መቼም ፈርዶብን አንዱን ችግር ተወያይተንበት ሳንቋጨው ሌላው እየተደረበብን፣ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ይመስል አንዱን አዳፍነን ወደ ሌላው ስንዘምት፣ አንዱንም እሳት ሳናጠፋው በየቦታው እየነደደ ያለው እሳት ተጋግሎ ማጥፋት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰን እኛኑ እንዳያቃጥለን መፍራት ጀመርኩ። እዚህ እሳት፣ እዚያም እሳት፣ ሁሉም ቦታ እሳት! እሳቱን የማጥፋት ግዴታ የተሰጣቸው አካላት ደግሞ ወይ ሙያውን በደንብ አልሰለጠኑበትም፣ ወይ ደግሞ እሳቱ የሸፈነው መሬት በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ማጥፋት አቅቷቸው በየቦታው እየተለበለብን ነው። የእናት አገራችንን ችግር በቅርብ ሆነን “ላለማየት ወስነን” ባህር ማዶ የከተምነው እንኳ ጪሱ እያሳደደ ሲያፍነን ማምለጫ ጠፍቶን፣ አጋጣሚ አግኝተን በተገናኘን ቁጥር በየካፌውና ካፌቴርያው ጥግ ይዘን፣ ከግዜር ሰላምታ በማስቀደም የምንጠያየቀው ስለዚሁ እየተቀጣጠለ ስላለው ያገራችን እሳት ነው። ወይ እሳቱን ላንዴና ለመጨረሻ አናጠፋ ወይ ደግሞ አይቆርጥልን እንዲችው እንደተቃጠልን ለራሳችንም ሳንኖር ችግሩን ለልጆቻችንም አውርሰነው ልንሄድ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቃጠሎ!

ያሁኑ ጽሁፌ ባገራችን ስላለው አጠቃላይ የፖሊቲካዊና ማህበረሰባዊ ቀውስ ሳይሆን፣ ለብዙ ጊዜ አንዳች አዎንታዊና ተስፋ የሚሰጥ መልዕክት ያበስራል ብለን የጠበቅነው ሰሞኑን በመዲናችን ለአስራ ሰባት ቀን በምሥጢር ሲካሄድ የነበረውን “የገዢውን ፓርቲ” መግለጫ  ውሳኔ እና ይህንን መግለጫ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበሰረው ደግሞ መንግሥትሳይሆን የአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች በመሆናቸው፣ ፓርቲና መንግሥት እንዴት አንድ ሊሆኑ እንደቻሉ ባጭሩ ለመዳሰስ ያህል ነው።

ይህ የፓርቲው መግለጫ አይሉት የፖሊቲካ ውሳኔ፣ ካቀፋቸው ስምንት የማጠቃለያ ነጥቦች መካከል አገሪቷ ውስጥ ለተንሰራፋው ቀውስ “የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር” ተጠያቂ ነው“ የሚለውን ብቻ ላነሳ እወዳለሁ። ሌላው በሙሉ ያው የተለመደው ባዶ የቃላት ጋጋታ በመሆናቸው ያላቀፈውን ይዘት ሰጥቼአቸው ጊዜ ከማጠፋ ብዬ ነው።

እንግዲህ ይህ በተለምዶ “ቀውስ” የምንለው ክስተት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባብዛኛው ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ክልል ህዝቦች “ህገ መንግሥታዊ መብታችን ተጥሷል፣ መልካም አስተዳደር ስለጠፋ ሰርተን መኖር አልቻልንም፣ ልጆቻችን ተምረው ሥራ ሊያገኙ አልቻሉም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ በየክልላችን ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር ህገ መንግሥታዊ መብታችንን በወያኔ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ተነፍገናል”፣ በማለት ከዳር እስከዳር የተሳፉበት ህዝባዊ ዓመጽን ነው። “የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር” እንግዲህ ተጠያቂ ነን ካሉ ህዝቡ መብቱን መጠየቁ ህጋዊ ነው፣ ስለሆነም፣ መብቴ ተጥሷል ብሎ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ለማቅረብ በሰልፍ ሲወጣ ዜጎችን መግደላችንና ማስገደላችን ወንጀል ስለሆነ ለጠፉት ነፍሳት ተጠያቂ ነኝ ማለቱ ነው። ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ይሉሃል ይህ ነው። የተፈፀመው ወንጀል ደግሞ የአስተዳደር ጉድለት ሳይሆን የዜጎችን ነፍስ የማጥፋት ወንጀል ስለሆነ፣ በሰማያዊው ቤት በይቅርታ ይታለፍ እንደሆን እንጂ በምድራዊው ህግ ግን በፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል በመሆኑ ሃያ ስድስት ዓመት ሙሉ ለአግዓዚ ጦርና የፀጥታ ኃይላት የመግደል ትዕዛዝ እየሰጠ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ዜጎቻችን ያስገደለ፣ ያሰረና ለሥቃይ የዳረገ ግለሰብና የመንግሥት አካል በሙሉ ለፍርድ ይቀርባሉ ብለው ቃል መግባታቸው ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል። በተጨማሪም፣ ለዓመታት ባገራችን የሌለ የምዕራቦች ፈጠራ ነው ብለው ሲክዱ የነበረውን አሁን ግን መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን በአስቸኳይ እንፈታዋቸዋለን ብለው በአደባባይ ለኢ ትዮጵያ ህዝብ ቃል መግባታቸው እጅግ በጣም የሚያስደስት ነገር ነበር። ቃል ደግሞ ቃል ነውና – ማጠፍ አይቻል ነገር!

ፓርቲና መንግሥት – አንድም ሁለትም?

እንደ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የቅንጦት ዕቃ በሆነባቸው በተለይም እንደ ኢህአዴግ ዓይነት ገና ሲመሰረት ዲሞክራሲያዊ ማዕከልን መመርያው አድርጎ ሲመራበትና ሲመራት እንደነበረው ሃገራችን፣ የፓርቲና የመንግሥትን “አንድነትና” “ልዩነት” የት ላይ እንደሆነ ለይቶ ማወቁ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ሆኖአል። ይህንን ግራ የሚያጋባ “ግንኙነት” በትክክል ለመረዳት ከህገ መንግሥታችን በላይ ሊያስረዳን የሚችል ስለሌለ፣ እስቲ ስለ ሥልጣን ባለቤትነት ምን እንደተጻፈ ማወቁ ሳይረዳን አይቀርምና አንዳንድ አንቀጾች በመጠቃቀስ፣ የኢህአዴግን “ሥላሴያዊ ተፈጥሮ” ቲዮሪ “ትክክለኝነት” እንፈትሽ።

የፓርቲ፣ የመንግሥትና የህዝብ “ሥላሴያዊ” “ተፈጥሮ” በዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው፣ ንጉሣዊ አገዛዝንና የከበርቴውን ሥርዓት በመቃወም አብዮት አካሂደው ባሸነፉ ሶሺያሊስትና ኮሙኒስት ፓርቲዎች ነበር። ያኔ እነሱ የከበርቴ ሥርዓቱን ገርስሰው፣ የማምረቻ መሳርያዎችን የህዝብ/የመንግሥት ንብረት ካደረጉ በኋላ፣ “ድል አድራጊው ፓርቲ” የወዛደሩናን የአርሶ አደሩን ጥቅም የሚያስጠብቅ “ብቸኛና አስተማማኝ ዘበኛ ስለነበረ”፣ ሚዲያን ጨምሮ መቆጣጠር አብዮቱን ከመቀልበስ ያድናል የሚል ነበር መመርያቸው። “ፓርቲው” ደግሞ ከህዝቡ በተውጣጡና ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ብለው መስዋዕት ለመሆን በተዘጋጁ የቁርጥ ቀን ልጆች ስለተዋቀረ፣ ብቸኛውየህዝብ ዕንባ ጠባቂ ነው በማለት “ህዝብ” “ገዢው ፓርቲና” “መንግሥት” አንድም ሶስትም ናቸው ብለው ደነገጉበትግሉ ሂደት የተሸነፉት ተቃዋሚ ኃይላት ደግሞ፣ ልክ ዛሬ ኢህአዴግ እንደሚያደርገው፣ ጸረ አብዮተኞች ተብለው ተፈረጁና በህይወትም ለመኖር መብት የላችሁም ተብለው ድረስ እየተጠቀመበት ያለው። የዚህ ሥርዓት አራማጅ የነበሩ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት “ገዢ ፓርቲዎች” ከ 1990 ጀምሮ ራሳቸው እየፈረካከሱ፣ ባንድ “ገዥ ፓርቲ” ፋንታ ብዙ ፓርቲዎች ፈጥረውና የፓርቲና የመንግሥት የሥራ ድርሻም የተለያዩ መሆናቸውን የሚደነግግ አዳዲስ ህግጋት ሲያወጡ፣ ኢህአዴግ ግን አውቆም ሆነ እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ላስራ ሰባት ዓመት በረሃ ውስጥ ይጠቀምበት የነበረውን የአስተዳደር ስልት አራት ኪሎም ከደረሰ በኋላ ተጣብቆበት ብሎ ቆጭ አለ።

የፖሊቲካ ፓርቲና መንግሥት ሁለት የተለያዩ ህበረተሰባዊ ተቋማት ናቸው። የፓርቲ አባላት፣ የፓርቲውን ወይም የድርጅቱን መስፈርት ባሟሉ ግለሰቦች ብቻ የተዋቀረ ነው። የፓርቲ አባል የመሆን መብት የለም። አባላቱን በራሱ መስፈርት መዝኖ የሚመለምላቸው የፓርቲው አመራር ስለሆነ፣ አንድ ዜጋ የፓርቲውን መስፈርት ባላማሟላቱ ሳይመለመል ቢቀር ህጋዊ መብት የለውምና የአቤቱታ ዕድል የለውም። መስፈርቱን አሟልተው አንዴ ከተመለመሉና የፓርቲ አባል ከሆኑ ደግሞ ተገዢነታቸው ለፓርቲው ብቻ ይሆናል። ጥሩ ከሰሩ የሚያወድሳቸውና የሚሾማቸው፣ ካጠፉ ደግሞ የሚቀጣቸው የፓርቲው አመራር ነው። የፓርቲውን መመርያ በመጣሱ ምክንያት አንድ አባል የሚቀጣው በፓርቲው ውስጣዊ የዲሲፕሊን አሰራር እንጂ ባገሪቷ ህግ አይደለም። የመንግሥት ሚና፣ የፓርቲዎቹ መተዳደርያ ደንብና አሰራር ላገሪቷ ህገ መንግሥትና ሌሎችም ህጎች ተጻራሪ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ብቻ ነው። ባጭሩ፣ ፓርቲው በመስፈርቱ መሰረት “የሚመቸውን” ዜጋ መልምሎ አባል ማድረግ ይችላል። አቶ መለስ ዜናዊም ያኔ እንዳሉት“የኢህአዴግን ዓላማ ከደገፈና መመርያውን እስከተቀበለ ድረስ፣ እንኳን ሰው፣ አህያም ቢሆን በአባልነት ልንቀበለው እንችላለን” ያለው ወርቅማ አባባል ጥሩ መልስ ይሰጣል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት (ፓርላማ) ግን በቀጥታ በህዝብ የተመረጡ ናቸው። የህዝብ ተወካይ ለመሆን ደግሞ ያገሪቷን የምርጫ ደንብ መስፈርት፣ ለምሳሌ፣ የዕድሜ ገደብን፣ የትምህርት ደረጃን፣ የግለሰብን የጤና ሁኔታና ሌላም ሌላ ህጋዊ መብቶችን ጥያቄ ያሟላ ዜጋ መሆን አለበት። በመሰረቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት የሚደረገው ውድድር በግለሰብ እንጂ በቡድን ደረጃ አይደለም። በለስ ቀንቷቸው ከተመረጡና ፓርላማ ከገቡ በኋላ ግን፣ በግል የተወዳደረውንም ሆነ በፓርቲ አባልነቱ ያሸነፈውን ግለሰብ የአሰራርና የተጠያቂነትን ሁኔታ የሚወስነው ያገሪቷ ህገ መንግሥት ብቻ ይሆናል። በሌላ አነጋገር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገዥነታቸውና ተጠያቂነታቸው ለመረጣቸው ህዝብና ለህገ መንግሥቱ እንጂ አባል ለሆኑበት ፓርቲ አይደለም ማንኛውንም የህዝብ ተወካይ ሊሽር የሚችለውም የመረጠው ህዝብ ነው እንጂ “ገዢ ፓርቲ” ወይም ሌላ አካል አይደለም።

ታድያ ዛሬ ኢህአዴግ “ገዢ ፓርቲ ነኝ” በማለት ያገሪቷን ፖሊቲካዊ፣ ማህበረሰባዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፖሊሲ የሚቀይሰውና፣ ያገሪቷን መከላከያና ያገር ውስጥ ጸጥታ መምርያ የማውጣት መብቱን ከየት አገኘው? ይህንን ሰሞኑን በወጣው የ“ኢህአዴግ መግለጫ” እንኳ ለምሳሌ እስረኞችን የመፍታት ጉዳይ የመንግሥት ሆኖ እያለ እንዴት ተጠሪነቱ ለህዝብ ያልሆነው አንድ የፖሊቲካ ፓርቲ በራሱ የውስጥ  ስብሰባ ላይ ሊወስን ቻለ? ያገሪቷንስ ጊዜያዊ ሁኔታስ ተወያይቶ እርምጃ መውሰድ የነበረበት “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” መሆን አልነበረበትም ወይ? ህገ መንግሥታችንስ ስለዚህ ምን ይላል?

የፌዴራል ህገ መንግሥታችን እንደ አንድ የህግ ሰነድ ከማንኛውም ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ካላቸው አገራት ህገ መንግሥት የማያንስ ይዘት ያለው ነው ማለት ይቻላል። ከሁሉም በላይ የሰው ልጅን መብት ማክበርና ማስከበርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ከሞላ ጎደል በተባበሩት መንግሥታትና የሰው ልጅ ማህበረሰብ በዘመናት ልምድ ያካበተውን የሰው ልጅን የማክበርና አብሮ የመኖር ተግባር ያካተተ ዘመናዊ ህገ መንግሥት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ህገ መንግሥቱ ካቀፋቸው 106 አንቀጾች ውስጥ 32ቱ ማለትም ከሩብ በላይ የሚሆነው፣ የግለሰብንና የቡድን የሰው ልጆችን መብት የማክበር ግዴታን የተመለከቱ ናቸው። የቀረው ደግሞ ከሞላ ጎደል፣ መንግሥትንና የመንግሥትን አመሰራረት፣ ሃላፊነቱንና ግዴታውን በዝርዝር የሚገልጽ ሆኖ፣ የፓርቲንና የመንግሥትን የመንግሥትን የሥራ ድርሻና  ኃላፊነት በትክክል አስቀምጧል።

ህገ መንግሥታችን ዓለም ዓቀፋዊ መሥፈርትን ያሟላል ብዬ ከላይ የሰነዘርኩትን አባባል በመረጃ ለመደገፍ ኢንዲያመቸኝ አንዳንዶቹን አንቀጾች ለመጥቀስ ቢፈቀድልኝና ከፌዴራል መንግሥቱ ምንነትና ተግባር ብጀምር፣

  • “የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፣ ተጠሪነቱም ለወከለው ህዝብ ነው፣” (አንቀጽ 50/3)፣
  • “የሃገሪቷን አጠቃላይ የኤኮኖሚ የማህበረሰባዊና የልማት ፖሊሲ ስታራተጂና ዕቅድ ያወጣል፣ ያስፈጽማል።አንቀጽ 51/6)
  • ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት ያገሪቷን መከላከያ  ኃይል ያሰማራል። አንቀጽ 51/4
  • “የምክር ቤቱ አባላት የመላው ህዝብ ተወካዮች ናቸው፣ ተገዢነታቸውም ለህገ መንግሥቱ፣ ለህዝቡና ለኅሊናቸውብቻ ነው” (አንቀጽ 54/4)፣

በፓርላማው አብላጫ መቀመጫ ስላለው ፓርቲ (ገዢ ፓርቲ) የሥራ ድርሻ ሀገ መንግሥቱ የሚከተለውን ይላል፣

  • በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖሊቲካ ድርጅት የፌዴራሉን መንግሥት የህግ አስፈጻሚ ክፍል ያደራጃል፣ ይመራል፣ (አንቀጽ 56)
  • በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖሊቲካ ድርጅት የመንግሥት የፖሊቲካ ሥልጣን ይረከባል፣

(አንቀጽ 73/2)

ታዲያ ኢህአዴግ “ገዢው ፓርቲ” እየተባለ ላለፉት 26 ዓመታት እንደ “ፌዴራል መንግሥት” አካል ያገሪቷን የማህበረሰባዊ የኤኮኖሚና የፖሊቲካን አቅጣጫ እየቀየሰ፣ ሶስቱንም የመንግሥት አካላት፣ ማለትም፣ ህግ አውጪ፣ዳኝነትና አስፈፃሚ አካልን ወክሎ በመንግሥት ስም ውሳኔ ሲያስተላልፍና ሲያስፈጽም የነበረው ከማን/በማን የተሰጠውን መብት ተጠቅሞ ነው የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ከላይ የጠቀስናቸው አንቀጽ 56 እና 73/2  የሚደነግጉት፣ በምርጫ ውድድሩ አሸንፎ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው ፓርቲ፣ የህግ አስፈጻሚ አካሉን ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ካቢኔውን እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ የህግ አስፈጻሚ አካላትን ያዋቅራል ይላሉ እንጂ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የሥራ ድርሻ ይወስዳል ወይም ይጋራል አይሉም።

ይህንን ህገ መንግሥቱ በግልጽ ያከፋፈለውን የሥራ ድርሻ ተላልፎ ነው እንግዲህ ኢህአዴግ፣ በፓርላማው አብላጫ ወንበር ስላገኘ ብቻ፣ “የፌዴራሉ መንግሥትንና የህግ አስፈጻሚውን” አካል የሥራ ድርሻ ደርቦ የያዘው። እንደ ደንቡማ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ፣ ተጠያቂነቱ ለራሱና ለአባላቱ ብቻ ስለሆነ ላለፉት አሥራ ሰባት ቀናት ፓርቲው ባካሄደው ስብሰባ ላይ ስለተነሱትና ስለተወያዩበት ነጥቦች ብሎም የደረሱበትን ውሳኔ ለህዝብ የማቅረብ ግዴታ አልነበረበትም። ውሳኔው ለህዝብ መቅረብ የነበረበት ደግሞ ለህዝቡ ተጠሪ በሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበር። ግን በሁለቱ መካከል በማያወላውል መልኩ የተሰመረው ህገ መንግሥታዊ ድንበር ከመጀመርያውም ባለመከበሩ፣ ዛሬ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ሳይሆን እንደ አንድ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል፣ ያለምንም ሃፍረት በአደባባይ ወጥቶ፣ “የፖሊቲካ እሥረኞችን ለመፍታትና” “ማዕከላዊን ለመዝጋት” መወሰኑን ሲነግረን ምን ያህል ከህግ በላይ የሆነ አምባገነን መንግሥት እንዳለን ያመለክታል።

በመሰረቱ ፓርላማው በኢህአዴግ አባላት ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ሥር መዋሉ በራሱ ምንም አደጋ አልነበረበትም። ግን ሁለት ችግሮች አሉበት፣ የመጀመርያው፣ ምርጫው እኩልና ፍትሃዊ አልነበረም። የመወዳደርያ ሜዳው ለተቃዋሚ ኃይሎች ጎርባጣ፣ ለኢህአዴግ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ረባዳ ነበረ። ሁለተኛውና ወሳኙ ደግሞ፣ የፓርላማውን መቀመጫ በሙሉ የያዙት የኢህአዴግ አባላት፣ ታማኝነታቸው፣ ተጠሪነታቸውና ተገዢነታቸው ”ለመረጣቸው” ህዝብ ሳይሆን አባል ለሆኑለት ለኢህአዴግ ፓርቲ ብቻ ነው። ይህ ነው እንግዲህ መሰረታዊው ችግር። ህገ መንግሥቱ የሚለው፣ “የምክር ቤቱ አባላት የመላው ህዝብ ተወካዮች ናቸው፣ ተገዢነታቸውም ለህገ መንግሥቱ፣ ለህዝቡና ለኅሊናቸው ብቻ ነው” ሲሆን በተግባር ግን የሚታየው፣ የፓርላማው አባላት በስብሰባ ወቅት ራሳቸውን የሚያዩት ልክ በኢህአዴግ ስብሰባ ላይ እንዳሉና ፓርላማው ደግሞ የፓርቲው መሰብሰብያ አዳራሽ እንደሆነ አድርገው ነው። በኔ ግምት፣ የፓርላማው መቶ በመቶ በመቆጣጠራቸው፣ መንግሥትና ፓርቲን ለያይተው እንዳያዩ ተጽዕኖ ያደረገባቸው ይመስላል። አለያማ፣ “የህዝብ ተወካዮቹ” እንደማንኛውም የሰው ልጅ፣ ተፈጥሮ የለገሳቸውንና በህገ መንግሥታችንም የተደነገገውን መብታቸውን በመጠቀም የተቃውሞ ድምጽ የማያሰሙት፣ፓርቲው የሚመራበት የዲሞክራሲያዊ ማዕከልነት መሪህ የግልን አስተሳሰብና፣ በአስተሳሰቡም መሰረት የመወሰንን መብት ስለሚከለክል ነው። የኢህአዴግ አባላት በፓርላማው ውስጥ በሚደረገው ምርጫ፣ ጭንቅላታቸው በአንድ ሞተር የሚንቀሳቀስ ይመስል፣ 547ቱም ባንድ ላይ እጃቸውን የሚያወጡት በፓርቲው ደንብና ሥርዓት (ዲሞክራሲያዊ ማእከልነት) ተመርተው ነው እንጂ በህገ መንግስቱ ውስጥ በተካተተው አንቀጽ 54/4 መሰረት የተደነገገውን መብታቸውን ተጠቅመው አይደለም ለማለት ነው።

መደምደሚያ

ባገሪቷ ውስጥ እየተከሰተ ላለው ቀውስ አንዳች ዓይነት “መፍትሄ” ይዞ ብቅ ይላል ብለን “በጉጉት ስንጠብቅ ለነበረው” ዜጎች፣ የዚህ የኢህአዴግ ከግማሽ ወር በላይ የፈጀ ምሥጢራዊ ስብሰባ መግለጫ ብዙም የሚያረካ ነገር አልታየበትም። አዎ፣ ህዝባዊ አመጹን ላነሳሳው መሰረታዊ ምክንያት የሰው ልጆች መብት መረገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የአንድ ድርጅት የበላይነት ብሎም በሌሎች ክልሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ እንደሆነ አምነው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ የሺዎችን ሰላማዊ ህዝብ ደም ያፈሰሱትንና ለእሥር የዳረጉትን የጸጥታ አስከባሪ ኃይላት ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድ አልተገለጸም። መግለጫው፣ አዎ አጥፍተናል ግን ይቅርታ አድርጉልንና የዚህን ምዕራፍ ዘግተን ወደ ፊት እንገሥግስ ይመስላል። ሃያ ስድስት ዓመት ሙሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ምድራዊ ሥቃይን ከግምት በላይ በሆነ መልኩ በወያኔ አሰቃዮች እጅ ያዩበትን “ማዕከላዊ”ን ለመዝጋት ባዶ የሆነ ቃል ከሚገቡልን፣ እስካሁን ድረስ ያሰቃየናቸውን ዜጎች ይቅርታ እንጠይቃለን፣ ባለሙያ አሰቃዮችንም ሆነ ለማሰቃየት ትዕዛዝ የሰጡትንም በህጉ መሰረት ለፍርድ እናቀርባለን፣ ካሁን ወዲያ ዜጎች ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው መንግሥትን በመቃወማቸው ብቻ ለእሥራትና ለሰቆቃ አይዳረጉም ቢሉን የበለጠ ያስደስተን ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን ዜጎችን ለእሥርና ሥቃይ የዳረገውን “የጸረ ሽብር” ዓዋጁን ያለምንም መዘግየት እናነሳለን ቢሉን ሌላ ተጨማሪ ደስታ ነበር የሚያጎናጽፈን። የቀረው በሙሉ፣ አቶ ለማ መገርሳ ፍርጥርጥ አድርገው ለኢትዮጵያ ህዝብ ከተናገሩት ዕውኔታ ሌላ፣ ያው ለዘመናት የለመድነው ባዶ የሆነ የቃላት ጋጋታ ነው። (የሚገርመው ደግሞ፣ እነዚህ “የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባላት“ በአደባባይ ቀርበው የመግለጫውን ይዘት ለጋዜጤኞች ሲያብራሩ ላየና ለሰማ ሰው፣ አቶ ለማና የቀሩት ሶስቱ “የኢህአዴግ የከፍተኛ አመራር አባላት” የሚያወሩት ስለተለያየ ስብሰባ ነበር የሚመስለው)።

ዲሞክራሲያዊ ማዕከልነት በተፈጥሮው ጸረ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ነው። እነ ሌኒን ያኔ በሥራ ላይ ያዋሉትም ይህ ጠፍቶአቸው ሳይሆን በጊዜው የነበረውን ጠንካራ የጸረ አብዮትን ኃይል ለመቋቋምና የሰርቶ አደሩን መንግሥት ኅልውና ለማስጠበቅ  ከዚያ የተሻለ የአሰራር ሥልት ስላልነበረ፣ አብዮተኛው መንግሥት እስኪጠናከር ድረስ የተጠቀሙበት ጊዜያዊ የአስተዳደር ስልት ነበር ይላሉ የዘመኑን ታሪክ የፈተሹ ምሁራን። ኢህአዴግ ግን “ለጊዜው” ሳይሆን “በቋሚነት” ነው እየተጠቀመበት ያለው። በኔ ግምት፣ ይህ የዲሞክራሲያዊ ማዕከል የአሰራር ስልት፣ በድህረ ወያኔ ኢትዮጵያም ከሚጠብቁን ፖሊቲካዊ ችግሮች ዋነኛው ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ዛሬ ተቃዋሚ ሆነው ኢህአዴግን የሚታገሉትን የፖሊቲካ ድርጅቶችን መርህና አሰራር ሳይ፣ አብዛኞቹ በውስጣቸው የተለያዩ አስተሳሰቦችን የማስተናገድና ልዩነትን አቻችሎ፣ ግን ደግሞ በሚያግባባ ነጥብ ላይ ተስማምቶ አብሮ የመጓዝን ባህል ገና ያልተዋሃዳቸው መሆኑን ሳስተውል፣ ቀሪውም ጉዞአችን እንዳለፈው ሁሉ አባጣ ጎባጣ የሞላበትና ተስፋ አስቆራጭ ይመስለኛል። ስለዚህ፣ ኢህአዴግን ከአርባ ዓመት በላይ የተጠቀመበትን የፓርቲውን የዲሞክራሲያዊ ማዕከልነትን አሰራር ከፓርላማው መድረክ አውጣ ብሎ ማሳመን ስለማይቻል፣ ከድህረ ወያኔ በኋላ የኢትዮጵያን ህዝብ በቅንነት ለማገልገል እንታገላለን የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ይህንን መሰረታዊ የሆነ “ልዩነትን አቻችሎ አብሮ መጓዝ”የሚለውንና የግለ ሰብ አስተሳሰብ የሚከበርበትን መርህ ካሁኑ መለማመድ ቢጀምሩ ይበጃል ባይ ነኝ። በተጨማሪም፣የሰው ልጅ ከልምድና ካለፈው ስህተት ይማራልና፣ ፓርቲን ከመንግሥት ጋር ማዳበላችን ባገራችን ላይ ካደረሰው አደጋ ተምራችሁ፣ ለወደፊት በሚረቀቀው የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ህገ መንግሥታችን ውስጥ የፓርቲና የመንግሥት የሥራ ድርሻ የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ የማስቀመጥ ግዴታ እንዳለባቸው ካሁኑ የበኩሌን ምክር ለመለገስ እሻለሁ።

በመጨረሻ  ላይ ለኢህአዴግ ያለኝን መደበኛ ምክሬን ብለግስ። ጸረ-ህገመንግሥታዊ መሪሃችሁና የአሰራር ሥልታችሁ አሁን ህዝቡ ካለበት የንቃት ደረጃ ጋር ስለማይጣጣምና፣ ህዝቡ ደግሞ ካሁን በኋላ ለመብቱ መዋጋቱን ስለማያቆም፣ የአሰራርና የአመራር ለውጥ በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ካልመለሳችሁ፣ አገራዊ ቀዉሱ አሁን ካለበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ ሊወርድ ስለሚችል አጥብቃችሁ ብታስቡበት ይሻላል ባይ ነኝ። ብቸኛው መፍትሄ፣ የፖሊቲካ ሥልጣንን ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በዕኩልነት ለመጋራት ፈቃደኛ መሆንና፣ በአንድ የድርድር ጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጦ የወደፊቷን የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መሰረት ለመጣል የሚችል የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ዝግጁ መሆን ብቻ ነው እላለሁ። ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የላችሁም። እግዜር አስተዋይ አዕምሮ ይስጣችሁ።

******

ጄነቫ፣ 3 ጃንዋሪ 2017 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኢትዮጵያን የምታለቅሰው በ"መሪዎቿና በውድ ልጆቿ" ነውና !! ጆሮ ያለው ይስማ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *