ህይወት ቁጥር ስፍር በሌላቸው ተከታታይ ፈተናዎችና ከባድ ጥያቄዎች የተሞላች ትምህርት ቤት መሆኗን ማንም ባለበት የእድሜ ዘመኑ የሚረዳው ጉዳይ ነው። ህይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ በተለያዩ ዓይነት ፈተናዎች ውስጥ ያልፋል፤ ይፈተናልም። ይህ የሚሆነው ደግሞ ወደውም ሆነ ተገደው ሊሆን ይችላል። ፈተናውን የመፈተኑ ጉዳይም እንዲሁ በጥሩ መልኩ የሚጠናቀቅና በውድቀት የሚያልፍ የሚሆንበት አጋጣሚም ሰፊ ነው።ፈተናን በውጤታማነት የማለፍ ስኬት የገጠመው ተሸላሚ ሲሆን፤ ፈተናው የከበዳቸውና ለሽልማት የሚያበቃቸውን ውጤት ያላገኙ ደግሞ ሽልማቱ ያመልጣቸዋል።

 ራሳቸውም እንዳያንሰራሩ አድርጎ ይመታቸዋል። ውድቀታቸውም የከፋ ይሆናል። የፈተናው መቅለልና መክበድ የሽልማቱን ዓይነትና መጠኑን እንዲሁም የውድቀቱን አይነት ይወስንለታል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ ይዘናቸው የቀረብነው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን የወደቁትን አንሱ መርጃ ማህበር ውስጥ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው ከህይወት ጋር ግብ ግብ የፈጠሩት አቶ አዕምሮ አወቀ አንዱ ናቸው። 
እንግዳችን በወጣትነት እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ በዳኝነት ሥራ ላይ ተሰማርተው አገርን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፤ አሁን ግን አለሁ ያላቸው አልነበረም።ከየወደቁት አንሱ  መርጃ ማህበር በስተቀር። ለጡረታም የሚሆን ገንዘብና ጉልበት እንዲሁም ልጅ የላቸውም። ስለዚህም ውጪ ላይ እንደሚጣል ቆሻሻ መንገድ ዳር ወድቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን ሳይደግስ አይጣላም ነውና ነገሩ ለነፍስ ያለ አንስቷቸው ዛሬ በመጦር ላይ ይገኛሉ። ታዲያ እኝህ የአገር ባለውለታ እንዴት መንገድ ዳር ወደቁ፤ መጀመሪያ የነበረው ህይወታቸው ምን ይመስላል ነበርና መሰል ጉዳዮችን በመዳሰስ በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ እንዲህም መሆን እንዳለ ለማስገንዘብ እንግዳችን አድርገን አቅርበናቸዋልና ከእርሳቸው ተማሩ አልን። መልካም ንባብ። 
ልጅነት 
እንግዳችን ተወልደው ያደጉት በደቡብ ጎንደር ሲሆን፤ በስንት ዓመተምህረት እንደተወለዱ ግን በቅጡ አያውቁትም። ምክንያቱም በወቅቱ ልደት፣ የውልደት ቀን  ማስታወስ ተብሎ ነገር ስለማይታወቅ ነው። በእርግጥ የተወለዱበት ጊዜ በዚህ ወቅት ነው ማለት ይቻል ነበር። ይሁንና እርሳቸው በእድሜ የገፉ ስለሆኑ ይህንንም ለማስታወስ ተቸግረዋል። ስለዚህ ዛሬ ላይ ሲታዩ በዘጠናዎቹ ቤት እንደሚገኙ ለተመለከታቸው ሰው መገመት አያዳግትም። 
እንግዳችን አቶ አዕምሮን ስናገኛቸው በአንድ ክፍል በርከት ብለው አልጋ ከያዙ ሰዎች መሀል አረፍ ብለው ነበር። ይሁንና ስለሳቸው ማንነትና ታሪክ ቅድሚያ ስለሰማን ታሪካቸውን ለመስማት በጣም ጓጉተን ነበር። አጠገባቸው ስንደርስም በከባድ ዕንቅልፍ ውስጥ ነበሩ። የድርጅቱ መስራችና ጠቋሚያችን አቶ ስንታየሁም ጠጋ ብለው ሊቀሰቅሷቸው ሞከሩ። በቀላሉ ግን አልተነሱም ነበር። ጥቂት ቆይቶ አዛውንቱ  እንደመንጠራራት ብለው ከዕንቅልፋቸው ባነኑ። አጋጣሚው እንዳያልፈን በመስጋትም ቶሎ እንዲቀሰቀሱ ጠየቅን። እርሱም ስማቸውን በመጥራት ቀሰቀሳቸውና ለምን እንደመጣን ነገራቸው። 
እሺታቸውን ገለጹ፤ ይሁን እንጂ እስኪረጋጉ እንጠብቅ በሚል ትንሽ ደቂቃ ስንጠብቅ እርሳቸውም የሄድን መስሏቸው ይሁን ጸሎት ሳያደርጉ ላለማውራት በግዕዝ ቋንቋ ጸሎታቸውን ይደግሙ ጀመር። በዚህ መካከል የግዕዝ ሊቅነታቸውን ተረዳን። ምክንያቱም አይነስውር ሳሉ መጽሐፍ የሚያነቡ ያህል ለረጅም ጊዜ ያነበንባሉ። ስለዚህም መጽሀፉን በቃላቸው እንደሚሉት ገመትን። ነገሩን አልን እንጂ «አይነስውራን ልበ ብርሃን ናቸው» ይባል የለ። እርሳቸውም እንዲሁ ሳይሆኑ አይቀሩም። ከብዙ ቆይታ በኋላ ነበር ለወጋችን መነሻ የሆነውን ጥያቄ ያቀረብነው። ምክንያቱም ጸሎታቸው ሲቋረጥ አይወዱም የሚል ነገር ሰምተናልና ነው። 
ከእሳቸው ጋር ለመወያየት ጮክ ብሎ መናገር ያስፈልጋል። ጆሯቸው በአግባቡ አይሰማም። አይኖቻቸውም ታውረዋል። እናም ህይወታቸውን እንዲያወሩን በጠየቅናቸው መሰረት ብዙ ፋታ እየወሰዱ እየቀነጠቡ ነገሩን። እንግዳችን አቶ አዕምሮ ምንም እንኳን የእድሜ ባለጸጋ ቢሆኑም የልጅነት ትዝታቸው ግን መቼም ከህሊናቸው አይጠፋምና ቁልጭ አድርገው ነበር ልጅነታቸውን እንዴት እንዳሳለፉት ያወጉን። በአካባቢው አሉ የሚባሉና የሚያስታርቁ አባት አሏቸው። ስለዚህም በሰፈሩ ልጆች ዘንድም ይሁን በትልልቅ ሰዎች ዘንድ እርሳቸውን የማይወድ ሰው አልነበረም። የካህን ዘርም ስለሆኑ ለእርሳቸው ልዩ ክብርን ከእያንዳንዱ ሊቅ ዘንድ ይቸራቸዋል። ታዲያ ይህ ሁኔታ ደግሞ እርሳቸውንም የቤተክህነቱ ተማሪና ቅኔ ዘራፊ እንዲሆኑ አስገድዷቸው ነበር። ስለዚህ በቅርቡ በሚገኙት የአብነት ትምህርት ቤቶች እየተዘዋወሩ ትምህርት ሲማሩ ቆዩ። 
የቤተ ክህነት ትምህርት እነርሱ ላሉበት ዘመን እጅግ ልዩ ትኩረት የሚሰጠውና ትልቅ ቦታ ላይ እንዲቀመጡ እድሉ የሚመቻችበት ጊዜ ነበር። ስለሆነም እርሳቸው «ሀ» ብለው የጀመሩትም «ፐ» ብለው የፈጸሙትም እዚሁ ቄስ ትምህርት ቤት ነው። በእርግጥ በወቅቱ እንደ ዛሬው መዋዕለ ህፃናት/ኬጂ/ የሚባል ትምህርት ቤት ስላልነበር ቤተሰቦቻቸው እንዳያሳፍሯቸው ሲሉ በቤት ውስጥ ያስጠኗቸው ነበር። ስለሆነም እንግዳችንም ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤታቸውን  የጨረሱት ቤተሰቦቻቸው ጋር በነበረው ትምህርት ነው። በዚህ ቤት ፊደልን ልቅም አድርገው ሸምድደውና በቂ የሚባለውን እውቀት ቀስመው ወደ የኔታ ቤት አመሩ። ማለትም በቅርብ ባለው የቄስ ትምህርት ቤት። 
ሌላኛው የትምህርት ጉዞ
እንግዳችን አቶ አዕምሮ በቤት ውስጥ የቀሰሙት እውቀት ጠቅሟቸው ኖሮ በአንድ ጊዜ ከፊደል ትምህርት ወደ ወንጌል ተዘዋወሩ። ከዚያም በእጥፍ እውቀታቸውን አጎልብተው ወደ ዳዊት፣ ድጓና ሌሎች ትምህርቶችን በተከታታይነት መማሩን ቀጠሉበት። ከትምህርቱ ጎን ለጎንም በአካባቢው ያለውን ማህበረሰብ በድቁና ማገልገላቸውን ተያያዙት። በዚህ ደግሞ ብዙዎች ያደንቋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
 ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ ልጃቸው ከዚህም በላይ በቤተክህነት ትምህርቱ እንዲቀጥሉ ይሻሉና ሁልጊዜ ይመክሯቸዋል። ይህ ምክራቸው በውስጣቸው የሰረጸው የዛሬው አዛውንት የትናንቱ ወጣት አቶ አዕምሮ ቅኔን ለመዝረፍ የጎጃሙን፣ የጎንደሩን ጨርሰው የሸዋውን ለመመልከት እስከ ሱልልታ ድረስ በእግራቸው ጭምር ተጉዘው ትምህርቱን መከታተል እንደቻሉ ያወሳሉ። በተለይ ሱልልታ ላይ መጥተው ትምህርት ለመቅሰም መምጣታቸውን ለመምህራቸው ሲናገሩ ገጥሟቸው የነበረውን ጉዳይ እጅግ አስገራሚ እንደነበር አውግተውናል። ሁኔታውን ለመልመድም ለጊዜው እንደተቸገሩ ያስታውሳሉ።
 በእርግጥ ይህ ባህሪ በሁሉም ቅኔ ተማሪም ሆነ የአብነት ተማሪ ህይወት ውስጥ የሚያጋጥም ነው፤ ነገር ግን ከቅኔ ቤት ቅኔ ቤት ይለያያል የሚሉት እንግዳችን፤ በዚህ ቤት ባህሪ ከአካባቢው ጋር የተቆራኘ ነበር። ይኸውም ተማሪው እየለመነ ሳይሆን እየሰራ እንዲማር ይደረጋል። በቆሎ ተማሪ ዘንድ ለምኖ ካልተማረ በስተቀር ትምህርቱ አይገባውም ተብሎ ስለሚታመን የትም ይሁን የትም ይለምናል። እዚህ አካባቢ ግን ይህ የለም። ስለዚህም ለእንግዳችን ልዩ ነገር እንዳገጥማቸው  ነው የነገሩን። 
መጀመሪያ አካባቢ «በርከት ያለ ስንቅ ሰንቃችሁ ካልመጣችሁ በስተቀር ይህ ቤት ለምናችሁ የምትተዳደሩበት ወይም የምትማሩበት አይደለም» ሲባሉ ያው የቅኔ ቤቱ ወይም የተማሪ ቤቱ መምህራን የተለመደ ፈተና ነው ብለው አምነው አልፈውት ነበር። ስለዚህም በቂ የሚሆነንን እህልና ድርቆሽ ይዘናል ሲሉ መልሰው እንዲቀበሏቸው አደረጉ። የሆነው ሆኖ ግን ትምህርቱን መከታተል ሲጀምሩ ያጋጠማቸው ተቃራኒ ነበር። የተባሉት ነገር እውነት ሆነ፤ መለመን አይቻልም። ነገር ግን ሰሌን እየሰሩ ለማህበረሰቡ በመሸጥ ራስን ማስተዳደር ይቻላል። ስለዚህም እንግዳችንም ሆኑ ሌሎች ተማሪዎች ይህንን ማድረግ ግዴታቸው ሆነ።  ማድረግ እንዳለባቸውም አመኑ።
 ግን አንድ ነገር በውስጣቸው ይፈትናቸው ነበር። ይኸውም ትምህርቱ አይገባኝ ይሆን? የሚለው ነው። የመለመኑ ዋና አላማ ታጥቶ ሳይሆን የችግርን ምንነት ተረድቶ ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት መስጠት ስለሆነ አሁን ይሰራል የተባለው ደግሞ ቁጭ ብሎ የሚሰራ መሆኑ ችግሩ እንብዛም አይታይምና ስጋትን ፈጠረባቸው። የሆነው ሆኖ ግን እንደምንም ቦታውንና ባህሪውን ለመዱት፤ በውስጡም ገብተው ውሃ ውስጥ እንደገባ አሳ ቅኔውን ያጣጥሙበት ጀመር። እንደውም ለሌሎች አርአያ የሚሆን ሥራ ማከናወን ጀመሩ። ሊቅነታቸውም ገኖ በመውጣቱ ብዙዎች ስለ እርሳቸው ያወሩና ያደንቋቸው ጀመር። በዚህ ሁኔታም ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመለሱ።  
መመለሳቸው ደግሞ አንድ የሚያስገርም እድልን አጎናጸፋቸው። ይኸውም ለቤተሰቦቻቸው በአካባቢው ዘንድ የሚሰጠው ግምት ከትምህርት አዋቂነታቸው ጋር ተዳምሮ በፍትህ ቢሮ የጽህፈት ሥራ እንዲጀምሩ እድሉ ተመቻቸላቸው። በእርግጥ በወቅቱ በአብነት ትምህርት ረቅቆ የወጣ ሰው ለብዙ የመንግስት መስሪያ ቤት ሥራ በኃላፊነትም ሆነ በተለያየ መልኩ ይታጭ ነበር። እንዲሰራም የተለያዩ አጋጣሚዎች ይፈጠሩለታል። ስለዚህም እንግዳችን አቶ አዕምሮም ይህንን እድል ነው ያገኙት። 
ወደ አዲስ አበባ መጥተው ፍትህ ቢሮ ውስጥ በፍትሀ ብሔር ጸሐፊነት እንዲቀጠሩም ተደረገ። በዚሁ ቢሮ በየጊዜው ያላቸው ብቃት እየተለካ እድገት እንዲያገኙም ሆኗል። በተወሰነ ዓመታት ውስጥም የዳኝነት ቦታን ለመረከብ ችለዋል። አቶ አይምሮ አወቀ ረጅሙን የዕድሜ ዘመን ያሳለፉትም በዚሁ በዳኝነት ሙያ ነው። በ1960ዎቹ መጀመሪያ በየአገሩ እየዞሩ ብዙዎችን ዳኝተዋልም። ዛሬ ላይ ሆነው የትላንት ማንነታ ቸውን ሲያስቡት ግን እንባ ይተናነቃቸዋል። ባሳለፉት መልካም ጊዜ የነበራቸው እውቅናና የሰዎች አክብሮትም ከፊታቸው ይደቀናል። ብዙዎች ከሚገኙበት ክፍል ተንጋለው ከተኙበት አልጋ ሲታዩ የመልካቸው ወዘና ፍጹም ጤነኛ ያስመስላቸዋል። እሳቸው ግን የሚናፍቁትን ጤና ካጡ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁንና አንደበተ ርቱዕነታቸው ግን ዛሬም እንዳለ ነው። ሲናሩ የሚያፈልቋቸው ቃላት ጨዋነታቸውን ይመሰ ክራሉ። በንግግራቸው መሀል ግጥም የሚለው ዕንባቸው እየተናነቀ ቢረብሻቸውም በዚያ ትንሽ እረፍትን በሚሰጠው እፎታ ይገቱትና ያለፈውን ህይወት መናገር ይጀምራሉ። 
በወቅቱ በስማቸው የተከበሩ፣ በዝናቸውም የታወቁ ነበሩ።በስራ በቆዩባቸው ዓመታት  ለተበደለ ፍትህን፣ ህግን ለጣሰም ቅጣትን ሲበይኑ ኖረዋል። የስራ ባህሪያቸው በአንድ  ስፍራ የማያቆያቸው በመሆኑም ብዙዎቹን የአገሪቱን ክፍለ አገራት አካለዋል። ለአብነትም ከአዲስ አበባ ሲወጡ ወደ ጅማ አምርተው ነበር። ከዚያም በዚሁ በጅማ አካባቢ ሰኮሮ በምትባል ቦታ ኃላፊ እንዲሆኑ ተደርጎም ተልከው ሰርተዋል፤ የከተማዋ አስተዳዳሪ በመሆንም ብዙዎችን መርተው ነበር። 
የቤተሰብ ሁኔታ
 እንግዳችን ከአንዱ አገር ወደ አንዱ ሲሉ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ትዳርን ሞክረዋል። ባሌ ጎባ በነበሩ ጊዜ አብረዋቸው የቆዩ ባለቤታቸውን የፈቱት «አትወልድም» በሚል ምክንያት ነበር። በጊዜው ትዳራቸውን በትነው የሞቀ  ጎጇቸውን ሲርቁም አንዳች ፀፀት አልተሰማቸውም። ጅማ ተቀይረው አዲስ ህይወት  እንደጀመሩ ደግሞ  ሌላዋን ቆንጆ አይተው ተመኙ። በዘመኑ ታዋቂ ዳኛ ለነበሩት ታላቅ ሰው የጋብቻውን  ፈቃድ የሚነፍግ የለምና በደስታ ተቀበሏቸው። እናም በአዲሱ ትዳራቸው ጥቂት እንደቆዩ ግን ወደ ሌላ አገር ሊቀየሩ መሆኑን ሰሙ። ምርጫ አልነበራ ቸውም። ማቄን፣ ጨርቄን ሳይሉ ለመንገዳቸው ጓዛቸውን ሸከፉ። 
ይህ ሲሆን ደግሞ አዲሷ ሙሽራ አልተከተ ለቻቸውም፣ የተጸነሰ ፍሬያቸውንም ለማየት አልታደሉም። ወደ ተመደቡበት ቦታ አመሩ፤ ልጃቸውም መወለዱንና ወንድ መሆኑን የሰሙት አመሻሽ ላይ ነበር። ይሁንና በጊዜው የተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት ከባድ ስለነበረ ፋታ ሰጥቷቸው ሊያዩት አልቻሉም። ስለዚህም በተመደቡበት ቦታ እያሉ ዓመታት ነጎዱ። 
በሰሩባቸው ዘመናት ግን ለእኔ የሚሉትን ቅርስ አልያዙም። ስለተወለደው ልጅ ማንነትም አላወቁም። እንዲህ የለፉበትና ጉልበታቸውን የጨረሱበት ሥራም በእድሜ ብዛት ሊያገላቸው ግድ ሆነ። አዲስ አበባ እንደገቡ የዳኝነት ሙያቸውን ተሰናበቱት። ምክንያቱም ያው እድሜ ሲደርስ ጡረታ መውጣት አለና ነው። ታዲያ እርሳቸውም በእድሜያቸው ብዛት እንደ ድሮው የሚፈጥኑ፣ በጤንነትም የሚሮጡ ጎበዝ አልሆኑምና በሌላ ዘርፍ ተሰማርቶ የመንግስት ሥራ ለማከናወን አልቻሉም ነበር።  
ዕድሚያቸው ሲገፋና አቅማቸው ሲደክም እርጅና ጉልበታቸውን ተረከበው። በድንገት የዓይናቸውን ብርሀንም አጡ። ይህ ደግሞ ተስፋ አስቆርጦ ሆድ አስባሳቸው። ይሄኔ ነበር የወጠኗቸውን በርካታ ጎጆዎችን ወደኋላ በትዝታ በመመለስ ያሰቧቸው። ተወልዷል ስለተባለው ወንድ ልጅም ጉጉት ያደረባቸው።ይባስ ብሎ ደግሞ በዕድሜያቸው ማምሻ «ግማሽ ጎኔ» ሲሉ የቀረቧቸውን ሴት እንኳን በባህሪያቸው አስቸጋሪነት አጥተዋቸዋል። ይህ እውነታ ደግሞ በስተርጅና መልሶ ትዳራቸውን እንዲያፈርሰው ሆኗል። አጋጣሚው ድንገት ከሚስታቸው ለተለዩት አይነስውሩ አባወራ  መግቢያ  አሳጥቶ አስጨነቃቸው። 
ሌላው የሥራ አማራጭ
በአዲስ አበባ ከተማም ቅድስተማርያም ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ መኖሪያ ቤት ተሰቷቸው መስራት ጀመሩ። በልጅነታቸው የያዙት የቄስ ትምህርት ስንቅ ሆናቸውና በመሪጌታነት ለማገልገል ዕድሉን ሰጣቸው።  ዕድሜና ጤና ማጣት የተፈራረቀባቸው ዳኛ አዕምሮ ግን እዚህም ቢሆን ብዙ ያልተመቻቸ ነገር ነበር የገጠማቸው። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ እንዳሰቡት ህይወትን ሊቀጥሉ አይችሉም። ምክንያቱም የዓይናቸው መታወርና የጆሯቸው በወጉ አለመስማት ኑሮን አክብዶ «የሰው ያለህ» አሰኝቷቸዋልና ነው። ለነገሩ ማን እማይሰራና የደከመን ሰው ይፈልጋል?ማንስ ሳይሰሩ መቀለብን ይሻል? ለዚህም ይመስላል በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመንፈስ እርካታ ሲባል በሚቸሯቸው ምግብና አልባሳት እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁስ ችሮታ የተወሰኑ ዓመታትን የቆዩት። 
የማታ ማታ ግን ይህም ቢሆን ባለበት መቀጠል አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ ወደ እርሳቸው ተጠግቶ ንጽህናቸውን የሚጠብቅላቸው የለም፤ ቤታቸውንም ቢሆን እንዲሁ የሚያጸዳው ጠፍቷል። ስለዚህም እንኳን እርሳቸው ጋር ሊቀረብ በአቅራቢያው ሆኖ ቅዳሴ ለማስቀደስም ሽታው አያስጠጋም። ቤቱ መጸዳጃም ሆኗል፤ ልብሳቸውም አይቀየርም። ይህ የተሰማቸውና ሰውዬው እንዲህ መቀጠል እንደሌለባቸው ያመኑት ካህናትና የቤተክርስቲያኑ አስተዳደሮች እኝህን ባለውለታ ላለመጣል ወስነው ወደ አንድ መርጃ ድርጅት ያመራሉ። ይኸውም የወደቁትን አንሱ የሚባለው ሲሆን፤ ያለባቸውን ችግር በመንገር እንዲያነሷቸው አደረጉ።  ድርጅቱም  ከወደቁበት ሊያነሷቸው፣ ልማደኞቹ እጆቻቸውንም ፈጥነው  ሊያነሱላቸው በሰፊው ዘረጉ፤ አንስተውም የሚገባቸውን እያደረጉላቸው ይገኛሉ። 
እንግዳችን አዛውንቱ አዕምሮ በንግግር ለዛቸው የተካኑ፣ በጨዋታቸውም ተራው ሰው ሳያውቅ የሚተርቡና የሚተራረቡ፣ አባባላቸው በአዕምሮ ላይ የሚጻፍ እንጂ የማይዘነጋ ነበሩ፤ ናቸውም። በተለይ የሚያዩትንና የሚታዘቡትን ነገር ሁሉ በጨዋታና በቀልድ እያዋዙ የሚገልጹበት ስልት ልዩ መሆኑን በወቅቱ ከነበራቸው ንግግርና በዚያ ወላልቀው በሚታዩት ጥርሶቻቸው መሀል ብልጭ ሲያደርጉና ፈገግታቸውን ሲገልጹ እንዲሁም  ያሳለፉትን ጊዜ ሲያወጉ ሲመለከቱ እውነትም በችግር መሳቅ እድሜን ያረዝማል፤ ችግርንም ያስረሳል እንዲሉ ያደርጎታል። 
ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ ቅዳሴ ማርያምን፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን እንዲሁም የኖሩበትን ቅኔን ከነ-አገባቡ በሚገባ እንዳጠናቀቁ የሚገልጹት እንግዳችን፤ በእድሜ መግፋት ምክንያት ዛሬ ማየት ባይችሉም የዚያን ጊዜው አዕምሮ ዐይናቸው እንጂ ልባቸው ብርሃን ነበረ እንዲሉ ይገደዳሉ። ወላጆቻቸውን በሞት በመነጠቃቸውና ልጃቸውን ባለማወቃቸው ዛሬ ላይ ሕይወታቸው ጎደሎ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ሲመለከቱ ደግሞ በእጅጉ ያዝኑላቸዋል። ከላይ እንደተባለው እጅ የዘረጋላቸው አካል አለ እንጂ የህይወት ፈተናው ከዚህም አልፎ እንዳይታዩ ያደርጋቸው እንደነበር ሲያስቡ ደግሞ የችግር አስከፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አይወስድብዎትም። 
እውቀትን ለመቅሰም ተማሪው ዝናቸውን እየሰማ፣ በመምህርነታቸው እየተደነቀ ለመማር ወደሚጎርፍበት ትምህርት ቤት ሁሉ በእግራቸው ጭምር እየተጓዙ ልምድን ወስደዋል። የተማሪነት ባህሪን በየሄዱበት ሁሉ አውቀዋል። ስለዚህም ለቤተክርስቲያን ይህንን እውቀት በመጠቀም ከልባቸው አገልግሎት ሰጥተዋል።  በመንግስት መስሪያ ቤትም ቢሆን እንዲሁ ያለምንም ፋታ ከ36 ዓመታት በላይ በችሎት ጸሐፊነትና ዳኝነት አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም ሰርተዋል። ይሁን እንጂ ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ሲወጡ ጉንዳን ወሯቸው፣ ትል እየፈላባቸው ነበር የወጡት፤በመንግስት መስሪያ ቤት ሳሉም ምንም እንኳን በደርግ ጊዜ ጡረተኛ ሆነው ቢወጡም ዛሬ ግን ጡረታ የሚባል አይከፈላቸውም። ውለታቸው ሙሉ ለሙሉ ተዘንግቷል። ስለዚህ አለኝታና መከታ የሆናቸው መርጃ ድርጅቱ ብቻ ነው።
 በጠባያቸው አስተዋይ ብልህና ንቁ እንዲሁም ቅን አሳቢ ሰው እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከውድቀታቸው ያነሳቸውና እቅፍ ድግፍ አድርጎ የሚያኖራቸው መርጃ ድርጅት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ አንዱ ሲሆኑ፤ ችኩልነትንና ሽንፈትን የማይወዱ፣ የማስተማር ፍቅር የተሰጣቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ። ለብዙ ሰዎች ዐይነ-ሥውር መሆን ድቅድቅ ጨለማን ያህል ከባድ ነው። እንደ አዛውንቱ አዕምሮ ላሉ ግን መንፈሰ-ጽኑ ሰዎች የዐይን ብርሃን የላቸውም ግን ያያሉ፣ ጆሯቸውም ላይሰማ ይችላል ግን ያዳምጣሉ፣ መልስም የመስጠት ብቃታቸው ዛሬ ላይ ካለው ወጣት በእጅጉ የላቀ ነው ይላሉ። አንደበታቸውም ተዘግቶ ሊሆን ይችላል ግን ዲዳ አይደሉም፤ ዐይነ-ሥውርነታቸው ከማየት ከመመራመርና ከማስተማር እንዲሁም በጎ ነገር ከማሰብ አልከለከላቸውምም ባይ ናቸው። ስለ እንግዳችን አቶ አዕምሮ ብዙ ነገር ማለት ይቻል ነበር። ይሁንና የእርሳቸው እረፍት ማጣትና ድካም ብዙ እንዳናወራቸው ገድቦናል። በተጨማሪም አምዳችን የሚይዘው ቦታ ውስን ነውና አንድ ሀሳብ ብቻ ሰንዝረን ሀሳባችንን እንቋጭ።
« የዕድሜ ባለጸጎችና የአገር ባለውለታዎች ዛሬ ላይ ሰርተው ውለታን መመለስ አይችሉም። ስለዚህ አገርን የሚወድ ሁሉ በፍቅር ሊንከባከቧቸውና ውለታችሁ ይህንን አድርጓል ሊሏቸው ይገባል። ታዛ ሆኖ ማስጠለልም ያስፈልጋል። የማይሰለቹት ዓይኖችና ሰፋፊ እጆችን በመዘርጋትም አለሁላችሁ የሚላቸው ሰው ያስፈልጋቸዋልና ባለውለታዎቻችንን  እናስብ» መልዕክታችን ነው። ሰላም!

ጽጌረዳ ጫንያለው Addis Zemen

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *