በጥር 2008 ዓም በማዕከላዊ እስረኞች የሚፈፀመውን ግፍ በመቃወም የርሃብ አድማ ተድርጎ ነበር። በርሃብ አድማው ወቅት ህመም ያለባቸው እስረኞች ምግብ እንዲበሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል። አቶ በቀለ ግን ህመሙ ይግደለኝ እንጅ አልበላም አለ። ለርሃብ አድማው ብሎ የሚወስደውን ክኒን አቋረጠ። ታምሞ ህክምና ሂድ ሲባል እንኳን ፈቃደኛ አልነበረም። ይህን የርሃብ አድማ አነሳስታችኋል ተብለው አቶ በቀለና ዮናታን ጣውላ ቤት ወደተባለው ክፍል ተቀየሩ። ከሳይቨርያ አንፃር ምቹ ነው። ነገር ግን እነ አቶ በቀለ ሳይቨርያን መረጡ።

ጣውላ ቤት ከምርመራ ክፍሉ ስር ያለ ክፍል ነው። ከላይ ሆነው በሌሊት እስረኛ ሲቀጠቅጡ ከስር ያለ እስረኛ ይሰማል። እነ አቶ በቀለ በተደጋጋሚ የምርመራ ክፍሉን ኃላፊዎች ያስጠራሉ፣ እንዲጠሯቸው ይጠይቃሉ። በአብዛኛው እስረኛ መርማሪ የሚያስጠራው ስለ ጉዳዩ ለማውራት ነው። እነ አቶ በቀለ መርማሪዎቹን ጠርተው “ለምን ወንድሞቻችን ታሰቃያላችሁ?” እያሉ ይጠይቃሉ፣ ይወቅሳሉ። መርማሪዎቹ አልሰማ ሲሏቸው “የወንድሞቻችን ስቃይ ከምንሰማ ወደ ሳይቨርያም ቢሆን ቀይሩን” ብለው በተደጋጋሚ ጠየቁ። በዚህ ምክንያት ከምቹው የእስር ቤቱ ክፍል ወደ ሌላ የከፋ የእስር ቤት ክፍል ተቀይረዋል።

አቶ በቀለ ማዕከላዊ በነበረበት ወቅት ግጥምና ዜማ አውጥቶ እስረኞች የሚፅናኑበት የትግል ዜማ አዘጋጅቷል። ከእስር ቤቱ ውጭም ፍርድ ቤት ሳይቀር ያዜሙታል። ከወጣቶች ጋር ባለው ቅርበት በ58 አመቱ እንደጓደኛ ይጠሩታል።

አቶ በቀለ አብረውት ለታሰሩት ምቹ ፀባይ ያለው ሰው ነው። በአንድ ወቅት እሱን ለመሰለል ሲባል በሙስና እንደተጠረጠረ ተደርጎ የገባን ጆሮ ጠቢ እንኳን እስኪፈታ በደንብ ተንከባክቦታል።

ሰብሰብ ብለው በኦሮምኛ ሲያወሩ ኦሮምኛ የማይችል አንድ ሰው አብሮ ቁጭ ካለ ለዛ ሰው ሲባል ወሬው በአማርኛ እንዲሆን ይጠይቃል። የአርማጭሆው አዋጁ አቡኃይ ጓደኛው ነው። አቶ በቀለ ስለ አዋጁ አውርቶ አይጠግብም። ተኳሹ ኃይሌ ማሞ ስለሚያከብራቸው በቀለ ሁሌም መልካም ነገር ያወሩለታል። “በቀለ ሰላማዊ ታጋይ አድርጎኛል” እያሉ እጃቸው እያጣመሩ ያሳዩንና ያወሩልን ነበር።

ማሩ ሰጥአርገው የድሮ አርበኛ ነው። ማሩ አበራ ጎባውን ካልገደልክ ተብሎ እምብይ በማለቱ የታሰረ የአርማጭሆ ሰው ነው። ማሩ በእርግጥም የአበራ ጓደኛ ነበር። በአንድ ወቅት ካድሬዎቹ አበራ ምህረት እንዲገባ አሳምነው ብለው ይወተውቱታል። ካድሬዎቹ ሲያስቸግሩት አበራን ጫካ ድረስ ሄዶ አናገረው፣ አበራ ግን ምህረት እንደማይገባ ገለፀለት። ምህረት እንዲገባ ጫካ ድረስ ሄዶ የጠየቀው ሌላ ሰው ቢሆን ኖሮ እሱም ምህረት ያደርግለት እንዳልነበር፣ ካድሬዎቹ በማሩ ላይ የሚያደርጉትን ውትወታ በመረዳት ቁጭ ብሎ ለማውራት እንደፈቀደ ገልፆለት ሸኘው።

በሌላ ጊዜ ካድሬዎቹ ማሩ ሰጥአርገውን ጎንደር ወስደው፣ አንዲት ዘመናዊ መኪና እያሳዩ፣ “ከእኛ ጋር እንደተጣላህ ታስወራለህ። ከዛም ትሸፍትና አበራ ጋር ትሆናለህ። አዘናግተህ ከኋላው መትተኸው ትመጣለህ። አበራን ከገደልከው ይችን ዘመናዊ መኪና እንሰጥሃለን” ይሉታል። ማሩ ግን በጓደኛው ላይ ይህን ማድረግ አልፈለገም። “አበራ ጓደኛዬ ነው። አበራን አልገድለውም። እንኳን ለዚህ መኪና፣ ከዚህ ከተማ ውስጥ ከፍ ከፍ ብሎ የሚታየውን ይህን ሁሉ ፎቅ እንሰጥሃለን ብትሉኝ አበራን አልገድለውም” ብሎ ለጥቅም ሲል ጓደኛውን እንደማይገድል ቁርጣቸው ነገራቸው።

ጊዜ ጠብቀው ታዋቂውን የድሮ አርበኛ ማሩን አሰሩት። እነ በቀለ ከታሰሩበት ሳይቨርያ ቁጥር 9 አስገቡት። ባልፈፀምኩት ነገር ታስሬያለሁ ያለው ማሩ ለመርማሪዎች ቃል ትንፍሽ አላለም። ምግብም አልቀምስም ብሎ የርሃብ አድማ አደረገ። 10 ቀን ሙሉ ምግብ አልቀመሰም። መርማሪዎች ቃልክን ስጥ የሚሉትን ትተው ምግብ እንዲበላ ይወተውቱታል። የማሩ የርሃብ አድማ ከሚጠበቀው በላይ ሲሆንና አካሉም ሲዳከም ምግብ እንዲበላ ያልለመነው እስረኛ አልነበረም። በመጨረሻ ግን በአንድ ሰው ምክር ምግብ ቀመሰ። በአቶ በቀለ። ማሩና በቀለ በጣም ይዋደዳሉ። ማሩ በቀለን ባገኘው ቁጥር “አንተዬ ዓለም ያን ግዜኮ የአንተን ምክር ባልሰማ ሙቼ ነበር።” ይለዋል። ማሩ፣ በርሃብ አድማው ምክንያት ሊሞት ተቃርቦ አቶ በቀለ ምግብ እያጎረሰ እንዳተረፈ ይናገራል። አቶ በቀለም የማሩን የርሃብ አድማ ጀብድ ለቀሪዎቹ ያወራናል።

ወደ ቂሊንጦ ከወረድን በኋላ ጥቁር ለብሶ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ተለመደ። እነ አቶ በቀለ ጥቁር ልብስ አውልቀው ሌላ ልብስ እንዲቀይሩ ፈቃደኛ አልሆኑም። በግድ ጥቁር ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ሲደረግ፣ ወደ ፍርድ ቤት በቁምጣና በካናቴራ መጥተዋል። ይህ ጥቁር የመልበስ ተቃውሞ ያስጨነቃቸው አሳሪዎች በጥቂት ጊዜ ውስጥ ርካሽ ብጫ ልብስ ይዘው ብቅ አሉ። እስር ቤት ውስጥ “ዱርዬ” ተብለው የሚጠሩ እስረኞች አሉ። “ዱርዬዎቹ” ለፖለቲካ እስረኛ ከፍ ያለ ክብር አላቸው። የሚያሰቃዩዋቸው የእስር ቤቱ አዛዦች የፖለቲካ እስረኛው በሚያሰማው ተቃውሞ ሲጨነቁ ማየት ያስደስታቸዋል። አሁን አሁን እንደበቀለ ካሉ ፖለቲከኞች ጋር እየዋሉ፣ እነሱም ግንባር ቀደም ታጋይ ሆነዋል። እነዚህ እስረኞች (ዱርዬዎቹ) ይህን ልብስ “በቀለ ገርባ” ይሉታል። እነ በቀለ ባደረጉት የጥቁር መልበስ ተቃውሞ ምክንያት የመጣ ነው በሚል ነው።

ዝዋይ ስቃይ ቤት እያለን እነ አቶ በቀለ ቂሊንጦ ጨለማ ቤት ነበሩ። ጨለማ ቤት እያሉ ነበር ቃጠሎው የተከሰተው። ይህን ቃጠሎ ሰበብ አድርገው በቀለን ለማጥቃት አቅደው እንደነበር በወቅቱ የዞን 1 ኃላፊ የነበረው ኮማንደር ዘሩ ዝዋይ ለነበረ አንድ የትህነግ/ህወሓት አባል ተናግሮ ነበር። ዘሩ “በግንቦት 7 ከተከሰሱት አግባው ሰጠኝን፣ በኦነግ ከተከሰሱት ደግሞ በቀለ ገርባን ነው መጀመርያ የምንከሰው” ብሎ አውርቷል። ጫናውን ፈርተው መሰለኝ አቶ በቀለን አልከሰሱትም። እንደ ዘሩ አባባል ግን ሰበብ ነው የሚፈልጉለት።

አሁን ደግሞ በቄ በጠና ታሞ ህክምና ማግኘት አልቻለም። ሰበብ እየፈለጉ የሚያጠቁት ሰው ሲታመም ለአሳሪዎቹ አስደሳች ነው። ለህመሙ ህክምና መንፈግ ቀርቶ ሌላ ማጥቂያ የሚፈልጉለት ሰው ነው!

አቶ በቀለ በብይን መለቀቅ ነበረበት። ግን ተከላከል ተባለ። ተከላከል የተባለበት አንቀፅ ከ6 ወር በላይ የሚያስቀጣ አይደለም። አቶ በቀለ ከታሰረ 2 አመት ከ2 ቀን ሆኖታል። ይህ የሶስት አመት ፍርድ ነው! ጥፋተኛ ቢሉት እንኳን ከ6 ወር በላይ ለማያስቀጣ ጉዳይ የ3 አመት ቅጣትን እየታሰረ፣ ህክምና እንዳያገኝ ሌላ ኢ ሰብአዊ የሆነ ቅጣት ተጥሎበታል።

(ጌታቸው ሺፈራው)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *