በማኅተመ ፍቅሬ – አንባቢ

ኢሕአዴግ ምን ያድርግ ታድያ ብዬ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ የወቅቱም ሆነ የጊዜው ብዙ ነገሮች ከትንሿ ቤት ጀምሮ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል፣ አገርና አኅጉርን አልፎ በዓለም ላይ የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የእርስ በእርስ ጦርነትና የአምባገነንት ተግባር በአጠቃላይ ሰይጣናዊ ሥራ ተንሰራፍቷል፡፡

አገራችንም ብትሆን በዚሁ ዓይነት ሒደት እያለፈች ትገኛለች፡፡ እውነት ነው አሁን ሁኔታዎች እየከፉ መጥተዋል፡፡ ምክንያቱም ሰው እርስ በርሱ እየተባላ ስለሆነ ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ እውነት ነው ባሳለፍናቸው ዘመናት ኃይልን መሠረት ያደረገ አንድነት ተገንብቷል፡፡ ለሁለት ሺሕ ዓመታት በኃይል የተመሠረተውን አንድነት ወደጎን በማለት፣ ኢሕአዴግ ሲመጣ በአንድ ጊዜ በፍቅር የተገነባ አድነት ለመመሥረት ሕገ መንግሥት አሻሻለ፣ ሥርዓት አበጀ፣ ብሎም ለሰፊው ሕዝብ አወጀ፡፡

መቼም ታስሮ የተፈታ ሁሉ አረማመዱን ማወቅ ይከብደዋል፡፡ አዋጁ በአጠቃላይ እንዲህ ነበር፡፡ ለዘመናት በኃይል ታስራችሁ እዚህ የደረሳችሁ ሕዝቦች ሆይ ዛሬ ነፃነታችሁ ታውጇል፡፡ ማንም የፈለገውን ሊጽፍና ሊናገር ሕገ መንግሥታዊ መብት ተሰጥቶታል፡፡ ማንም በፈለገው ክልልና ቦታ ሄዶ የመሥራትና የመኖር መብት አለው፡፡ ማንም ተቃዋሚ ፓርቲ መሥርቶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መወዳደር ይችላል፣ ወዘተ የሚሉ ነገሮች በስፋት ለሕዝቡ ተሰበኩ፡፡ በአጠቃላይ ነፃነቱ ተሰጠ፣ ተነገረ፡፡

ታዲያ ሕዝብ የተሰጠውን መብት በሕግ ለመጠቀም በሚያደርገው እንቅስቃሴ በነገሮች አተገባበርና አተረጓጎም ችግሮች እየተፈጠሩ መጡ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው ከመሪ ድርጅቱ መሻል ሲገባቸው፣ እነሱም የዘመናት ቁስል እያከኩ ሕዝብ በሰላም እንዳይኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአገራችን ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

እንግዲህ ያለውን ሁኔታ መንግሥት ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ እንደሆነባት እውነት ሲሆን፣ ነገር ግን ይኼንን ዕድል በሰፊው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ በሚዲያው ዘርፍ ያሉና ፖለቲከኞች ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ እንግዲህ ይኼንን አጋጣሚ ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ አንዱ ሲሆን፣ እሑድን መሠረት ያደረገ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ጀምሯል፡፡

እኔ በግሌ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ በጣም ጥሩ ነገር እንደሆነ እያሰብኩኝ፣ በአንዱ ማለትም ታኅሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በአምባሳደር ሲኒማ የተደረገውን መድረክ በአካል ታድሚያለሁ፡፡ እናም ጠብቄ የሄድኩት ነገር ሁኖ ካገኘሁት ጋር ሳነፃፅረው፣ የውይይት መድረኩ ምንም እንኳን ጅምር ነው ብለን ብናስብም፣ ምንም የተለየ ቁምነገር ላገኝበት አልቻልኩም፡፡

የውይይቱ ጥሪ መሠረት ያደረገው አገራችን እየተከተለች ያለችው የብሔር ፖለቲካ ላስከተለው ችግር መፍትሔው ምንድነው? የሚለውን በአጠቃላይ የመፍትሔ ሐሳብ ለማንሳት መነሻ ያደረገ ነበር፡፡ በመድረኩ አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር የመነሻ ጽሑፍ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱም በአንድ ጎን ብሔር፣ ዘርና ቋንቋ መሠረት አድርጎ የቀረበና ታሪክን በማዛባት እውነታውን የረሳ መነሻ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የሠራቸውን ጥፋቶች እሱ በሚመስለው መንገድ እየተነተነ፣ እንደ ምንጊዜውም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ነበር በዚህ ምሁር የቀረበው፡፡ በእውነት ከአንድ ምሁር የማይጠበቅ ነገር ነበር፡፡

ከመድረኩ ታዳሚዎች በአብዛኛው የቀረበው ስሜትን መሠረት ያደረገ ሆይ ሆይታ ብቻ ነው፡፡ እውነት ነው ስለችግር ለማውራት ማንም ይከብደዋል ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን የችግሮቹን ምንጭና መፍትሔ ጎን ለጎን መተንተን ከስሜት ከመነዳት ሊያድነን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ጽሑፍ አቅራቢው እንዲህ ብሎ በመሀል ድንገት ጥሩ ነገር ተናግሮ ነበር፡፡ ‹‹የቀደመ አስከፊ ታሪካችንን ትተን መልካም ነገራችንን በጋራ ማሳደግ አለብን፤›› የሚለው ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ ቢሆንም ያቀረበው ጽሑፍ በሙሉ አንድን ብሔር መሠረት ያደረገና ያገለለ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ኢሕአዴግን ተጠያቂ ያደረገ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎችና አንዳንድ ምሑራን ሲናገሩ አንዱ ችግራቸው ያለፈውን መንግሥት ለሁሉም ነገር ኢሕአዴግ ተጠያቂ ያደርጋል ነበር፡፡ ግን እውነታው ራሳቸውም እንዲሁ ነው እያደረጉ የሚገኙት፡፡ ኧረ ለመሆኑ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ለማን ጠቀመ? ተናጋሪው ራሱ ኢሕአዴግን የሁሉ ችግር ተጠያቂ እያደረገ ሲተነትን ነበር፡፡ ታዲያ ማነው የተሻለው?

ሥልጣን ሳይዙ ስለአንድ ብሔር መጥፎነት፣ የተለየ ተጠቃሚነት፣ ወዘተ እያወሩ ሥልጣኑን ሲይዙ ይህን ብሔር ምን ሊያደርጉት ነው? ሊያጠፉት? ሊገነጥሉት? ሊደመስሱት? ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

አሁን ከኢሕአዴግ የሚሻል ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልጋል፡፡ ሰላምን ብቻ የሚፈልግ፣ አንድነትን የሚሰብክ፣ ዕድገትን የሚያመጣ ስትራቴጂ ነድፎ አገርን ለማሳደግ የሚያቅድ ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልጋል እንጂ፣ የተፈጠረውን ግርግር አጋጣሚ በማድረግ ጥላቻውን አብዝቶና አጋኖ ሕዝብ በማባላት መንግሥት እንዲወድቅ አድርጎ ሥልጣን ለመቆጣጠር ማሰብ፣ መራመድ፣ መተግበር የማይሆን ነው፡፡ የሰማያዊ መድረክ ተሳታፊዎችም ቢሆኑ ከሁለት ታዳሚዎች ውጪ ሌሎች እንዲሁ በስሜት የሚናገሩና የሚራመዱ ነበሩ፡፡

ዛሬ እኮ በተቃዋሚ ረድፍ ያሉ አባላትና ደጋፊዎች እነሱን ለማስደሰት ስለዕድገት ዕቅድ ከማውራት ይልቅ ወያኔ አረመኔ ነው፣ ኢሕአዴግ ሕዝብን ያባላል፣ ወዘተ ብሎ መድረክ ላይ ማውራትና መናገር እኮ ከፍተኛ ጭብጨባ ያስገኛል፡፡ ታዲያ ይኼ ነው የትውልድ ዕድገት? ይህ ነው መለኪያው? ምን ያህል ክፍተት እየተፈጠረ እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው፡፡

ውድ አንባቢያን እኔን ግን መፍትሔ ምን ይሆን ብትሉኝ ችግሩን ከማውራት በዘለለ መፍትሔ ይሆናሉ ብዬ ያሰብኩዋቸው መድረኩ ላይ ማቅረብ ፈልጌ ተዘጋጅቼ የነበረ ቢሆንም፣ አቅጣጫው ግን ሌላ ስለነበር እዚያ ከመናገር ለእናተው ባካፍል ይሻላል ብዬ ይኼው ሐሳቤን እያጋራሁ ነው፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ውይይት እንደ ውይይት ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ጥሩ ጅማሬ ነው ብለን መነሳት ብንችልም፣ የተለየ መፍትሔ ያልተነገረበትና ጥላቻ በስፋት የተሰነዘረበት መድረክ ነበር፡፡ ጽሑፍ አቅራቢውም ቢሆን የመሰሉትን መጥፎ ነገሮች ከተነተነ በኋላ የመፍትሔ ሐሳብ እንኳን ሳይሰጥ ነበር የቋጨው፡፡ በእርግጥ መግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ሁሉም ነገር በገፍ መሆን አልነበረበትም፡፡ ሒደቱን ጠብቆ መሆን ነበረበት፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ወይም ሕዝብ የነበረበት ሁኔታ፣ የዕድገት ሁኔታ፣ የትምህርት ሁኔታ፣ የኑሮው ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ለሥልጣኔ ቅርበቱ ተጠንቶና ተሞክሮ ውጤቱ ታይቶ ነበር መሆን የነበረበት፡፡ 

እርግጥ ነው ሁሉም የኢትዮጵያ ችግር ምንድነው ሲባል ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ስለሆነ ነው የሚሉት፡፡ ምን ይደረግ ሲባል ደግሞ ወደ ቀድሞ ክፍለ አገር ይመለስ ይላሉ፡፡ በውይይቱ መድረክ ትንሽ ከስሜታዊ ሐሳብ ወጥቶ አመለካከቱን የተናገረው ሰው እንዲህ ብሎ ነበር የጠየቀው፣ ‹‹ዕውን ይኼ ይቻላል?›› እኔም ደግሜ ልጠይቅ እውነት ኦሮሚያ የተባለው ክልል ወደ አራት ወይ ከዚያ በላይ ይከፋፈል ቢባል ሕዝቡ ይስማማል? እኔ በበኩሌ ጥናት ቢሠራበት እመርጣለሁ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ምንም እንኳን የመፍትሔ ሐሳብ ያልተነሳበት፣ ዓላማውና ሁኔታው እንደ ሌሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች የኢሕአዴግን ሥርዓት ማፍረስ ላይ ያመዘነ ነበር፡፡

በአጠቃላይ አገራችን ኢትዮጵያን እስከ መቼ የሚነሳው ኃይል ሁሉ የአዲስ ሥርዓት መለማመጃ ለማድረግ እንደሚፈልጋት አይገባኝም፡፡ እንደ እኔ ከሆነ አሁን ሥርዓት ማፍረስ ወይም ማቋቋም ሳይሆን ችግሩ ድህነት ነው፡፡ ድህነት አገር ውስጥ ከተንሰራፋ ሥራ አጥነት ይስፋፋል፡፡ በሥራ አጥነትና በድህነት ውስጥ የሚኖር ሰው ደግሞ ሌባ፣ ዘራፊ፣ ወንበዴና አመፀኛ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ካልበላ ስለሚሞት ነው፡፡

ለዚህም ነው በአንድ ወቅት ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች በአገሬው ሰዎች ይውጡልን ተብለው እስከ ሞት የደረሱት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥራ አጥነት ነበር፡፡ አሁንም በክልሎች ብሔር ተለይቶ የሚደረግ እንቅስቃሴ እኛ ሳንበላ ሌላ ብሔር እንዴት እኛ አከባቢ ይኖራል የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን እንዲህ አልነበርንም፡፡ ነገር ግን ሆነ፡፡ ስለዚህ በሆነው ላይ ነው መነገር ያለበት፡፡

ድህነት እኮ ከባድ ነው፡፡ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ብዙ ችግር ይፈጠራል፡፡ ችግር ቤተሰብንም እርስ በርስ ያጋድላል፡፡ ስለዚህ የአገራችን ጠላት ድህነት ነው፡፡ ሰው፣ የፖለቲካ ፓርቲው፣ መንግሥት፣ ሁሉም በድህነት ላይ ሊነጋገር ይገባል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ስትራቴጂ ነድፈው ካለው አገዛዝ የሚበልጡበትን አማራጭ ማቅረብ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ያለውን ችግር ከማቀጣጠል በዘለለ ምንም መፍትሔ አይመጣም፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው መፍትሔ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰብስበው እንዴት ከአገራችን ድህነት ማጥፋት እንደምንችል ማሰብና መመራመር አለባቸው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው አገራዊ እርቅ ገለ መሌ ሳይሆን፣ እንዴት ድህነት ያበቃል? እንዴት ወደ ዕድገት በፍጥነት ሕዝቡንም በማስተባበር መሄድ ይቻላል? ነው መባል ያለበት፡፡

ሁለተኛ በአገራችን ያለው ሌላው ዋናው ችግር የፓርቲ የበላይነት ነው፡፡ ይኼ ማለት አሁን ባለው ሁኔታ ከመንግሥት ሥልጣን ይልቅ የፓርቲ ሥልጣን ገኖ የወጣበት አሠራር ነው ያለው፡፡ ይኼ መለወጥ አለበት፡፡ እርግጥ ነው የመንግሥት ሥልጣን ለማምጣት ከፓርላሜንታዊ ይልቅ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የተሻለ ዕድል አለው፡፡ ሕዝብ በቀጥታ ፓርቲን ሳይሆን ግለብን የሚመርጥ ሲሆን፣ ፓርቲዎች የተጠያቂነት ዕድላቸው በጣም ይቀንሳል፡፡ ስለሆነም አካባቢው የመረጠውን መሪ ራሱ ይጠይቃል፣ ራሱ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ አንድ ባለሥልጣን በተሰሳተና መጥፎ ነገር ባደረገ ቁጥር ፓርቲ የሚወቀስበት ተያይዞም ሥርዓቱ የሚወገዝበት ሁኔታ ይጠፋል፡፡

ታዲያ በአገራችን ኢትዮጵያ ይኼ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል ለሚለው ጥያቄ፣ እንደኔ አሁን ባለው የሕዝብ ቁርኝትና አመለካከት መተግበር ከባድ ነው፡፡ ግን መፍትሔ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብሔር መሠረት ያደረጉ ክልሎች ማለትም ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ በአብዛኛው ትግራይና አፋር በፖለቲካ ሲስተማቸውና በምርጫ ሥርዓታቸው ፓርቲን ካማከለ ሥርዓት ወጥተው፣ በቀጥታ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲ የወከላቸውም ሆኑ ግለሰቦች ለአስተዳዳሪነት፣ ለከንቲባነት ብሎም ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ማስቻል ነው፡፡ አሁንም አንድ ብሔር ያለባቸው ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማዎች በሙሉ በቀጥታ ምርጫ አስተዳዳሪያቸውን የሚመርጡበት ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡

በአገር ደረጃ ግን የፓርላማ አብላጫ ፓርቲ እንዲቀጥል ተደርጎ አሸናፊውን ፓርቲ የግንባሩ ሊቀመንበር ሳይሆን የሚወክለው፣ ተመራጭን የአገሪቱ መሪ የሚያደርግ ሥርዓት ሊተገበር ይገባል፡፡ መንግሥት ይኼንን እንደ አንድ ትልቅ ግብዓት ሊጠቀምበት ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሦስተኛው መፍትሔ አገራዊ አንድነት የሚያጎለብቱ ነገሮችን በሚገባ ወስኖ ወደ ሥራ መግባት ነው፡፡ እነዚህም ብሔር ያልተጠቀሰበት ተመሳሳይ መታወቂያ ማድረግ፣ ባንዲራ አንድ ብቻ ማድረግ፣ እንዲሁም ብሔራዊ መዝሙርም ቢሆን አንድ ማድረግና ግንባር የተባለ የፖለቲካ አደረጃጀት ማጥፋትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያመሳስሉን በጣም በርካታ ነገሮች ይዘን ይቅርና ሌሎች ሕዝቦች እኮ ከማይመስሉዋቸው የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣… ካላቸው የውጭ ዜጎች ጋር ተስማምተውና ተፋቅረው ይኖራሉ፡፡ እናም ሁሉም ለሰላም ብቻ እንዲነሳ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ሰላማችን ይብዛ፡፡ ፈጣሪ ሰላምን ይስጠን፡፡

ከአዘጋጁ፡- reporter ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል fikre100@gmail.com  አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ምርጫ ደርሷልና በራችሁን ብቻ ሳይሆን ልባችሁንም ክፈቱ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *