ወዳጆቼ ስለጨቋኝ ከተማ ቢወራልዎ እርግጠኛ ነኝ ከተማዋ በበርካታ ችግሮች የታጠረች፣መሰረተ ልማቷ በበቂ ሁኔታ ያልተሟላና ህዝቦች የሚጉላሉባትና የሚ ማረሩባት ከተማ ሳትሆን አይቀርም የሚል ግምት ሊያድርብዎት ይችላል፡፡ እርስዎ ይሄን ቢያስቡም የከተማዋ የጨቋኝነት ምስጢር ግን ሌላ ነው፡፡

በብዙ የዓለማችን ከተሞች የኛንም ጨምሮ ሰዎች አንድን ድርጊት እንዳይፈፅሙ የሚከለክሉ በርካታ ምልክቶች በየቦታው ተተክለው ተለጥፈው ወዘተ ይገኛሉ፡፡ከሰሞኑ ስካይ ኒውስ ለንባብ ያበቃው ፅሁፍ እንደሚያመለክተው፤ ዳውሊሽ የተሰኘችውና በደቡብ እንግሊዝ የባህር ዳርቻ አካባቢ የምትገኘው ከተማ በበርካታ ‹‹ ይህን ማድረግ ክልክል ነው!!›› በሚሉ ምልክቶች በመጨናነቋ በጎብኚዎች ዘንድ ‹‹ጨቋኟ ከተማ›› የሚል ስያሜን አትርፋለች፡፡

ከተማዋን ለመጎብኘት ዕድል ያጋጠመው በድረገፅ ላይ የሚፅፍ አንድ ግለሰብ በከተማዋ የተለጠፉት እና የተሰቀሉት ከልካይ ምልክቶችን ከታዘበ በኋላ ‹‹ፍፁም እንደ ልብ እንዳልንቀሳቀስ አግደውኛል›› ሲል በምሬት ገልጾታል፡፡

ዘገባው እንደሚያስረዳው፤ በከተማዋ ‹‹ወፎችን መመገብ ክልክል ነው!!››፣‹‹ውሻ ይዞ መንቀሳቀስ ክልክል ነው!!››፣ ‹‹ለዳክዬዎች ፍርፋሪ ዳቦ መመገብ ይመርዛቸዋል!!›› የሚሉና ሌሎችም ከልካይ ምልክቶች እጅግ የበዙ ከመሆኑ አንጻር ከተማዋን የጎበኘው የድረ ገፅ ፀሐፊ ‹‹ዳውሊሽ የድሮ ከተማ መስላለች፤ በበርካታ የክልከላ ምልክቶች ተጨናንቃለች በዚህም በጎብኚዎቿ ላይ የጭቆና ስሜት አሳድራለች፡፡›› ሲል ነበር የገለፀው፡፡ ጎብኚዎች ወደከተማዋ ሲመጡ የክልከላ ምልክቶቹን ከሚያዩ ይልቅ «በእንኳን ደህና መጣችሁ» መልዕክት መቀበል ያስፈልጋል። ሲልም ነው በጽሑፉ ላይ ያሳፈረው፡፡

በህይወት ዘመኑ ከጎበኛቸው ቦታዎች ሁሉ ይህች ከተማ የተለየች መሆኗን አመልክቶ፣ በዚህ ዓይነት የክልከላ ምልክት የተጨናነቀ ከተማም አጋጥሞት እንደማያቅም ጠቁሟል፡፡

የከተማዋ ከንቲባ አማካሪ ሚስተር ማረቲን ሪንግሊ በበኩላቸው በከተማዋ በርካታ የክልከላ ምልክቶች መኖራቸውን ተከትሎ ጎብኚዎች ቅሬታ እያስነሱ መሆኑን በመገንዘብ ምልክቶቹን በመቀነስ ከተማዋ በጎብኚዎች ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት እንዲኖራት እንደሚሰራም ለስካይ ኒውስ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከተማዋ ጨቋኝ ናት ለማለት አልደፍርም፤ይሁን እንጂ አንዳንድ የክልከላ ምልክቶችን በመቀነስና በተሻሉ ቃላት ቀይሮ በመፃፍ ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል ሲሉም የከንቲባው አማካሪ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጨቋኟ ከተማ››

አስናቀ ፀጋዬ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *