሏል፡፡ ሴትና ወንድ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ፀድቀው ተግባራዊ ሆነዋል፡፡

140 የዓለም አገሮች በሴቶች ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶችን የተመለከቱ ሕጎችን አውጥተዋል፡፡ 144 የሚሆኑ ደግሞ በፆታዊ ትንኮሳ ላይ ትኩረት ያደረጉ ድንጋጌዎች አውጥተዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች የሴት ልጅን ጥቃት ለመከላከል ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራም ይሠራሉ እየሠሩም ይገኛሉ፡፡

 ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን ወንዶች በሴቶች ላይ የነበራቸውን የበላይነት በማይናቅ ደረጃ እንዲቀንስ ያደረገው ቢሆንም ችግሩ ግን አሁንም ድረስ አሳሳቢ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ሴቶች ከጥቃት አልዳኑም፡፡ የወንድ የበላይነት ከዚህ ቀደም ከነበረበት ጣሪያ ማውረድ ቢቻልም ሴት ልጅን ለማሳደግ ያለውን ፈተና ለብዙዎች የተደበቀ አይደለም፡፡

የሴቶችን መብት የሚያስከብሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈራሚ ከሆኑ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሴትን መብት ለማስከበር በተለያዩ መድረኮች የሚሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም ቀላይ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ያለዕድሜ ጋብቻን፣ ጠለፋን፣ አስገድዶ መድፈርንና ለሌሎችም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ጨርሶ ማስቀረት ግን የማይፈታ ህልም ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚመደበው የሴት ልጅ ግርዛት ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ የሚተገበር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በየመን፣ በኢራቅ፣ በኢንዶኔዥያና በሌሎች የእስያ አገሮች እንዲሁም በ27 የአፍሪካ አገሮች ይፈጸማል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ዩኒሴፍ ያወጣው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በዓለም ላይ የሚገኙ 200 ሚሊዮን ሴቶች የዚህ ድርጊት ሰለባ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሰለባዎች ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሲሆኑ፣ ከዓመታት በፊት የወጣ አንድ ጥናት በአገሪቱ 23.8 ሚሊዮን ሴቶች የተገረዙ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ይህንን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ድርጊቱን በስፋት በመፈጸም የሚታወቁ ናቸው፡፡

ያለዕድሜ ጋብቻና ጠለፋንም በተመለከተ በዘመቻ መልክ እስካሁን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም ችግሩን ማጥፋት ግን ከባድ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የተደረገ የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ ጤና ቅኝት እንደሚያመለክተው ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ሥልጣኔ እንዳለበባት በሚታመነው በአዲስ አበባ 15 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የሚዳሩት ከ18 ዓመት በታች ሳሉ ነው፡፡ እንደ አገር ደግሞ በኢትዮጵያ ከ15 እስከ 19 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 13 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የልጅ እናት የሚሆኑት በልጅነታቸው ነው፡፡ ያለእድሜ ጋብቻ መጠኑ ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን፣ 23 በመቶ በአፋር፣ 19 በመቶ በሶማሌ፣ 17 በመቶ በኦሮሚያና በሐረር፣ 16 በመቶ በጋምቤላ፣ 8 በመቶ ደግሞ በአማራ ክልሎች ይፈፀማል፡፡ ሴቶች የሚያገቡበት አማካይ ዕድሜም 16.5 በመቶ መሆኑን መዘገባችንም የሚታወስ ነው፡፡

ባህልና ልማድን ሽፋን አድርገው በሴቶች ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች በተጨማሪም አስገድዶ መድፈር፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ድብደባና ሌሎችም ሴቶች በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው በደህንነት ሥጋት የተሸበበ እንዲሆን ያደረጉ የወንድን የበላይነት የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ከጥቃቱ አድራሾች መካከል ባሎችና የቅርብ ዘመዶች መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

በጥንዶች መካከል የሚከሰት አስገድዶ የመድፈር ድርጊትን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ሰነዶች ተግባሩን እንደ ፆታው ጥቃት ይፈርጃሉ፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ስምምነት ፈራሚ በመሆን ድርጊቱን ሕገወጥ መሆኑን ተቀብላለች፡፡ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ግን ከወረቀት ባለፈ ምን ድረስ እንደሆነ ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ስምምነቱ ተግባራዊ የሚደረግበት የሕግ ማዕቀፍም ገና አልተዘጋጀም፡፡ የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ ድርጊቱን በተመለከተ የሚለው ነገር የለም፡፡

አጋጣሚው በትዳር ውስጥ የሚፈጸም የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ሕገወጥ እንደሆነ ቢታወቅም ድርጊቱን የፈጸመው ባል የሚቀጣበት የሕግ ማዕቀፍ የለምና ባሌ ደፍሮኛል ብላ ክስ የምትመሰርት ወይዘሮ ትርፏ ልፋት፣ ሲያልፍም መሳለቂያ መሆን ነው፡፡

‹‹Analysis of Marital Rape in Ethiopia in the Context of International Human rights›› በሚል እ.ኤ.አ. በ2014 የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው፣ አብዛኛው በትዳር ውስጥ የሚፈጸም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሪፖርት አይደረግም፡፡ ለዚህም ድርጊቱ ፈጻሚው እንዲቀጣ የሚደረግበት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ አንድ ወንድ ሚስቱን አስገድዶ እንዲደፍራት ፈቃድ የመስጠት ያህል መሆኑን ያብራራል፡፡

የወንጀል ሕጉ ሲሻሻል በትዳር ውስጥ የሚፈጸመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲካተት ሐሳቡ ቀርቦ እንደነበር የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሳባ ገብረመድህን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ማኅበረሰቡ ስለ ጉዳዩ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ድርጊቱን በወንጀል የሚያስጠይቅበት አግባብ እንዲኖር ማድረጉ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል በሚል በይደር መታለፉን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕጋዊ መሠረት ባይኖረውም ግንዛቤ ለመፍጠር ያህል ሚስትን አስገድዶ መድፈር ፆታዊ ጥቃት እንደሆነ እናስተምራለን፤›› በማለት አገሪቱ ከዓመታት በፊት ያፀደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት ተግባራዊ የሚደረግበት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የተፈጠረውን ክፍተት ይናገራሉ፡፡

በትዳር ውስጥ ከሚፈጸመውና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ባሻገር ሕፃናት በጎረቤት፣ በቤተሰብ አባላት፣ በመምህራቸው አልያም በሌሎች ግለሰቦች ተገደው የመደፈራቸው ዜና በየጊዜው ይሰማል፡፡

በዚህ ረገድ ጎረምሶች ለሰባት ተፈራርቀው የደፈሯትና ሕይወቷ ያለፈውን የሃና ሎላንጎን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ መሰል አጋጣሚዎች ሴቶች በተለየ ለአደጋ ተጋላጭ እንዲሆኑ፣ በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ እንቅስቃሴያቸው ሥጋት ውስጥ እንዲወድቅ እያደረገው ይገኛል፡፡ በቅርቡ ሜክሲኮ አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ በስለት ተወግታ ስለሞተችው ታዳጊ ሰምቶ ለሴት ልጁ ያልተጨነቀ፣ ያልተደናገጠ ሰው አልነበረም፡፡ ክስተቱ መሰል ድርጊቶችን ለሚፈጽሙ ወንዶች ሴትን ማጥቃት ምን ያህል ቀላል መሆኑን ያሳየና ሴቶች በሰላም ወጥተው ስለመመለሳቸው ዋስትና አለመኖሩን ያሳየ ነበር፡፡

ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት ገደማ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 02 ጐሮ በሚባል ቦታ ባል የ22 ዓመት የትዳር ጓደኛውን በቅናት መንፈስ አንገቷን ቀልቶ ገድሏል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት በምዕራብ ጎጃም ቡሬ ከተማ ውስጥ የተፈጸመው ወንጀልም የሚታወስ ነው፡፡ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ሚስት ወደ ወላጆቿ ቤት ሄዳ ነበር፡፡ እዚያ መሄዷ ግን ለደኅንነቷ ዋስትና የሰጠ አልነበረም፡፡ ባል የቤተሰቦቿ ቤት ድረስ ሄዶ ነበር የአምስት ወር ነፍሰጡር ሚስቱን የገደላት፡፡

በስድስት ዓመታት በፊትም በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበና ድልድይ አካባቢ አንድ ግለሰብ ሚስቱን፣ አክስቷንና እናቷን ሽጉጥ ተኩሶ ገድሏል፡፡ በ21 ዓመቷ ካሚላት ሙህዲን ላይ አሲድ የደፋው ወጣት ድርጊትም ሰብዓዊነትን ጥያቄ ውስጥ የከተተ አስደንጋጭ ጥቃት መነጋገሪያ ነበር፡፡ ደምበል ፊት ለፊት ሚስቱን 17 ጊዜ በሽጉጥ ተኩስ የገደለው ግለሰብ፣ ሆስተስ ሚስቱን ዓይን በስለት ጐልጉሎ በማውጣት ለዓይነ ስውር የዳረገው ወንጀለኛ ድርጊት ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር፡፡

ከቀናት በፊት በፈረንሳይ በኢትዮጵያዊዋ የረጅም ርቀት ሯጭ በዝናሽ ገዝሙ ላይ በወንድ ጓደኛዋ የደረሰው የግድያ ወንጀልም በርካቶችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ የ27 ዓመቷ ዝናሽ ስታድ ፍሮንሴ የተባለውን የፈረንሳይ አትሌቲክስ ክለብ የተቀላቀለችው በቅርቡ ነበር፡፡ አስከሬኗ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ የተገኘው በጥቆማ እንደነበር የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ዘግቧል፡፡ ግድያውን የፈጸመው የ28 ዓመቱ ጓደኛዋ በዋንጫ እንደመታትና በትራስ አፍኖ እንደገደላትም አምኗል፡፡

ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድህን እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ የተዘጋጀ ልዩ ሕግና ለቃሉም ትርጉም የሚሰጥ የተዘጋጀ ፖሊሲ የለም፡፡ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚነሱ የጥቃት ዓይነቶችን ተከትሎ መሥራቱ ደግሞ ወጥ የሆነ አሠራር እንዳይኖር አድርጓል፡፡

በወንጀል ሕጉ ያልተካተቱ ነገር ግን ፆታዊ ጥቃት የሆኑ አዳዲስ ድርጊቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ድርጊቶች መካከል አሲድ መድፋት አንዱ ነው፡፡ አሲድ ማፍሰስ ተጎጂዋን ሙሉ ለሙሉ የሚቀይር እንዳልነበረች የሚያደርግ ድርጊት ነው፡፡ ነገር ግን ድርጊቱን አስመልክቶ በግልጽ የተቀመጠ አንቀጽ ባለመኖሩ ድርጊቱን የፈጸመው ተጠርጣሪ የሚከሰሰው በአካል ማጉደል፣ ጫን ሲል ደግሞ በነፍስ ማጥፋት ነው፡፡

‹‹ግለሰቡ እኔ ነፍሷን ለማጥፋት አስቤ አይደለም ይላል፡፡ ስለዚህም ክሱ በአካል ማጉደል፣ አንድ ዓይኗን አጥፍቷል በሚል ይሆናል፤›› በማለት ፆታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች ራሲን የቻለ ትርጓሜና ህግ ባለመሰጠቱ የተፈጠረውን የሕግ ክፍተት ወ/ሮ ሳባ ይናገራሉ፡፡

እንደ ሴት ልጅ ግርዛት፣ ድድ ማስቧጠጥ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አስቀጪ አልነበሩም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ድርጊቱን ሲፈጽሙ የተገኙ በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ጠለፋን በተመለከተ የነበረው ሕግ ጠላፊው እስካገባት ድረስ በወንጀል የሚያስጠይቀው አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕጉ ተሻሽሎ ጠላፊው በየትኛውም አግባብ እንዲጠየቅ የሚያስገድደው ሆኗል፡፡ አስገድዶ መድፈርን በተመለከተ ወንጀሉን በፈጸሙ ላይ ይጣል የነበረው ቅጣት እምብዛም የነበር ሲሆን፣ ጠንከር ባለ ሕግ እንዲለወጥ መደረጉን ወይዘሮ ሳባ ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን ተሻሽለው የወጡ ሕጎች ጥቃቱን በመቀነስ ረገድ ምን ያህል ሚና ተጫውተዋል የሚለው ጉዳይ አሁንም አጠቃያቂ ነው፡፡ ‹‹የሚጣሉት ቅጣቶች አስፈሪና ከልካይ አይደሉም፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ የሚሰማው ጥቃት በጣም ብዙና ለመግለፅም የሚከብድ ነው፡፡ የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት አሁንም በጣም ችግር ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ሳባ በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል የሚለውን ነገር መለስ ብሎ መገምገሙ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 የወጣው የሥነ ሕዝብ የጤና ጥናት 68 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች፣ አርባ አምስት በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ሚስትን መምታት ምክንያታዊ መሠረት አለው ብለው ያምናሉ፡፡ 41 በመቶ የሚሆኑ ከ20 እስከ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ይዳራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስምንት በመቶ የሚሆኑት 15 ዓመት ሳይሞላቸው የሚዳሩ መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡

በመንግስታቱ ማህበር የሴቶች ጉዳይን የሚከታተለው ዩኤንውመን ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት መግቢያ ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ 25 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለመጀመርያ ጊዜ ፆታዊ ግንኙነት ያደረጉት በፈቃዳቸው ሳይሆን በሚያጋጥማቸው ማስፈራሪያ ነው፡፡ 35 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ሚስት ጥቃቱ የደረሰባት ከባለቤቷ ጋር ወሲብ አልፈጽምም ብላ ከሆነ ችግሩ የባለቤቷ ሳይሆን የእሷ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ 31 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጥቃቱ የደረሰባት ልጇን በአግባቡ ባለመያዟ እንደሆነ የባሏ ዱላ ይገባታል ብለው ያምናሉ፡፡ ባሎችም ሚስቶቻቸውን መምታት ተገቢ እንደሆነ የሚያምኑ ሲሆን፣ ተቀባይነቱም በሶማሌ ክልል 58 በመቶ፣ በደቡብ ክልል 56 በመቶ እንደሚደርስ ጥናቱ ያሳያል፡፡

ሴቶች ለቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ከሚያደርጓቸው ምክያቶች መካከል ያለዕድሜ ጋብቻ ዋነኛ እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ ሴቶች የሚያገቡበት አማካዩ ዕድሜ 21 ሲሆን፣ በአማራ ክልል ደግሞ 14.7 ዓመት ነው፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ ጥቃት ከክልል ክልል የተለያየ ነው፡፡ ከፍተኛው በአማራ ክልል የተመዘገበው 44.8 በመቶ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል 34.1 በመቶ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 31 በመቶ ነው፡፡

ያለዕድሜ ጋብቻና አስገድዶ መድፈር በሴቶች ላይ የሚያደርሰው አካላዊና አዕምሯዊ ጤና ከባድ ነው፡፡ ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን እንዲያጠፉ፣ የአዕምሮ ሕመምተኛ እንዲሆኑ፣ ለፌስቱላ እንዲጋለጡ፣ ከማኅበረሰቡ ተገልለው እንዲኖሩ ምክንያት ነው፡፡

የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ እነዚህን ማረፊያ ያጡ ሴቶች ተቀብሎ አስፈላጊውን ከለላ የሚያደርግላቸው የመጠለያ ማዕከል መኖርም ወሳኝ ነው፡፡ አስፈላጊውን የሥነ ልቦና ዕርዳታ፣ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ አለሁ የሚላቸውና ወደ ሙሉ ማንነታቸው የሚመልሳቸው አካል አስፈላጊነት አስፈላጊነት ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡

ይሁንና በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች የሚገኙት 12 መጠለያ ማዕከላት ብቻ በመሆናቸው አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ አምስቱ በአዲስ አበባ፣ ሁለት በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አንድ በአማራ ክልል፣ ሁለት በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ክልል አንድ፣ በድሬዳዋ አንድ ተሠራጭተው ይገኛሉ፡፡

‹‹መንግሥት በየክልሉ የሴቶች ማቆያ ማዕከላት ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን እስካሁን በመንግሥት የተገነባ ማቆያ ተመረቀ ሲባል አልሰማሁም፡፡ ለዚህም ያሉት ውስን መጠለያዎች ከአቅም በላይ እንዲጨናነቁ ሆኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የመጠለያ ማዕከላት በፍጥነት መገንባት አለባቸው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሳባ ይህንን ለማድረግም ርህራሄና ሰብአዊነት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

ለዚህ ዓለም መውደቅና መነሳት ወራጅና ማገር ሴትም ወንድም ናቸው፡፡ ሁለቱም በተፈጥሮ ሚዛን እኩል ናቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ ዋጋ የለውም፡፡ ይህም በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ያለው ለወንዶች ያደላ አመለካከት ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው ፍሬፈርስኪ መሆኑን ያሳያል፡፡ ለዚህም የሴቶችን ጥቃት፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ሴቶችን ያሳተፈ ፖለቲካና ሌሎችም ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ፍትሃዊ ማድረግ የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ 

ማስታወሻ – ሴት ሆኖ መወለድና የአስተሳሰብ ድርቅ የሚለው በዋናው  ርዕስ ላይ የታከለ ነው

Related stories   Speaking Truth to Power, Samantha: Stop Defending Ethiopia’s “Proud Boys”!

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *