★ ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሚያዚያ 24 እና ለሚያዚያ ተይዟል።

የእነ ኦሊያድ መዝገብ ለዛሬ ታህሳስ 18/2010 በአዳሪ ተቀጥሮ የነበረው ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በሚል ነው። በአዳሪ ቀርበው እንደሚሰሙ የተነገራቸው ሶሰት ምስክሮች እና አንድ በዛሬው እለት የቀረበ ምስክር በአጠቃላይ አራት የአቃቤ ህግ ምስክሮች መቅረባቸው ተረጋግጧል። አቃቤህግም የቀረቡት አራቱም ምስክሮቹ በተለያየ ጭብጥ የሚመሰክሩ መሆናቸውን አሳውቆ፤ በመጀመሪያ የምስክርነት ቃሉን የሚሰጠው ዘነበ የተባለ ምስክር መሆኑን እና ከ1ኛ ተከሳሽ ኦሊያድ በቀለ እንዲሁም ከ4ኛ ተከሳሽ ኢፋ ገመቹ ኢሜል ውስጥ ( 358 ገፅ ከኦሊያድ እና 27 ገፅ ከኢፋ ) የተገኘ ማስረጃ ሲወጣ የታዘበውን የሚያስረዳ መሆኑን በጭብጥነት አስመዝግቧል።

ምስክሩ (ዘነበ) የኮልፌ ክፍለ ከተማ የኢህአዴግ ድርጅት አመራር እንደሆነ እና በኦሊያድ እና በኢፋ ላይ ሊመሰክር መምጣቱን ፍርድ ቤቱ ባቀረበለት ጥያቄ መልሷል። በመቀጠልም ታህሳስ 5 ቀን 2009 ዓም ከሰአት 8 ሰአት ላይ ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቁጥር 31 መገኘቱን፣ ከኦሊያድ በቀለ ከኢሜሉ የወጣ በኦሮምኛ የተፃፈ 358 ገፅ ፕሪንት ተደርጎ ሲወጣ 1ኛ ተከሳሽ ኦሊያድ የኔ ነው ብሎ ሲፈርም እሱም መፈረሙን፤ ፅሁፎቹን ምስክሩም ተከሳሹም እንዳላነበቧቸው፤ ፕሪንት የተደረጉት የተለያዩ የኦሮምኛ ፅሁፎች፣ ግጥሞች እና 3ት የኦሮምኛ ዘፈኖችን የያዙ ሲዲዎችም እንደ ነበሩ፤ ይዘታቸው ለሽብር የሚያነሳሱ እና በአንድም በሌላም ነውጥ ሊያነሳሱ እንደሚችሉ መረዳቱን፤ በሲዲው ላይ የነበሩት ዘፈኖችም በአንድም በሌላም ለሽብር እና ለብጥብጥ ሊያነሳሱ የሚችሉ መሆናቸውን፤ ከ4ኛ ተከሳሽ ኢፋ ገመቹ ኢሜል ውስጥም 27 ገፅ መውጣቱን፤ ተከሳሹ ከኔ የተገኘ ነው ብሎ ሲፈርም እሱም መፈረሙን፤ ሁለቱም ተከሳሾች ሲፈርሙ ነፃ እንደነበሩ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

የኦሮምኛ ቋንቋ ሳይችል የሲዲዎቹን ይዘት እና ፅሁፎቹን ሳያነብ አጠቃላይ ይዘቱ ሽብር እና አመፅ ያነሳሳል ሊል የቻለው እንዴት እንደሆነ ከዳኞችም ከጠበቃም ጥያቄዎች ቀርበውለት፤ ከተከሳሾቹ ኢሜል ፕሪንት ሲደረግ በወቅቱ የነበረው መርማሪ ኦሮምኛ የሚችል በመሆኑ ከሱ እንደተረዳ ተናግሯል።

ቀጥሎ የሚቀርበው ምስክር ከ2ኛ ተከሳሽ ሞይቡኑ ምስጋኑ ቤት በፍተሻ ወቅት የተገኙ ነገሮችን እንደሚያስረዳ አቃቤህግ በጭብጥነት አሲዟል። 
ምስክሩ ሲሳይ ስሜ እንደሚባል፤ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሞይቡን ምስጋኑ ቤት ሲፈተሽ ከወረዳ ሃላፊ የሆነ ሰው ያስፈልጋል ተብሎ እንደተጠራ፤ ቤቱ ሲፈተሽ ፦ዘጠኝ መፅሃፍት –ኦሮምኛ እና አማርኛ ፣ ቶሺባ ላፕቶፕ፣ ሁለት ሳምሰንግ ተች ሞባይሎች፣ ሶስት የባንክ ደረሰኝ፣ ሁለት የባንክ ደብተር ፣ ሲዲኤምአር ፣ ቀይ ፍላሽ እና ሁለት ሚሞሪ ካርድ ሪደር ሲገኝ ማየቱን ፤ ቤቱ ሲፈተሽ የፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ ይኑር አይኑር እንደማያውቅ ገልፇል።

በሶስተኝነት የሚመሰክረው ጥላዬ ይርጋ እንደሚባል እና የሚመሰክረው ከ2ኛ ተከሳሽ ሞይቡኑ ምስጋኑ ኢሜል ውስጥ 27 ገፅ መረጃ ሲወጣ በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቁጥር 31 ተገኝቶ የታዘበውን የሚያስረዳ መሆኑን አቃቤ ህግ አስረድቷል። 
ምስክሩ ጥላዬ ይርጋ ቀርቦም ከማእከላዊ ስሙን የረሳው መርማሪ ኮማንደር ፖሊስ ደውሎለት ታዛቢ እንዲሆን ጠርቶት ታህሳስ 5/2009 8 ሰአት አካባቢ ቢሮ ቁጥር 31 እንደተገኘ፤ ከ2ኛ ተከሳሽ ኢሜል 37 ገፅ የቅስቀሳ ወረቀቶች ፕሪንት ሲደረግ ተከሳሹ የኔ ነው ብሎ ሲፈርም እሱም መፈረሙን፤ ተከሳሹ ፅሁፉን ሳያነብ እንደፈረመ፤ ፕሪንት ከተደረገው ውስጥ በአማርኛ የተፃፈው አመፅ የመቀስቀስ ዝንባሌ እንዳየበት፤ ተከሳሹ እና መርማሪው በአማርኛ ቋንቋ ሲግባቡ እንደነበር መስክሯል። የተከሳሽ ጠበቃ በመስቀለኛ እንዲታዘብ የጠራው መርማሪ ምን ብሎ እንደጠራው ጠይቆት፤ “ለስራ ጉዳይ እፈልግሃለው ብሎ ጠራኝ” ብሎ የመለሰ ሲሆን ተመሳሳይ ጥያቄ ከዳኞች ቀርቦለት “የምርመራ ስራ እንሰራለን እሱን ትታዘባለህ ብሎ ነው የጠራኝ” ብሎ መልሷል። ምስክሩ ተከሳሹ ሞይቦን ከመርማሪው ጋር በአማርኛ ይግባባ እንደነበረ በዋና ጥያቄ ሲጠየቅ መልሶ ነበር። አቃቤ ህግ በድጋሜ ጥያቄ “ተከሳሹ ከመርማሪው ጋር ምን ያክል ይግባባ ነበር?” ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ፤ ተከሳሹ አማርኛ ብዙም እንደማይናገር እና ኢሜሉን እና ፓስወርዱን እንዲያስገባ መርማሪው ሲነግረው ብቻ በአማርኛ እንዳወሩ ገልፇል። 
በመጨረሻ የቀረበው ምስክር በትላንትናው እለት ቀርባ ከመሰከረችው (አመለወርቅ ገመቹ) ጋር ተመሳሳይ ጭብጥ (3ኛ ተከሳሽ ቀነኒ ታምሩ የእምነት ቃሏን በነፃ ፈቃዷ እንደሰጠች የሚያስረዱ) መሆኑን አቃቤ ህግ ተነግሯል።

ምስክሩ ሳሙኤል ተሾመ እንደሚባል፤ የካቲት 16/2009 ለግል ጉዳይ (ጉዳዩን አልናገርም ብሏል) ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ሄዶ መርማሪ ታዛቢ እንዲሆን ጠይቆት ከጠዋቱ 4:00 ላይ ቢሮ ቁጥር 30 መገኘቱን፤ እዛም 3ኛ ተከሳሽ የሆነችው ቀነኒ ቃሏን ስትሰጥ እንደሰማ፤ የኦነግ አባላትን እንደምታደራጅ፣ ከደምቢ ዶሎ ቦንብ ለማምጣት መስማማቷን እንደገለፀች፣ ሰባት የደምቢዶሎ ልጆች በኦነግ አባልነት እንደመለመለች፣ ለሷ እና ለሰባቱ ክላሽ እንደሚያስፈልግ መናገሯን፣ ለኦነግየ ወጣቶች ድምፅ በዜና ዘጋቢነት ስትሰራ እንደነበር፤ የኦነግ አባላትን ስትመለምል የኦሮሞ ህዝብ እየተበደለ እንደሆነ እና መብቱን እንደተቀማ እየገለፀችላቸው መሆኑን፤ የመለመለቻቸውን ሰባት ሰዎች ስም እና ስልክ ቁጥር እንደተናገረች፤ እድሜዋን አድራሻዋን እና የቤተሰቧን ሁኔታ መናገሯን ነገር ግን እንደማያስታውሰው፤ እንዲሁም በምትፈርምበት ሰአት የመጨናነቅ እና የመፍራት ሁኔታ ይታይባት እንደነበር መስክሯል።

የተከሳሽ ጠበቃ ተከሳሿ እድሜዋን፣ አድራሻዋን እና የቤተሰብ ሁኔታዋን ብትናገርም ምስክሩ አላስታውሰውም ማለቱን አስታውሶ፤ የተቀሩትን ዝርዝር ጉዳዮች እንዴት ሊያስታውሰው እንደቻለ ጠይቆት ሲመልስ በወቅቱ የምትናገረውን ነገር ትኩረት ሰጥቶ ሲሰማ እንደነበረ ገልፇል።

አቃቤ ህግ በድጋሜ ጥያቄ ተከሳሿ ለምን የፍርሃት ስሜት እንደታየባት ምስክሩን ሲጠይቀው፤ “ፖሊስ ጣቢያ ማናችንም ስንሄድ የመረባበሽ ነገር ይኖራል፤ ነፃ አንሆንም።” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

በእለቱ የቀረቡት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰምተው በማለቃቸው መዝገቡን የሚያየው 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሚያዚያ 24 እና ለሚያዚያ 25/2010 ይዟል።

Ethiopia Human Rights Project

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *