አንዱዋለም አራጌ፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ፣ የልጆች አባት፣ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ነዉ። አንዱዋለም ስለ ትጥቅ ትግል ያለዉን አመለካከት አውቃለሁ። በየትኛዉም መድረክና ፍርድ ቤት፣ መጽህፍ ቅዱስ ላይ እጄን ጭኜ የምመሰክረዉ ነዉ። አንዱዋለም አራጌ የግንቦት ስባት አባል ወይንም ሽብርተኛ ነው የሚለውን፣ በምን መስፈርትና መልኩ ልቀበለው አልችልም።

– ግርማ ካሳ

ዛሬ ስለአንድ የማክበረውና የማደንቀው ወዳጄ፣ የኢትዮጵያ አንጋፋ ልጅ መጻፍ ፈለኩ። አንዱዋለም አራጌ። « የግንቦት ሰባትን ተእልኮ ለማስፈጸም አገር ዉስጥ በሕቡእ (ስዉር) ይንቀሳቀሳል በሰላማዊ ትግል እንታገላለን የሚሉ የፓርቲዎችን ሽፋን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ በመሆኑ በቂ ማስረጃ አቅርበናል» የሚል ክስ ነው አቃቤ ሕግ ያቀረበበት።

አንዱዋለም ያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሲያደርግ የነበረው በግልጽና በገሃድ ነበር። ለተለያዩ ፓልቶክ ክፍሎች፣ አገር ዉስጥና በዉጭ ለሚገኙ ሜዲያዎች በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሰጥቷል። በአገር ቤት፣ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ዉይይቶችና ስብሰባዎች ያቀረባቸው ንግግሮች በሙሉ የተደበቁ አይደሉም። ዉጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር (አንዱም እኔው ነበርኩ) ፣ ብዙ ጊዜ በስልክ ሃሳቦችን ተለዋዉጧል። በስልክ ያደረጋቸው ንግግሮችም፣ 24 ሰዓት የሰላማዊ ተቃዋሚ መሪዎችን ስልክ በሚጠልፈው ቴሌ ዘንድ የተሰሙ ናቸው። ቤቱና ቢሮዉ ከላይ እስከ ታች ተበርብረዉ ፣ የሚስጥራዊ የኮሚኒኬሽን መሳሪያዎች፣ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ ሚስጥራዊ ሰነዶች አልተገኙም። ኤሜሎቹ በሙሉ ተነበዋል። አንዱዋለምን ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያገናኝ፣ በሕቡእ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የሚያመለክት አንዳች መረጃ አቃቤ ሕግ አላቀረበም። የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ፡ አንደኛ አቃቤ ሕግ ምስክር አስጠንቶ፣ ዳኞችም ደግሞ ከደህንነት ሃላፊዎች መመሪያ ተሰጧቸው ነው።

አንዱዋለም አራጌ፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ፣ የልጆች አባት፣ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ነዉ። አንዱዋለም ስለ ትጥቅ ትግል ያለዉን አመለካከት አውቃለሁ። በየትኛዉም መድረክና ፍርድ ቤት፣ መጽህፍ ቅዱስ ላይ እጄን ጭኜ የምመሰክረዉ ነዉ። አንዱዋለም አራጌ የግንቦት ስባት አባል ወይንም ሽብርተኛ ነው የሚለውን፣ በምን መስፈርትና መልኩ ልቀበለው አልችልም።

ይህ ቤተሰብ አያሳዝንም? የእነሱ መከራ ሌላውን እንዴት ያስደስታል? እነዚህ ህጻናትስ ?

በጣም ያሳዝናል። እንደ አንዱዋለም አራጌ አይነት አገር ወዳድ ዜጎች፣ አገራቸዉን በመዉደዳቸው፣ የሕዝብ መብት ይከበር በማለታቸው፣ «ሽብርተኞች» በሚል አሳዛኝ ክስ ሲታሰሩ ማየት፣ አገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች ቀና ብለው የሚራመዱባት ሳይሆን ፣ አሳፋሪ ድራማ የሚካሄድባት፣ ሕግ መቀለጃ የሆነባት አገር መሆኗ፣ በርግጥ ልብን የሚያደማ ነው።

ገዢው ፓርቲ ለአሥራ ሰባት ቀናት ካደረገው ስብሰባ በኋላ እስረኞችን እንዲፈታ ቃል ቢገባም እስካሁን እንደዉም ሌሎችን ማሰር ቀጠለ እንጂ የተፈታ የለም። አሁንም ኢሕአዴጎች ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው ፣ በአደባባይ ቃል የገቡትን እንዲጠብቁ ፣መልካም ነገር እንዲያደርህጉ እነርሱን ማነጋገርና ለማሳመን መሞከር፣ ማበረታታት ተገቢ ነዉ የሚል እምነት አለኝ።

ሆኖም ግን ሁሉንም ነገር ከነርሱ ጠብቆ ቁጭ ማለቱ ግን፣ እጅግ በጣም ትልቅ ስህተት ነው። እነርሱ ቢሰሙ መልካም ነዉ፤ ካልሆነ ግን እያንዳንዳችን መብታችንን የማስከበር ሃላፊነት ያለብን ይመስለኛል። እነ አንዱዋለም ታስረዋል። ነገ እያንዳንዳችን ቤት ይንኳኳል ። ዛሬ ሊመቸን ይችላል። ነገር ግን ለሕይወታችን ምንም ዋስትና አይኖረንም። አንድ የመንግስት ባለስልጣን ፊታችንን አይቶ ከጠላን፣ በቀላሉ ወደ ወህኒ ሊወረወረን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ማወቅ አለብን። አለን የምንለውን ቢዝነስ አንዱ ከፈለገዉ፣ «ያለ የሌለዉን እያመጡ፣ ይሄን ያህል ግብር ክፈል» ተብለን ከጨዋታ ዉጭ በቀላሉ ልንሆን የምንችልበት አገር ነዉ ያለችን። አቤት የምንልበት የሕግ ስርዓት የለም። አብዛኞቹ ዳኞች በመመሪያ የሚፈርዱ ካድሬዎች ናቸው። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ፣ ሕግ የበላይ የሆነባት፣ ለሁሉ ዜጎቸ እኩል የሆነች፣ ኢትዮጵያዊያን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የሚችሉባት፣ መቀባባል፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም ፣ ፍትህና ወንድማማችነት የሰፈነባት፣ የበለጸገች አገር እንድትሆን፣ እያንዳንዳችን የድርሻችንን መወጣት አለብን። ዳር ሆኖ ተቀመጦ ማውራት ይብቃ። ሌሎች ለምን እንዲህ አላደረጉም ብሎ መክሰስ ይብቃ። ሌሎች ሞተው በነርሱ አስክሬን ላይ ተረማመደን ለመሻሻል መሞከር ይብቃ። አገራችን የእስክንደር፣ ወይንም የአንዱዋለም፣ ወይንም ዶር መራራ ጉዲና፣ ወይንም ኮሎኤል ደመቀ ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ናት፣ ሁላችንም ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሌሎች ነጻ እንዲያወጡን ሳንጠብቅ፣ የድርሻችንን እንወጣ።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *