የኢፊዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመጭዉ ረቡዕ ጥር 9/2010 ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት  በግብፅ ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ እየተገለፀ ነዉ። በዚህ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት ኢትዮጵያ እየገነባችዉ ያለዉ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀርብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በተለይም  ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ዉድቅ የተደረገዉ። 

 የዓለም ባንክ  ያደራድረን ጥያቄ በግብፅ በኩል በድጋሚ ሊቀርብ ይችላል ተብሏል። 
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች በጎርጎሮሳዊዉ ሚያዚያ 30፤ 2011 ዓ.ም ወዲህ የአባይ ወንዝ ዋነኛ ተጠቃሚ ከሆነችዉ ግብፅ ጋር ያለዉ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ ቆይቷል።ይህንን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መካከል በአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ዙሪያ በርካታ ዉይይቶች የተካሄዱ ቢሆንም  አሁንም ድረስ ጉዳዩ ሁነኛ መቋጫ አላገኘም። እናም ዉይይቱ አሁንም ድረስ ቀጥሏል። የሰሞኑ የጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጉብኝትም ሌሎች በርካታ ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ይነሱበታል ቢባልም፤ የህዳሴዉ ግድብ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ዋነኛ አጀንዳ መሆኑ እንደማይቀር ከወዲሁ እየተነገረ ነዉ።  በቅርቡ ግብፅ በተናጠል ያነሳችዉንና  በኢትዮጵያ በኩል ተቃዉሞ የገጠመዉን  የዓለም ባንክ ያደራድረን ጥያቄም በዚሁ ጉብኝት በድጋሚ ሊቀርብ እንደሚችልም እየተገለፀ ነዉ። በኢትዮጵያ የዉጭ ግንኙነት ስትራቴጅካዊ ጥናት ኢንስቲቲዩት ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይነቴ እንደሚሉት ጥያቄዉ በድጋሚ ቢቀርብም ግብፅ ኢትዮጵያና ሱዳን ከተስማሙበት የቴክኒክ ኮሚቴ ስምምነት ዉጭ  በመሆኑ  በኢትዮጵያ በኩል የተለየ አቋም አይጠበቅም።Äthiopien Grand Renaissance Staudamm al-Sisi al-Bashir Desalegn (Ashraf Shazly/AFP/Getty Images)
የዓባይ ዉኃን የጋራ አጠቃቀም በተመለከተ ቀደም ሲል በተፋሰሱ ሀገራት በኋላም በግብጽ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሦስትዮሽ ዉይይት እየተካሄደ የነበረ ቢሆንም  ግብፅ ከዚህ ዉይይት አፈንግጣ  በሦስተኛ ወገን እንደራደር ሀሳብ ይዛ ብቅ ማለቷ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌላኛዋ የወንዙ ተጠቃሚ ሀገር ሱዳንንም ከግብጽ ጋር እያወዛገበ ነዉ። ከዚሁ ጋር በተገናኘም ሱዳን ከሰሞኑ ግብፅ የሚገኙ አምባሳደሯን ወደ ሀገሯ ጠርታ እንደነበር ሲገለፅ ቆይቷል። የግብጽ አቋም በተለያዩ ጊዜ ሲለዋወጥ መቆየቱን የሚናገሩት ተመራማሪዉ ነገር ግን ፤የግብፅ አቋም የቱንም ያህል ተለዋዋጭ ቢሆንም የሦስቱን ሀገሮች ጥቅም ያማከለ ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል የተያዘዉ አቋም ሊቀየር አይችልም። ተመራማሪዉ በትናንትናዉ እለት ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር  የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶከተር ወርቅነህ ገበየ ያደረጉት ዉይይትም ይህንን የሚያመላክት ይመስላል ነዉ የሚሉት።Ägypten Kairo Nil-Fluss (Imago/Zumapress)
እንደ አቶ አበበ ገለፃ የሦስተኛ ወገን ድርድርን በተመለከተ በኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን  የዉኃ ሀብት ሚንስትሮች የሚመራዉ  የቴክኒክ ኮሚቴ በጉዳዩ  ላይ የጋራ ስምምነት ከደረሰ  ብቻ የሚፈጸም ነዉ።  ግብፅ በተናጠል ያቀረበችዉ የዓለም ባንክ  ያደራድረን ጥያቄ ይህንን የስምምነት ሥነ -ስርዓት የጣሰ በመሆኑ መቼም  ቢሆን በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም ብለዋል።ያም ሆኖ ግን ጥያቄዉ ለግብፅ የሀገር ዉስጥ የፖለቲካ ፍጆታ መቀጠሉ የማይቀር ነዉ ይላሉ።
በግብፅ በኩል የዓባይን ጉዳይ ከተፋሰሱ ሀገራት አልፎ ወደ ዓለም ዓቀፉ መድረክ  ለማምጣት የሚደረገዉ ሙከራ  ከዉስጣዊ ፖለቲካ ፍጆታነቱ ባሻገር በመካከለኛዉ ምስራቅና በአካባቢዉ ያለዉን ፖለቲካዊ ሁኔታም ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አቶ አበበ ጨምረዉ ገልፀዋል። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሃይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *