በአሁኑ ሰዓት የሕዝብ አልገዛም ባይነት አገሪችንን እያናወጣት ይገኛል። በየቀኑ ይህንን ያህል ቁጥር ሰዉ በዚህን አካባቢ በአጋዚ፣ በመከላከያ ሠራዊት ወይም በፌዴራል ፖሊስ ተገደለ የሚል ዜና መስማት እየተለመደ መጥቷል። የዜጎች ሕይወት እንዲሁ እንደዋዛ ሲቀጠፍ ከመስማት በላይ በእጅጉ የሚያሳዝን ነገር የለም። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነዉ ደግሞ በዚህ ብቻ እንደሚቆም ዋስትና የሌለን መሆኑ ላይ ነዉ። ችግሩን መፍታት እንጂ ለምን ትከፋለህ፣ ለምንስ ብሶት አንገሸገሸህ፣ ለምንስ ምሬት ዉስጥ ትገባለህ … ወዘተ በሚል መግደልና ማንገላታት ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ግን ሊረዱት ይገባል።

በሕዝቡ ላይ የተጫነዉ ቀንበር ሊሸከመዉ ከሚችለዉ በላይ በመሆኑ ተቃዉሞዉን ለማሰማት በአደባባይ መዉጣት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ሊቆጠሩ ነዉ። አልገዛም ባይነት እየጎለበተ ቢሄድም ለብሶት መነሻ የሆኑትን የአንድ ብሔር የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት፣ ሥርዓቱ የተዘፈቀበት ሥር የሰደደ ሙስና፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር … ወዘተ አስመልክቶ ከመንግሥት በኩል አንዳችም የማሻሻያ እርምጃ የመዉሰድ ተነሳሽነት አልታየም። እንደዉም ወያኔ ይህንኑ ሥርዓት በተሻለ ብቃት ያስፈጽማሉ ተብሎ የታመነባቸዉን ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልንና ወ/ሮ ፈትለወርቅን (ሞንጆሪኖ) የሕ.ወ.አ.ት. ዋናና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟቸዋል። ሾልከዉ ከሚወጡ መረጃዎችና ድርጅቱ ካወጣዉ መግለጫ መረዳት እንደሚቻለዉ በዚህ እንደማራቶን በተራዘመ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉን ችግር ስለመፍታት የዉይይት አጀንዳ ሆኖ አለመቅረቡ በራሱ ሥርዓቱን የሚዘዉሩት ሰዎች ምን ያህል ከሕዝብ ጥቅም የራቁ መሆናቸዉን ያረጋግጣል።

ከሁሉም በላይ ያስደነቀኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ በትናንታዉ ዕለት (Dec. 18, 2017) ለሕዝብ ያስተላለፉት መልእክት ነዉ። በመግለጫቸዉ ላይ ከመንግሥት ቁጥጥር በላይ የሆነ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን አልካዱም። እንዲሁም “የጸጥታ አስከባሪ” ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች መገደላቸዉንና መቁሰላቸዉን አምነዋል። ሆኖም ግን ከንግግራቸዉ ዉስጥ ሕዝቡና ተማሪዎች ስለሚያነሷቸዉ ጥያቄዎችና ስለመፍትሔዎቻቸዉ ያነሡት አንድም ነጥብ የለም። እንደዉም የአካባቢዉን ሰላም ለማስጠበቅ በሚል ሰበብ “የጸጥታ ኃይሎች” ተግባራቸዉን እንደሚቀጥሉ ነዉ ያሰመሩበት። በተጨማሪም “የሐሰትና የተጋነነ መረጃ” ያሰራጫሉ በሚሏቸዉ የሕዝብና የግል ሚዲያዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወሰድ ለማስፈራራት ሙከራ አድርገዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ መነሻ የሆነዉ በቅርቡ እንዳዲስ ያገረሸዉ በሱማሌና በኦሮምያ ክልል የተከሰተዉ ግጭት እንዲሁም በአማራ፣ በኦሮምያና ትግራይ ዉስጥ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የተከሰቱት ብሔር ተኮር ግጭቶች እንደሆኑ መረዳት ይቻላል። በጨለንቆ ከ18 ሰዎች በላይ ለመገደልና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት የሆነዉ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ በሶማሌ ልዩ ኃይል በመገደሉ ምክንያት ለተቃዉሞ በወጣዉ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ እንደሆነ በተለያየ የዜና ማሰራጫዎች ተዘግቧል። በወቅቱ ሕዝቡ ተቃዉሞዉን በሰላማዊ መንገድ ከማሰማት ዉጭ የፈጸመዉ ሕገ ወጥ ተግባር ሳይኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጸጥታ ኃይላት” የሚሏቸዉ የመከላከያ ወይም የአጋዚ ሠራዊት በሕዝቡ ላይ ተኩስ መክፈታቸዉ ከፍተኛ ዉግዘት አስከትሏል። የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳም ድርጊቱን ከማዉገዝ ባሻገር የመከላከያ ሠራዊት አባላት በማን ትእዛዝ እንደገቡና ለምን ድርጊቱን እንደፈጸሙ አስቀድመዉ አለማወቃቸዉን በማዉሳት ይህንን ትእዛዝ የሰጡት አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊም ይህንኑ አጠናክረዋል። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸዉ ላይ የጨለንቆን ጉዳይ ጨምሮ “የጸጥታ ኃይሎች” ተልእኮዋቸዉን በመፈጸም ላይ እንዳሉ ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ መንግሥት አሠራሩን ተከትሎ እንደሚያጣራና ለሕዝብ እንደሚያሳዉቁ ገልጸዋል። ነጥቡ ያለዉ ግን ከሕገ መንግሥቱ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰነዘሩት አሳብ ምን ያህል ያስኬዳል የሚለዉ ላይ ነዉ።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 (2) (ሰ) መሠረት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለዉ በክልሉ ላይ ነዉ። ሆኖም ግን ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ በሚያጋጥምበት ጊዜ የክልሉ መሥተዳድር ጥያቄ በማቅረብ የፌዴራል መንግሥት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል እንዲሰማራ ሊያደርግ እንደሚችል በአንቀጽ 51 ንዑስ ቁጥር 14 ላይ ተደንግጓል። እነዚህ ድንጋጌዎች በግልጽ እንደሚያስቀምጡት የክልል መሥተዳድሮች ጥያቄ ካላቀረቡ በስተቀር የመከላከያ ሠራዊት ክልል ዉስጥ በመግባት ማናቸዉንም የኃይል ተግባር የመፈጸም ሥልጣን አይኖረዉም ማለት ነዉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የመከላከያ ሠራዊት ጨለንቆ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እንዲሠራ የኦሮምያ ክልል የፊዴራል መንግሥትን እንዳልጠየቁ ራሳቸዉ ፕሬዝዳንቱ ስለገለጹ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በመተላለፍ መከላከያ ሠራዊቱን ወደጨለንቆ ያሰማራዉ ግለሰብ ወይም አካል ሕገ ወጥ ተግባር ስለመፈጸሙ የሚያጠራጥር አይደለም ማለት ነዉ። በዚህም መሠረት ትእዛዙን የሰጠዉ አካልና እንዳግባብነቱ እርምጃዉን የወሰዱት የሠራዊት አባላት ለደረሰዉ የሕይወት መጥፋትና የመቁሰል አደጋ ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በመሸፋፈን “ … ተልኳቸዉን በመፈጸም ላይ እንዳሉ ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ … ” በሚል ሠራዊቱ ወደ ክልሉ የመግባት ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት በማለፍ እንደተለመደዉ የተወሰደዉ የኃይል እርምጃ ተመጣጣኝ ነበር/አይደለም ወደሚል የማጣራት ሒደት እንደሚኬድ አመላክተዋል። ይህ አካኼድ በዋንኛነት መጠየቅ ያለበትን አካል/ግለሰብ በማዳን ወደሌሎች የማላከክና የተፈጸመዉን የጥፋት ደረጃ ዝቅ የሚያደረግ በመሆኑ በፍጹም ተቀባይነት የለዉም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥት ተጥሶና የክልሉ መብት ተደፍሮ የዜጎች ሕይወት በመጥፋቱና ለብዙዎች መቁሰል በርግጥ የሚቆረቆሩ ከሆነ የማጣራት ሔደቱ መጀመር ያለበት ካለክልሉ ጥያቄ መከላከያ ሠራዊቱን ያሰማራዉ አካል ማነዉ ከሚል መሆን ይኖርበታል። ይህ አካኼድ ለዚህ ለተነሣዉ ጉዳይ ብቻ የሚያገለግል አይደለም። በተመሳሳይ ካለክልል ጥያቄና እዉቅና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደክልሎች በመዝለቅ ሕዝቡንና ተማሪዎችን የመግደል፣ የማቁሰል፣ የመደብደብና የማንገላታት ተግባር እንዲፈጽሙ የሚያዙ አካላት/ግለሰቦች እንዲጠየቁ የማድረግ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደርዕሰ ብሔርነታቸዉና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛኝነታቸዉ ይህንን ኃላፊነት መወጣት ካልቻሉ በደፈናዉ “ለሞቱትና ጉዳት ለደረሰባቸዉ ዜጎቻችን አዝናለሁ” በሚል ብቻ ከንፈርን መምጠጥ ዋጋ የለዉም። ችግሩንም ከማባባስ ዉጭ የሚፈይደዉ ነገር አይኖርም።

ቸር ይግጠመን    

 መኮንን አሻግሬ (ቨርጂኒያ አሜሪካ)    ታህሳስ 2010 (Dec. 2017)   mekonnen_ashagre@yahoo.com 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *