ኢሕአዴግ የሕዝብ አመኔታ የነበረው ይመስል ይህንኑ መልሶ ስለማግኘት የሚናገረው የመጀመርያው ስህተት ነው፡፡ መንግሥት በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚቀየር ስለመሆኑ እምነት የሚያሳድር ነገር ጠፍቶ እርሙ በወጣበት አገር፣ በኅብረተሰቡ መሠረታዊ ሀቆች ላይ የተፈተለ የፖለቲካ አቋምና ምግባርም ወደ ሕዝብ ደርሶ በማያውቅበት አገር በሕዝብ ድጋፍ የሚታቀፍ መንግሥት አይኖርም፡፡ በዚህ መለኪያም ሆነ በተግባርም ኢሕአዴግ በሕዝቦች ዕቅፍ ተሞሽሮ አያውቅም፡፡ ኢሕአዴግ በተከታታይ ምርጫዎች ‹‹ማሸነፍ›› የቻለው ሕዝብ በአማራጮች ላይ ከሚደረግ የፍላጎቶች ውድድር የፈለቀ ድምፅ ሰጥቶት ሳይሆን የግዱን፣ የኑሮ ግዴታውን (የመንግሥት ፍላጎትን) ለማሟላት ያደረገው ነው፡፡ ይህ ራሱ እንኳንስ የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ሕጋዊነትን (ሌጅትመሲን) እንኳን የሚያሳጣ ጠንቅ ነው፡፡

በገነት ዓለሙ ሪፖርተር ተሟገት

ኢሕአዴግ 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የጀመረው ሁለተኛውና ‹‹እንደ ገና በጥልቀት የመታደስ›› ንቅናቄው ዛሬም ከአንድ ዓመት ከሩብ ያህል በቀጠለ ተከታታይ፣ እያገረሸና አላባራ እያለ ካስቸገረ ሁከት፣ ቀውስና አለመረጋጋት ጋር እንዳጋጠመን ይገኛል፡፡ ‹‹ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅታችን ኢሕአዴግ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በርካታ አበረታች ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም፣ በሚፈለገው ደረጃ ጥልቀት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመልሰን ወደ አዘቅቱ መመለስ መጀመራችንን [ድርጅቱ] በትክክል አስቀምጧል›› ያለው ኢሕአዴግ ራሱ ከታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባካሄደው የ17 ቀናት ግምገማ መካከል ታኅሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገና ስብሰባና ግምገማ ላይ በነበረበት ወቅት በሰጠው በዚሁ የታኅሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫው፣ ‹‹የድርጅታችን ሥራ አስፈጻሚ ለአገራችን ሕዝቦች ጥያቄ በተሟላ መልኩ መመለስና ለፌዴራል ሥርዓታችን በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ለዚህ ግብ ዝግጅት አስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችለውን የተሳካ ውይይትና መተጋገል በፅናት ቀጥሎበት በቅርብ ጊዜ በድል የሚጠናቀቅ›› መሆኑን ገልጾ፣ ‹‹ሒደቱንም ለመላው የአገራችን ሕዝቦችና ለኢሕአዴግ አባላት በተከታታይ የሚገልጽ መሆኑን›› ‹‹አስገንዝቦን›› ነበር፡፡ ስለ ‹‹ሒደቱም›› ምንም ነገር ሳንሰማ ከታኅሳስ 10 ቀኑ መግለጫ ሌላ ተከታይም ተከታታይም ዜና ሳይነገረን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ራሱ አሥራ ሰባት ቀናት መፍጀቱንና መጠናቀቁን፣ መግለጫውም በማግሥቱ የሚቀርብልን መሆኑን የኢሕአዴግ መልካም ፈቃድ ሆኖ የተነገረን ታኅሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡

ኢሕአዴግ ‹‹በፅናት የቀጠለበትን›› የ‹‹ውይይትና መተጋገል›› ሒደት በተከታታይ ይገለጽልሃል የተባለው፣ በተለይም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚለው ዜጋና ሚዲያ በድል የተጠናቀቀውን የአሥራ ሰባት ቀናት ግምገማ መግለጫ ሙሉ ቃል ለመስማት ሌላ ተጨማሪ 24 ሰዓታት (ሲደመር) መጠበቅ ነበረባቸው፡፡

እንዲያም ሆኖ በታወቀ ምክንያት በተደበላለቀ ስሜት፣ በተስፋም፣ ይበልጡንም በሰቀቀን ‹‹ሲጠበቅ የቆየው›› መግለጫ የኢሕዴግን ልብ የሚናገር፣ ኢሕአዴግ ራሱ የልቡን የተናገረበት ስለመሆኑ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በጠመዝማዛና በተመሰጠረ ቋንቋ በመጻፉ፣ ድርብ ድርብርብ ትርጉም ጋር ግብ ግብ እንድንገጥም የሚያደርገን በመሆኑ፣ ይህ እንዲህ ማለት ነው ወይስ ሌላ እያልን የተቸገርንበት ድርብርብ አነጋገር የነገሠበት መግለጫ ነው፡፡ ይህንን ለማፍታታትና ጭብጡን ፈታትቶ፣ ለመጠየቅና ለማብራራት የደፈረ የመንግሥት ሚዲያም የፓርቲም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣንም እስካሁን ብቅ ሲል አላየሁም፡፡

ኢሕአዴግ በመግለጫው፣ ‹‹ለተፈጸመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤›› ቢለንም በራሱ፣ በድርጅቱና በአገራችን ውስጥ ‹‹የሚታዩ ልዩ ልዩ ችግሮችን በጊዜና በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት ባለመቻሉ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ኃላፊነቱን ከመውሰድ በተጨማሪ›› ይቅርታ እጠይቃለሁ ቢልም፣ ከልብ የመነጨ ፀፀቱን ቢገልጽም፣ ስለስህተት እንጂ ስለጥፋት የማይናገር፣ ማንንም የማይነካና ጥፋትን የማይጠቁም ገለጻ የተደረተበት ነው፡፡ የፓርቲውን የኢትዮጵያን ‹‹ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ›› ለሕዝብ እነግራለሁ ያለ መግለጫ ይበልጥ እየደበዘዘ ከመጣው የአገላለጽ ቋንቋና የአስተሳሰብ ጉም አለመጥራቱና ነፃ አለመውጣቱ የመጀመርያው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጎት፣ የአገር ችግርና ሕመም በግልጽ የሚነገርበት ዘመን አሁንም በቀጠሮ ሊያድር ነው የሚያሰኝ ነው፡፡

ከመስከረም 16 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው በምርጫ ቦርድም የተመዘገበውና በሥራ ላይ ያለው የድርጅቱ የመተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 7(3) የኢሕአዴግ አሠራሮች በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን፣ የበላይ አካላት ውሳኔዎች በተለየ ሁኔታ በሚስጥር ተጠብቀው እንዲቆዩ ካልተወሰነ በስተቀር በተዋረድ ለአባላት መገለጽ እንዳለባቸው፣ በተለየ ሁኔታ በሚስጥርነት ተጠብቀው ሊቆዩ የሚችሉ ጉዳዮች በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎራ ላይ ጉዳት የማስከተል ውጤት ያላቸው ጉዳዮች ብቻ መሆናቸውን፣ በተለይም በኢሕአዴግ ከፍተኛ የአመራር አካላት የሚወሰድና በአገሪቱና በሕዝቦቿ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ አቋሞችን ሁሉ ከአስፈላጊው ማብራሪያ ጋር ለሕዝብ በተገቢው ወቅት መገለጽ እንዳለባቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አካላት ለወሰኗቸው ውሳኔዎች ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው፣ ከዚህ በተጨማሪም ኃላፊነትን ባለመወጣት ወይም ከተሰጠ ኃላፊነት ውጪ መሠማራት ተጠያቂ እንደሚያደርግ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ላይ ኢሕአዴግ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ‹‹ተጠያቂነቱ እንደ ሁኔታው በግንባሩ ወይም በሚመለከተው ድርጀት መተዳደሪያ ደንብ ወይም በአገሪቱ ሕጎች መሠረት ሊፈጸም ይችላል›› የሚል መሽሎኪያ አማራጭ የዘየደ ቢመስለውም፣ ኢሕአዴግን ከግልጽነትና ከተጠያቂነት ግዴታውና ግዳጁ ነፃ የሚያደርገው ቀርቶ የሰጠው መግለጫ ሁሉንም እውነትና እውነቱን በሙሉ ዘርግፎ የሚናገር ባለመሆኑ የጠየቀውን ይቅርታ የሚያሰጠው ምክንያት ተፈልጎ እንዲታጣ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ ‹‹ . . . ለተፈጸመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል›› መባሉን ስንሰማ፣ የመጠየቅም ሆነ ሳይጠየቁ የመቅረት ጉዳይ የሕግ ጉዳይ ነው ወይስ የ‹‹ስምምነት›› የሚል ጥያቄና ጥርጣሬ ያነሳል፡፡ መጠየቅ የኢሕአዴግ ወይም የሌላ ፓርቲ የቢሻኝ ውሳኔ ጉዳይ ነው ወይ? ያስብላል፡፡

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

የኢሕአዴግ መግለጫ ከልብ የመነጨ ፀፀት የገለጸበት፣ ኃላፊነት የወሰደበት፣ ይቅርታም የጠየቀበትና አገራችን ችግር ውስጥ መሆኗን ቢያሳይም የችግሩን ስፋት፣ ጥልቀት፣ አሳሳቢነት፣ እንዲሁም የእሱን ኃላፊነትና ተጠያቂነት አገሪቱ በእሱ አማካይነት በደረሰችበት ‹‹እጅግ የሚስጎመዥ ሁኔታ››፣ ድርጅቱ በከፈለው መስዋዕትነትና ‹‹ድል በድል በማስመዝገብ ዕንቁ ታሪኩ››፣ ወዘተ እንዲካካስለት የሚጠየቅ መሆኑን ሚስጥር አላደረገም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የምንገኝበትን አስደንጋጭ ሁኔታ ‹‹ጊዜያዊ ችግሮች›› ይላቸዋል፡፡ ምክንያታቸውንም ‹‹በፈጸምናቸው ስህተቶች›› ላይ ብቻ የሚላከኩ አይደሉም፡፡ ‹‹ከዕድገታችን ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች ተወጥራ የቆየችበት ሁኔታ መፈጠሩን . . .  ገምግሟል›› ማለት የኢሕአዴግን ምክንያትና ቋንቋ ሁሉ ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢሕአዴግ ችግሮችን ጊዜያዊ በማድረግ ሳይወሰን የ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ›› ያደርጋቸዋል፡፡

ኢሕአዴግ በመግለጫው መጨረሻ ላይ፣ ባደረገው ‹‹ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ›› ላይ በመመሥረት ‹‹አጣዳፊ ችግሮችን እየፈታ፣ ለዘላቂ ለውጥ መሥራት እንዳለበት›› የወሰነው የሚከተሉት ብሎ በስምንት ተራ ቁጥር በዘረዘራቸው ‹‹አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ›› ነው፡፡ እዚህ ዝርዝር ውስጥ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ፣ የፓርቲዎች መርህ አልባ ግንኙነት፣ የፕሬስና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የሕዝብ አመኔታ፣ የሕዝብ ጥያቄ፣ ፌዴራላዊ ሥርዓትና አገራዊ አንድነት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ የሚሉ ቃላትና ጽንሰ ሐሳቦች ታጭቀዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከሚጠሩበት ሐረግ/ስያሜ በላይ፣ ወይም ካነገቡት መፈክር ውጪ፣ ወይም ካንጠለጠሉት መፈክር ቢጤ መለያ የዘለለ ያልተፍታቱ፣ የሕዝብ ግንዛቤና ንቃት ያልሆኑ፣ አፋዊ ኳኳቴ ብቻ ሆነው የቀሩ ሕገ መንግሥታዊ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ሌሎቹ የገዥው ፓርቲ የሐሳብ ፈለጎች መታወቂያ ብቻ ሆነው ያረፉ የጠራ መግለጫ ያልተሰጣቸው ትርጉም አልሰጥ ያሉ ቃላት ናቸው፡፡ እንደ ‹‹አገራዊ አንድነት›› ያሉት ደግሞ ‹‹የትምክህቱ ጎራ›› መታወቂያ ሆነው የዘለቁ፣ የተረሱና ተደፍቀው ቆይተው አሁን አሁን የተነሱ ሐሳቦችም አሉ፡፡

ሁሉንምና እያንዳንዱን ነቅሶ ለማሳየት ጊዜውና ቦታው ብቻ ሳይሆን አቅሙና ችሎታውም ሲበዛ ይገዳል፡፡ ዋነኛው ደግሞ የኋለኛው ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አንዳንዶችን ጉዳዮች እያነሳሁ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የሕዝብ እምነት

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ የሕዝብ ‹‹አመኔታን መልሶ ስለማግኘት›› የተናገረው በመግለጫው 5ኛ ተራ ቁጥር ላይ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔው ወይም ‹‹አቅጣጫ››ው መጀመርያ በአገራችን የተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኛው ሚስጥር የሕዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ነው›› ይለናል፡፡ ቀጥሎም የሕዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ መወሰኑን፣ ሕዝብ የሚደመጥበትና ወሳኝነቱ በሚገባ የሚረጋገጥበት ዕድል እንዲሰፋ አጽንኦት መስጠቱን፣ በተለይም ወጣቶች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሚገባ ለመመለስና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና በልማት ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ በተሟላ ለማረጋገጥ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ይነግረናል፡፡

ኢሕአዴግ የሕዝብ አመኔታ የነበረው ይመስል ይህንኑ መልሶ ስለማግኘት የሚናገረው የመጀመርያው ስህተት ነው፡፡ መንግሥት በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚቀየር ስለመሆኑ እምነት የሚያሳድር ነገር ጠፍቶ እርሙ በወጣበት አገር፣ በኅብረተሰቡ መሠረታዊ ሀቆች ላይ የተፈተለ የፖለቲካ አቋምና ምግባርም ወደ ሕዝብ ደርሶ በማያውቅበት አገር በሕዝብ ድጋፍ የሚታቀፍ መንግሥት አይኖርም፡፡ በዚህ መለኪያም ሆነ በተግባርም ኢሕአዴግ በሕዝቦች ዕቅፍ ተሞሽሮ አያውቅም፡፡ ኢሕአዴግ በተከታታይ ምርጫዎች ‹‹ማሸነፍ›› የቻለው ሕዝብ በአማራጮች ላይ ከሚደረግ የፍላጎቶች ውድድር የፈለቀ ድምፅ ሰጥቶት ሳይሆን የግዱን፣ የኑሮ ግዴታውን (የመንግሥት ፍላጎትን) ለማሟላት ያደረገው ነው፡፡ ይህ ራሱ እንኳንስ የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ ሕጋዊነትን (ሌጅትመሲን) እንኳን የሚያሳጣ ጠንቅ ነው፡፡

ኢሕአዴግ የሕዝብ አመኔታን መልሶ ለማግኘትና ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ወስኛለሁ የሚለው በተራ ቁጥር አንድ ‹‹አቅጣጫው›› ውስጥ ፍላጎት መግለጫዎችን፣ ጥያቄ ማቅረቢያዎችን (ሠልፍ፣ ስብሰባ፣ ንግግር) ‹‹በሕግ የበላይነት›› ስም አልታገስም እያለ ነው፡፡ የሕዝብ አመኔታ የሚያውቅ መንግሥት የሕዝብን የድምፅ መተማመኛ አጣለሁ፣ ተጋልጬ እጠየቃለሁ የሚል ፍርኃት ሳያሠጋው ተቃውሞን በኃይል ለመደፍጠጥ አይደፍርም፡፡ በሕዝብ ዘንድ መታመን የሚኖረው የአንድ ፓርቲ ተቀባይነት በፕሮግራሙ ፋይዳ ላይ፣ የፓርቲው ገዥነት በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ላይ  የተንጠለጠለ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ የመንግሥትንና የሕዝብን መተማመን የሚያሰፍነው ይህ መተማመንም ለሰላም መሠረት የሚሆነው የመንግሥት ሥራ አካሄድ በሕዝብ ዓይንና ጠያቂነት ሥር የወደቀ እንደሆነ ነው፡፡

Related stories   ኢትዮጵያን የምታለቅሰው በ"መሪዎቿና በውድ ልጆቿ" ነውና !! ጆሮ ያለው ይስማ!!

ይህን የመሰለ ዋስትና ያለው ሕዝብ ከመንግሥት ጋር እልክ አይጋባም፣ ቀኑ ሲደርስ አለዚያም ከቀኑ በፊት በሚያሳድረው ተፅዕኖ የመንግሥት ሥልጣን ለያዘው ፓርቲ የስንብት ‹‹ዋራንት›› ይቆርጥለታል፡፡ በመንግሥት በኩል በሕዝብ ላይ መዘባነንና መደንፋት የሚቀረው፣ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰውም የሕዝብን የድምፅ መተማመኛ እናጣለን ተጋልጠን እንጠየቃለን ብሎ መሥጋት ሳይኖር ተቃውሞን፣ ሠልፍን፣ በኃይል ማኮላሸት የሚባል ነገር የሚቀረው፣ በሕዝብም አንፃር ሌላ ዓይነት የትግል ዘዴ የማይታሰበው እንዲህ ያለ መተማመኛ ሲኖር ነው፡፡

ኢሕአዴግን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን ለማወቅ ለሚፈልግ ሁሉ አንድ አብነት ልጠቁም፡፡ ከመሥሪያ ቤት እስከ ሠፈር የተዘረጋው የመንግሥት የአምስት ለአንድና የሬዲዮና የቴሌቪዥኑ የፕሮፓጋንዳ ንዝንዝ ከማስመረሩ የተነሳ፣ ሕዝብ ልቡንና ጆሮውን አልሰጥም በማለቱ ምክንያት ስለ ‹‹ሕገወጥ እርድ››፣ ስለ አተት (ኮሌራ) ጥንቃቄ የሚሰጠውን ትምህርትና መረጃ እንኳ ‹‹ወዲያ ተወን!›› ብሎ ጥሎ እስከመሄድ ያደረሰ ነው፡፡ አተትን የመሰለ አጣዳፊ የጥንቃቄ መልዕክትን በቅጡ ለማስተዋልና ለመስማት የለገመና የተዘጋ ልቦናና ጆሮ የተጋረጠበት መንግሥት ነው ያላንዳች ተጨባጭ ለውጥ የሕዝብን አመኔታ መልሶ ስለማግኘት ‹‹አቅጣጫ ማስቀመጥ›› የሚወስነው፡፡

አገራዊ አንድነት

ድኅረ 2008 ዓ.ም. ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከአገራዊ አንድነት ጋር ታይቶ በማይታወቅና ባልተለመደ ሁኔታ የተቀነቀነበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከዚያም አልፎ በአንድ ግለሰብ ውስጥ ስለሚገኝ የተባበሩት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ማለትም ድብልቅነትና ቅይጥነት በመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሳያባራ መነገር ተጀምሯል፡፡ የታኅሳስ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የመንግሥቱ ቴሌዚዥን ዜናም በአንድ ግቢ ውስጥ ስለሚኖሩ፣ ከዚያም አልፎና ብሶ በአንድ ማድቤት ውስጥ በወረፋ ምግብ ስለሚያበስሉ ብሔር ብሔረሰቦች ዘግቦልናል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ደግሞ ‹‹ . . በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ የተሠራው ሥራ መሆን የሚችለውን ያህል ውጤት ሳያመጣ እንደቀረ . . . ›› ማረጋገጡን ገልጾ፣ ‹‹ብሔረሰባዊና አገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ በመገንባት በኩል የታየውን ጉድለት በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ መፍታት እንደሚኖርብን ታምኖበታል፤›› ብሎናል፡፡ የተሠራው ሥራ ውጤት ሳያመጣ ቀረ ወይስ ያገኘነው የእጃችንን ነው? ኢሕአዴግ ከአሮጌው ቀፎ ወጥቶ ከሕዝብ ጋር ፊት ለፊትና በግልጽ ሊነጋገርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በእኔ በኩል አገራዊ አንድነትን ለአደጋ ያጋለጠው ብሔረሰባዊ ልዩነቶችን ባጠበቀ ማንነትና ጎጆኛነት ልቦናና ኑሮ ስለተከታተፈ ነው፡፡ ለሕዝቦች ሰላም አደጋ የፈጠረው ይኼው ጉዳይ ነው፡፡ የጎጆኛነት አስተሳስብን ያነገሠው ደግሞ በተቃውሞም በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ውስጥ የተስፋፋውና ‹‹ሃይማኖት›› ሆኖ የተቋቋመው ብሔርተኝነት ነው፡፡

ኢትዮጰያ ውስጥ የደራው ጎጆኛት ባለ ባላ ነው፡፡ የባላው አንድ መንትያ ማንነትን አኮማትሮ የብሔር/ብሔረሰብነት ተለዋጭ መጠሪያ አድርጎታል፡፡ ስለማንነት ከተወራ ስለብሔር/ብሔረሰብነት መወራት ሆኗል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ማንነትንና የማንነት አካባበቢን አውቆ ለእምዬ አካባቢ ልማት መዋድቅ፣ የትም (በሩቅም በቅርብም) እየሠሩ ወደ እናት ምድር ማፍሰስ የሁሉም ጎጆኛነት ብሌን ሆኗል፡፡ በባላው ሌላ ጎን ደግሞ፣ ብሔረሰቦችንና ክልሎችን እንደ ሉዓላዊ አድርጎ ማየት፣ በአስተደደር ክልል ያለ የተፈጥሮ ሀብትን (መሬትን፣ ማዕድናትና ውኃን) ሁሉ የክልል፣ ከክልልም ሌሎችን የማይጨምር የነባር ብሔር/ብሔረሰቦች የብቻ ሀብት አድርጎ ማሰብ አለ፡፡

እነዚህ ሁለት መንትያ አስተሳሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱበትንና እንጀራና ልጆች ያፈሩበትን የትኛውንም ሥፍራ አገሬ ብሎ መቁጠርን በጣጥሰዋል፡፡ በየአካባቢው ባለቤት ከሚባሉት ነባር ብሔረሰቦች ውጪ የሆኑ ማኅበረሰቦችንና ግለሰቦችን ያለቤታቸው የሚኖሩ ባይተዋሮች/ሁለተኛ ‹‹ዜጎች›› አድርጓል፡፡ ከዚያም አልፎ የማፈናቀልና የግጭት መነሻ ሆኗል፡፡ ከብሔረሰብ ብጤኛነትና ከአካባቢ ልጅነት የዘለለው የአገር ልጅነት፣ የቅይጥ ዝርያነት፣ በረዥም ዘመን ማኅበራዊና ባህላዊ መስተጋብር ውስጥ የተገኙ የጋራ ገጽታዎችና ትስስሮች ድንግዝግዝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዛሬው የተሳሰረ ዓለም ውስጥ፣ ያውም በአፍሪካ ቀንድ እምብርት ውስጥ ቁርጥራጭ አገር መሆንን እንደ መብት ማየት በእሳትና በትርምስ ውስጥ መኖርን፣ ድህነትንና ጉልበት የለሽነትን እንደ መብት መቁጠር መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ሉዓላዊነት (በራስ ዕጣና ጉዞ ላይ ራስ ወሳኝ የመሆን ሥልጣን) እንኳን በብሔር/ብሔረሰብ ደረጃ ይቅርና፣ እንኳን በኢትዮጵያ ደረጃ ይቅርና፣ በእነ አሜሪካም ደረጃ በዓለማዊ መጠቃለል ከጊዜ ጊዜ ተቆነጣጥሮ የተመናመነ ነገር መሆኑ፣ ትምህርት በቀመሱ ሰዎች አካባቢ እንኳ ተራ ግንዛቤ አልሆነም፡፡

ሰላምና ተያይዞ የማደግ ዕድል ከእጃችን አፈትልኮ እንዳያመልጥ ከፈለግን ከአገር ልጅነት ትቅቅፍ ጋር የብሔር መብትንና መከባበርን ማጣጣም ግዳችን ነው፡፡ የትኛውንም የአገር ልጅ በእኩልነትና በወገንነት ማየት፣ የትም ሥፍራ ላይ አገሬ ብሎ በኩራት መኖርን፣ የየትኛውንም አካባቢ የልማት ጉዳት የእኔ ብሎ መቆርቆርን ማጎልበት አዘላለቃችንን በእጅጉ ይወስናል፡፡ ማጎልበት ሲባልም በአዳራሽና በጋዜጣ የመስበክ ጉዳይ ሳይሆን አመለካከቱን በተግባር ለመኖር የመቻል ነገር ነው፡፡ ይህን አመለካከት የምር ለመኖር ከፈለግን ደግሞ እስካሁን ያለውን የፓርቲ አደረጃጀት ከመከለስ አናመልጥም፡፡ ኢሕአዴግ በአደባባይ ሊያፈርጠው ለራሱም ሊውጠው የሚገባ ዓቢይ ጉዳይ አንዱ ይህ ነው፡፡ ብዙ ማኅበረሰቦችን ባካተተ የአካባቢ አስተዳደር ላይ አንዱን ወይም ሌላውን ብሔረሰብ መሠረት አድርጎ የተደራጀ ፓርቲ ሥልጣን መያዝ አይኖርበትም፡፡ የየራስ ጠባብ ወገንን የመጥቀም ሩጫንና ንቁሪያን ለማዳከም ከተፈለገ፣ የአካባቢ ፓርቲዎች የየአካባቢያቸውን ሕዝብ በጥቅሉ መሠረት አድርገውና የፓርቲ በራቸውን ክፍት አድርገው መደራጀታቸው ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ አገር አቀፍ (ፌዴራላዊ) ሥልጣንን በተመለከተም ብሔርተኛ ቡድኖች ግንባር በሚባል ከለላ ተወሽቀው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር (የሁሉንም ሕዝብ የጋራ ጥቅምና ጠባብ አካባቢያዊ ተልዕኮዎችን የሚያስተናብሩበትና አንዱ ተልዕኮ ሌላውን ሊጎዳ የሚችልበት የሁለትዮሽ ሥራ መቀየር ይኖርበታል ማለትም በፌዴራል ሥልጣን ላይ የመውጣት መብት ኅብረ ብሔራዊ ስም ከመለጠፍ ጋር ሳይሆን በአግባቡ አገር አቀፍ ስብስብ ያለው ውህድ ፓርቲ ከመፍጠር ጋር መገጣጠም አለበት፡፡

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

ይህ ማሻሻያ በፓርቲዎች ድርድር አማካይነት እንደሚነሳው የተወሰኑ ምክር ቤታዊ ወንበሮች ለተቃዋሚዎች ከሚያቋድስ ለውጥ ጋር አብሮ መጥቶ ሕግ ቢደረግ፣ ለውጡ የሚጠይቀው ሥራ ተገባደደ ማለት አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ በአገሪቱ ችግሮች ላይ የተብላላ አገራዊ ምክክር አድርጎ ሰፊ መግባባት የመፍጠርና የሕዝቦችን ተስፋ የሚሞላ ትኩስ መሠረት የመጣል አካል ሆኖ ካልመጣ በቀር፣ እዚህም እዚያም በሚታየው ገንታራነት ላይ ከአናት ለመጫን ቢሞከር ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ ትኩስ መሠረት የመጣል ተግባር ግን መጀመር አለበት፡፡ ከድህነታችን እኩል የሚያናጨን እንክትክታችን መውጣቱ በመሆኑ ክፋቱን እንደገና አስረግጠን እንመልከት፡፡ ሕገ መንግሥቱን ከቋንቋ እስከ እሳቤ ድረስ የመንቀስና የማጎልበት ሥራንም ይጨምራል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 40(3) ላይ የአገሪቱ መሬት የጠቅላላ ሕዝቦቿ የጋራ ይዞታ መሆኑን ቢደነግግም፣ የማንነት ጥያቄና ተግባራዊነት በተወሰነ ምድር ላይ ባለቤትነትን የማስከበርና የመተሳሰብ ጉዳይ ሆነዋል፡፡ የቅርጫው ትግልም እስከ ትንንሽ ወረዳዎች ድረስ ዘልቆ የእኔ ነው ባዩ ንትርክና ግብ ግብ በዚያው ልክ ተባዝተዋል፡፡ በሌላ ጎን የተወሰነች ምድር ‹‹ባለቤቷ›› ታወቀ ማለት የገዥነቱ መብት የማን እንደሆነ ተለየ ማለት ነውና የባለቤትነት መብት ከፀደቀለት ማኅበረሰብ/ማኅበረሰቦች ውጪ ያሉ ወገኖች ባይተዋርነት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ‹‹የባለቤት››/የዋና ማኅበረሰብን መብቶችና ዕድሎች አብልጦና አስፍቶ የንዑሳኑን ወይም ‹‹የባይተዋሮች››ን የማሳነስና የማጥበብ ድርጊት ተገቢ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ “የአገሩ” ባለቤት ከሆነው ማኅበረሰብ ሰዎች ይበልጥ በሀብት የከበረ “መጤ” በዚያ ካለ በዘራፊ ዓይን ማየትም መጣ፡፡ የእሱን ብጤዎች መድፈቅና የእኛ የሚባሉ ቱጃሮች መፍጠር ዓላማም ሆነ፡፡ አድልኦና አበላላጭነቱ መቆሚያ አጣ፡፡ ከትምህርትና ከሥራ ዕድሎች አንስቶ እስከ ሕግ ማስከበርና እስከ ዳኝነት ሥራ ድረስ ዘለቀ፡፡ በማስፈራራትም ሆነ በማሳበቢያ ጥፋት በ‹‹መጤ›› ላይ የማባረር ዕርምጃ መውሰድ የማያስገርምና ቀጪ ያጣ ሆነ፡፡ ምክንያቱም “ብሔረሰቦች ሉአላዊ ናቸው” የሚል ኢሕገ መግሥታዊ አስተሳሰብ፣ እንኳን በአካባቢው ያሉትን በፌዴራል ደረጃም የተቀመጡ ሹሞችን ሳይቀር ሲያሳስት ይታያል፡፡ በመጤዎች ላይ ጥቃት የማድረስ ድርጊት እየተደጋገመ የተፈጸመው (በቅርቡ ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. የተከሰተው) የክፍልፋይነት ርዕዮተ ዓለምና ተግባሩ ስላልታረመ፣ የትም እኩል የመኖር (ቢያጠፉም ባሉበት ሥፍራ ያለአድልኦ በሕግ ፊት የመቆም) መብት ስላልተቋቋመ የዜግነት እኩልነት በቆፎው የቀረ ስለሆነ ነው፡፡

እናም በግልና በጅምላ ሲካሄዱ የኖሩ አድልኦዎች ያመረቷቸው የመቃቃር፣ የቂምና የጥላቻ ማጦች የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ የመተሳሰብና የመተጋገዝ አቅም እንዲዝል አድርገዋል፡፡ መቃቃርና ጥላቻ ህሊናን እየመዘመዘ ምክንያታዊ አስተሳሰብን ከልክሏል የመበቃቀል ፍላጎትን እየቀሰቀሰ ተስማምቶ የመኖር ብርታትን ያነክታል፡፡ በደሎችን በአንድ ላይ እንቢ የማለት ኅብረትን አሳጥቷል፡፡ ለመጫወቻነት አጋልጦ ሰጥቷል፡፡ ከዚያም አልፎ መቋሰልና ጥላቻ  ደርጅቶ ሲቆይ የሚያስገኘው የመጨረሻ ውጤት እርስ በርስ እየተፋጁ መጠፋፋት ነው፡፡ ይህንን የቀመሱና በእኛ የደረሰ በእናንተ እንዳይደርስ እወቁበት የሚል ማስጠንቀቂያ የሚረጩ ልምዶች በአፍሪካም ሆነ ከአፍሪካ ውጪ በርካቶች ናቸው፡፡ ግን ቆም ብሎ ትምህርት መውሰድና አካሄድን ማረም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገና ደካማ ነው፡፡ በተለይ በመንግሥት በኩል እሳት ብልጭ ሲል ከመንከውክውና እሳት ከማጥፋት ያለፈ ዘላቂ መፍትሔ ማድረግ የዋዛ ችግር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአገዛዙ ርዕዮተ ዓለምና ብሂል ከዚህ ማለፍን የሚቀናቀንና የንቁሪያ ጣጣዎችን የሚፈለፍል በመሆኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ምን አለ? ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *