… በዚህ ውሳኔያቸው መጀመሪያ ላይ ጥገኝነት ያልጠየቀው ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የጠየቀውንም ይነፍጉታል። ሥራና የሚከራይ ቤት እንዳያገኝ ያደርጉታል። ይህ ነው የእኛ እጣ ፈንታ … ከጊዜ በኋላ የቀሩትን በግድ እንዲወጡ ያስፈርሟቸዋል አልያም እስር ቤት ያስገቧቸዋል። በዚህ መንገድ ስደተኛው ወደ ሞትና ስቃይ እየሄደ ስለሆነ ጭንቀቱን የሚያሰማለትና የሚሰማው አካል ይፈልጋል … ቢቢሲ አማርኛ

ባለፈው ሳምንት የእስራኤል መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ከአገሪቷ እንዲወጡ ካልሆነ ደግሞ እስር እንደሚጠብቃቸው አስጠንቅቋል።

እነኚህ እስራኤል የኢኮኖሚ ስደተኞች ናቸው የምትላቸው ሰዎች፤ አገራቸው ውስጥ ያለው አስተዳደር ገፍቶ ያስወጣቸው፣ በሞትና ህይወት መሃል ሆኖው የሰሃራ በረሃንና የሜድትራንያን ባህር አቋርጠው የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞች እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብም ከገጠማቸው አሳሳቢ ሁኔታ እንዲታደጋቸው እየተማፀኑ ነው።

“የስደተኛው ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ”

ጥገኝነት ጠይቆ ለሰባት ዓመታት በእስራኤል የኖሮው ኤርትራዊው ኃይለ መንግስትአብ፤ በአገሪቷ ተስፋ አስቆራጭ አያያዝ እንዳለና የሚታየው ተስፋ እንደሌለ ይናገራል።

እሱ እንደሚለው የስደት ህይወት ከባድ ነው። “ከ2006 ጀምሮ የምንኖሮው ህይወት ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው። ጥገኝነት ከጠየቅንበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን 10 ሰዎች ብቻ ናቸው ህጋዊ የመኖርያ ፍቃድ ያገኙት” ይላል።

የእስራኤል መንግሥት ባለፉት ዓመታት አፍሪካውያን ስደተኞችን ለማስወጣት ከዛተባት ጊዜ አንስቶ ‘ሆሎት’ የተባለ የስደተኞች ማቆያ በመስራት በርካታ ስደተኞችን ለ20 ወራት አስቀምጧቸዋለች።

ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ የአገሪቷ ፍርድ ቤት ማቆያው መዘጋት አለበት በማለቱ የአፍሪካ ስደተኞችን ከእስራኤል ለማስወጣት ወስኗል።

እስራኤል በሕገ-ወጥ መንገድ ገቡ ከምትላቸው 38 ሺ አፍሪካውያን ስደተኞች ከግማሽ የሚበልጡት ኤርትራዊያን ሲሆኑ ስምንት ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ሱዳናዊያን ናቸው።

አሁን ላይ ከባድ ፈተና ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገረው ኃይለ “የስደተኛው ህይወት ከጥዱ ወደ ማጡ ነው። የተሻለ ነገር ስላላየበት አብዛኛው ጥገኝነት ሳይጠይቅ ነው የቆየው። ጠይቋል የሚባለውም እንኳ ጥያቄው ምላስ ስላላገኘ ተስፋ የሚያደርግበት ነገር የለም” ይላል።

በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትምህርት የምትሰጠው አስማይት መርሃጽዮን እስራኤል ለስደተኛው የአገሯን ሕግ ለማሳወቅ የሰራችው ነገር የለም። ስለዚህም ስደተኛው ተስፋ በመቁረጥ ለችግር ተጋልጧል ትላለች።

“የአፍሪካ ስደተኞች ተስፋ ቆርጠው ከአገሪቱ እንዲወጡ በተደጋጋሚ ሕጎቻቸውን እየቀየሩ ሲያስጨንቋቸው ነው የኖሩት። ስደተኛ እስራኤል ከገባ ቀን ጀምሮ ህይወቱን ጠልቶ እንዲወጣ ነው የምናደርገው ነበር የሚሉት” አለች።

ጨምራም ለዚህ ሁሉ ምክንያት ጥቁሮችን አለመውደድ ነው ትላለች። “ሌላ ምክንያት የላቸውም፡ ጥቁር ካለመውደዳቸው የተነሳ ነው እንጂ፤ ከ80ሺ በላይ ሕገ-ወጥ ነጭ ስደተኞች አሉ። አንድም አልነኳቸውም” ስትል ገልጻልናለች።

በአሁኑ ጊዜ እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ህይወታቸውን ከሞትና ከሁለተኛ የስደት እንግልት የሚያድንላቸው አካል እየፈለጉ ነው።

ኃይለ መንግስተኣብImage copyrightHAILE MENGSTEAB

እጣቸው ፈንታቸው ምን ይሆን?

እስራኤል የኪስ ገንዘብ እየሰጠች ልታስወጣቸው ከምትፈልጋቸው ስደተኞች መካከል ባለትዳርና ህጻናት የሚቆዩበት እድል አለ። ከዚህ በተጨማሪ ስደተኞቹ በፍቃዳቸው ሰብአዊ በሆነ መንገድ እንደሚመለሱ ነው ባለስልጣናት የሚገልፁት። ይሁን እንጂ እውነታው ይህ አይደለም በማለት ስደተኞቹም ሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አይቀበሉትም።

ህጻናት እና ባለትዳሮች የሚቆዩበት እድል አለ ቢባልም የተቀሩትን ስደተኞች ይቀበላሉ ወደ ሚባሉት አገራት ሊልኳቸው ስለማይችሉ ቀስ በቀስ ሊያስወጧቸው ዕቅድ አላቸው ይላሉ።

“በዚህ ውሳኔያቸው መጀመሪያ ላይ ጥገኝነት ያልጠየቀው ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የጠየቀውንም ይነፍጉታል። ሥራና የሚከራይ ቤት እንዳያገኝ ያደርጉታል። ይህ ነው የእኛ እጣ ፈንታ” ሲል ይናገራል ኃይለ። አስማይትም ”ህጻናትና ሴት ልጆችን ምን ሊያደርጓቸው ነው?” በማለት ትጠይቃለች።

“ከጊዜ በኋላ የቀሩትን በግድ እንዲወጡ ያስፈርሟቸዋል አልያም እስር ቤት ያስገቧቸዋል። በዚህ መንገድ ስደተኛው ወደ ሞትና ስቃይ እየሄደ ስለሆነ ጭንቀቱን የሚያሰማለትና የሚሰማው አካል ይፈልጋል” ትላለች።

“በእኛ ላይ የሚፈፀመው በደል ከባድ ነው። የሚቀጥሩን እስራኤላዊያን 16 በመቶ ግብር እንዲከፍሉ ስለሚደረግ፤ አንድ ኤርትራዊ ከሚቀጥሩ ሁለት ነጮች ቢቀጥሩ ይመርጣሉ” ይላል ኃይለ የስደተኛው እጣ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት እንደማያዳግት በመግለጽ።

አስማይት መርሃጽዮንImage copyrightASMITE MERHATSYON

የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች

በእስራኤል ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትና ሌሎች ሲቪክ ማህበራት የእስራኤል መንግሥት ውሳኔን በማውገዝ፤ እርምጃው የስደተኞች ህይወት አደጋ ላይ የሚጥልና ሰብአዊ ያልሆነ ድርጊት ነው በማለት አውግዘውታል።

አሳፍ የተባለ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድንም ውሳኔው የስደተኞችን እጣ ፈንታ አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት አውግዞታል።

አዲ ድሮሪ አብርሃም ከአሳፍ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ስደተኞቹን ለመቀበል ከእስራኤል ጋር ስምምነት ፈርመዋል የሚባሉት ኡጋንዳና ሩዋንዳ ከእስራኤል ጋር ተስማምወተው፤ ተገደው የሚመጡትን ስደተኞች ይቀበላሉ? የሚል ትልቅ ጥያቄ መጠየቅ አለብን ትላለች።

“እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ ከባድ ፈተና ያለፉ፣ ስጋትና ውስጥ የሚገኙ፣ የታመሙ ስደተኞች ናቸው ያሉት። አፍሪካ ቀጥሎም ዓለም ምን ለማድረግ ነው ያሰቡት የሚል ጥያቄ አለን። ውጡ የተባሉት አፍሪካውያን ስደተኞች ናቸው። ኤርትራውያን ደግሞ አፍሪካውያን ናቸው። አፍሪካውያን ወደ አፍሪካ መላክ ለውጥ አያመጣም” በማለት ጉዳዩ ጠንካራ ትግል ያስፈልገዋል ትላለች አዲ።

“አብዛኞቹ ኤርትራዊያን ስለሆኑ ስለእነርሱ ህይወት ነው የምንጠይቀው። ወደ ሌላ አፍሪካ አገር መላክ ደህንነታቸው ምንኛ የተጠበቀ ያደርገዋል? በቅርብ ዓመታት በዚህ ሁኔታ የተመለሱ ስደተኞች በሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ሜድትራንያን አድርገው ወደ ከፋ ስደት ነው የተጓዙት። እዚህ ላይም ስንት ህይወት ነው የሚከፈለው?” በማለት ትጠይቃለች።

ኃይለ መንግሥትአብም የእስራኤል መንግሥት አብዛኛው ኤርትራዊ ስደተኛ ፖለቲካዊ ጥገኝነት የሚፈልግ እንደሆነ ሊገነዘብ ይገባል ነው የሚለው።

“ማር ለመፈለግ ማር ትቶ የሚወጣ ሰው የለም። ማንነታችን እንዲጠፋና ተበታትነን እንድንቀር የሚያደርግ ፖለቲካዊ ሁኔታ ስላለ አገራችን ትተን እየወጣን ነው” ይላል።

”የሩዋንዳ መንግሥት እየገዛን ነው” የምትለው አስማይት ”ዝምታ የመረጡትን የዓለም ሰብአዊ መብት ተሟጋችና አገራትም የእስራኤልን መንግሥት ሊማጸኑና ሊያሳምኑ ይገባል” ትላለች።

የኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ምላሽ

ባለፈው ሳምንት ኡጋንዳ ከእስራኤል የሚመለሱ አፍሪካውያን ስደተኞችን እንደማትቀበል ገልጻለች። ቀደም ሲል አሳፍ የሚገኝበት ሰባት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በዚህ ጉዳይ ላይ ለሩዋንዳ መንግሥት ደብዳቤ ጽፈው ነበር።

የሩዋንዳ መንግሥት ግን የሰጠው መልስ ባይኖርም፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ አዲ ድሮሪ አብርሃም ተናግራለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ እስር ቤት ወይም በግድ በአውሮፕላን እናሳፍራቸዋለን በሚልበት ጊዜ፤ ከኡጋንዳና ሩዋንዳ የተለያየ ነገር ነው እየሰማን ያለነው ትላለች።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *