የት እና ለማን አቤት ይባላል ?! አጠቃላይ የዳኝነት ሥርዓቱ የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ፍትሕ’ን እንዴት ማግኘት ይቻላል ?! የጥያቄው መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት የመንግስት ባለስልጣናት እንዳይመሰክሩ መደረጉ ህገመንግስቱን በግልጽ የሚቃረን ትዕዛዝ መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ እያለ፤ የተከሳሾት ሕጋዊ መብታቸው መነፈጋቸው አልበቃ ብሎ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ቅጣት መጣሉ በይበልጥ የሚያሳዝን አሳፋሪ ድርጊት ነው።

(ይድነቃቸው ከበደ )

በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ለተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ ፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በመቅረብ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በተከሳሾች የተጠየቁ ሲሆን ፤ እነኚህ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተለያየ ምክንያት በማቅረብ ፍርድ ቤት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት እንዳልቻሉ መገለጹ የሚታወስ ነው። አቶ ለማ መገርሳ እና ሌሎች ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በሁለት ተከታታይ ቀጠሮ በስብሰባ ምክንያት መቅረብ እንዳልቻሉ ሆኖም ግን ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ጠይቀው እንደነበረ የሚታወቅ ነው። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጊዜ መጣበብ ምክንያት ቀርበው መመስከር እንደማይችሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት በደብዳቤ ገልጾ ነበር።

ይሁን እንጂ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የመንግስት ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳይመሰክሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል ። የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ ያሉ የመከላከያ ምስክሮች አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ እና ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ለመመስከር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ጠይቀው ሳለ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ያለው ትዕዛዝ መስጠቱ የፍትሕ ስርዓቱ ምን ያህል የተበላሸ እንደሆነ የሚያመላክት ነው ። ፍርድ ቤቱ ለሰጠው ትዕዛዝ እንደ ምክንያት የጠቀሰው ” በሚረባና በማይረባ ጉዳይ የመንግስት ባለስልጣናት ለምስክርነት መቅረብ የለባቸውም” በማለት ጭምር ነው።

ነገር ግን በህገመንግስቱ አንቀፅ 20 በግልፅ እንደተቀመጠው ፤ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማናቸውንም ክስ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርብ ጥሪ የተደረገለት ሳይቀርብ የቀረ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 448 መሰረት ክስ ሊቀርብበት ከመቻሉም በተጨማሪ በፖሊስ ተይዞ እንዲቀርብ በፍርድቤቱ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ህጉ ያዛል ። ሆኖም ግን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በግልጽ የተከሳሾችን ሕጋዊ መብት በመጋፋት ከላይ የተገለጹት የሕግ ድንጋጌዎች ወደጎን በመተው ” በሚረባና በማይረባ ጉዳይ የመንግስት ባለስልጣናት ለምስክርነት መቅረብ የለባቸውም “በማለት የሰጠው ትዕዛዝ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ሥርዓት ምን ያህል የተበላሻ ጭምር እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

በዚህ ረገድ ሕገመንግስቱንና ሌሎች የሀገሪቱን ሕጎች በእንዲህ መልኩ የሚደፈጥጥ ዳኛ ለሚፈጽማቸው ተግባራት ህጋዊ ስርዓቱን ጠብቆ አቤት በማለት መፍትሔ ማግኘት የሚጠበቅ ጤናማ አካሄደ ቢሆንም፤ የት እና ለማን አቤት ይባላል ?! አጠቃላይ የዳኝነት ሥርዓቱ የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ፍትሕ’ን እንዴት ማግኘት ይቻላል ?! የጥያቄው መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት የመንግስት ባለስልጣናት እንዳይመሰክሩ መደረጉ ህገመንግስቱን በግልጽ የሚቃረን ትዕዛዝ መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ እያለ፤ የተከሳሾት ሕጋዊ መብታቸው መነፈጋቸው አልበቃ ብሎ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ቅጣት መጣሉ በይበልጥ የሚያሳዝን አሳፋሪ ድርጊት ነው።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በተጠርጠሩ አራት ተከሳሾች ብይን ሰጠ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *