አክሎግ ቢራራ (ዶር)እንደሌሎቹ ወገኖቸና ተቆርቋሪ የሆኑ የመላው ዓለም ተመልካቾችና ታዛቢዎች “የምሰማው የጠቅላይ ሚንስተር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መግለጫ እውነት ነው ወይንስ ቅዠት” ብየ ተከራከርኩ። ይኼ ኢህአዴግን የመጠራጠር ሁኔታ  የሚያሳየው የኢህአዴግ አገዛዝ በምንም ሊታመን የማይችል፤ የፖለቲካ ንግድን ከሌሎች የተማረ፤ በሕዝብ ስም የሚያታልል፤ የሚያባብል፤ የሚያዘናጋና ሕዝብን “ትጥቅ አስፈች” የሆነ፤ እያጠቃ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ላይ ነኝ የሚል ወዘተ መሆኑን ነው።

(አክሎግ ቢራራ (ዶር)

እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን መሰረታዊ ችግሮች በራሳችን ውይይትና ድርድር፤ በቀና፤ በመልካምና ማንንም በማያገል አስተሳሰብና የፖለቲካ ሂደት ለመፍታት እንችላለን። ይህ የቅንነት ብሄራዊ አመለካከትና ሂደት የሚጠይቃቸው አስኳል ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ከድርጅት፤ ከብሄርና ከኃይማኖት፤ ከግልና ከቡድን የኢኮኖሚ ጥቅሞች በላይ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማስቀደምን ይጠይቃሉ። ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም መቆም የተቀደሰ ተልእኮና ተግባር ነው። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፤ ህወሓት በበላይነት ሲያስተዳድረው የቆየው የኢህአዴግ አገዛዝ የሕዝብ የፖለቲካ ስልጣንንና የኢኮኖሚ ጥቅሞች አግባብነትን ወደ ጎን አስቀምጦ ራሱን አገልግሎበታል።

ይህ ለሕዝብ ታዛዢና አገልጋይ ለመሆን ያልቻለና ያልፈቀደ አገዛዝ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ የበላይነቱን ይዞ ለመግዛት እንደማይችል የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ እምቢተኛነቱን መስዋእት እየከፈለ አስመክሯል። ታላቁን የተሃድሶን ግድብ በሕዝብ ባጀት የሚሰራው አገዛዝ ሕዝብን ለማነጋገር፤ የሕዝብን ድምጽ ለመስማት፤ የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት ምንም ፈቃደኛነት አያሳይም፤ ብቃትም የለውም። ሕዝብን፤ በተለይ ወጣቱን ትውልድ ለማነጋገር የማይችልበት ዋና ምክንያት ይህን ትውልድ ስለሚፈራው ብቻ ነው። ሌላ ምክንያት ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። ሕዝብን የሚፈራ አገዛዝ ደሞ፤ ከሕዝብ የሚፈራው ነገር አለ ማለት ነው። ስለሆነም፤ የአገዛዝ ለውጥ አስፈላጊ ነው።

ባለፉት ሳምንታት በብዙ ድህረ ገጾች የተሰራጨውና በአገር ቤት ጋዜጣ ታትሞ ሕዝብ የሚነጋገርበት “የኢህአዴግ ኑዛዜ ወይንስ የለውጥ አቅጣጫ? —አማራጩ ሕዝብን የስልጣኑ ባለቤት ማድረግ ብቻ ነው” የሚለው ትንተና ይዘት፤ መግለጫው የየትኛው ኢህአዴግ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬ ነበር። በአጭሩ እንዲህ ይላል።

“በህወሓት የበላይነት የሚገዛው የኢህአዴግ የስራ አስኪያጅና አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ የሕዝብን ባጀት ተጠቅሞ፤ ለሶስት ሳምንታት ያህል የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች ካላዘነ በኋላ መግለጫ አውጥቶ ሕዝብን እያነጋገረ ነው። ይህ የምስጢር ጉባኤ የተካሄደው የህወሓት የስራ አስፈጻሚ ቡድን ለሳምንታት በመቀሌ የዝግ ችሎት አድርጎ ራሱን በአዲስ መልክ አወቅሬአለሁ ካለ በኋላ ነው። ቡድኑ አጠናክሮ የወጣው አሁንም ራሱን የስልጣን መአከል አድርጎ እንዴት የበላይ ሆኘ እገዛለሁ በሚል የህወሓቶችን ቀጣይነት የሚያሳይ ስልት መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የኢህአዴግ አመራር ክብደት የሰጠው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስልጣን ሳይሆን ለአዲሱ የህወሓት አመራር የበላይነት መሆኑ በግልጽ ይታያል።

ኢህአዴግ፤ ሕዝብን ላስቆጡትና ለአስነሱት፤ ለእልቂቶች፤ ለፖለቲካ እስረኞች፤ ለፍልሰቶች፤ ለስደት፤ ለአገሪቱ በውጭ ኃይሎች መከበብ፤ ለማህበረሰባዊና ለሰብአዊ መብቶች መታፈን፤ ለኑሮ ውድነት፤ ለፍጽሙ ድህነት፤ ለስራ አጥነት፤  ለሕዝብ የፖለቲካ ስልጣን አለመኖር ወዘተ ምንም አይነት አጥጋቢ መልስ አልሰጠም። The root causes that prompted popular resistance for the past two years remain intact. ችግሮቹ ካልተፈቱ በስተቀር ሕዝባዊው አመጽ በኃይል ቢታፈንም አያቆምም።”

አሁንም የትኛው ኢህአዴግ ነው አዲስ መግለጫ የሰጠው፤ እንዴትስ ይታመናል? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ነው። ቁም ነገሩ፤ የሕዝቡ ተከታታይ ግፊትና ጩኸት፤ ለትግል ያለውን ቁርጠኝነት ሂደት ኢህአዴግን ያሳሰበው መሆኑ ነው። በሌላ አነጋገር የተለያዩ ኢህአዴጎች ቢኖሩም ባይኖሩም መግለጫዎቹ የሚያሳዩት የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠንካራነት፤ መተባበርና ለፍትህ-ርትእ፤ ለነጻነትና ለእውነተኛ ዲሞክራሳዊ አማራጭ መቆም የሚያሳይ ሂደት መሆኑንና፤ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ ተግዳሮቶችና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ሲነጻጸር አገሪቱን ለመምራት ጥራትና ብቃት እንደሌለው ነው።

የዚህ ትንተና መሰረታዊ ሃሳብ ኢህአዴግ ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመደለል፤ ለመሸንገል፤ ለማታለልና ከፋፍሎ ለመግዛት አይችሉም የሚል ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ትግልና በራሱ መስዋእትነት ያሳየውና የሚያሳየው የማያባራ ትግል ራሱ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት እንዲሆን ነው። ልጆቹ ተገድለው፤ ቆስለው፤ ተሰቃይተው፤ ተሰደው፤ መብታቸው ታፍኖ ወዘተ ወዘተ ብሄራዊ መግባባት ሊኖር አይችልም። ያለው ብቸኛ አማራጭ፤ የሕዝቡን እሮሮ፤ የሕዝቡን ጩኸት፤ የሕዝቡን ፍላጎትና ምኞች አያዳመጡና እያከበሩ መሰረታዊ ችግሮችን ስር ነቀል በሆነ መልካቸው ለመፍታት መድፈር ነው። የመንግሥት ስርዓት ለውጥ ያስፈልጋል ብየ የምከራከረው ለዚህ ነው።

የሕዝብን ባጀት በመጠቀም ስብሰባዎችን በማካሄድ፤ ህወሓቶች ለሳምንታት ተሰበሰቡ፤ ራሳቸውን ገመገሙ፤ ተተኪዎቻቸውን መሪዎች መረጡ፤ ከእኛ ውጭ ማንም ሊገዛ አይችልም ብለው ወሰኑ፤ እኔ ካልገዛሁ ኢትዮጱያ ትፈርሳለች የሚል መልእክት በሚቆጣጠሯቸው የመገናኛ ብዙሃን አስተላለፉ። በአጭሩ ራሳቸውን “አጠናክረው” ወጡ። ኢህአዴግ ጎራውን እንዲለይ ለማስገደድ ሞከሩ። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ለሶስት ሳምንታት ያህል የዝግ ችሎት አደረገ፤ ራሱን ገመገመ፤ ተቸ፤ መግለጫ አወጣ። ሕዝብን ይቅርታ ጠየቀ። መግለጫ ካወጣ በኋላ ብዙ ቀናት ሳያልፉ በ January 3, 2018 መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያጓጓ፤ ምንም ያልተጠበቀ፤ ፋይዳ ቢስ፤ መግለጫ ይፋ አደረገ።

እኔም እንደሌሎቹ ወገኖቸና ተቆርቋሪ የሆኑ የመላው ዓለም ተመልካቾችና ታዛቢዎች “የምሰማው የጠቅላይ ሚንስተር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መግለጫ እውነት ነው ወይንስ ቅዠት” ብየ ተከራከርኩ። ይኼ ኢህአዴግን የመጠራጠር ሁኔታ  የሚያሳየው የኢህአዴግ አገዛዝ በምንም ሊታመን የማይችል፤ የፖለቲካ ንግድን ከሌሎች የተማረ፤ በሕዝብ ስም የሚያታልል፤ የሚያባብል፤ የሚያዘናጋና ሕዝብን “ትጥቅ አስፈች” የሆነ፤ እያጠቃ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ላይ ነኝ የሚል ወዘተ መሆኑን ነው። ኢህአዴግ ከሃያ ሰባት ዓመታት የአፈና አገዛዝ በኋላ አሁንም ስልጣኑን ለሌሎች ለማስተላለፍ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል።

ብሄራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግ እኔም ሆንኩ ሌሎች ለማሳመን ስንሞክር ቆይተናል። የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ስንጠይቅ ኢህአዴግ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ “በኢትዮጵያ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም” ሲሉ ቆይተው ነበር።  ታዲያ የሚለቀቁት እስረኞች ከሰማይ ወረዱ?

Associated Press (AP), BBC,, VOA, DW, the Washington Post እና ሌሎች በመግለጫው ላይ ተረባርበውበታል። እኔን ያስገረመኝ፤ የህወሓቶች አፈቀላጢንና አሞጋሽ የሆነው ሪፖርተር የተባለው ጋዜጣ ለመግለጫው የሰጠው ሽፋን ነው። January 3, 2018 “በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱ ተገለጸ” በሚል ርእስ የጻፈውን ዜና ሲሰማ ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። “ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱና ‹‹ማዕከላዊ›› በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማዕከል እንደሚዘጋ ዛሬ አስታወቁ፡፡ አራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጀቶች ሊቃነ መናብርት በጋራ በሰጡት መግለጫ እዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት  አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫው እንዳስታወቁት፣ በዓቃቤ ሕግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር ላይ የሚገኙና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞችም ሆኑ የተለያዩ ግለሰቦች ይፈታሉ፡፡ ይህም የሚደረገው የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ መሆኑን ገልጸው፣ ታሳሪዎቹ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ እንደሚለቀቁ አረጋግጠዋል፡፡”

በሃሰት የተከሰሰ ግለሰብ ይቅርታ የሚጠየቅባት አገር ብቸኛዋ ኢትዮጵያ መሆኗ ነው። ይኼን መልካም ነው እንበል። ሆኖም፤ በብዙ ሽህ የሚገመቱት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ከጅምሩ የታሰሩት በጥፋታቸው አይደለም። የሚታሰሩት ለሰብአዊ መብቶች መከበር፤ ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ለብሄራዊ ክብርና ለዲሞክራሲ ድምጽ ስላሰሙ ነው። ከሳሹ ገዢው ቡድን፤ መርማሪው ገዢው ቡድን፤ ገራፊው ገዢው ቡድን፤ አቃቤ ሕጉና ፈራጁ ገዢው ቡድን በሆነባት ኢትዮጵያ ሃቁን ወይንም እውነት የሚባለውን እሴት ከውሸቱና ከፈጠራው መረጃ ለመለየት አይቻልም።

ስለሆነም፤ እውነቱን ከውሸቱ ለመለየት ያልቻለ ቡድን መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት አይችልም። ሁሉን የፖለቲካ እስረኞች ይፍታ ወይንም አይፍታ የሚጠቁም መረጃ የለንም። ጠቅላይ ሚንስትሩ እስረኞች ይፈታሉ ብሎ ከተናገረ ሁለት ሳምንት ሊሆን ነው። እስካሁን የተፈታ ግለሰብ የለም። እንዲያውም፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ “የተናገርኩትን በትክክል አልተረዳችሁትም” የሚል ድምጽ አሰምቷል። አስቦ ለመናገር አለመቻሉ ያስገርማል።

በዚህ ትንተና የማቀርባቸው መልስ ማግኘት ያለባቸው አስኳል ጉዳዮች አሉ።

ኢህአዴግ “በእስር ቤት ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን” ለመፍታት ሲወስን፤

አንድ፤ እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች ማንን ያካትታሉ? በሚታወቁና በማይታወቁ እስር ቤቶች የታሰሩት በብዙ ሽህ የሚገመቱት እስረኞች ይፈታሉ ወይንስ የሚፈቱት የዓለምን ሕብረተሰብ ለማባበል ሲባል ዓለም የሚያውቃቸውን፤ Amnesty International, Human Rights Watch, the Committee to Protect Journalists (CPJ), the Department of State, U.S. A. እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የመዘገቧቸውን ብቻ ነው?

ሁለት፤ ኢህአዴግን ሕዝብ ስለማያምነው፤ እነዚህ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መቸ ይፈታሉ? የሁሉ እስረኞች ስም ዝርዝር መቸ ይፋ ይሆናል?

ሶስት፤ “ማዕከላዊ የሚባለው የምርመራ ተቋም በደርግ ዘመን በእስር ቤትነት እስረኞችን ለማሰቃየት ይውል እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ተዘግቶ ወደ ሙዚየምነት ይቀየራል ብለዋል።” ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት እስካሁን ድረስ ያሰራቸው በብዙ ሽህ የሚገመቱ የፖለቲካ እስረኞች ከማንም መንግሥት ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። ደርግ የራሱ ተቃዋሚ የሆኑትን ግለሰቦች የሚያስርበትን ማእከላዊና ሌሎች እንደ ማእከላዊ የሆኑ እስር ቤቶች እየተጠቀመ በአስር እጅ ወይንም ከዚያ በላይ በሚገመት መጠን አገሪቱን “የእስር ቤት” ያደረገው ኢህአዴግ ነው። ደርግ እስር ቤቱን የተጠቀመበት “እስረኞችን ለማሰቃየት” ነበር ከተባለ ኢህአዴግ ከደርግ የባሰ፤ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ እስረኞችን ይዞ ለማሰቃየት ያስገገደደው ምክንያት ምንድን ነው? ኢህአዴግ ራሱን ባያታልል መልካም ነበር፤ ግን ራሱን ለመተቸት አይችልም።

አራት፤ በብዙ ሽህዎች የሚገመቱት፤ የሚፈቱ ፖለቲከኞች፤ የህሊና ግለሰቦች፤ ጋዜጠኞች፤ የፖለቲካና የመንፈስ መሪዎች ማንነት፤ የስም ዝርዝርና የት እስር ቤት እንደታሰሩ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጽ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?

አምስት፤ ግለሰቦችን ለማሰር ከአንድ ሰዓት በታች የማይወስድበት ህወሓት/ኢህአዴግ፤ እስረኞችን ለመፍታት ወይንም ላለመፍታት ወራቶች የሚወስድበት ምክንያት ምንድን ነው?

ስድስት፤ ለመሆኑ አራቱ የኢህአዴግ የጎሳ ስብስቦች ሊቃነመናብርት በጉዳዩ ላይ በአንድ ድምጽ ይናገራሉ? ለዚህ ይሆን በአንድ ጉዳይ ላይ የተምታቱና እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ መግለጫዎች የሚሰሙት?

ሰባት፤ የሕዝቡን እምቢተኛነት አስመልክቶ ቢቢሲ በ 17 October 2016፡ “Seven things banned under Ethiopia’s state of emergency” በሚል እርእስ ያቀረባቸው ለሕዝብ ጸር የሆኑትስ ህጎችና መመሪያወች ይነሳሉ ወይንስ እንዳሉ ይቀጥላሉ?

እነዚህም በከፊል የሚከተሉት ናቸው፤

 • የማህበረሰባዊ መገናኛዎች፤ የሞባየልና ኢንተርኔት ክትትል፤ የጋዤጦች ስርጭቶች ነጻነት
 • የውጭ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት፤ ለምሳሌ፤ Esat and OMN, Amhara Voice radio et
 • ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅዳቸው ሰላማዊ ሰልፎ
 • በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመንቀሳቀስ፤ የመሰብሰብና አቤቱታን የማቅረብ መብት
 • ማንኛውንም የእጅ ሆነ የሰንደቅ አላማ የአቋም መግለጫ መብት
 • የውጭ ታዛቢዎችና የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር የጠየቁት እልቂትን የሚመረምር ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በነጻነት የመንቀሳቀ መብት።

ብሄራዊ መግባባትንና የፖለቲካውን ምህዳር ሰፊና ስኬታማ ለማድረግ መፈጸም የሚገባቸው ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል፤

 1. የህወሓት/ኢህአዴግ መሳሪያ የሆነው የጸረ-ሽብርተኛ አዋጅ ሳይውል ሳያድር መነሳት አለበት፤
 2. በተመሳሳይ ህወሓት/ኢህአዴግ የማህበረሰብ ድርጅቶችን ለማፈንና ለማጥፋት ያወጀው፤ የዲሞክራሲ ማነቆ የሆነው Charities and Societies Proclamation መነሳት አለበት፤
 3. ዲሞክራሲ ያለ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ሚና ሊመሰረት አይኖርም፤
 4. ህወሓት/ኢህአዴግ የመገናኛ ብዙሃንን ለመቆጣጠር በሚያመች ሁኔታ ያወጀውና ተግባራዊ ያደረገው መነሳት አለበት፤
 5. የፌደራል ፖሊስ፤ ልዩ ኃይል፤ የደህንነትና የመከላከያ ኃይሎች በሙሉ ከህወሓት/ከኢህአዴግ ቁጥጥር ውጭ መሆን አለባቸው። የደህንነትና የመከላከያ ተቋሞች አገርን ከውጭ ጠላቶችና ወረራ ለመከላከል እንጅ ሕዝብን ለማፈንና ለመቅጣት መሳሪያ መሆን የለባቸውም።
 6. የምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤቶች ከህወሓት/ኢህአዴግ ቁጥጥር ነጻ መሆን አለባቸው።

እነዚህ ሃሳቦች ለፍትህ-ርትእ፤ ለዲሞክራሳዊ ስርዓት የማይቀር አማራጭ፤ ለሰላምና ለእርጋታ፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ናቸው። ኢህአዴግ የአገሪቱንና የሕዝቡን ችግሮች ለመወጣት የሚችለው ሕዝቡን በማባበልና በመደለል አይደለም፤ የሕዝቡን ጥያቄዎች በማያሻማ ደረጃ በመመለስና ሕዝቡ የፖለቲካው ስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን በማመቻቸት ብቻ ነው። በገቢር መታየት ያለበት መስፈርት ሕዝቡ የፖለቲካው ስልጣን ባለቤት እንዲሆን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማመቻቸት ነው። ይኼም ብሄራዊ አንድነትን የሚያንጸባርቅ የሽግግር መንግሥት አስፈላጊ መሆኑን መቀበልን ይጠይቃል።

ምእራፍ አንድ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች መፍታት መሆኑን እቀበላለሁ፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ድምጼን አሰማለሁ። በተከታታይ መሰራት ያለባቸውን ለመጠቆም ሞክሬአለሁ። የውጭ መንግሥታትና ታዋቂ ተቋማት የሚሉት አግባብ ስላለው በከፊል እጠቅሳቸዋለሁ።

AP January 3, 2018 “In a surprise move, Ethiopia’s leader on Wednesday announced plans to drop charges against political prisoners and close a notorious prison camp in what he called an effort to “widen the democratic space for all.” This is the first time the government has acknowledged holding political prisoners.” ይህ ምእራፍ እውነት መሆኑ የሚታየው ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ ነው።

የአሜሪካና የአውሮፓ ምክር ቤቶች በተደጋጋሚ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፤ የፖለቲካው ምህዳር እንዲስፋፋ፤ የመገናኛ ብዙሃን የገዢው ፓርቲ መሳሪያ መሆናቸው እንዲያቆም ወዘተ ጠይቀዋል። ይኼን በሚመለከት ለአለፉት ብዙ አመታት ብዙ መረጃዎችና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ጠቁሜአለሁ።

ኢህአዴግ ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ሃላፊው Chairman Royce እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህና ሰብአዊ መብቶች መከበር አስፈላጊነትና ወሳኝነት ጠንካራ አቋም ያላቸው Congressman Coffman በተከታታይ መግለጫዎች አቅርበዋል። January 3, 2018 ሮይስ እንዲህ ብለዋል።

“Ethiopia has finally acknowledged that it holds political prisoners. Now, the government should quickly follow through on its commitments to release them and close a prison camp notorious for torture. If Ethiopia is to remain a strong U.S. partner and a source of stability in a dangerous region, the government must respect the rights of the Ethiopian people.”

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው የምመኘው የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ የኢህአዴግ አገዛዝ የወሰደውንና የሚወስደውን ጭካኔ ማውገዙንና ግድያውና አፈናው እንዲቆም መግለጹን ነው። In July, 2017 “The Foreign Affairs Committee unanimously passed a resolution in July condemning excessive use of force by Ethiopian security services that has resulted in the deaths of protesters, and the wrongful detainment of journalists, students, activists and political leaders.”

በተመሳሳይ፤ ኮፍማን እንዲህ ብለዋል። “While Ethiopia’s government” has announced that it will release all political prisoners and is “closing down one of its torture camps, is a step in the right direction— all human rights violations by the Ethiopian government must come to an end.  The Ethiopian government has engaged in terrorist acts against its own people and such behavior is unacceptable and I will continue, as I have, to make sure that the United States holds the Ethiopian government responsible for all of its promises in respecting the human rights of all of the Ethiopian people.”

እኒህ የኢትዮጵያ ወዳጅ ያሳሰቡት ትክክል ነው። ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች የህወሓት/ኢህአዴግ የአፈና መሳሪያዎች መወገድ አለባቸው።

ለማጠቃለል፤

አንድ፤ ኢህአዴግ በገባው ቃል መሰረት በማንኛውም የአገሪቱ እስር ቤቶች የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው፤

ሁለት፤ ሁሉንም ባለድርሻዎች የሚያሳትፍ የፖለቲካ ሽግግር ውይይትና ድርድር በአስቸኳ መጀመር አለበት፤

ሶስት፤ ይህም ማለት ኢህአዴግ አገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚለውን አሳሳች አመለካከት ወደጎን ትቶ ከሁሉም ጋር ለብሄራዊ ውይይትና ድርድር ፈቃደኛ መሆኑን ለኢትዮጱያ ሕዝብ ማስታወቅ አለበት፤

አራት፤ ፍትሃዊነትንና ነጻነትን የሚያመለክት ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው ከላይ የተጠቀሱት አፋኝ ህጎች፤ መመሪያዎችና ተቋሞች ሲለወጡ ነው፤ አምስት፤ የሽብርተኛውና የማህበረሰባዊ ተቋሞች ህጎች በአስቸኳይ መነሳት አለባቸው፤

ስድት፤ የመናገር፤ የመጻፍ፤ የመሰብሰብና የመንቀሳቀስ መብቶች በማያሻማ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ቃል ኪዳን መግባት አለበት፤

ሰባት፤ የምርጫ ቦርድ፤ ፍርድ ቤቶች፤ የፌደራል ፖሊስ፤ ብሄራዊ ደህነት፤ መከላከያና ሌሎች ቁልፍ ተቋሞች ከህወሓት/ኢህአዴግ ነጻ መሆን አለባቸው፤

ስምንት፤ ደህንነት፤ የፌደራል ፖሊስ፤ ልዩ ኃይሎችና መከላከያ ከአሁን በኋላ በሕዝብ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡና የህወሓት/ኢህአዴግ መሳሪያ እንዳይሆኑ የኢህአዴግ አመራር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ኪዳን መግባት አለበት፤

ዘጠኝ፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንደ ተራ ነገር የተወሰደው የህወሓት የበላይነት–ለምሳሌ፤ በፌደራል ባጀት ስርጭት፤ በውጭ ግንኙነት፤ በኢንቬስትመንት፤ በተፈጥሮ ኃብት ይዘት የሚደረገው ግፍ ማቆም አለበት።

አስር፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃብት እንጂ የህወሓት መነገጃ መሆን የለባቸውም፤

አስራ አንድ፤ በኢህአዴግ ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች፤ በተለይ ብአዴንና ኦህዴድ “የሚወክሉትን ሕዝብ” ተአመኔታና ተቀባይነት  ለማሳየትና ለማስመስከር የሚችሉት፤ ያለምንም ማመንታት፤ ከሕዝቡ ጎን ሲቆሙ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄራዊ አንድነት ይለምልም!

January 15, 2018

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *