ምስኪን እናቶችን እናስብ፣ ተስፋቸው የሚቀጠፍባቸውን ወላጆች እናስብ፣ በማያውቀው ሊጠፋ ለተዘጋጀው አዲስ ትውልድ እናስብ፣ ኢትዮጵያ መጥፋቷንም እናስብ፣ አገር አልባ እንዳንሆን እናስብ፣ የሚገስጽ፣ የሚያርቅ፣ ተው የሚሉ አባቶ እንደሌሉን እናስብ፣ በአምላክ ጥበበ የምንኖር ባዶዎች እንደሆን እናስብ፣ የሃይማኖት መሪዎሽም እንደሌሉን እናስብ፣ እንዳንከስም እናስብ…..የዘር ፖለቲካ የሰውነትን  ልቡናና ቀልብ የሚበላ ቫይረስ ነውና   ከዘር ከረጢት የምንወጣበትን መንገድ እኛው ራሳችን እንፈልግ። ሚዲያዎችም እኛን ጨምሮ በሰከነና በረጋ መንገድ እንስራ። ሲያልቅ አይምርምና ሁሉም በጥበብ ይሁን። ከዘላለም ሃዘን እናመልጥ ዘንድ እኛው ራሳችን እንትጋ!!  ዛሬም ተማሪዎች ሞቱ!! ነገስ? ጉዞው ወዴት ነው? ካልሆነ ሁሉም በየክልላቸው ይማሩ!! 

በአስደንጋጭ መረጃዎች ተወጥረናል። ከየ አቅጣጫው የሚሰማው ዜና ሁሉ እረፍት የሚነሳ ነው። መንግስትን የጠቀሙ የሚመስላቸው በተነፈሱ ቁጥር የሕዝብን ስሜት ያጎሻሉ። ራሱ የመንግስት የሚባለው ሚዲያም ቢሆን ሕዝብ የሚያውቀውን ጉዳይ እየሸመጠጠ በገዛ እጁ ታማኝነትን አጥቷል። ሰሚ አልባ ሆኗል።
ማህበራዊ ሚዲያዎችም በአብዛኛው የተራ አሉባልታ ፋብሪካና ተራ አተካራ የሚሰራጭባቸው ናቸው። አንዳንዶች ፈር ይዘው ቢሰሩም ሰሚው ለአተካራና ለተራ እንካ ሰላምታ ቅድሚያ የሰጠ ይመስላል። እናም በዚህ ሁሉ መሃል የሚወርደው የመረጃ ናዳ እንደ ሰደደ እሳት ሕዝብ ዘነድ እየደረሰ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል። በሌላ አነጋገር በኢህአዴግ ቅጥ ያጣ አመራር ምሬት ተደራቢ ሆኖ ቁጣን ያነሳሳል።
ኢህአዴግ በሚዲያ የገጠመውን ፈተና ለመቋቋም ከኢንተርኔት አፈና ጀምሮ ጣቢያ እሰከማዘጋት ቢዘልቅም፣ ዞሮ ዞሮ ኢኮኖሚውንና ኢንቨስትመንቱን እየበላበት ጣጣው ባለ ሁለት ስለት ቢላዋ ሆኖበታል። እንዲህም ሆኖ በሁሉም ቦታ የሚደረገው ሁሉ ከምስልና ከቪዲዮ ጋር ተቆራኝቶ የአደባባይ ጉዳይ እየሆነበት አነገዳግዶታል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ሳላ ወደ ቁርጥ የፖለቲካ መፍትሄ ከመግባት ይልቅ በየጊዜው ” እየተጠገነ” እስከ ምጽዓት የመግዛት ሃሳቡን ከማሳየት የዘለለ ነገር ሲያደርግ አልታየም። ” ጥልቅ ተሃድሶ ” ብሎ የመበስበስና የመሽተትን በሽታ ለማስወገድ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ቢንጠራወዝም ውጤቱ ” እኔ ተጠግኜ ልግዛ” ከሚል እሳቤ ያለፈ ባለመሆኑ የፖለቲካውን ግለት ጨመረው እንጂ አላባረደውም።
ኢህአዴግ የራሱ ግብር ያስኮረፈውን ሁሉ እየነካካ አስቀየመ። በወጉ ሊያዝ የሚችልን ተቃውሞ በጥይት ማስተናገድ ጀምሮ ሃዘንን በሁሉም ቤት ረጨ። እናም ሆድ የባሳቸው፣ ሃዘን የገባቸው፣ አንጀታቸው በገባባቸው ሃዘን መጠን የተበጠሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ራሱ በየቀኑ አራባ። በተከለው ድንኳን መጠን ቂም ተቋጠረበት። እና የዚህ የቂም ነዶ በየመድረኩ ይወዘወዝ ጀመር።

Image may contain: one or more people, people standing and outdoor
ብሄር፣ ጎሳና ስፍራ ሳይመርጥ ሁሉም ጋር እየተንደረደረ በመግባት ደም አፈሰሰ። ” እህቶቼ” የሚላቸው ድርጅቶችም የተዘረጋውን የ”ጋራ ሲስተም” አመከኑት። ከረከሩት። አንዳንዱን መዋቅር አነተቡት። አንዳንድ ስፍራዎች እንደታየው ” ዞሮ ዞሮ መግቢያው” እንደሚባለው ወደ ” ወገኖቻቸው” አደሉ። ይህ ቀድሞውንም የሚገመት ቢሆንም የአሁኑ በማይታሰብ ደረጃ አደባባይ ታየ። ይህን ጊዜ ቀደም ሲል ሹክሹክታ ደረጃውን ጨመረ።አንድ ብሄር ላይ አንደበትን ማላቀቅ፣ ቃላት ሳይመርጡ፣ ስም እየጠሩ ማሳጣት ድፍረት የማይጠይቅ ሆነ። እንደውም ኢህአዴግን ወደ እናት ስሙ ህወሃት መለሱት።
ስራዊቱም ፣ ፖሊሱም፣ መከላከያውም ሆን የኢኮኖሚውን ድርሻ ዳታና ስም እየተጠራ የአንድ ክልል እንደሆነ መረጃዎች ከቀድሞው ይልቅ በማህበራዊ ገጾች ናኙ። የማህበራዊ ገጾች የስርጭት ፍጥነት እንደ ብርሃን አይነት ነውና፣ በሚፈሰው የአድማ ጥሪ መጠን ማስተባበል ሳይቻል ቀረ። በሕዝብ ስም ቢማልም ሰሚ በመጥፋቱ ሁሉም ከላይ እነደተባለው ጣቱን ወደ ትግራይ በጅምላ መቀሰር ያዘ። 
በተለይም ያለፉት ሁለት ዓመታት የተወሰዱ እርምጃዎች የአብሮነትን ስሜት አደረቁ። አብሮነት በደረቀ ቁጥር ህዝብን እንደ ጠላት መፈረጅ ቀላል ሆነ። ይህ በየእለቱ ቤንዚን ሲርከፈከፍበት የቆየ መሻከር መጨረሻ ላይ እመደቡ ላይ አረፈ።
መደቡ የጎሳ ፖለቲካ በመሆኑ አብሮነት በከስመ ቁጥር ብሄርተኛነት አበበ። ይህ ገና ከጅምሩ ” አይጠቅመንም” በሚል ማሳሰቢያ፣ ምክርና ማስጠንቀቂያ ሲቀርብበት የነበረው ቫይረስ ከወቅቱ ህጻናት ጋር ተጣብቶ አደገ። በስተመጨረሻ አሁን እነደታየው ሁለት ወንድማማች ክለቦች ኳስ መጫወት ተሳናቸው። አብረው ትምህርት ገበታ መቀመጥ አዲዮስ!! ገደል ገባ።
አዲግራት የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ተወግረውና ከፎቅ ተጥለው ሞቱ። ቆሰሉ። እንደ ጥንት ዘመን ተወገሩ። ቀጥሎ ደግሞ በሻምቡ ካምፓስ የትግራይ ልጆች ተወገሩ፣ ተፈነከቱ፣ ከፎቅ ተጣሉ። ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ወልደያ፣ አምቦ …. ተማሪዎች አመጹ። በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ጠላት ተደረጉ።
ይህ ዜና አይደለም። ይህ ለወገን ሊተላለፍ የሚገባ መረጃ አይደልም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በጎሳ መባላት አንገት የሚያስደፋ፣ የሚያሳፍር፣ የሚቀፍ፣ የሚያም፣ መቆሚያው ዳሩ የማይታወቅ የምንግዜም ቅሌታችን ነውና።
ህወሃት እንደ ፓርቲ አርጅቷል። በአመለካከትም ደረጃ ቢሆን የሚከተለው ጊዜው ያለፈበት ፍልስፍና ነው። በዚህ ላይ ሁሉም ዜጋ በጥርጣሬ የሚያየውና እምነት የከዳው ድርጅት ከሆነ ቆይቷል። አቶ መለስ ዜናዊ አገራዊ ስሜት ያላቸውን፣ እሳቸውን የሚፈታተኑዋቸውን በሙሉ አስወገደው እንደ እቃ ቤት ድርጅቱን የብቻቸው አድርገውት ስለኖሩ ዛሬ የበቃ አመራርም የለውም።
ይህንን እውነት በአፍ ሳይሆን በእውነት ተቀብሎ ማስተካከል ውል ያለው ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ችግር ሲፈጠር የትግራይ ህዝብን ሌላው ህዝብ ሊያጠፋው እንደሆነ በመስበክ ንጹሃን ውስጥ መደበቁ ያመጣው ጣጣ አገሪቱንም፣ መጪውንም ትውልድ፣ ሁሉም አብሮ የሚያመነዥግ ውፍጮ የመትከል ያህል ሆነ። ይህ ” ውርስ” እየተባለ የሚለፈለፍለት የዘር ፖለቲካ እንዳይበላን ምን ይሁን? የሚለውን ጉዳይ መዞ ማሰብና መደሃኒት መፈልጉ ላይ መረባረብ ካልተቻለ መጨረሻው የእድሜ ልክ ጸጸት ከመሆን አያልፍምና እንጠንቀቅ።
እድሜ ልክ ለመግዛት ማሰብ በራሱ ሌሎችን ያለማክበር በሽታና የዘር ፖለቲካን የሚያቀጣጥል ነዳጅ በመሆኑ ህወሃት ለሁሉም ዓይነት ለውጥ ራሱን እንዲያዘጋጅ ወዳጆቹ ሊያስገድዱት ግድ ይላል። ሌሎችም ቢሆኑ ልዩነታቸውን ለህዝብ ፍርድ አስቀምጠው የጋራ መድረክ በመፍጠር አገሪቱ ላይ እርቅ ሊሰፍን የሚችልበትን ሁኔታ ለማፋጠን አስገዳጅ ወደ መሆን የሚሸጋገሩበት መላ ሊፈልጉ ይገባል።
ሚዲያ አስፈላጊነቱና ህዝብን በማንቃት በኩል ያለው ሚና የገዘፈ መሆኑ በውል የታወቀ ስለሆነ ኢህአዴግም ሆነ ህወሃት ነጻ መሬት ካልያዘ፣ ተዋግቶ ድል ካልጨበጠ… ከምሉ እርቅን ከሚያሰልሉ እልኸኛ አስተሳሰቦች በመውጣት እገሌ ከገሌ ሳይባል ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ውዳጆቹ እጁን ሊጠመዝዙት ግድ ነው።
ምስኪን እናቶችን እናስብ፣ ተስፋቸው የሚቀጠፍባቸውን ወላጆች እናስብ፣ በማያውቀው ሊጠፋ ለተዘጋጀው አዲስ ትውልድ እናስብ፣ ኢትዮጵያ መጥፋቷንም እናስብ፣ አገር አልባ እንዳንሆን እናስብ፣ የሚገስጽ፣ የሚያርቅ፣ ተው የሚሉ አባቶ እንደሌሉን እናስብ፣ በአምላክ ጥበበ የምንኖር ባዶዎች እንደሆን እናስብ፣ የሃይማኖት መሪዎሽም እንደሌሉን እናስብ፣ እንዳንከስም እናስብ…..የዘር ፖለቲካ የሰውነትን  ልቡናና ቀልብ የሚበላ ቫይረስ ነውና   ከዘር ከረጢት የምንወጣበትን መንገድ እኛው ራሳችን እንፈልግ። ሚዲያዎችም እኛን ጨምሮ በሰከነና በረጋ መንገድ እንስራ። ሲያልቅ አይምርምና ሁሉም በጥበብ ይሁን። ከዘላለም ሃዘን እናመልጥ ዘንድ እኛው ራሳችን እንትጋ!!  ዛሬም ተማሪዎች ሞቱ!! ነገስ? ጉዞው ወዴት ነው? ካልሆነ ሁሉም በየክልላቸው ይማሩ!! 

አቶ አዲሱ ቂጤሳ የሚከተለውን ብለዋል

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ ትናንት ታህሳስ 2/2010 ከምሽቱ 6:00 ሰዓት አካባቢ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ በተሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት እንዳለፈ መረጃ ደረሶናል። በዚህ ግጭት የተሳተፉ እና የሰው ህይወት በማጥፋት የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በዚህ ግጭት ምክንያት ውድ ህይወታቸውን ላጡ ወንድሞቻችን የተሰማንን ልባዊ ሀዘን እየገለፅን ለዘመድ ወዳጆቻቸው መፅናናትን እምመኛለን። ዝርዝር መረጃ እንደደረሰን እናቀርባለን።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *