‹‹በሒደት ላይ ባለ ጉዳይ ፕሬዚዳንቱ እኔን ጠርተው ማነጋገራቸው በዳኝነት ሥራ ጣልቃ መግባት ነው›› ዳኛ ቅድስት ጽጌ

‹‹ፕሬዚዳንቱ ጠርተው ቢያነጋግሯቸውም ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገቡም›› የፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ

በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት እንደተገኙ የቀረበላቸው ጥያቄ በአጠቃላይ ስለ እሳቸው የትምህርት ሁኔታ፣ እንዴት እንደ ተሾሙና ልጅ ስለመሆናቸው እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ቅድስት፣ ስለግል ሁኔታቸው መጠየቅ እንደሌለባቸው ምላሽ ሰጥተው በዋናነት ለምን እንደተፈለጉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹የዲሲፕሊን አቤቱታ ቀርቦብሻል፣ በእሱ ጉዳይ ላነጋግርሽ ነው የጠራሁሽ፤›› የሚል ምላሽ ሲያቀርቡላቸው፣ የዲሲፕሊን አቤቱታ እንዴት እንደሚቀርብ የራሱ የሆነ ሥርዓት እንዳለውና የቀረበውም ዲሲፕሊን አቤቱታ በሚስጥር ተይዞ ከተመረመረ በኋላ፣ እውነት ሆኖ ሲገኝ ምላሽ እንዲሰጡበት ከእነ አቤቱታው ከሚደርሳቸው በስተቀር፣ እየመረመሩት በሚገኝ ጉዳይ ላይ በጽሕፈት ቤት ተጠርተው ሊጠየቁ እንደማይገባ በመግለጽ ወደ ሥራቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል…… VIA – ሪፖርተር አማርኛ 

 

 ታምሩ ጽጌ

በፍርድ ቤት ተከራካሪ ወገን የዲሲፕሊን አቤቱታ ቀርቦባቸው በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የቀረበው አቤቱታ ሲመረመር የቀረበው የዲሲፕሊን አቤቱታ ተገቢ መሆኑ በአብላጫ ድምፅ በመረጋገጡ፣ ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ የተላለፈባቸው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ሦስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዳኛ ጉዳይ ጥያቄ አስነሳ፡፡ ምንም እንኳን የዳኛዋ ከሥራ መሰናበት የሚረጋገጠው ወይም የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው ሹመቱን በሰጣቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሆንም፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አብላጫ ድምፅ ያስተላለፈው ውሳኔ ሕግን ያልተከተለ፣ የዳኝነት ነፃነትን የሚጋፋና ተዓማኒነት የጎደለው መሆኑን ውሳኔ የተላለፈባቸው ዳኛ ይናገራሉ፡፡

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በአብላጫ ድምፅ ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሦስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ እስከ ኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በሥራ ላይ የነበሩት ዳኛ ወ/ሮ ቅድስት ጽጌ ይባላሉ፡፡ ወ/ሮ ቅድስት በተጠቀሰው ችሎት በመሥራት ላይ እያሉ በአንድ ከውርስ ጋር በተገናኘ የክስ መዝገብ ለተከታታይ ሦስት ጊዜያት የዲሲፕሊን ክስ እንደቀረበባቸው የሚገልጽ ደብዳቤ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ ፊርማ ውጪ ተደርጎ የጽሑፍ መልስ እንዲሰጡ እንደ ደረሳቸው በመግለጽ፣ ከዳኝነት ሥራቸው እንዴት ሊታገዱ እንደቻሉ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የክስ መዝገቡ ገና በሒደት ላይ ያለ በመሆኑና በቀጣይ በሚደረገው የፍርድ ቤት ክርክር ላይ ተፅዕኖ ስለሚኖረው፣ የአቤቱታ አቅራቢውን ማንነትና ዝርዝር ጉዳዩን መግለጽ ሥነ ምግባሩም የሚፈቅድ ባለመሆኑ ከመግለጽ ተቆጥበው፣ ከዳኝነት ሥራቸው ስለተሰናበቱበት ጉዳይ ወ/ሮ ቅድስት አስረድተዋል፡፡

ዳኛዋ እንደገለጹት፣ ከዳኝነት ሥራ ተሰናብተሻል የተባሉበት ጉዳይ በተገለጸው ችሎት ከሚቀርቡ የተለያዩ ክርክሮች መካከል የሚገኝ የውርስ ክርክር ነው፡፡ በወራሾች መካከል ስምምነት ባለመኖሩ የውርስ ንብረቱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሬጅስትራር ጠባቂነት በተሾመ ንብረት አስተዳዳሪ እንዲቆይ ተደርጎ፣ የወራሾች ማንነት እየተጣራ ባለበት ሁኔታ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ ጽሕፈት ቤታቸው ድረስ ጠርተው እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፡፡

በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት እንደተገኙ የቀረበላቸው ጥያቄ በአጠቃላይ ስለ እሳቸው የትምህርት ሁኔታ፣ እንዴት እንደ ተሾሙና ልጅ ስለመሆናቸው እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ቅድስት፣ ስለግል ሁኔታቸው መጠየቅ እንደሌለባቸው ምላሽ ሰጥተው በዋናነት ለምን እንደተፈለጉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹የዲሲፕሊን አቤቱታ ቀርቦብሻል፣ በእሱ ጉዳይ ላነጋግርሽ ነው የጠራሁሽ፤›› የሚል ምላሽ ሲያቀርቡላቸው፣ የዲሲፕሊን አቤቱታ እንዴት እንደሚቀርብ የራሱ የሆነ ሥርዓት እንዳለውና የቀረበውም ዲሲፕሊን አቤቱታ በሚስጥር ተይዞ ከተመረመረ በኋላ፣ እውነት ሆኖ ሲገኝ ምላሽ እንዲሰጡበት ከእነ አቤቱታው ከሚደርሳቸው በስተቀር፣ እየመረመሩት በሚገኝ ጉዳይ ላይ በጽሕፈት ቤት ተጠርተው ሊጠየቁ እንደማይገባ በመግለጽ ወደ ሥራቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡ ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላም አጠቃላይ የዳኞች ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ወቅት፣ አንድ ዳኛ የሚሠራው ህሊናንና ሕግን መሠረት አድርጎ ብቻ መሆኑን፣ ሲሾምም ሊታይ የሚገባው የተቀመጠውን ለዳኝነት የሚያስፈልግ መሥፈርት ማሟላቱን እንጂ፣ ከዚህ ውጪ ያለው ነገር ተገቢ እንዳልሆነና በቀጣይ የዳኝነት ነፃነት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን የሚገልጽ አስተያየት መስጠታቸውን ወ/ሮ ቅድስት አክለዋል፡፡  

ሲመረምሩት በነበረው የውርስ ክርክር መዝገብ ላይ ፕሬዚዳንቱ ካነጋገሯቸው በኋላ፣ በእንጥልጥል ላይ ባለ መዝገብ የሚያየውን ዳኛ ኃላፊዎች ማነጋገራቸው ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን በመገንዘብ፣ ምንም እንኳን እሳቸው ነፃ ሆነው በመዝገቡ ላይ ውሳኔ ቢሰጡ ጉዳዩ በገለልተኛነት የታየ ሊመስል ስለማይችል፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 27(1ሠ) መሠረት፣ ራሳቸውን ከችሎቱ መጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ማንሳታቸውንም ዳኛዋ ተናግረዋል፡፡

ራሳቸውን ከውርስ ክርክሩ ካነሱ በኃላ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በመዝገቡ ላይ ተከራካሪ በሆኑት አመልካች በተለያዩ ቀናት ሦስት ጊዜ የዲሲፕሊን አቤቱታ እንደቀረበባቸው ተገልጾ በጽሑፍ መልስ እንዲሰጡ፣ በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሰብሳቢና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ ፊርማ ወጪ የተደረገ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አስረድተዋል፡፡

ከደብዳቤው ጋር ተያይዞ የቀረበላቸው የአቤቱታ ሰነድ የዲሲፕሊን አቤቱታ አቅራቢው ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፣ የውርስ ንብረቱን እንዲያጣሩ የተሾሙት ግለሰብ የማስተዳደር አቅም እንደሌላቸው ጠቅሰው እንዲቀየሩ ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ባለመቀበሉ ንብረት እንዲባክን መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የውርስ ቤቶች የሚከራዩ ቢሆንም የኪራዩ ገንዘብ በሞዴል 85 ሊያዝ ሲገባው፣ ያለደረሰኝ እንዲሰበሰብና ገቢ እንዳይደረግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ዳኛዋ እንዲነሱ አመልክተው አልነሳም ማለታቸው፣ ለንብረት አስተዳዳሪ ተገቢ ያልሆነ ደመወዝ እንዲከፈል መወሰኑ፣ ያላግባብ አስተያየት ሳይጠየቁና ምላሽ ሳይሰጡ ጥፋተኛ ተብለው በአንድ ወር እስራት መቀጣታቸውና አመክሮ መከልከላቸውን ገልጸው፣ ተከራካሪው የዲሲፕሊን አቤቱታ ያቀረቡባቸው መሆኑን እንደሚያስረዳ ዳኛዋ ገልጸዋል፡፡

ዳኛዋ በውርሱ የክርክር ሒደት ከላይ የተጠቀሱት ስህተቶች ወይም የዲሲፕሊን ግድፈቶች እንደተፈጸሙባቸው አድርገው አቤቱታ አቅራቢው ለጉባዔው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ፣ ዝርዝር ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ የክርክር መዝገቡ የቆየና በሌላ ዳኛ ተዘግቶ የነበረና እሳቸውም ከኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እያዩት መሆኑን፣ አስተዳዳሪ የተሾመው በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በሬጂስተር መሆኑንና ከእሳቸው ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ለጉባዔው ምላሽ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ ንብረት አስተዳዳሪው ያለደረሰኝ ገንዘብ እንደሚቀበሉና ገቢ እንደማያደርጉ የቀረበላቸው አቤቱታ እንደሌለ፣ ነገር ግን በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተሰጠን ትዕዛዝ የእሳቸው ችሎት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረጉን፣ ለችሎት እንዲነሱ የቀረበው አቤቱታ ውድቅ የተደረገው፣ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ (27 እና 28) መሠረት መሆን እንዳለበት ጠቁመው፣ የቀረበባቸው አቤቱታ የሕግ ድጋፍ ስለሌለው ውድቅ መደረጉን በማስረዳት ከእነ ማስረጃው አቅርበዋል፡፡ ለንብረት አስተዳዳሪው በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 959 መሠረት የአገልግሎት አበል መወሰኑን፣ ትዕዛዝ መስጠታቸውንና ይኼም የሆነው ከውርስ ንብረቶቹ በወር የሚገባውን 30,000 ብር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ስህተት ቢሆን እንኳን በይግባኝ ሊታረም የሚገባው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢው አንድ ወር ሊታሰሩ የቻሉት፣ የውርስ ንብረት በሆነው ቤት ውስጥ ከነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. መኖር በመጀመራቸውና ይኼም የሆነው ንብረት አስተዳዳሪ ከተሾመና እንዲያስተዳድር ከተደረገ በኃላ ሲሆን፣ የኪራይ ገንዘብ ለሁሉም ባለድርሻዎች መሆኑን ተከትሎ ክፍፍል እስከሚፈጸም ድረስ ተለይቶ እንዲቀመጥ ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ በመጣሳቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሕጉንና ‘ፕሮሲጀሩን’ ጠብቆ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን መወሰኑንም ከእነ ማስረጃው ለጉባዔው ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመጣሱም የተሰጠው ቅጣት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 448(1ሐ) መሠረት ተገቢ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አመክሮን በሚመለከት መብቱ የማረሚያ ቤት መሆኑንና ማረሚያ ቤቱ ሲፈቅድ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 203(2) መሠረት ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ቢሆንም፣ የቀረበላቸው ነገር እንደሌለና ፍፁም ሐሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ንብረት አስተዳዳሪ እንዲሾም በችሎት ትዕዛዝ ከመስጠታቸው ውጪ፣ የተሾሙትን ግለሰብ እንደማያውቋቸውና ከሥራ ባለፈ ግንኙነት እንደሌላቸው፣ አቤቱታ አቅራቢውንም በችሎት ሲቀርቡ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ዕውቅና ወይም ማኅበራዊ ግንኙነት እንደሌላቸው በማስረዳት ‹‹እምቢ ካልክ አሁንም አስርሃለሁ፤› ብለውኛል የሚለው አቤቱታ ሐሰት መሆኑን፣ እንዲያውም የበላይ ኃላፊ ካነጋገሯቸው በኋላ ተፅዕኖ ይፈጥራል በማለት ራሳቸውን ከመዝገቡ ማንሳታቸውን ለጉባዔው እንዳስረዱ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው በአማራ ክልል በዳኝነት በሠሩባቸው ጊዜያትና በፌዴራልም እየሠሩ ባሉባቸው ጊዜያት፣ ሥራቸውን ከህሊናና ከሕግ ጋር ብቻ በማገናኘት የሚሠሩና በኃላፊዎችም ሆነ በቅርብ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ደንበኞች በአስተያየት መስጫ ላይ በሚያሰፍሩት ዕይታ መልካም ነገር እንዳላቸው እንጂ፣ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ሠርተው እንደማያውቁ ምስክሮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በሚሠሩት መዝገብ ላይ ተጠርተው አስተያየት መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑንና በዳኝነት ሥራ ላይ ጣልቃ መግባትና ነፃነት ማሳጣት መሆኑን መግለጻቸው ካልሆነ በስተቀር፣ የዲሲፕሊን አቤቱታ ቀርቦባቸዋል ተብሎና ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት እንደፈጸሙ መረጋገጡ ተገልጾ፣ ከኅዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከዳኝነት ሥራ እንዲሰናበቱ የተደረሰበት ውሳኔ፣ አሳዛኝና ሕግን ያልተከተለ አሠራር መሆኑን መንግሥት፣ የሙያው ባለቤቶችና ሕዝብ እንዲያውቅላቸው አሳስበዋል፡፡

ዳኛዋ ከሕግ አግባብ ውጪ ከዳኝነት ሥራ እንዲሰናበቱ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አሳልፏል ስለተባለው ውሳኔ ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለአቶ ዳኜ መላኩ ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ አቶ ዳኜ በሥራ ምክንያት እንዳልተመቻቸው በሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ በኩል በመግለጽ፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ኢንስፔክሽንና ፍርድ ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ መንግሥቱ፣ የጉባዔው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን በላይና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ልዑል ሐጎስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የጉባዔው ኃላፊዎች እንደተናገሩት፣ ወ/ሮ ቅድስትን ፕሬዚዳንቱ ጠርተው ያነጋገሯቸው በተለየ ጉዳይ ወይም እሳቸው እንደሚሉት የዳኝነት ነፃነታቸውን ለማሳጣት ሳይሆን፣ ሌሎች ዳኞችንም ሆነ ሠራተኞችን እንደሚያነጋግሩት ስለአጠቃላይ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም ቅሬታ ያለው ባለጉዳይ በቀጥታ ለፕሬዚዳንቱ ወይም ለጉባዔው ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችል የተናገሩት ኃላፊዎቹ፣ በዳኛዋ ላይ የዲሲፕሊን አቤቱታ ያቀረቡትም ግለሰብ መብታቸውን ተጠቅመው ‹‹ያላግባብ ሀብቴ ተመዘበረ፤››  ብለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ ሦስት ጊዜያት አቤቱታ በመቅረቡ በሒደት ላይ ባለው ጉዳይ ላይ ሳይሆን፣ አጠቃላይ አሠራርን በሚመለከት አቶ ዳኜ ወ/ሮ ቅድስትን ጠርተው ሲያነጋግሩ በቢሮአቸው እንደነበሩ አቶ ዮናስ መንግሥቱ ተናግረዋል፡፡ አቶ ዳኜ ወደ ሥልጣን የመጡት በቅርቡ ስለሆነ ወ/ሮ ቅድስትን ሲያገኟቸው ለመተዋወቅ ያህል የት እንደ ተማሩና መቼ ዳኝነት እንደ ጀመሩ ጠየቋቸው እንጂ፣ የእሳቸውን ክብር ለመንካት ወይም በያዙት ሥራ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እንዳልሆነ አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡

ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት በርካታ አቤቱታዎች እንደሚቀርቡ የጠቆሙት አቶ ዮናስ፣ በወ/ሮ ቅድስት ላይ የቀረበውም የዲሲፕሊን አቤቱታ ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቤቱታው እንደ መጣ ጉዳዩን የመረመረው እሳቸው የሚመሩት ኢንስፔክሽንና ፍርድ ምርመራ ዳይሬክቶሬት መሆኑን አስታውሰው፣ የቀረበባቸው አቤቱታ ትክክለኛ መሆኑ በመረጋገጡ ወደ ጉባዔው መመራቱንና አሠራሩም ይኼው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ጉባዔው ተወያይቶበት ዳኛዋ ፈጽመዋል የተባለው የዲሲፕሊን ግድፈት ትክክለኛ ሆኖ በመገኘቱ፣ በሙሉ ድምፅ ከዳኝነት እንዲሰናበቱ ውሳኔ ተላልፎ፣ ውሳኔውን ወደ ሚያፀድቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ዮናስ በሙሉ ድምፅ እንደፀደቀ ቢናገሩም፣ አቶ ዳኜ የፈረሙበት የውሳኔ ደብዳቤ በአብላጫ ድምፅ የተወሰነ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ወ/ሮ ቅድስት በሒደት ላይ ባለ የክስ መዝገብና በእሳቸውም ላይ የተላለፈው ውሳኔ መጨረሻው ሳይታወቅ ወደ መገናኛ ብዙኃን መሄዳቸው ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ልዑል ሐጎስ፣ መገናኛ ብዙኃንም የመጨረሻውን ውሳኔ ጠብቀው ውሳኔውን ቢተቹ የተሻለ ይሆን እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ቅድስት በአካል ቀርበው ለጉባዔው ማስረዳት እንደሚፈልጉ በደብዳቤ መግለጻቸውን፣ ነገር ግን ሊጠሩ እንዳልቻሉና ውሳኔው ከተሰጠ በኃላም የውሳኔው ግልባጭ እንደተከለከሉ የተናገሩ ቢሆንም፣ አቶ ሰለሞን ግን ክርክር እንደ ተደረገበትና ዳኛዋ በሚገባ ማስተባበላቸውን አስረድተዋል፡፡ ዳኛ በሙያ ግድፈት፣ ውሳኔ በማዘግየት፣ በዲሲፕሊን ጉድለትና በተለያዩ ከሙያው ሥነ ምግባር ወጪ በሆኑባቸው ጉዳዮች ሊጠየቁ እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ የዳኛዋ ግን ለምን እንደተለየና ትኩረት ሊሰጠው እንደቻለ እንዳልገባቸው ተናግረዋል፡፡ የዳኛዋ ጉዳይ አዲስ ነገር የሆነው ወደ መገናኛ ብዙኃን በመሄዳቸው እንጂ፣ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለው አክለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሥራ አባክባሪና ታች ድረስ ዝቅ ብለው በመሥራታቸው ሞዴል ሆነው ሊጠቀሱ የሚገባቸው እንጂ፣ በዳኝነት ነፃነት ጣልቃ የሚገቡና ተፅዕኖ የሚፈጥሩ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *