የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች- እንደምን አመሻችሁ በቅርቡ በተለያዩ የሐገራችን አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሐገራችንን ሰላም እና መረጋጋት የሚያውኩ ችግሮች ታይተዋል፡፡ በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የህዝብ ሐብት እና ንብረት ወድሟል፡፡ እጅግ የምሳሳለትን የሰላም፤ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግባንታ ሥራችንን የሚጎዱ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መከሰቱ ይታወቃል፡፡ የፈዴራል መንግሥት ከሁለቱ የክልል መንግሥታት ጋር በቅርበት በመሥራት ችግሩ እንዲቀረፍ ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ጉዳዩ እልባት ወደ ሚያገኝበት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ነበር፡፡ ሆኖም በቅርቡ ግጭቱ እንደገና ያገረሸ ሲሆን በነጹሀን ዜጎቻችን ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳትና የሐብትና ንብረት ውድመት በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ በድሮሎቢ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ ለደህንነታቸው ሲባል በአካባቢው በአቅራቢያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች የጅምላ ግዲያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በራሴና በፌዴራል መንግሥት ስም በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰው አዳጋ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጅዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላው የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡