• ምስክሮቹ በክስተቱ ላይ እንጅ በማንም ላይ ልንመሰክር አልመጠንም ብለዋል

በማህሌት ፋንታሁን

ታህሳስ 1 2008 ዓም በአንዋር መስኪድ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ሰበብ የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተበት አህመድ ሙስጠፋ ላይ ምስክሮች ተሰሙ። ዛሬ ጥር 10/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፅደታ ምድብ 4ኛ ችሎት የነበረው ቀጠሮ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በመሆኑም ቀርበው ከነበሩት አራት ምሰክሮች ሶስቱ መስክረዋል። የቀረው አንዱ ምስክር ከመሰከሩት ሶስቱ ምስክሮች ጋር ተመሳሳይ ምስክርነት ስለሚሰጥ አቃቤ ህግ አልፈልገውም በማለቱ እንዲመለስ ተደርጓል።

ምስክርነታቸውን የሰጡት ሶስቱ ግለሰቦች ታህሳስ 1 2008 አርብ ቀን አንዋር መስጊድ ሰላት ካደረጉ በኋላ የፍንዳታ ድምፅ እንደሰሙ፣ የተጎዱ ሰዎች እንደነበሩ እና ድርጊቱን የፈፀመውን አካል ማንነት ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል። ሁለቱ ምስክሮች በወቅቱ በተፈጠረው ፍንዳታ በፍንጥርጣሪው ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ከተወሰዱ በኋላ እራሳቸውን ሊያቁ እንደቻሉ እና ህክምና ሲከታተሉ እንደነበር መስክረዋል።

የመጀመሪያው ምስክር ማን ላይ ለመመስከር እንደመጡ ሲጠየቁ “ማንም ላይ ልመሰክር አልመጣሁም” ብለዋል። ታህሳስ 1 2008 ዓም አንዋር መስጊድ በተፈጠረ ፍንዳታ ልጃቸው ላይ የደረሰውን አደጋ ለመመስከር መምጣታቸውን ተናግረዋል። ሁለተኛው የ1ኛ ምስክር ልጅ ሲሆን 17 ዓመቱ እንደሆነ ገልፆ፣ ታህሳስ 1 2008 በነበረው ፍንዳታ ኩላሊቱን እና እግሩን ፍንጣሪ መትቶት ሆስፒታል ከገባ በኋላ ነፍሱን ማወቁን፣ ለሳምንት ያክል ለመተንፈስ ይቸገር እንደነበረ ፣ ፍንዳታ እንደነበር ከሌካ ሰው እንደሰማ እና ያፈነዳውን ሰው ማንነት ግን እንደማያቅ ተናግሯል። የ1ኛ እና 2ኛ ምስክር ምስክርነት ከተሰማ በኋላ የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ “ተከሳሹ ላይ የሰጡት ምስክርነት ስለሌለ መስቀለኛ ጥያቄ የለንም” በማለት መስቀለኛ ጥያቄ ሳያቀርብ ቀርቷል።

ሶስተኛው ምስክር በዕለቱ በደረሰው ፍንዳታ ፍንጥርጣሪው ባደረሰበት አደጋ ደረቱን እና ጭንቅላቱን ተጎድቶ እንደነበረ፣ ህክምና ሲከታተል መቆየቱን እና ደም ወደ ውስጥ በመፍሰሱ ምክንያት አንድ አይኑ ማየት አለመቻሉን መስክሯል። የፍንዳታው መንስኤ በተመለከተ፣ ፍንዳታው የተከሰተው ትራንስፎርመር ተቃጥሎ ነው እንዲሁም ቦንብ ፈንድቶ ነው የሚሉም እንዳሉ ስለ ፍንዳታው እርግጠኛ ያልሆነ ምስክርነት ሰጥቷል። ፍንዳታውን የፈፀመው ማን እንደሆነ እንደማያውቅ ተናግሯል። በሌላ በኩል ተከላካይ ጠበቃው ምስክሩ ሃኪም ቤት ሄዶ በነበረበት ወቅት የደረሰበት አደጋ መንስኤው ምን መሆኑን የተገለፀለት ነገር ካለ ጠይቆት፤ ሃኪሙ ጉዳቱ የተከሰተበት በቦንብ ፍንጣሪ መሆኑን እንደገለፀለት መስክሯል።

አቃቤ ህግ ቀሪ 9 ምስክሮች ቢኖሩትም “ተጨማሪ ነገር ስለማያስረዱልኝ በተሰሙት ምስክሮች ብይን ይሰራልኝ” ብሎ፤ ብይኑን ለመስራት ለየካቲት 8 ቀጠሮ ተሰጥቷል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *