“Our true nationality is mankind.”H.G.

የቴዲ ተስፋ! በተስፋ ቢሱ የፖለቲካ ጋንግሪን ውስጥ

ይህ ክስተት የሆነ የጥበብ ሰው ሁሌም ተሰፋኛ ነው። ተስፋ የሚያደርገው ደግም በተስፋ ቢሱ የአገራችን የፖለቲካ ጋንግሪን ውስጥ ሆኖ ነው። ቴዲ አፍሮ ስርዓት የበደለው፣ የረገጠው፣ የሚከታተለው፣ ጫና የሚያደርግበት፣ ሁሌም ምክንያት የሚፈልግለት፣ ከዚህም በላይ ቃታቸውን ደጋግመው ቢስቡበት ምኞታቸው የሆነ ምክንያት አልባ “ሰዎች” አጠገብ የሚኖር ቁጥር በማይሰፍራቸው የሚወደድ ሰው ነው።

በጥበብ ስራው፣ አቅሙ፣ ጥልቀቱ እንዲሁም ወቅትን በመምረጥ የሚቀኘው ቴዎድሮስ ስለምን በውስን በጣም ጥቂት የህወሃት ሰዎች ይጠላል? ምን አደረጋቸው? የሚለው ጉዳይ መልስ ባይኖረውም ዛሬ ላይ እነዚሁ ክፍሎች ” አገሪቱ” ከሚለው የመለስ አስተምህሮት ” ኢትዮጵያችን” በደሚለው ፖለቲካ መዘዋወራቸውን / ከልብ ከሆነ ማለት ነው/ በሚያበስሩን ውቅት ላይ ሆነው የዚህን ድንቅ ጥበበኛ ስራዎች ላይ የጣሉትን እግዳቸውን የማያነሱበት ምክንያት ግልጽ አይሆንም። ጥርጣሬም ያስነሳል።

የቴዎድሮስ ኢትዮጵያ ዘፈን ስሜት የሚያፈካ፣ የጠወለገ የአገር ስሜትን የሚያነሳሳ፣ ለውስጥ የሚሆን ቅባ ቅዱስ ያለው፣ ምህላ ጭምር የሆነ፣ የጸሎት ያህል የሚነዝር፣ የመቃተት ያህል ቃለ መሃላ የተሞላ፣ እንደ መንፈስ የሚወርድ፣ እንደ ንዳድ የሚያግል፣ ሲቀበሉትና ሲደጋግሙት እንደ ማተብ የሚታተም፣ ልብን የሚያስደልቅ… ወዘተ ዜማ ነው። ይህን ዜማ በሕዝብ ሚዲያዎች እንዳይተላለፍ ማገድ፣ ማሳገድ፣ ማስቆለፍ ፍጹም የጤናም አይመስልም። ምክንያትም የሚቀርበበት አይደለም።

የአማራ መገናኛ በሞራል ኪሳራ አንገቱ ተቀንጥሶ መሞቱን ያወጀው ” ማር እስከ ጧፍን ” ደጋግሞ ለማሰራጨት ቅድሚያ ወረፋ ከመያዝ ይልቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ከሚያቅለሸልሻቸው ትዕዛዝ ተቀብሎ ዘፈኑን ላለማሰራጨት የወሰነ እለት ነው። ይህንኑ ጉዳይ በክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ” የከሰርነው እኛና የክልላችን ሕዝብ ነው” በሚል በራሳቸው የብአዴን ሰዎች ትችት ቀርቦበታል። ሰሚ ግን የለም። የሌሎች ክልሎች ሚዲያዎችም ቢሆኑ በተመሳሳይ ጎድሎባቸዋል። እንደ አገርም መሳቂያዎች ናቸው።

Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?

ሁሉም ቀርቶ ዛሬ ” ጥልቅ ተሃድሶ፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት…” በሚባልበት አደገኛ ወቅት፣ አገሪቱን ከጥላቻ ፖለቲካ ለመታደግ የሚሰሙ ባለግርማዎች በሌሉበት አገር፣ ይህንን ባለሙያ ከፊት አለማሰለፍ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አስቅድሞ ዜግነት መቀየር፣ ማንነትን መካድ አለያም በሽፍጥ በተለወሰ የስም “ኢትዮጵያዊነት” መኖር ግድ ነው።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ጉዳይና እምነት ሳይሰለቹ እንደሚጓዙ እሙን ቢሆንም፣ አካሄዱ ጥያቄ ቢኖረውም “ኢትዮጵያና ኤርትራን እናስታርቅ” የሚሉት ክፍሎች ሰሞኑን ቴዲ ላነሳው ጉዳይ ቀዳሚ የድጋፍ ድምጽ ባሰሙ ነበር። የእርቅን ሃሳብ ምትሃት በሆነው የጥበብ ሃይል ለማስተጋባት የሚምል ሰው ሲነሳ ዝምታ አሁንም ግልጽ አይደለም። ቴዲ ህልሙ ፍቅር ነው። ቴዲ ህልሙ ሰብአዊነት ነው። የቴዲ ህልም ሁላችንም የሚል ነው። ቴዲ ከጥፋታችን እንማር፣ መልካሙን እንያዝ፣ ለወደፊታችን ከማይበጀን ጉዳይ እንራቅ ነው። ይህ ሃሳብ ለወደፊትም ይሰራልና እንስማው!! ድጋፍ እንስጠው። ኢህአዴግ ” መታደሱ” ከሚታይበት ዋናው ማረጋገጫ አንዱና ትልቁ ጉዳይ በጥላቻ ከተማና እስር ቤት ውስጥ ያሰሩዋቸውን ነጻ መልቀቅ ሲጀመር ነው።

ቲዲ ተስፋ አለው። አስመራ ደርሶ እርቅ ሊዘራ ይመኛል። “ጥልቅ” የሚለው ኢትዮጵያዊነት ሁሉንም እኩል አቅፎ ማየትን ይመኛል።  በጋንግሪን በሚመሰለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሆኖ ተሳፋ ያደርጋል። ለቴዲ ምኞት መልካም ምኞት እንላለን። ጎልጉል የሚከተለውን ትርጉም ዜና አቅርቧል።

አስመራ ላይ የሙዚቃ ድግስ ማቅረብ – የቴዲ ተስፋ!

ለዓመታት በአገር ውስጥ የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) እንዳያሳይ የታገደው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አስመራ ላይ የሙዚቃ ድግስ ለማቅረብ ተስፋ እንደሚያደርግ ተናገረ። ችግሮቻችንን አራግፈን ወደፊት መጓዝ አለብን ብሏል።

ዴይሊ ሜይል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስን ጠቅሶ እንደዘገበው በእርሱ ላይ እየደረሰ ያለው ነገር እንዳለ ሆኖ ቴዲ “በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ላይ” ትኩረት ማድረግ መቀጠሉን ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቤቱ ዘና ባለ ሁኔታ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል።

የልጅነት ዘመኑን በማስታወስ ቴዲ ሲናገር፤ “ልጅ ሆኜ እንደ አንድ አገር ስንኖር አስታውሳለሁ፤ አንድ የምናውቃት አገር ኢትዮጵያ የምትባል ነበረች፤ አሁን በዚህ ዘመን ግን የምንታወቀው በዘራችን ነው፤ ይህ ደግሞ እጅግ አደገኛ እየሆነ መጥቷል” ብሏል።

ህወሓት በቴዲ የጥበብ ሥራዎች ላይ ማዕቀብ በመጣሉ በተለይ ተደናቂነትን ያገኘው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው አዲሱ አልበሙም ሆነ ቀደምት ሥራዎቹ እንደሌሎቹ ባለሙያዎች ህወሓት በተቆጣጠረው ሚዲያ ላይ አይሰሙም። አንዳንዶች ይህንን አስመልክተው ሲናገሩ፤ የቴዲ 17 መርፌ ሙዚቃም ይሁን እቴጌ ወይም ባልደራሱ ወይም ማር እስከ ጧፍ ሁሉም ህወሓትን ያስበረግጉታል።

“ጥቁር ሰው” የተሰኘው አልበሙ ህወሓት ከፈጠረው የዘር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ በኦሮሞ ብሔረተኞች ዘንድ ስሙ እንዲጠለሽ ብዙ ተሠርቶበታል። እነ ጃዋር መሐመድ ያደረጉት የበቀል እርምጃ ከህወሓት እኩይ ተግባር ባልተናነሰ መልኩ የቴዲ ሥራ ለሕዝብ እንዳይቀርብ ብዙ እንቅፋትን ፈጥረው አልፈዋል። የቴዲ ኮንሰርት ስፖንሰር አድራጊ የነበረው ሃይኒከን ቢራ በዚህ ዘመቻ ምክንያት ራሱን ማግለሉ የሚታወስ ነው። (ይህንን አስመልክቶ ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ አትሞት የነበረውን ዘገባ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)።

ቤቱ ግድግዳ ላይ በተሰቀለ የምኒልክ ጎራዴ አጠገብ ተቀምጦ ቴዲ ስለተካሄደበት ይህን መሰሉ ህገወጥ ዘመቻ ይህንን ይላል፤ “ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ቀደምት ነገሥታት አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች ሊኖሩ ይችላሉ። አመለካከታቸውን ባከብርም የኔን አመለካከት መውደዳቸውም ወይም አለመውደዳቸው እውነቱን አይለውጠውም።”

በሙስሊምና ክርስቲያን መካከል ሰላምና ፍቅር፣ መግባባት እንዲኖር የሚያዜመው ቴዲ ከህወሓት ሌላ በርካታ ነቃፊና ስም አጥፊዎችም በዘመኑ አላጣም። በአድናቂዎቹ ሴቶች ጡት ላይ ይፈርማል በማለት ስለ እርሱ ሲናገሩ ለነበሩ የሰጠው ምላሽ በኢትዮጵያ በውጭ አድናቆትን እንዳተረፈለት ዴይሊ ሜይል ዘግቧል። እንደ ኢትዮጵያዊ ይህንን ዓይነት ነገር ፈጽሞ ሊያደርገው እንደማይችል ነው ቴዲ የተናገረው። ይህንን በመደገፍ ይመስላል የአፍሮ ኤፍ ኤም ፕሮግራም ኃላፊ የሆነው ኢዮኤል ሰሎሞን “(ቴዲ) የሚሰብከው የሚኖረውን ነው፤ እኛ እንወደዋለን፤ ኢትዮጵያውያን ይወዱታል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

“ኢትዮጵያ” አልበሙ የምረቃ ፕሮግራም የተቋረጠበት ቴዲ አፍሮ፤ ለአዲሱ ዓመት (2010) ያቀደው ኮንሰርትም ተከልክሏል። አሁንም ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ለገና ኮንሰርት ለማቅረብ ያቀረበው ጥያቄ እንዲፀድቅለት እየጠበቀ ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ በሙያውና በሙዚቃው ስለ ኢትዮጵያ ከመሥራት ምንም እንደማያዳክመው ተናግሯል።

የቴዲ ምኞት እና ተስፋ ግን በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም፤ እስከ አስመራ የዘለቀ ነው። እዚያ የሙዚቃ ድግስ ለማቅረብ ተስፋ ያደርጋል። “የሚያስፈልገን የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርባይነት መንፈስ ነው። ምክንያቱም አሁን ያሉት ችግሮች የታሪክ ቅሬታዎች ያመጧቸው ውጤቶች ናቸው። ልናራግፋቸው፤ ወደኋላ ትተናቸው ልንሄድ ይገባል” ይላል ቴዲ አፍሮ።

ዘገባው ከነፎቶው የተጠናቀረው ከዴይሊሜይል ድረገጽ ነው።

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0