” አሁን በአገሪቱ ከሕገመንግስት ዉጭ በሰዉ ልጅ ላይ እየተፈፀመ ያለዉን የሰበዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ስላለባቸዉ  ፓርላማዉ ከእሳቸዉ ጋር ሊወያይ ይፈልጋል። እኛም እንደ ፓርላማ አባላት መጠየቅ የምንፈልገዉ የሰዉ ግድያ ለምን አልቆመም? በመንግስት በኩል ይህን ለማስቆም እስካሁን ምን እየተሰራ ነዉ? ይህን ለማስቆም ምን መደረግ አለበት፣ ለምን አልቆመም፣ ለምን አላስቆማችሁም? የሚሉ ጥያቄዎች በዋናነት የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸዉ።»

ሙሉ በሙሉ ኢህአዴግ የሚወከልበት የተወካዮች ምክር ቤት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አገሪቱ የገባችበትን ብሄር ላይ ያተኮረ ግጭት አስመልክቶ ባስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጡዋቸው ጠይቀው ምላሽ ባለማግኘታቸው ሁለት መደበኛ ስብሰባ አለማድረጋቸው ተሰማ። አቶ ሃይለማሪያም ማብራሪያ እስከሚሰጡ ድረስም መደበኛ ስብሰባዎችን ለማቋረጥ አቋም መያዛቸው ታውቋል።

ሪፖርተር የምክር ቤት ምንጮቹን ጠቅሶ ሲዘግብ ጥያቄውን ያቀረቡት ምን ያህል እንደሆኑ በአሃዝ አልተመለከተም። ይሁንና ሁለቱ በፓርላማ ሰፊ መቀመጫ ያላቸው ኦህዴድና ብአዴን መሆናቸውን ገልጿል። እንደ ፓርላማ መቀመጫ ስሌት ከሆነ ይህ ቁጥር የፓርላማው አብላጫ ነው። 

ኦህዴድ 178፣ ብአዴን 134 ወንበር አላቸው። አጠቃላይ ካለው 547 የፓርላማ መቀመጫ ውስጥ ሁለቱ ድርጅቶች 312 መቀመጫዎች አሉዋቸው። ሰፊ የሕዝብ ቁጥር፣ የቆዳ ስፋትና ሰፊ የፖለቲካ አቅም ማንቀሳቅስ የሚችሉት ሁለቱ ድርጅቶች ወደዚህ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት በየድርጅታቸው መክረዋል። የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 108፣ ትግራይ ክልል 37፣ አዲስ አበባ 23 መቀመጫዎች ሲኖሯቸዉ፤ ቀሪዉ በሌሎች አጋር ድርጅቶች መሆኑን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

የአገሪቱ ትልቁ የስልጣን አካል የሆነው የኢህአዴግ ፓርላማ፤ የኢህአዴግ ” ሊቀመንበርና” ራሱ ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሰየማቸውን አቶ ሃይለማርያም ማብራሪያ እንዲሰጡት ላቀረበው ጥያቄ ከምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን ያመለከተው ዘገባ በዚሁም የተነሳ ” ባለፈው ሳምንት ሐሙስና ማክሰኞ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የፓርላማው መደበኛ ስብሰባ አለመካሄዱ ታውቋል” ብሏል።

በህወሃትና በሁለቱ አጋር ድርጅቶች መካከል ውስጥ ውስጡን ሲሰማ የነበረው ቅሬታ ወደ አደባባይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ጉዳዮች ቢነሱም ፓርላማው በዚህ ደረጃ የማፈንገጥ ምልክት ያሳያል የሚል ግምት አልነበረም። አቶ ሃይለማሪያምን ሊሞግት ጥሪ ያቀረቡት ሁለቱ ድርጅቶች ምን አቋም እንደሚይዙ በሪፖርተር ዜና አልተብራራም። ይሁን እንጂ አሁን ስጋት እየሆነ በመጣው የዘር ግጭት ላይ ያተኮረ መሆኑ ግን ተመልክቷል። 

በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት የምክር ቤቱ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በወር አንድ ጊዜ ጠርተው ትኩረት ባደረጉበት የሥራ አፈጻጸማቸው ላይ ማብራሪያ መጠየቅ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት ሁለት ጊዜ ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡

በዚሁ ግዴታ መሰረት አቶ ሃይለማሪያም ጥሪውን ተቀብለው ለሚሞገቱት ምላሽ መስጠት ግዴታቸው ነው። እንደሚባለው ፓርላማው ካመረረ ከዛም በላይ አቋም ሊወስድባቸው በህግ የተደገፈ መብት አለው።  ዘገባው መደበኛ ስብሰባዎች መቋረጣቸውን ሲጠቁም ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በፕሮግራማቸው መሠረት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ምንጮች እንዳረጋገጡለት ጽፏል።

አባ ዱላ ገመዳ አሁን በአገሪቱ በተለይም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ባለው ግድያና ረገጣ ሳቢያ በአፈ ጉባኤነት ለመቀጠል እንደሚቸገሩ መናገራቸው አይዘነጋም። በአማራና በኦሮሚያ ክልል የህዝብ እንቢተኛነት በማየሉ የህወሃት ወዳጅ የነበሩት ኦህዴድና ብአዴን እያደር ወደ ህዝብ ሃሳብ መመለሳቸው በድርጅቱ ውስጥ መፈርከስን፣ አለመተማመንን፣ ማፈንገጥን ማስከተሉ በድርጅት ልሳኖችና ደጋፊዎች ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ሁለቱ ድርጅቶች በህዝብ ለህዝብ ስብሰባቸው ላይ ያሳዩት መናበብ፣ ብአዴን ልደቱን በጨፌ አዳራጭ ሲያከብር  አባዱላ ያቀረቡት ደምና እትብትን ያቆራኘ ንግግር፣ ” የኦሮሞ ደም ደሜ ነው፣ የማራ ደም ደሜ ነው” የሚሉት መፈክሮች በእርግጥም ሁለቱ ድርጅቶች ወዴት እያመሩ ነው? የሚል ሃሳብ ካስነሳ ቆይቷል።

ባለተለመደ ሁኔታ አቶ ለማ መገርሳ በተለያዩ መድረኮች የሚያሰሟቸው ንግግሮች ላለፉት 25 ዓመታት በኢህአዴግ ደረጃ ያልተለመዱ፣ እንደውም የማይወደዱ፣ ልብን የሚነኩና የላላውን ኢትዮጵያዊነት የሚያነሳሱ መሆናቸው፣ በኢትዮጵያ የዘር ፍጅት ያሰጋቸውን ተስፋ እንዲያዩ ያደረገ መሆኑ ጽንፈኞች ኦህዴድን እንዲያጥላሉ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ከአቶ ጁነዲን ስንብት በሁዋላ አቶ አባዱላ የገነቡት ኦህዴድ ይዘቱ ” ሲፋቅ ኦነግ” በሚል መለስ በለጋው ዘመን ሲሞላፈጡበት የነበረው ዓይነት አለመሆኑንን ብዙዎች ይናገራሉ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ እየበሰለ የመጣውና የተማረውን ክፍል ያካተተው ኦህዴድ በተለይ ዛሬ ላይ በስልክ፣ በሚሞ፣ በቀላጤ ” ይህን አድርግ” የማይባልበት ደረጃ መድረሱን የሚናገሩ ክፍሎች፣ በተመሳስይ ብአዴን ውስጥ ከውስን አመራሮች በቀር ተመሳሳይ አቋም መኖሩን ያሰምሩበታል። ይህ አሁን በፓርላማ ደረጃ የተነሳው ሃሳብም የዚሁ የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች ብስለት ያመጣው መሆኑንን ያምናሉ። እናም አሁን ፓርላማው ያፈነግጥ ይሆነ? ኢህአዴግ ከኢህአዴግ ሊያፈነግጥ? ግንባሩ ወዴት? አቶ ሃይለማሪያም የሚመሩት ድርጅት ከማን ጋር ሊያብር ይገባዋል? 

የጀርመን ድምጽ ይህንን ዘግቧል ” …ግድያ ለምን አልቆመም ” የፓርላማው ጥያቄ

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *