በእነ ጉርሜሳ አያኖ ክስ መዝገብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረው መቅረብ ያልቻሉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፖሊስ ተገደው ፍርድ ቤት በመቅረብ እንዲመሰክሩላቸው 4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀርበው እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ ልኮ የነበር ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጊዜ መጣበብ ምክንያት መቅረብ እንዳልቻሉ ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥቷል። የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት የሰጠው መልስ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀርበው መመስከር አይችሉም ወይም በጊዜ መጣበብ አልተመቻቸው የሚል መሆኑ ግልፅ እንዳልሆነ፣ መልሱ መመስከር አይችሉም ከሆነ ትክክል ስላልሆነ የሚመቻቸው ጊዜ ተጣርቶ እንዲመሰክሩ እንዲመቻች ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል 4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በመከላከያ ምስክርነት የጠሯቸው በግለሰብ ደረጃ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት መልስ መስጠቱ አግባብ አይደለም ብለዋል። ለፍርድ ቤቱ የተሰጠው መልስ መጥተው አይመሰክሩም የሚል ከሆነም በፖሊስ ተገደው እንዲመሰክሩላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ አቶ ኃይለማርያም የሚደርሷቸውን ደብዳቤዎች የሚቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት በመሆኑ ምላሽ መስጠቱ አግባብ እንደሆነ፣ ከተሰጠመው መልስ አንፃርም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስክርነት እንዲታለፍ ጠይቋል። አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ቀድሞ በችሎት የተወሰነ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ያነሳው ጥያቄ አግባብ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

ከአቶ ኃይለማርያም ውጭ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ወ/ሮ ጫልቱ ሰኒ እና አቶ አባዱላ ገመዳ ትዕዛዙ የተላከላቸው ቢሆንም ለመድረሱ ማረጋገጫ ደረሰኝ እንዳላገኙ ጠበቃው ገልፀዋል። ለባለስልጣናቱ ትዕዛዝ መላክ እንደማይችሉ በመግለፅ ፍርድ ቤቱ እንዲልክላቸው ገልፀው፣ ፍርድ ቤቱም ወስኖ የነበር ቢሆንም የፍርድ ቤቱ ፅ/ቤት ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ውጭ ጠበቆቹን አድርሱ እንዳላቸው አቶ አምሃ ገልፀዋል። ከባለስልጣናቱ በተጨማሪ የ4ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ ያልቀረቡ ሲሆን የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ ትዕዛዙን አድርሻለሁ ብላለች።

በጌታቸው ሺፈራው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *