ከሁሉም በላይ እስረኞችን ለመጠየቅ ለሚንከራተቱ፣ ቤተሰባቸው ጎሎባቸው በህሊና ሲማቅቁ ለነበሩ፣ የቤተሰብ ፍቅር ለተጓደለባችሁ፣ ከፖለቲካው በላይ ህሊናችሁ ላዘነና ለተጨነቃችሁ፣ ለሕዝብ ብላችሁ ወህኒ ስትማቅቁ ለነበራችሁ በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ። ” የታሰሩት ይፈቱ” በሚል ለታገላችሁ፣ እየታገላችሁ ላላችሁ፣ ለሞታችሁና አካላችሁ ለጎደለ ” ሰላማዊ የአገር ውስጥ ታጋዮች” ሰላማዊ ትግል አሸናፊ እንደሆነ አያችሁ። 

በመላው አገሪቱ በሚባል ደረጃ ተነስቶ በነበረውና አሁን ድረስ በቀጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ እንዲሁም በውጪው ዓለም በሚገኙ ዜጎች ትብብር በሰላማዊ መንገድ የተፈጠረው ጫና ከዕለት ዕለት እየከረረ አገሪቱ አሁን ያላችበት ደረጃ መድረሱ ገሃድ ነው። ራሱ ኢህአዴግም ሆነ አበር ድርጅቶቹ በየፊናቸው ወቅቱ አሳሳቢ መሆኑንም በተደጋጋሚ ከስጋት ባለፈ ሲያስታውቁ ነበር። አሁንም ድረስ ይህንኑ እየወተወቱ ነው።

አገሪቱ ከገባቸበት የፖለቲካ ቀውስና የዘር ጥላቻ ትብትብ ጋር ተዳምሮ ለተነሳው ተቃውሞ እርቅ አስፈላጊ መሆኑንን ራሱን ተቃዋሚ ተብለው የታሰሩት ከሚሰድቡት በላይ ራሱን እያቆሸሸ ንስሃ መግባቱን ያስታወቀው ኢህአዴግ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መወሰኑን ይፋ ለማድረግ ተገዷል። እስር ችግሩን የሚያሰፋ እንጂ የሚያቀል አለመሆኑን የተገነዘበው ኢህአዴግ፣ ይህንኑ ይፋ ያደረገውን ጉዳይ ውሎ ሳያድር ሲያስተባብል፣ ሲሰርዝና ሲደልዝ መታየቱ ከቀውሱ በላይ መነጋገሪያ ሆኖ ስንብቷል። 

merera

ዛሬ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌታቸው አምባዬ በሁለት መስፈርት በተደረገ ማጣራት 115 እስረኞች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቀዋል። የደቡብ ክልል ደግሞ 413 እስረኞችን በተመሳሳይ ለመፍታት መወሰኑንና ስማቸውን ይፋ እንደሚያደርግ መግለጹ ተሰምቷል። በሌሎች ክልሎችም ይቀጥላል።

ከጅምሩ ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት አገሪቱ ወደ እውነተኛ እርቅ እንድታመራ ሁሉም ወገኖች ቀናነት እንዲላበሱ ያሳስባሉ። ኢትዮጵያ ያለ እርቅ ምንም አይነት መፍትሄ እንደማይኖራት የሚናገሩና የሚያምኑ ሰላማዊ ትግል እንዲጎለብት ኢህአዴግ ራሱን እንዲያዘጋጅና ድጋፍ እንዲሰጥ ይማጸናሉ። በዚህ ዘመን ” ጨፍን ላሞኝህ” የሚለው ፖለቲካና ህልመኛነት ስለማይሰራ ኢህአዴግ ፈቃደኛ አልሆንም ቢል እንኳን እንደማይሳካለት እነዚህ ክፍሎች ያሳስባሉ። 

ሰላማዊ ትግል፣ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያለው ንቅናቄ ሊከስም ስለማይችል ወደ ሰላማዊ ሽግግር፣ ሰላማዊ ምርጫ፣ በህዝብ ድምጽ ስለመገዛት ከወዲሁ ማስተማመኛ በመስጠት እስር ቢት ሲማቅቁ የነበሩትን ብቻ ሳይሆን በቁም የታሰሩትም ሳይሸማቀቁ በፈለጉት መልኩ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ኢህአዴግ መድረኩን እንዲከፍት ጥሪ የሚያስተላልፉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም። በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ በህዝብ የተመረጡ መሪዎች አገር የሚያስተዳድሩበት ዘይቤ ሲረጋገጥ እስር ቤት መገንባት፣ ለመከላከያና ደህንነት የሚመደብ በጀት፣ የእርስ በእርስ ስለላ ቆሞ ሁሉም አይኑንን በውጪ ወራሪ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይገደዳል ሲሉም ምኞታቸውን ይገልጻሉ።

mrera and beqele

ከሁሉም በላይ አሁን በቀረቡት ሁለት መስፈርቶች መሰረት ክሳቸው የተቋረጠባቸው ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ወገኖች ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸው መሆኑንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መልቀቅ ለነገ እንደማይባል በርካቶች እየገለጹ ነው። ሁለተኛው ዙርና ሶስተኛ የተባለው ዙር በሁለት ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ከሃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። የታሰሩት ጀነራሎች፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች መኮንኖች ሊፈቱ እንደማይችሉ አቃቤው ምልክት ሰጥተዋል። 

ቢቢሲ አምርኛው ክፍል ይህንን ዘግቧል

Related stories   የአምነስቲ " ሽንቁረ ብዙ" ሪፖርት የተከፋዮች የቲውተር ዜና ድምር

ኦሮሚያና አማራ ክልል የሚፈቱ እስረኞችን እየለዩ ነው

ከደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ክልል በተጨማሪ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል በጉዳዩ ላይ ምን እየሰራ ነው ስንል ጠይቀናል። የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ኮሚኒኬሽን ሃለፊ አቶ ታዬ ደንደዓ ክልሉ ”የክስ መዝገቦችን እያጣራን ነው። እሰከ ጥር 12 ድረስ አጣርተን እንጨርሳለን” ብለዋል።

”የፖለቲካ ተሳትፎ የሚባል ወንጀል የለም። ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር ተያይዞ የታሰሩ በሙሉ ይፈታሉ።”

እንደ አቶ ታዬ ከሆነ ክልሉ እስረኞች የሚፈቱበት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ የለም። ”በሽብር፣ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመናድ ሙከራ አድርገዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸውም ይፈታሉ” ይላሉ አቶ ታዬ።

ይሁን እንጂ በግል ጸብ የሰው ህይወት ያጠፉ ወይም አካል ጉዳት ያደረሱ ግን ይህ ምህረት አይመለከታቸውም ብለዋል።

አቶ ማሩ ቸኮል የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ክልሉ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ ነው ብለዋል። ክልሉ ልክ የፌደራል አቃቤ ሕጉ እንዳስቀመጣቸው ያሉ መስፈርቶች የሚኖሩት ሲሆን “እኛም የምንከተለው አካሄድ ተመሳሳይ ይሆናል” ብለዋል።

“ክሶችን የፌደራል ወይም የክልሉ ስልጣን የሆነውን የመለየት ስራም ይሰራል። ከዛ በኋላ የሚለቀቁትን እስረኞች ለሕዝቡም ለመገናኛ ብዙሃንም ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

በክልሉ የተዋቀረው ኮሚቴ ከርእሰ መስተዳድሩ፣ ከክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ እና ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ተወያይቷል ያሉት አቶ ማሩ በዚህ መግለጫ ወቅት የሚፈቱ ታራሚዎች ስም ዝርዝር ለምን አልደረሰም ለሚለው ጥያቄ የደቡብ ክልል ቀድሞ ተዘጋጅቶ ካልሆነ በስተቀር ታራሚው በርካታ ስለሆነ እና የማያዳግም ስራ ለመስራት እንዲያስችል እየሰራን ነው።

“ከዚህ በላይ ባይዘገይ እኔም ደስ ይለኛል ታራሚዎቹ ተለይተው እንዳለቁም ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፋና የሚከተለውን ዘግቧል 

ዶክተር መረራ ጉዲና እና ዶክተር ወልደሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ በፌደራል ደረጃ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 115 ሰዎች ክስ ተቋረጠ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በደረሰው መረጃ መሰረት ከደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን 361 እና ከኮንሶ ወረዳ 52 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋርጣል።

ሌሎች ክልሎችም ክሳቸው የሚቋረጥላቸው ተጠርጣሪዎች እና በይቅርታ የሚለቀቁ ግለሰቦችን በመለየት ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።” መባሉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ዛሬ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በሰጠው መግለጫ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር መቋረጡን አስታውቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ዛሬና ነገ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ እንደሚለቀቁ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *