“ዛሬ የምንቃወመውንም ሆነ የምንደግፈውን ጉዳይ መለየት ተስኖናል” ይላል። ይቀጥልና ቴዲ አፍሮ ባህር ዳር ኮንሰርቱን እንዲያቀርብ የተፈቀደው በህዝብ ትግል ግፊትና ጫና ነው። የቴዲ አፍሮን ዘፈኖች ግብር በሚከፍልበት ቴሌቪዥን እንዳይመለከት የተፈረደበት ህዝብ፣ ከቴዲ ጋር ማር እስከጧፍን በባህር ዳር እንዲያስነካው መፈቀዱ የህዝብ ትግል ውጤት ቢሆንም፣ ክልሉ ‘ በአክብሮት’ ፈቃድ መስጠቱ በበጎነት የሚታይ ነው። ኮንሰርቱ ከስያሜው ጀምሮ ታላቅ ዓላማ ያለው በመሆኑም የሚሰጡ አስተያየቶች በማስተዋል የተሞሉ መሆን ይገባቸዋል። አጉራ ዘለል አስተያየትና ዓላማው ግራ የሚያጋባ ተቃውሞ መሰራጨት ከአማራ ክልል ካድሬዎች ማነስ ነው። 

የቴዲ ሙሉ መልዕክት

ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር!

በቅድሚያ በባሕር ዳር ከተማ በታላቁ ብሔራዊ ስታድየም ” ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ” በሚል ጉዞ የሙዚቃ ዝግጅቴን እንደማቀርብ ካሳወኩበት ጊዜ ጀምሮ በመላው አለም የምትገኙ አድናቂዎቼ ላሳያችሁኝ ፍቅርና ላደረሳችሁኝ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክቶቻችሁ የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ቀደም ብለን የሙዚቃ ድግሳችንን ልናቀርብ ያቀድንበት ጥር 12 ቀን በጥምቀት ማግስት በታላቅ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ ድምቀት ከሚከበረው የቃና ዘገሊላ ክብረ በአል ጋር በመገጣጠሙ ፥ ራቅ ካሉ ከተሞች ወደ ባሕር ዳር ለምትመጡት አድናቂዎቼ አስቸጋሪ እንደሚሆንባችሁ በተለይም የታሪካዊቷ ጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በደብዳቤ፣ በስልክና በኦፊሻላዊው የፌስ ቡክ ገፄ ገልፃችሁልኛል።

እኔም እጅግ ከምወደውና ከማከብረው የጎንደር ሕዝብ እንዲሁም ከተለያዩ የሃገራችን ከተሞች ከሚኖሩ አክባሪዎቼና አድናቂዎቼ የቀረበልኝን ይህን የቀን ይቀየርልን ጥያቄ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሙዚቃ ድግሳችንን በቃና ዘገሊላ ማግስት ዕሁድ ጥር 13 ቀን በታላቁ ብሔራዊ ስታድየም ለማካሄድ መወሰናችንን ከአክብሮት ጋር እያሳወቅሁ ፤ ኑና ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላምና ስለ አንድነት አብረን እንዘምር እላለሁ።

ከምንም በላይ ደግሞ ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት ኢትዮጵያዊነት የሚደምቅበትና ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ የሚታይበት ምሽት ይሆናልና በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የምትገኙ ወዳጆቻችን መጥታችሁ እንድምትደሰቱ እርግጠኞች ነን።

ሃገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !
ፍቅር ያሸንፋል !

ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

ቴዲ አፍሮ በባህር ዳር ስታዲየም የሚያቀርበው ” ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የሙዚቃ ኮንሰርት መራዘሙን አቶ ንጉሱ ጥላሁንም አረጋግጠዋል። የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ በፌስ ቡክ ገጻቸው እንዳረጋገጡት ኮንሰርቱ የተራዘመው በአንድ ቀን ነው። የሙዚቃ ድግሱ እንደሚካሄድ ከተሰማ በሁዋላ በማህበራዊ ገጾች የሚሰራጩ አንዳንድ አስተያየቶች መላ ቅጡ የጠፋ ፣በአብዛኛው በትክክለኛ ማንነት በማይታወቁ ተራ አሉባልተኞች የተሰየሙ፣ ሆነው ተስተውለዋል።
 

ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሰሁን – ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ዝግጅት ወደ ጥር 13 ቀን 2010  ዓም መዛወሩን የገለጹት አቶ ንጉሱ መረጃውን ዘግይተው በማሰራጨታቸው ይቅርታ ብለዋል። ለመዘግየታቸው የሰጡት ምክንያት ” ከኔት ወርክ ውጪ ስለነበርኩ ” የሚል ነው። ኮንሰርቱ የተራዘመው በህዝብ ጥያቄ መሆኑንንም አመልክተዋል። እሳቸው ይህንን መረጃ በሰጡበት ገጻቸው ስር ” ህዝብን መስማት ከቴዲ ተማሩ” በሚል የቀን ለውጥ የተደረገው በአርቲስቱ አማካይነት መሆኑንን የሚያመላክት አስተያየት ተሰጥቷል።

በባህርዳር ከተማ የሚካሄደው “የፍቅር ጉዞ የሙዚቃ ኮንሰርት” ሰፊ ዓላማ ያነገበ ሆኖ ሳለ፣ በጎልደፈ ብዕር ወፈፌ አስተያየት መሰንዘር አግባብ እንዳልሆነ አስተያየት ተሰጥቷል። ቀደም ሲል የተመረጠውን ቀን አስመልክቶ መስተካከል የሚገባው ጉዳይ ካላ በጨዋነት አስተያየት ማቅረብ አግባብ እንደሚሆን እኒሁ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን የሚያቀርበውን የፍቅር ጉዞ የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት አስመልክቶ መሰረት የሌለው አስተያተ መሰንዘር ከምን የመነጨ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ” አማራ ነን” የሚል ታቤላ ተሸክመው በስውር ማንነት የሚገለገሉ እንደሆኑ ሲራክ ዳኔል የተባሉ አስተያተታቸውን አቅርበዋል። 

የአማራ ክልል ከታች ባለው መልኩ የቀረበለትን ጥያቄ በክብር መቀበሉ ምስጋና ብሎም አድናቆት ሊያስቸረው ይገባል። የህዝብ ድምጽ በመሆኑ ብቻ መብቶቹን ለተነፈገው ቴዎድሮስ ካሳሁን የአማራ ክልል የክብር ምላሽ መስጠቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ማር እስከጧፍን በክልሉ ቴሌቪዥን የመመልከት እድል ለተነፈገ ህዝብ፣ የአማራ ክልል የሰጠው ምላሽ አገር ቤት ባለው ሰላማዊ የህዝብ ትግል የተገኘ ውጤት መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም። 

እውቁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዴ አፍሮ/በጥምቀት ማግስት ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በክልላችን መዲና ውቢቷ ባህር ዳር ከተማ ግዙፉ ስታዲየም ” ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ” በሚል ርዕስ የሙዚቃ ኮንስርት ለማዘጋጀት ወደ ባህር ዳር ሊያቀና ነው። ኮንሰርቱ ስለ ሰላም ፣ስለ ፍቅር፣ስለአንድነት ፣ስለ አብሮነት እና ስለ የኢትዮጵያዊት የሚቀነቀንበት ሲሆን በክልላችን ልንሰራቸው ካቀድናው የህዝብ ለህዝብ ስራዎች አንዱ ሰለሆነ የክልላችን መንግስት እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የአርቲስቱን ጥያቄ በታላቅ አክብሮት ተቀብለውታል። የውቢቷ ባህር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ኮንሰርቱ የተሳካ ይሆን ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ሙሉ እምነታችን ሲሆን በክልላችን የተለያዩ አካባቢዎች መሰል የአንድነት ፣ የሰላም እና የፍቅር መድረኮችን በመፍጠር አገራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር የምንሰራቸውን ስራዎች ከህዝባችን ጋር በመሆን አጠናክረን የምንቀጥል መሆናችንን እንገልፃለን። – አቶ ንጉሱ ጥላሁን 

 

Related stories   በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ ዶላር ተያዘ

እንደምን ሰነበታችሁ ?

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *