የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ቢተሰቦቻቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። አቶ በቀለ ገርባ በተደጋጋሚ ከዚህ ችሎት ፍትሃዊ ውሳኔ አልጠብቅም ሲሉም ተናግረዋል። በዋስ እንዲፈቱም ተወስኖ ነበር። አቶ በቀለ በተከሰሱበት መዝግብ ያሉትን ጨምሮ ችሎቱ የበየነው ባይታወቅም ምስክሮች እየተሰሙ ነው። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በስራ ብዛት የጽሁፍ ምላሽ የሰጡ ሲሆን አቶ ለማ መገርሳና አባ ዱላ ገመዳ ስለመገኘታቸው የተባለ ነገር የለም። ፋና ከዚህ የሚከተለውን ዘግቧል

አቶ በቀለ ገርባ በተከሰሱበት የወንጀል አንቀፅ የመከላከያ ምስክሮች ለመስማት የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ቀጠሮ ይዟል። የተከሳሹ ምስክሮች ዛሬን ጨምሮ ለቀጣይ ሶስት ቀናት በችሎቱ ውሎ ቀርበው ምስክርነታቸው ይሰማል ተብሎ ይጠበቃል።

አያና ጉርሜሳ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላና የቀድሞ የኦፌኮ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ናቸው በመዝገቡ ክስ የተመሰረተባቸው። በዚህ መዝገብ ላይ አቶ በቀለ ገርባ በተከሰሱበት ህዝብን ለአመጽ ማነሳሳት ወንጀል ተከላከሉ መባላቸው ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም አቶ በቀለ ገርባ በመከላከያ ምስክርነት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና አቶ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ ሌሎችንም በመከላከያ ምስክርነት አቅርበዋል።

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን ለዛሬ የቀጠረው የተከሳሹን መከላከያ ምስክሮችን ለማድመጥ ነው።

በዚህም መሰረት የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቃ ለ1ኛ መከላከያ ምስክር ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የፍርድ ቤቱን መጥሪያ ወረቀት ወስደው ማስረከባቸውን ማረጋገጫ ወረቀት ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩም በችሎቱ ቀርበው ለመመስከር በከፍተኛ የስራ ጫና እና የጊዜ መጣበብ የተነሳ በችሎቱ መገኘት አለመቻላቸውን በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት አማካኝነት በተጻፈ ደብዳቤ ለችሎቱ በጽሁፍ አስረድተዋል።

ሌሎቹ በምስክርነት የተጠቀሱት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተደራራቢ የስራ ጫና እንደሚኖርባቸው ከግምት በማስገባትም ፍርድ ቤቱ ለቀጣይ ሁለት ቀናት የዚህን መዝገብ ምስክሮች ለማድመጥ እንደሚሰየምም በችሎቱ ተገልጿል።

በዚህ መዝገብ ሌላው አቶ በቀለ ገርባ በመከላከያ ምስክርነት ከያዟቸው ግለሰቦች መካከል አቶ አንዷለም አራጌ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አልቀረቡም።ፍርድ ቤቱም የቀሩበትን ምክንያት በማጣራት በነገው የችሎቱ ውሎ ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ትእዛዝ ሰጥቷል።

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛው የወንጀል ችሎት ጠቅላይ ሚንስትሩ በላኩት የጽሁፍ ምላሽ ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት አልያም በምላሹ ላይ የግራ ቀኙን አስተያየት አካተው በችሎቱ ማብቂያ ትእዛዝ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በዚሁ መዝገብ ላይ ያሉት 15ኛ እና 16ኛ ተከሳሾች ሳንከላከል ብይን ይሰጠን ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰዓትም ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ የተጠቀሱ ሌሎች ተከሳሾችን የምስክርነት ቃል በማድመጥ ላይ ይገኛል።

በሰለሞን ጥበበስላሴ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Ethiopia: Lies, Damn Lies, Axum and the West – by Jeff Pearce

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *