ክቡር ፕረዚደንት እንኳን ወደ ኣዲሱ 2018 ዓም ኣሸጋገረን። ባለፈው ሳምንት የኣልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ፡ በታንኮችና በኣውሮፕላኖች የታጀበ የግብጽና የኢማራት ሰራዊት በሳዋ መስፈራቸውን ኣስተጋብቶ ነበር። ይህ ኣሉባልታ  ካለ ምንም ማጣራት እንዳለ በሌሎች የዓለም መገናኛ ብዙሃን ተደጋግሟል። የዚህ ኣሉባልታ መንስኤና ዓላማ ምንድንነው? የተለመደው የኣልጀዚራ የማጠልሸት ዘመቻ ኣካል ነው ወይንስ ሌሎች ቅርንጫፎች ኣሉት?

ይህን ወሬ ከኣቡዳቢ ስመለስ ኣውሮፕላን  ላይ ነው መጀመርያ የሰማሁት። ኣሁን ወደ ዋና ይዘቱ ሳትገባ ምንድንነው ካልከኝ የ 2018 ጆክ ወይም ቀልድ ነው የምለው። በዋናው ይዘት ላይ ብዙ ኣርእስቶችን በማዛመድ ልነናገርበት እንችላለን። ይህ ማለት ደግሞ ምንድንነው ዓላማው? የግዜው ኣጋጣሚስ እንዴት ሊገለጽ ይችላል? ከሌሎች በዚህ በቀጠናችን ወይንም ኣጎራባቾቻችን ከምንለው ኣካባቢ ጋር ምን ትስስር ኣለው? ብዙ ጥያቄዎችን በማንሳት መናገር ይቻላል። መጀመርያ ነገር ኣዲስ ኣርእስት ኣይደለም። ከግዜ ጋር ኣስቀድመው ኣሰራጭተዋቸው ለነበሩት ሃሰቶች ዘንቢል ወይ መቋጠርያ ነው።

በዚሁ ማለቂያ በሌለው ዘንቢል የማይሰብሰብ ነገር የለም። ኣብነት በማንሳት ብዙ መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም እንኳን እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሃሰቶች መዘዛቸውንና እድገታቸውን ስትመለከት ለኔ የጾረና ሁኔታ ነው ትዝ የሚለኝ። በጾሮና ከጥቃቱ በፊት የወያኔ ካድሬዎች ወታደሮቻቸውን “በግንባሩ ውስጥ ግብጻውያን ወታደሮች ኣሉ” ብለው ነግረዋቸው ነበር። ይህ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎችና በተለይዩ መንገዶች ይሰራጭ ነበር። እንዲህ ዓይነት ተረት-ተረት መናገር ግን ምን ቁምነገር ኣለው? በዚህ ኣካባቢ ስለ ግብጽ ያለው ኣመለካከት ኣሉታዊ ነው።  በተለይ ወያኔ ይህን ለምን ሊጠቀምበት ይችላል የሚለው ሌላ ትልቅ ኣርእስት ነው። ነገ-ርግን ወደ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ተመልሰህ ከተመለከትክ፡  እንዲህ ዓይነት የፈጠራ  ወሬ ሰምቶና ኣምኖ ወደ ጦርነቱ በመግባት ገብቶ፡ የረገፈው ሰው፡ የተከፈለው ዋጋና ኪሳራ፡ በጣም ኣሳዛኝ ነው።

እንዲህ ዓይነቱን ሃሰት ምን ልታመሃኝበት ትችላለህ? ዓላማ ካለው እንዲህና እንዲህ ብለህ መናገር ትችል ይሆናል።  “ግብጽ በኤርትራ ኣለች፡” “ግብጽ በኤርትራ ወታደሮች ኣሏት”፡ “የጦር መሳርያ ኣለ”፡ “ሚሳይሎች ኣሉ”፡ የማይነገር ኣሉባልታ የለም። ይህ ትናንት ኣልጀዚራ ያመጣው፡ ምናልባት ከዘንቢሉ ውስጥ እፍኝ ብቻ ነው ብለህ መናገር ይቻላል። ከዚያ በኋላ ተጋግሎ የነበረው በተለይ ሱዳንን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት “በደቡብ ባረንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የግብጽ ወታደሮች ኣሉ” እየተባለ ሲካሄድ የነበረውም ሌላ ኣሉባልታ ነው። ይህ ኣሉባልታ  ከታመኑ ምንጮች ያገኘነው እየተባለ ነበር የሚሰራጨው።  የሱዳንና የወያኔ የስለላና የጸጥታ ኣካላት በከሰላ ተሰበሰበው፡ “ግብጽ የት ነው ያለችው? ምን እያደረገች ነው?” ብለው ገመገሙ ተባለ። ይህ ግን መጨረሻ ላይ ምንድን ነው ካልከኝ መፈብረክ ነው፡ ማለት የሃሰት ማምረቻ ፋብሪካ ነው።

ከዚህ በኋላ “ይህን ያክል ወታደሮች ኣሉ” በማለት ትዋሻለህ። ያሰራጩት ሃሰት እንዲታመን ለማድረግ ደግሞ የቦታና የሰዎችን ስም ትጠቅሳለህ ማለት ነው። ለኣብነት እነዚህ በደቡብ ባረንቱ ኣሉ የተባሉትን የሚያስተባብር ተኽለ ማንጁስ የሚባል ጀነራል ኣለ ተብሎ ሪፖርቱ ላይ ተጻፈ። ለኣንድ የማያውቅ ወይንም የዋህ ሰው እንደዚህ ዓይነት ሃሰት መናገር ምንድንነው ፋይዳው? የሚያስገርመው ግን ለተራ ወይንም ለማያውቅ ሰው ብቻ ሳይሆን ውሳኔ ለሚወስዱ ተቋማት ወይንም ባለስልጣናት እንዲህ ዓይነት የሃሰት መረጃ፡ ወዴት ያመራቸዋል? ይህ የሳዋ ጉዳይ የቀለለው ነው። በኣገላለጽ ይህን ሳዝጅ ወይንም ደንቆሮ ጆክ ልትለው ትችላለህ። ምክንያቱም በፍጥነት የሚጋለጥ ወይንም እርቃኑን የሚቀር ሃሰት ከሆነ ቀላል ነው ማለት ነው። ስለዚህ  ሃሰት ማሰራጨት ቢፈለግም እንኳን ግዜ የሚወስድ ሰዉን ትንሽ የሚያዘገየው፡ ምናልባትም እውነት ይሆን እንዴ በማለት የሚያጠራጥረውና፡  ትንሽ ሚዛን ኣለው የሚያስብል መሆን ኣለበት። ኣሁን እየቀለለና እየቀለለ መምጣቱ፡ የፈብራኪዎቹ ቅሌትን ነው የሚያሳየው ።

እንዲህ ዓይነት ሃሰት ሲፈበርኩ ትንሽ ፍንጭ ማለት ሰሚውን ለማሳሳት ወይንም ለማደናገር የሚችሉበትን መንገድ ለምን ኣያፈላልጉም? ይህን ሃሰት ያስተጋባው ኣልጀዚራ ብዙ ሰው ነው የሚያውቀው። ኣልጀዚራ ግን የመተግበርያ መሳርያ ነው። ማን ይደጉመዋል፡ ማን ያዘዋል፡ ማን ያሰራዋል ብዙ ኣርእስቶች ኣሉ። ከዚያ በኋላ የሚመጣው ግን እንዲህ ዓይነቱን ወሬ እንዴት ነው ያሰራጨው? ምክንያቱስ? የኣልጀዚራ ማእከል በኣዲስኣበባ ሲመሰረት፡ የኣልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያን ፕሮግራሞች ሳይሆን በኤርትራ ላይ ኣነጣጥረው ለሚካሄዱ የተለያዩ ሌሎች ኣጀንዳዎች ማስተባበርያ መድረክ ተብሎ ነው ጽህፈትቤት የተመሰረተው። ልክ እንደ ኣንድ ትልቅ ፍጻሜ ደግሞ “ኣልጀዚራ በኣዲስኣበባ ተመሰረተ ተብሎ” ብዙ ዳንኪራዎች ተረገጡለት። በተለያዩ ጽሁፎችና በጋዜጦችም ጭምር ተነገረለት። ማን ነው የሚያካሂደው? እንዴት ኣድርገውስ ነው የሚያካሂዱት ብዙ ወሬዎች ነበረው። ለማንኛውም በኤርትራ ላይ ያነጣጠረን የተለያየ ጠብኣጫሪነት የሚያስተባብርና ለዚሁ የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ የሚሰጥ ተቋም ተመሰረተ።

ኣሁን ይህ የሳዋው ኣሉባልታ እዚያ ነው የተፈበረከው።  ኣቀራረቡንና ቃላቱን እንዲሁም የሃሰቱን ይዘት  እንዲታመን ታደገዋለህ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ግን ማርስ ላይ ነው የሚኖሩት እንዴ? የሚያስብል ነው። የሚገርመው ከዚያ በኋላ ሃሰቱ ረዥም ሳይጓዝ ተጋለጠ። ሲ. ቲ. ጂ. ኤን. የሚባል ኣንድ የቻይና የቴሌቪዥን ጣቢያ ኣለ። ይህ የሃሰት ወሬ ሲስተጋባ ደግሞ በካይሮ የሚገኘው የሲ. ቲ. ጂ. ኤን. ኮርስፐንደንት ኣልጀዚራ ስላሰራጨው ወሬ ኣዋቂ ነው ተብሎ ንግግር እንዲያደርግ ተጋበዘ። በንግግሩ ላይ ደግሞ፡ የሳዋ ደሴት ኢማራት እንዳሉባት ነው የማውቀው፡ ግብጻውያን እንዳሉባትና እንደሌሉባት ግን ኣረጋግጨ ኣላውቅም ኣላቸው። ኣሁን ሃሰቱን ገምተው። ይህን ሰው ሳዋ የምትባል ደሴት ኣለችን? የትኛው ባህር ላይስ ትገኛለች? ብለህ ብትጠይቀው ምንድን ነው የሚለው? ያውም በኣንድ ትልቅ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው እየተናገረ ያለው። ከዚያ በኋላ ይህን ጉዳይ ያልተናገረበት የለም። የ ኣር. ቲ. ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናገረበት፡ ሌሎች ታላላቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም “ኣልጀዚራ ያሰራጨው” እያሉ ኣመጡት። መለስ ብለህ ስትመለከተው ምናልባት በኋላ ላይ በሌሎች ኣርእስቶች ላይ እንነጋገርበታለን፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከሁሉም በፊት ይህ የወያኔ ቅሌት መገለጫ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወያኔን የሚያሰሩት ወገኖች ቅሌት ነው፡ ፡ ወያኔ ኣሽከር ነው፡ የኣሰሪዎቹ ሎሌ ማለት ነው።

ካልሆነ ወያኔ የራሱ ኣጀንዳ ኣለው፡ የራሱ እቅድ ኣለው ፡ ሊመታው የፈለገው ግብ ኣለው ብለህ መናገር ይህንን ቡድን ኣካብዶ ማየትና የራሱ ያልሆነ ያለ ዓቅሙ ስም መስጠት ነው የሚሆነው።  ይህ ቀደም ሲል በጾሮና ላይ  ሲነገር ከነበረው ጀምሮ፡ ”የለም እምባሶይራ ላይ በእንዲህ ኣልቲትዩድ የሚሰራ የእስራኤል የሳርቬላንስ ጣቢያ ኣለ። በዳህላክ እስራኤልና ኢራን ጣቢያዎች ኣሏቸው” ሲባል የነበረው የባዮቹን ቅሌት ያጋለጠ ነው። ምናልባት ሃሰት ቀኑ ሲደርስ ይቀልላል ይበንናል ለማለት ትችላለህ። ይህ የመጨረሻው ማለት የሳዋው ኣሉባልታ ከሁሉም የቀለለ ነው። እዚያ ያለው ሰውስ ምን ይላል? ትንሽ እውቀት ሊኖርህ ይገባል። በዋናነትሳ እነዚያ የግብጽ ወታደሮች ከዚያ በኋላ ምንድን ነው የሚያደርጉት? ሰውን መጠየቅ ኣትችልም እንዴ? ? ከሳዋ ተነስተው የት ነው የሚሄዱት? ለማን ነው ስጋት የሚሆኑት? ግብጻውያን በርግጥ በሱዳን ላይ የነጣጠረ እቅድ ካላቸው ማለት ሴራም ይሁን ሌላ ሃሳብ ያላቸው ከሆነ በሰሜን በኩል ግብጽን ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር ኣይሰፋም እንዴ ኣይቀርብም እንዴ? ለምን ከሳዋ? ወይንም ለምን ከኤርትራ? ለምን ከባረንቱ? ለምን ከሃይኮታ?

ለምን በጸሮና በኩል ? ማንን ለማስፈራራት ነው ? ወያኔን ? የእዉነቱን ለመናገር ወሬው የገለባን ያክል የቀለለ ነው ። ስለዚህ ለምን ዓላማ ነው ብለህ መናገር መቻል አለብህ ። ዓላማው በዋነኝነት አቅጣጫ ለማስቀየር የሚደረግ የእዉር ድንብር ፍርጠጣ ነው ። ይህ ደግሞ የፍጻሜዎችን አቅጣጫ ለማስቀየር ነው ። ወያኔና የወያኔ ጌቶች ያሉበት ሁኔታ ፡ ምናልባት ወደ ኋላ ላይ ተመልሰን እንናገርበታለን ፡ በጭንቀት ላይ ጭንቀት እየተፈጠረ በሄደ መጠን ፡ ከዚህ ጭንቀት እንዴት ታመልጣለህ ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው ። ወደ ኋላ ላይ የወያኔና የኢትዮጵያን ወቅታዊ  ሁኔታዎች በተመለከተ እንናገርበታለን ።  ዓላማው ግን የእዉር ድንብር ወደ ፊት ፍርጠጣ በዋነኝነት ደግሞ አቅጣጫ ለማስቀየር የሚደረግ ነው ። እንዲህ ዓይነቱን ነገር ደግሞ ከወያኔና ከአሰሪዎቹ ባሻገር ሌሎች ብዙዎች ይፈልጉታል ። ወያኔን የሚያሰሩት ብዙዎች ናቸው ። ባለፉት ሁለት ዓመታት በወያኔና ባሰሪዎቹ  የታየው የሞራል ዉድቀት ይበልጥ ገሃድ እየሆነ ፡ ችግሩ እየተወሳሰበ መምጣቱ ኣስጨንቋቸዋል። ፡ በአንድ በኩል ፡ ባለፉት 25 ዓመታት በኤርትራ ላይ የተካሄደው ጠብ አጫሪነት አልሰራም ። የዚህ ህዝብና የዚህ አገር ሃይል ማለትም የኤርትራ ፡ ሁሉንም ጠብ አጫሪነቶች መክቶ ተሻግሮታል ። ስለዚህ ሁለት የተቃረኑ ሁኔታዎች ነው የታዩት ።

ይህ ደግሞ በዚህ አካባቢ አጀንዳቸውን ያስፈጽምላቸው ዘንድ ተንከባክበው ሲያሰሩት የነበረው የወያኔ ሃይል እየተዳከመ ፡ እየተመናመነ ፡ እየተበታተነ ፡ መጥፎ ሊባል የሚችል ሁኔታ ላይ ሲወድቅ ፡ በተቃራኒው በጠብ አጫሪነታቸው ፡ ሊያዳክሙትና ሊያኮላሹት ያሰቡት ሃይል ግን እንደፍላጎታቸው አልተዳከመም ። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ነው የፈጠረው ። ስለዚህ በዜና ፡ በስነ አእምሮ ፡ በተለያየ መንገድ የተደረገው ቀጣይ የሆነ ጠብ አጫሪነት ስላልሰራ ፡ አሁን መጨረሻ ላይ ደግሞ እንደ ምክንያት ወይም እንደ ሰበብ የግብጽ ስም ተነሳ ። በነበረው ኣሉባልታ ላይ የግብጹን ሁኔታ ስታክልበት ደግሞ ርእሰ ጉዳዩን ይበልጥ ታገዝፈዋለህ ተብሎ የታሰበ ነው። “ግብጽ ጾሮና ላይ ሰፍራለች፥ ግብጽ ባረንቱ ላይ ሰፍራለች  ፡ ግብጽ ሃይኮታ ላይ ሰፍራለች ፡ ግብጽ ሳዋ ላይ ሰፍራለች እያልክ ደግሞ ትዋሻለህ ማለት ነው ። ዋነኛ መልእክቱ ያነጣጠረው ወደ ሱዳን ነው ።

ምክንያቱም የግብጽ ኤርትራ ላይ መገኘት ወይም መስፈር ለሱዳን ስጋትን የሚፈጥር ነው ። ስለዚህ ሱዳን ዉስጥ በሚገኙ ልዩ ጥቅመኞችና በወያኔ መካከል ( ከርእሰ ጉዳዩ ለመዉጣት አልፈልግም እንጂ ) በርካታ የሚያነጋግሩ ነጥቦች አሉ ። ምናልባት ቀኑ ሲደርስ ይጠቀስ ይሆናል ። ይህ ህብረት ( እኔ እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ህብረት፡  ያልተቀደሰ ኪዳን ነው የምለው) ልዩ ጥቅመኞችና የሱዳንን ህዝብ ሊያሳስቱና አስፈላጊ ወዳልሆነ ችግር ዉስጥ ሊዘፍቁ የሚፈልጉ ፡ በወያኔ በኩል ደግሞ ፡ ሱዳንን ወደነሱ ጎራ አስገብቶ አሰሪዎቻቸው ሲያደርጉት እንደቆዩት ማለት ነው – ኪዳኑን – ጸረ -ኤርትራ ፡ ጸረ ግብጽ ፡ ጸረ የአካባቢው የተለያዩ ሃይሎች እንዲሆን አድርገህ ለማነሳሳት ትችላለህ  ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ወሬ ሲነሳ ፡ ወዴት አቅጣጫ ተጓዘ ወይንም ደግሞ እድገቱ ወዴት ነው ካልን ፡ ዓላማው ሱዳንን ከኤርትራ ጋር ቀጥታዊ ወደ ሆነ ግጭት ለማስገባት ነው ። ወደ እንዲህ ዓይነቱ ግጭት ለማስገባት ደግሞ  ፡ ሱዳን ይህንን ዉሸት አምኖ ፡ ወይም እንዲያምነው ፈልጎ ፡ የድንበር መዝጋት ፡ በድንበሩ አካባቢ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ ኣለበት ማለት ነው ። በመጨረሻ ያለኝ መረጃ እንደሚያመለከተው – ይህ ወሬ ሲቀጣጠል ፡ ባለፈው ሳምንት ወያኔ በሱዳን መሬት  በከሰላ ደቡብ (ዉላያት ፧?) ሰራዊት ለማስፈር ፡ ወያኔና ሱዳን ስምምነት አድርገዋል።  የሚሰፍረው ሰራዊት መጠን ምን ያህል ነው ፥ ምናልባት ዝርዝሩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ይኖራል ።

ለሚሰፍረው ሰራዊት ቀለብ የሚሸፍነው ወይም የሚከፍለው ደግሞ የሱዳን መንግስት ነው ተብሏል ።  ይህ ትንታኔ ሳይሆን የተጨበጠ መረጃ ነው ። እንዴት ነው የሚተገበረው ? መጨረሻ ላይስ ምንድን ነው ያሚያደርገው ? የግብጽ ሰራዊት ከሳዋ ተነስቶ ሱዳንን ሲያጠቃ ፡ ከአካባቢው – የወያኔ ሰራዊት ይሰፍርበታል ከተባለበት አካባቢ ማለት ነው – ከዚያ ተነስቶ እንዲዋጋ ማለት ነው ። እንዲህ ዓይነቱ ተረት ተረት ፡ እንዲህ አይነቱ የወሬ ፍብረካ ዓላማው አቅጣጫ ለማስቀየር ፡ ግጭት ለመፍጠር ፡ ጠብ አጫሪነትን ለመፍጠር ነው ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የተፈጠረዉን ግጭት ራስህ መልሰህ ታስዳድርዋለህ ማለት ነው ። ዘ ኤንድ ጃስቲፋይስ ዘ ሚንስ ። ይህ ማለት የፈለግከው ግጭት ሲፈጠር መጨረሻ ላይ ራስህ ታስተዳድረዋለህ ማለት ነው ። ይህ ደግሞ ወደፊት የሚደረግ የእዉር የድንብር ፍርጠጣና ፡ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በመሸፋፈን ‘ ርእሰ ጉዳዩን ከአቅጣጫው ያወጠዋል ማለት ነው ። በርካታ ምሳሌዎችን ጠቅሰን መናገር እንችላለን ። ይህ ደግሞ ለኔ ሁልግዜም አእምሮ ዉስጥ ብልጭ የሚለውን የኮሊን ፓወልን ዉሸት የሚያስታውስ ነው ።

ኮሊን ፓወል በጸጥታው ምክር ቤት ፡ እነሆ ኢራቅ ውስጥ እልቂት አስከታዩ የጦር መሳርያ ኣለ ፡ እነሆ እንዲህ ዓይነት ነገር እያለ ፡ በኢራቅ ላይ ሊፈጽሙት ያሰቡትን የማጥቃት እርምጃ ምክንያታዊ ለማድረግ ፡ ዉሸት ፈበረከ ። የጸጥታው ምክር ቤት ላይ ደረትህን ነፍተህ ሰዉ አመነም አላመነም ያንዲት ታላቅ አገር የመከላከያ ሚኒስትር ሊያዉም ደግሞ ምን የመሰለ ዝና ያለው ሰው ፡ እንዲህ አይነቱን ዉሸት ፈብርኮ በኢራቅ ላይ ወረራ ተፈጸመ ። ኢራቅ በአሁኑ ወቅት የት ነው ያለችው ? በኢራቅ ላይ ለተፈጸመው ዉድመት መንስኤው እንዲህ አይነቱ ዉሸት እንደሆነ ይህ የኢራቁ ኣንድ ተጠቃሽ ምስሌ ነው ። በሌሎች የተለያዩ ቦታዎችም ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል ። ይህንን እንደ ኣብነት ወስደን ከተመለከትነው ፡ ይህ አሁን እይተካሄደ ያለው የወደፊት የእዉር ድንብር ፍርጠጣ ሌላ ቴንሽን ወይም ዉጥረት መፍጠር ኣለብን ተብሎ፡  ለማቀጣጠልና ለመፈርጠጥ እንዲቻል የቤት ዉስጥ ወይም  የአገር ዉስጥ ችግርን መፍታት ባልተቻለ ግዜ ፡ ትኩረትን ወደ ዉጭ ለማዞር የታቀደ ነው ። የኤርትራና የግብጽ ግንኙነት ምንድን ነው ? ኤርትራና ግብጽ እንዴት አድርገው ተስማምተው እንዲህ አይነት ነገር ለማድረግ ይወስናሉ ? እነኚያ ተንታኞች ፡ አዋቂዎች ሊቃዉንቶች የሚባሉት ፡ ኤርትራና ግብጽ አጀንዳ አላቸው እያሉ የሚያነሱት ብዙ ብዙ ነጥብ አለ ።

እንደ ወያኔ አባባል ፡ የሚሊኒየም ግድብንና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን እየጠቀስክ ፡ ግብጽ ኢትዮጵያን ማዳከም ስለምትፈልግ ፡ ኤርትራን እንደ የስትራቴጅው  የጦር ቀስት ( spear head) አድርገህ ታቀርባታለህ ።  ኤርትራ መጠቀሚያ እንደሆነች በማስመሰል ፥ የሌሎችን አጀንዳ ነው የምታስፈጽመው እያልክ ዉሸት ታሰራጫለህ ። በዚህ አካባቢ በሱዳን ፥ በኢትዮጵያ ፡ በሌሎችም የተለያዩ ቦታዎች እንዲህ አይነቱ ዉሸት ቅሌቱ ብቻ ሳይሆን ፡ የስርጭቱ ሁኔታም አስገራሚ ነው ። ምክንያቱም ፡ አሁን ካለው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የሚዲያ ስፋትና ተደራራቢነት ፡ ዉሸት አሰራጭተህ ለማሳመን ይቻላል የሚል ፍልስፍና አለ ። በተለያዩ የመረጃ ማእከሎች  ፡ ዜና በተደጋጋሚ ስታሰራጭ ፡ ወሳኝ የሚባሉ ሃላፊዎች ወይም ደግሞ ተቋማት ፡ ሰበብ ለመፍጠር እንደ ምክንያት ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል ። አምነዉም ሆነ  ፡ ምናልባት ሊሆን ይችላል በማለትም ይሁን  ዉሳኔ በመዉሰድ ገደል ዉስጥ ይገባሉ ።

ከዚያ በኋላ ትርምሱን ታስተዳድርዋለህ ማለት ነው ። ይህ ሁሉ የተናገርንበት ምክንያት ምንድነው ? እንዴት አድርገህ ነው የምታሰራጨው ? እንዴትስ አድርገህ ነው የምታሳምነው ? መጨረሻ ላይ ልትመታው የፈለከው ግብስ ? ያው ይህ የጠቀስኩት ነው ። ሰራዊት የት ነው የምታሰማራው ? ከየት የመጣ ሰራዊት ነው ? ምንድን ነው የሚያደርገው ?  የወያኔ ሰራዊት ከሰላ ዉስጥ ወይም ደግሞ ደቡብ ከሰላ ዉስጥ ተሰማርቶ ወይንም  መሽጎ ምንድን ነው የሚያደርገው ? ‘መረዊ’ ዉስጥ በሚገኘው የአየር ሃይል ሰፈር የወያኔ አየር ሃይል እንቅስቃሴ ታየ ፡ ፡ እንዲህ ሆነ እንዲያ ተደረገ እየተባለ ይናፈሳል። . . . የወያኔ ጨዋታ አብቅቶለታል ። ግዜ ሊሸምት ይችል ይሆናል ። ቀጣይ የሆነው እንክብካቤም ይቀጥል ይሆናል ።

የተለያዩ ሁኔታዎችም እንደዚሁ ሊባል ይቻላል ። ነገር ግን ፡ 25 ዓመታት ይበቃል ። ግዜው ደርሷል ። የአለም ሁኔታ እየተቀያየረ ነው ። በዚህ ቀጠና ፡ በዚህ አዋሳኝ አካባቢ ያለው ሁኔታ እየተቀያየረ ነው ። የእውር ድንብር ፍርጠጣ ፡ ወይም ደግሞ በፕሮግራም የሚደረግ ፍርጠጣ ፡ ርእሰ ጉዳዮችን ለማዳፈን መሞከርና  አቅጣጫቸውን ለማስቀየር መኳተን አይቻልም ። እንዲህ አይነቱን ርካሽ ጨዋታና እንደገለባ የቀለለ ዉሸት እያስተጋባህ መቀጠል አይቻልም ። የአልጀዚራ ጡሩምባ መንፋትም ቢሆን የሚያመጣው ለዉጥ የለም ። ለኢትዮጵያ ፡ ለሱዳንና ለግብጽ ህዝቦች መተላለፍ ያለበት መልእክትም ይበቃል የሚባልበት ግዜ  ነው ።

እንዲህ መሰሉን ዉሽት በየቀኑ እየፈበረክ ፡ የአድማጭን ደሮ ማደንቆርና ፡ የሰዉን አስተሳሰብ ለማስቀየር መሞከር ግዜው አብቅቷል ። እኛ ምን እናደርጋለን ? ምንስ እናስባለን ? ምንስ እንላለን ? አልጀዚራ ወሬዉን ካሰራጨበት ግዜ ጀምረን ኣልተዘናጋንም። ጉዳዩ ቀናት በልቶ ይነፍሳል። እንደ ዱቄት ያልቃል። ግን ምንድን ነው ሁኔታው በመገባ መታወቅ ኣለበት። ያልሰማው መስማት መቻል ኣለበት። ከሁሉም በፊት እንዲህ ዓይነት ደንቆሮ ሃሰት ኣሰራጭተህ፡ ልትመታው የፈለግከው ግብ የሚያስከትለውን መዘዝ ሳትገመግምና ለማን  እንደምታስተላልፈው፡ እንዴት እንደምታስተላልፈው ሳታውቅ መንጎድ? በእውነቱ ይህ የወያኔን ጭንቀትና ቅሌት የሚያረጋግጥ ነው። ምናልበት ሱዳን ውስጥ ይህን ጉዳይ ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ልዩ ጥቅም ፈላጊዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። ይህ ኣሁን መልሶ መላልሶ እንዲህ ቢሆን፡ የለም! ድንበር ተዘጋ፡ ድንበር ተከፈተ፡ ይህን ያክል ላንድክሩዘር ኣለፉ፡ ይህን ያህል ላንድክሩዘር በዚህ ሄዱ፡ እንትን የጫኑ ወዘተ… እንዲህ የመሳሰለ ገጽታ በጋዜጣ ታወጣለህ። ይህ የሱዳንን ህዝብ ጥቅም የሚወክል ኣይደለም።

በማንኛውም መንገድ ከሱዳን ህዝብ ጋር የሚያገናኝ ጉዳይ የለውም። ኣስቀድሜ እንደጠቀስኩት ሁከት በመፍጠር ሁከቱን ለማስተዳደር ያለመ ስለሆነ፡ ንቁበት፡ ዓይናችሁን ክፈቱ፡ ጆሯችሁን ኮርኩሩት፡ በደንብ ኣዳምጡ፡ በቀጠናችን እንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች መምጣት የለባቸውም። እንዲህ ዓይነት ቀልድ ወይንም ፌዝ በማንኛውም ሁኔታ ስር ማንኛውንም ሰው ማሳሳት የለበትም። ኤርትራ ውስጥ ሆነን ምን እናደርጋለን –  ቁጭ ብለን ፊልሙን እንመለከታዋለን ። ስታር ዎርስ በለው ፋንታዚያ – የሆነው ይሁን – ፊልም ነው ። ሰው በእንዲህ ዓይነቱ ዉሸት የተሰላቸ በመሆኑ ፡ ሌላ ስራ ብታፈላልጉ ይሻላል ። ባለፉት 25 ዓመታት ያስከተላችሁትን ኪስራ አቋርጡት ። የእዉነቱን ለመናገር ሱዳን ዉስጥ የሚገኙት ልዩ ጥቅመኞች ደግሞ ፡ ወያኔን ወይም የኢትዮጵያን ህዝብ ወደዉት አይደለም ። ኤርትራና ኢትዮጵያ ከተስማሙ ፡ በዚህ አካባቢ ተኝተን ማደር አንችልም የሚል ስጋት ስላለባቸው ነው ።

ከዚህ በፊት ከነበረው የቀድሞው ስርዓት ጀምሮ የነበረ አስተሳሰብ ነው ። ከ1991 በኋላ ሁኔታዎች ሲቀየሩ ፡ ሁኔታው በአዋሳኙ አካባቢዎች የተሻለ እድል ፈጥሮ ነበር ። ኤርትራና ኢትዮጵያ ተባብረው በዚህ ቀጠና ፡ አመርቂ ፡ አዎንታዊና ገንቢ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ይባል በነበረበት ወቅት የፈጠረው ስጋት ተቀጥያ ነው ፡፡ “እነዚህ የሱዳንን ህዝብ የማይወክሉ ፡        አናሳዎች የምላቸዉና ከወያኔ ጋር ተመሳጥረው የሚሰሩ ጥቅም አሳዳጆች ፡ ‘ በቃችሁ ! በኤርትራና በሱዳን ህዝቦች መካከል እንዲህ መሰሉን ትርምስና የድንበር ግጭት ለመፍጠር የሚደረገው ሙከራ ትርጉም ስለሌለው ፡ እጃችሁን ሰብስቡ ። እኛም ቢሆን ወደ እንዲህ አይነቱ አዙሪት ዉስጥ ለመግባት ዝግጁ አይደለንም ።” የሚለዉ መልእክት ነው መተላለፍ ያለበት ። ይህ ነው በተደጋጋሚ መነሳት አለበት የምንለው ርእሰ ጉዳይ  ። ከኛ የዉስጥ ጉዳይ ጋር አያይዘን መመልከት እንችላለን ። ከጎረቤቶቻችን ጋር ካለን ግንኙነት ጋርም እንዲሁ አያይዘን እንድንመለከተው እድል ይከፍትልናል ። ከዚህ ሁሉ ቅሌትና ጭንቀት ጋር . . በህዝቦች መካከል ጦርነት ቀስቅሰህና ትርምስን ፈጥረህ ፡ ተመልሰህ ይህንኑ ለማስተዳደር የሚደረግ ሙከራ .. . ምን ማለት ነው? ይበቃናል ። የእዉነቱን ለመናገር ፡ በእንዲህ አይነት መልኩ 25 ዓመታት ተከስሯል  ።  ስለዚህ ከኣጠቃላይ ኪሳራዉና ክህዝቦች ኪሳራ ብዙ ነገሮችን ስለተማርን ፡ በኔ በኩል ” ከዚህ በኋላ ይበቃችኋል ” ማለት ነው የምፈልገው  ።

እሺ ወደ ቀጣዩ ጥያቄ እንሸጋገር ክቡር ፕረዘደንት ፡ – በእርግጥ ጥያቄው አሁን ሲገልጹት ከነበሩት ነገር ጋር የተያያዘ ነው ፡ ባለፈው ወር ቱርክ በሶማልያ ካላት ወታደራዊ ህልዉና በተጨማሪ በሱዳንም የጦር ሰፈር የማቋቋም እቅድ እንዳላት በዜና አዉታሮች ተገልጾ ነበር ። የአፍሪካ ቀንድ በሃያላን አገሮችና በመካከለኛው ምስራቅ  አገሮች ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ጫና ስር ያለና ከርሱ ጋ የተሳሰረ ነው የሚሉ ትንታኔዎችም ስላሉ በኛ በኩል ይህንን ሁኔታ እንዴት እንመለከተዋለን ? የዚህ አካባቢን ዳይናሚካዊ ግንኙነት  ከዚህ በፊትም በከፊል ገልጸዉት የነበረ ቢሆንም  – በጉዳዩ ላይ የኤርትራ ህዝብ አቋም ምን ይመስላል ?

ሁል ግዜም ቢሆን እንዲህ ዓይነቶችን ጉዳዮች ፡ ከአጠቃላይ ይዘቱ ወጣ አድርገህ መመልከት አለብህ ። ማለትም አጠቃላይ ይዘቱ  ጋር ደምረህ መመልከት አለብህ ። ቀዝቃዛው ጦርነት ሲጠናቀቅ ባለፉት 25 ዓመታት ብቸኛ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ይፈጠራል ሲባል ፡ በቀጠናችን የታዩ ለውጦች አሉ ።  ካሳዛኞቹ ለውጦች ዉስጥ አንዱ የሶማሊያ ሁኔታ ነው ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጠቀስ እንደነበረው ፡ የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ራሱን የቻለ ደንብና መመሪያዎች አሉት ። በምን ዓይነት ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ነው ብለህ ከጠየቅክ በአንድ አዋሳኝ አካባቢ የሆነ ክፍተት ሲፈጠር ፡ ያለመረጋጋቱ መንስኤ የፈጠረው ክፍተት ነው ። የነዚህ አገሮች ወይም የየአገራቱ መንግስታት ከነባራዊው መስመራቸው ሲወጡ ክፍተት ይፈጠራል ። ይህ ክፍትተ ደግሞ ላለመረጋጋቱ መንስኤ ይሆናል ። በ1991 ወይም ደግሞ በ80ዎቹ መጨረሻ ላይ ቀዝቃዛው ጦርነት ሲጠናቀቅ ፡ ከአፍጋኒስታን እስከ ሶቭየት ህብረት መበታተን ድረስ –  በዚህ ቀጠናችን ወይም ደግሞ አዋሳኛችን በምንለው አካባቢ ምን ተፈጠረ ? የአፍጋኒስታኑን ልናስታዉሰው እንችላለን ።

ኣፍጋኒስታን ከኛ በጣም የራቀና፥ ኣዋሳኞቻችን ከምንላቸው ኣገሮች ውጭ ቢሆንም እንኳን ፡ እስካሁን ድረስ ክፍተት ኣለ። በኣፍጋኒስታን ያለውን ሁኔታ የማያውቀው ሰው የለም። ችግሩ በምን ምክንያት ተፈጠረ” ለምንስ እስካሁን ድረስ  ቀጠለ ካልን ፡ በኣካባቢው ያለው ጫና ሊታየን ይችላል። የኢራቅ ችግርም ትልቅ ክፍተተ ነው። ስለ ዒራቅ ብዙ ሊነገር ወይም ሊተነተን ይችላል። ይህ ትናንት  የተፈጠረው የኣይሲስ ሁኔታን ጨምረህ የተለያዩ የኣሸባሪዎች ክስተቶች ጋር ተደምሮ በኣካባቢው ያለው ውጥረት መያዣ መጨበጫ የለውም።  ስምንት ዓመት የፈጀው የኢራንና የዒራቅ ጦርነት፡ ሳዳም ሁሴን ኩዌትን ለመውረር ያሳየው ኣጉራ ዘለልነትና መዘዙ ቀደም ብዩ የጠቀስኩት እነ ኮሊን ፓወል  በዒራቅ የጀመሩት ወረራና በኣገሪቱ የደረሰው ውድመት ብቻ ሳይሆን በዒራቅ የተፈጠረው  ክፍተትም  ቀላል ኣይደለም። የሶሪያንም ሁኔታ እያየነው ነው። በሊባኖስ ያለው ክፍተትም የተለየ ኣይደለም። በመጨረሻ ሁሉንም ሁኔታዎች ጠቅለል ባለ ሁኔታ ማየት ይቻላል። ይህ በቀጠናውም  ሆነ በኣዋሳኙ ኣገሮች ሰላም እንዳይሰፍን ምን ጫና ፈጥሯል። ኣንድ በኣንድ ደማምረህ ለማየት ይቻላል።

በሊቢያ  የተፈጠረው ሁኔታ ትናንት የተደረገ ነው ብለን ለመናገር እንችላለን። ኣስቀድሞ ግን የሶማሊያ ህልውና ያከተመበት ሁኔታ ኣለ። ቀደም ሲል ከቀረበው ጥያቄ ጋር የሚያያዝ ሃሰትን ፈብርከህ ውሳኔ የመስጠት ሁኔታ ታይቷል። በ2009 ዓ/ም በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የማዕቀብ ውሳኔ ሲሰጥ ቀደም ሲል ሲነገር የነበረው “ኤርትራ ሁለት ሺ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ልካለች፡” “ኤርትራ እንዲህ ኣድርጋለች፡” እየተባለ ስለ ሶማሊያ በክሊንተንና በቡሽ ኣስተዳደር ባለስልጣኖች ሲነገርና ሲፈበረክ የነበረው ውሸት  ትዝታው ከኣምሯችን የሚጠፋ ኣይደለም። ሶማሊያ የኣፍሪካው ቀንድ ኣገር ናት።

በጣም እስትራቴጅካዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ ኣስፈላጊነት  ያላት ኣገር ናት። ህዝቧ የሚያኮራና በዚህ ቀጠና ከፍተኛና ገንቢ ኣስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ህዝብ ነው።  ሆኖም ግን ሶማሊያ ባለፈው ሩብ ዘመን ህልውና ኣልነበራትም፡ እንደ ኣገርም የለችም። ያ ሁሉ ሰፊ መሬት የኣልሸባብም ይሁን የሌሎች ኣሸባሪ ቡድኖች መፈልፈያ ሆነ። የወያኔ ጌቶችና ወያኔ ለ25 ዓመታት “ሶማሊያ መበታተን ኣለባት።”  እያሉ የሰሩበት ሁኔታ ትራጂዲ ነው ሊባል ይችላል። የሶማሊያ ህዝብ በ1960 ዓመተ ምህረት ነጻነቱን ሲጎናጸፍ ሰሜንና ደቡብ  ተብለው ተከፋፍለው  የጣልያንና የእንግሊዝ ሶማሊላንድ ይባሉ እንዳልነበሩ ሁሉ  በገዛ ፍቃዳቸው ተዋህደው ኣንድነት ፈጠሩ። ይህ ሁኔታ በኣፍሪካ ክፍለ ኣህጉር ልዩ ክስተት ነው። ከዚህም ባሻገር ወደ ኦጋዴን ፥ ጅቡቲ፥ ሰሜንና፥ ምስራቅ ኬንያ፡ ለመያዝ ሃሳብ ነበራቸው። ያም ሆኖ ግን የሶማሊያ ኣገራዊነትና ጀግንነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ለቀጠናችን ኣብነት ሆኗል ብለህ መናገር ይቻላል። ኣገሪቱን የመገንባት ጉዞ ሲጀመር የመጀመሪያው ውህደት ሲፈጸም የተወሰደው እርምጃ ጎሰኝነትን ማጥፋት ነበር። ይህም እንደ ኣንድ ትምህርት ሰጪ ተኣምራታዊ እርምጃ ታየ። ሶማሊያ ከኣዋሳኞቻችን ኣገሮች እንደ እንድ  ጠንካራ ኣገር  ነበረች። ይህችን ኣገር ኣዳክመህ ለመበታተን እንዲያመች የጦር ኣበጋዞች ተፈጠሩ። የሶማሊያ ህዝብ ደካማ ጎን ነው የሚባለውን የጎሰኘነትና የጎጠንነት ጉዳይ ተጠቅመው ህብረተሰቡን እርስ በርሱ እንዲፋጠጥ ወይም ቨርቲካል ፖላራይዜሽን ፈጥረህ እርስ በርሱ እንዲዋጋ ለማድረግ ተሰራበት። የጎጠኝነትና የጎሰኝነት ወኪሎች ነን የሚሉ የጦር ኣበጋዞች ከበላይ ሆነው እንዲያስተዳድሩ ሁኔታዎች ተፈጠሩላቸው።  የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲገቡም ኣደረጉ። ከዚያ በኋላ እነዚሁ ሃያልን የሚባሉት ኣድፍራሾች ሶማሊያ ህልውናዋ የሚያከትምበትን ሴራ ሸረቡ። በ2002 ዓ/ም የኣሜሪካ የኣገር ደህንነት መስሪያ ቤት ሰነዶች ወይም ናሽናል ሴኩሪቲ እስትራቴጂ፡  የቀጠናው ሃያላን ወይም መልህቆች መፈጠር እንዳለባቸው ያሳያል ። ይህም  ኢትዮጵያ የኣፍሪካው ቀንድ መልህቅ ወይም ፖሊስ መሆን ኣለባት ፡ ይልና የኣካባቢው ኣውራ ትሆንና ሌሎችን በስሯ ታስተዳድራለች የሚል ነው። ከኣንድ ጎራ ዓለማዊ  ኢኮኖሚያው ስርዓት መፈጠር ጋር ሶማሊያ እንደ ታርጌት ተወሰደች ማለት ነው። ለመልህቅነት የተበረጡት በዋናነት ወያኔ እንዲሁም በዚህ ኣካባቢ ያሉ ደካማ ስርኣቶች ናቸው።  በኬንያና በጅቡቲ ያለውም ሁኔታ ከዚህ ጋር ተያይዞ  ነው የሚታየው። ገዢዎቹ የሶሚሊያ ህልውና ለኣገራዊ ደህንነታችን ስጋት ነው የሚል ፐርሰፕሽን ስለ ፈጠሩ ነው። ከውጭ የመጣውን ኣጀንዳ በዚህ በኣፍሪካው ቀንድ ኣካባቢ በውክልና የሚያስተናግደው ወያኔ ወይም የጌቶቹን ኣጀንዳ በተግባር ላይ የሚያውል ስርዓት መፈጠር ኣለበት ተባለ። ስለ ኤርትራ መናገር እንችላለን፡ ስለራሳችን ከመናገራችን ይልቅ ኣርእስቱ የሶማሊያ ስለሆነ በዚሁ እንቀጥል። ሶማሊያ ባለፉት 25 ዓመታት ሉኣላዊነቷ ተበርዞ  ኣንድነቷና ውህደቷ ኣንዳልነበረ ሆነ። ህዝቧ እርስ በርሱ እንዲናቆር ተደረገ። በኣሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ የተንሰራፋውን ኣልሸባብንና የባህር ላይ ሽፍቶችን መመከት ይችል የነበረው ጠንካራ የመከላከያና የጸጥታ ሃይል እንዲፈርስ ተደረገ። በኣፍሪካው ቀንድ ሃያል የኣየር ሃይል የነበረው የሶማሊያ ነው፡ ኣሁን ግን እንደሌለ ሆኗል። የሶማሊያ ህልውና ኣከተመ። ዚያድ ባሬ በነበሩበት ወይም በመጨረሻ ዘመናቸው ኣልኢቲሃድ ነበረ። ይህ በእስልምና  ስም ይደረግ የነበረው ኣክራሪነት ወይም የኣሸባሪ ስርዓት መገልገያ ነው የነበረው። የሶማሊያ ህልውና እንዲያከትም ምክንያት መፍጠር ተፈለገ። የወያኔ ወረራ ካለ የጸጥታው ምክር ቤት ፍቃድና ውክልና  ከወያኔ ጌቶች በተሰጠ ትእዛዝ የተፈጸመ ነው። ሶስቱም የኣሜሪካ ኣስተዳደሮች ማለትም ከክሊንተን ወደ ቡሽ  ከዚያም እስከ ኦባማ ይህንን ጉዳይ እምነታቸው ኣድርገው ይጓዙ ስለነበርና ጌቶቻቸውም ሆኑ ታዛዞቻቸው ይህንኑ መርሃ ግብር ለመተግበር እቅድ ስለነበራቸው የሶማሊያን እንደ ኣገር ህልውና ማክተም ወይም መደምሰስ ምክንያት ማድረግ ነበረባቸው። ይህን ኣሁን ኣልሸባብ ብለው ዘወትር የሚናገሩበት ድርጅት ማን ነው የሚደግፈው? ማን ነው ገንዘብ የሚሰጠው?  ሎጀስቲክ የሚቸረው ማን ነው? ብለን መጠየቅ እንችላለን። የቱርክ ጣልቃ ገብነት በሶማሊያ ለምን ኣስፈለገ፥ ቱርኮች  ኣሸባሪነትን ቦታው ላይ ሄደን እንዋጋለን  ሊሉ ይችሉ ይሆናል ።  ኣልሸባብና ሌሎች ኣሸባሪ ድርጅቶችን ለመዋጋት ብለህ  ወደ ሶማሊያ መጓዝ? ኣንዲህ ኣይነት ቀልድ ማንን ለማደናገር ይችላል?

ሶማልያ እንደ ኣዲስ መገንባት ወይንም ሪኮንስቲትዩት መሆን ኣለባት። ሶማልያን ለመበታተን፡ ከካርታ ለማጥፋት… የሚደረጉ ኣጀንዳዎች በሙሉ በዚህ ኣካባቢ መዘዝ ኣላቸው። መዘዞቹ ደግሞ የዚህ ኣካባቢ ኣለመረጋጋት ነው የሚሆነው። ሶማልያን በታትነህ በጎሳዎችና በጎጥ ከፋፍለህ የጦር ኣበጋዞች የውጊያ ቦታ ወይንም ጫካ እንድትሆን ማድረግ፡ ተቋማትንና ኢኮኖሚውን ኣውድመህ ኣልሸባብን እዋጋለሁ የምትል ከሆነ፡ ትልቅ ስህተት ነው። ይህን ከሶማልያውያን በላይ  ሊሰራው የሚችል የለም። ሶማልያ ወደ ቀድሞ ነባራዊ  ሁኔታዋ ተመልሳ፡ የራሷን መንግስት ስትመሰርት የራሷን ተቋማት ስትገነባና ስትጠናከር ብቻ ነው ይህን መዋጋት የሚቻለው። በኣፍሪካው ቀንድ ሊመጣ በሚችለው መረጋጋት ኣስተዋጽኦ እንዲኖረው ከተፈለገ፡ ሶማላውያን እሴቶቻቸውን፡ ኣገራቸውንና ሉኣላዊነታቸውን ኣረጋግጠው፡ ተቋማታቸውን ፈጥረው  ይህን ችግር ራሳቸው መቃወም ብቻ ነው ያለባቸው። በሶማልያ ህዝብና መንግስት ምትክ የመጣ ቢመጣ ይህን ተግባራዊ ሊያደርግ ኣይችልም።… ወያኔ እዛ ገብቶ ምን ኣደረገ? ኣልሸባብን ኣጠፋ? ማንን ተዋግቶ ኣጸዳ ? የኣፍሪካ ህብረት ሰራዊት እዚያ ኣለ ሲባል በመስማት ጆሯችን ደነቆረ። ኣልሸባብን ኣጠፉውን? የዚህን ኣካባቢ መረጋጋት የሚያደፈርሰውን ተቃውሞ ደመሰሱትን? እዚያ የማይገቡ ኣገሮች የሉም። ጂቡቲ ገብታለች፡ ኡጋንዳ ገብታለች፡ ኬንያም ገብታለች።

ዋናው ነገር ፡ ጨዋታውን ለማያውቅ የሚያውቅ ይመስለው ይሆናል። በዋናነት ሁኔታው ኣሁን ባለበት መቀጠል መቻል ኣለበት ባዮች ናቸው። ግዜ እየወሰደ ሲሄድ ሆምጥጦ ሊስተካከል ከማይችልበት ደረጃ ይደርስና፡ ከዚያ በኋላ ቀውሱንና፡ ሁከቱን እንደ ፈለግከው ልታስተዳድረው ትችላለህ የሚል ኣካሄድ ነው በተግባር እያየነው ያለነው። “በኣሁኑ ግዜ ሶማልያ ውስጥ ሽብርተኝነት ኣለ፡ ሁከት ኣለ፡ ሶማልያ ያለመረጋጋት ጠንቅ ናት” ብለው የሚናገሩት፡ አለመረጋጋቱን የሚፈጥሩት ወገኖች ናቸው። የመጀመርያ ተጠያቂዎች ደግሞ እነሱው ናቸው።  ሶማላውያን ከፈለጉ በኮንፈደሬሽን ኣልያም በፈደሬሽን መንግስት እንዲኖራቸው ከሻቱ ጉዳዩ  የራሳቸው  የሶማሊያዉያን ጉዳይ ወይም ምርጫ ነው። የሶማልያ ህዝብ መንግስት ቢመሰርት ኖሮ ፡ በባህር ላይ ሽፍትነት ኣልያም በሽብርተኝነት፡  ለዚህ ኣካባቢ ያለመረጋጋት ጠንቅ እየሆኑ ባሉት የተለያዩ ተጽእኖዎች፡ በህንዳዊ ውቅያኖስ፡  በኣፍሪካው ቀንድ፡ በኤደን ባህረ-ሰላጤ፡ በየመን እያየነው ባለነው ሁከት፡ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው በጠቅላላው እየታየ ባለው ሁከት በርግጥ የራሱ የሆነ ኣዎንታዊ ኣስተዋጽኦ ማድረግ በቻለ ነበር ። የሶማልያን ህዝብ በታትነህ ለማዳከም የሚቀርበው ቀላሉ ምክንያት አሁን እየታየ እንዳለው”ሽብርተኝነት” የሚል ነው።

ቱርክ ምን ለማድረግ ነው እዚያ የገባችው ? በእውነቱ ኣንድ የዋህ ወይንም  የማያውቅ ጠያቂ ብዙ መጠየቅ ይችላል። የማያውቅ ሊናገር ይችላል። እዚህ ኣካባቢ ኣውራ ነን ወይንም ኣውራ እንሆናለን ከሚሉት ሃይሎች ኣንዷ ቱርክ ነች። ኣንዴ ኣውሮጳ ህብረት ውስጥ በመግባት ትልቅ ቦታ ለመያዝ ትፈልጋለች፡ የኔቶ ኣባል መሆኗ ደግሞ ትልቅ የመጫወቻ ካርታ ሆኖላታል። ስርዓቱ የሙስሊም ብራዘር-ሁድ ካርታን ይዞ ነው በዚህ ኣካባቢ መንቀሳቀስ የሚፈልገው። ኣስቀድሞ የግብጽ ተጠቅሶ ነበር። “በዚህ ኣካባቢ ግብጽ መኖር የለባትም ፡ ግብጽ እንደ የቀጠናው ሃይል ሆና መኖር የለባትም” ከሚሉት መካከል ኣንዱ የቱርክ ተከታታይ ስርዓት ነው። ይህ የኣሁኑ የሶማልያ ጣልቃገብነት ማማሃኛ የሚባለው፡ በዋናነት ወደ ቀጠናው ደቡባዊ ጫፍ በመሄድ፡ እዚያ ሁኔታውን እንዳለ ማስቀጠል ነው። በዚህም በኣካባቢው ያለህን ተጽእኖ እንዲያሻቅብ ታደርጋለህ ማለት ነው። ከወያኔ ጋር፡ በሱዳን ካለው ስርዓት ጋር ፡ ከተለያዩ ቱርክ ልታደርገው ከምትፈልጋቸው ጋር፡ ምንድን ናቸው ዓላማዎቹ? በሶማልያ ውስጥ ባለው ሽብርተኝነት ላይ ያነጣጠረ ነው ወይንስ የሶማልያን ህዝብ ለመተካት? ምን ለማድረግ ነው እዚያ የገባው? በማን ውክልና? እዚያ የኣፍሪካ ህብረት ወይም  የተባበሩት መንግስታት ህልዉና አለ ብለን ልንናገር እንችላለን ። ይህ ግን የተለየ ኣርእስት ነው። በምን ዓይነት መንገድ ቱርክ በሶማልያ ሰራዊት ልታሰፍር ትችላለች? ሞቃድሾ ውስጥ ካለው መንግስት ጋር ተስማምተን ነው ያደረግነው ማለት ይችሉ ይሆናል ። ነገር ግን ይህም ቢሆን በርካታ አንኳር ጥያቄዎችን የሚያጭር ነው።

ቱርክም ትሁን ሌሎች በዚህ አካባቢና ቀጠና ሃያላን ነን የሚሉ ወምም ደግሞ ለመሆን  የሚፈልጉ አገሮች ባለፉው ሩብ ዘመን የተፈጠረዉን የተወሳሰበ ሁኔታና ትርምስ ይበልጥ ከማሳደግ በስተቀር ፡ ለትርምሱ መፍትሔ ያስገኘ ሃይል የለም ። በሱማሊያም ይሁን በደቡብ ሱዳን ያለው ሁኔታ በኢትዮጵያም ይሁን በየመን እየተመለከትነው ያለነው እዉነታ ፡ በሌሎችም አካባቢዎች እንዲሁ ከአፍጋኒስታን ጀምሮ እስከ ኢራቅ ሶርያና ሊባኖስ ያሉ ሁኔታዎች የትርምሱ እድሜ እንዲራዘም ፡ ይበልጥ እንዲወሳሰብ እንዳደረገው እያየነው ያለነው ነገር ነው ። ስቃዩና ነዉጡ ይበልጥ እንዲባባስ ለማድረግ ፡ ከዉጭ የተጫነዉን የተለያየ አጀንዳ ወይም ደግሞ ከሩቅ የዉጭ አካባቢዎች የሚመጣዉን አጀንዳ  አንድ ፥ ሁለት ፥ ሶስት ብለን አንድባንድ  መዘርዘር እንችላለን ። በነዚህ አገር ዉስጥ ካለው የአገር ዉስጥ  ችግር ሌላ ፡ የቀጠናው ሃያላን ነን በሚሉ ወገኖች ከሚወሳሰቡ ችግሮች መካከል የቱርኩ አንዱ መታያ ወይም ምሳሌ ነው  ። ይህንን ሁኔታ ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ አለማቀፋዊ ነን የሚሉ የዉጭ ሃይሎችም እየተከተሉት ያለዉ አካሄድም እንደዚሁ ፡ የሁሉንም ስሞች መጥቀስ እንችላለን ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያለን ፖሊሲ የማይቀየር ነው ። በኛ ስሜታዊ አስተያየት ሳይሆን የሶማሊያ ህዝብ እፎይ ብሎ እንዲያድር ከተፈለገ ፡ ከረሃብና ከድህነት ማጥ ዉስጥ ወጥቶ ወደ ልማት ጎደና እንዲቀላቀል ከተፈለገ ፡ ከሁሉም በፊት የነጻነቱና የሉዓላዊነቱ ባለቤት መሆን አለበት ። የራሱ የሆነ መንግስት ሊኖረው ይገባል ። በመጨረሻም የራሱ የሆነ የጸጥታ ተቋማትን ሊፈጥር ይገባል ። እሱን ወክለን የሶማሊያን ህዝብ ልናስተዳድረው እንችላለን ፥ የአገሪቱን ጸጥታ ልናስከብር እንችላለን ፡ ልማትን ልናመጣለት እንችላለን” የሚል የፖለቲካ ትንታኔ ኣይሰራም። ፡ ባለፉት 25 ዓመታት ምንድን ነው የተመለከትነው ? በአሁኑ ወቅት የቱርክ ወደዚያ መግባትስ ምን ሊባል ይችላል ? ብለህ ማንኛዉንም የዋህ ሰው ልትጠይቅ ትችላለህ ። እንዲህ መሰሉ ችግር ምናልባት ከሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ጋር ሊነገርበት ይችላል ። አንኳሩ ርእሰ ነገር ፡ ያለፉት 25 ዓመታት የሶማሊያ ሁኔታ ነው ። ሶማሊያ ወዴት እየተጓዘች ነው ?በእዉነቱ  ሶማሊያ የዚህ አዋሳኝ አካባቢ አካል ሆና ገንቢ አስተዋጽኦ እንድታበረክት ከተፈለገ ፡ ነጻነቷ ሊረጋገጥላት ይገባል ። ድጋፍ ማድረግ የፈለገ ሊደግፍ ይችላል ። በዚህ በኩል ምንም ችግር የለም ። ከሁሉም በፊት ግን ፡ አሸባሪነት አለ ፥ አልቃዒዳ አለ ፥ አልሸባብ አለ ፡ ሌሎችም የተለያዩ የባህር ላይ ሽፍቶች አሉ ፥ እነርሱን ለማጥፋት ወዘተ እየተባለ የተለያዩ ምክንያቶችን በማስተጋባት ፡ በአገሪቱ የባሕር ጠረፍ ላይ የሰፈሩ ሃይሎች ማለቂያ የላቸዉም ። የባህር ላይ ሽፍትነትን እንዋጋለን ተብሎ ምክንያት ይፈጠራል ። ይህ አካባቢ የተለያዩ ሃያላን ነን የሚሉ የቀጠናም ሆነ የአለም አገሮች መናኻርያ ነው የሆነው ። ስታምፒት ማለት ነው ። ይህ አካባቢ ሰላም እንዲያገኝ ከተፈለገ ፡ ከሁሉም በፊት  የአካባቢው ህዝቦች ምን ማድረግ አለባቸው  ? ምን ይሻለናል ፥ ምንስ ያዋጣናል ? በራሳችን አቅም ማድረግ የምንችለዉን ፡እናደርጋለን ። ከአቅማችን በላይ ከሆነና ፡ እንዲረዱን ከፈለግን ደግሞ በጋራ ሆነን ፡ ሊረዱን የሚችሉትን ‘ አግዙን” እንላለን ። ከዚህ ዉጭ ግን በተወካዮቻቸው ፡ ወይም በሚያገለግሏቸው ሃይሎች በኩል ይህን አካባቢ ለመቆጣጠር መሞከር ፡ ዉጤቱ ባለፉት 25 ዓመታት በሶማልያ እንዳየነው በእጅጉ አሰቃቂ ሁኔታ ነው የሚያስከትለው። ሌሎች አስቀድመን የተናገርንባቸው  “ግብጽ ሳዋ ላይ ሰፍራለች “ የሚለውና ሌሎች ኣሉባልታዎች ፡ የወያኔን ክስረትና በኢትዮጵያ የመጨረሻ መድረክ ላይ መገኘቱን የሚያመላክት ነው ። የሶማሊያ ህዝብ ከ19ኛዉና 20ኛው ክፍለዘመን ፡ እስካሁኑ የ21ኛው ክፍለዘመን ፡ እንደዚህ አዋሳኝ አካባቢ ወሳኝ ሃይል መጠን ሃላፊነቱን እሱ ራሱ ተሸክሞ ፡ ተዋናይ ሊሆን ይገባል ። ቱርክ እዚያ ሶማልያ ውስጥ መገኘቷ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም ። በቦታው መገኘቷም አስፈላጊነት የለዉም ። የወያኔን አይተነዋል ። በዚያ ቦታ ላይ የሚገኙ የአፍሪካም የአለም  የሚባሉ የተለያዩ ሃይሎች ምን ፈየዱ ? ምንድን ነው የሚፈይዱት ነገር ? ምናልባት ኬንያ ፥ ወያኔና ጅቡቲ፡ ሁኔታው ባለበት መቀጠሉ በርካታ ትርፍ የሚያስገኝላቸው ሊመስላቸው ይችላል ። ግን በማን ዋጋ ?  ወይም በማን ጭዳነት ? በሶማሊያ ህዝብ ዋጋ ይሆን ዘንድ ሊፈቀድ አይገባዉም ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሆነ የጸጥታው ምክርቤት  በእርግጥም ካሉ ፡ እነዚህን ባለፉት 25 ዓመታት በዚህ አካባቢ የታዩ ላለመረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ክፍተቶችንና የሶማሊያን ጉዳይ ሃቀኛ መፍትሔ ሊደረጉለት ይገባል በማለት ሁሉንም በዚህ አካባቢ አደፍራሽ ሚና ያላቸዉን ወገኖች እጃቸዉን እንዲሰበስቡ ሊነግሯቸው ይገባል ፡ እኛም ከዚህ ዉጭ የምናስተላለፈው ሌላ ጥሪ የለንም ።

ክቡር ፕረዚደንት! ቱርክ ሱዳን ውስጥ ወታደራዊ ካምፕ ለማቋቋም እንደምትፈልግ ወይንም እቅድ እንዳላት ነው የሚገለጸውና ይህን እንዴት ይመለከቱታል?

መጀመርያ  ይህ ነገር እውነት ነው ኣይደለም ኣረጋግጠን ነው መናገር ያለብን ። የሱዳን መንግስት እንደ ማንኛውም ኣገር ከቱርክ ጋር የፈለገውን ሉኣላዊ ግኑኝነት ሊመሰርት ይችላል። ወታደራዊ ካምፕ መፍቀድ ከፈለገም ሊፈቅድ ይችላል። መጨረሻ ላይ ግን ለምን በስዋኪን የሚለው ጥያቄ ነው የሚመጣው። የግዜ ተዛማጅነቱ ቀላል ሊመስል ይችል ይሆናል። መጨረሻ ላይ ግን ይህ እርምጃ መስፋፋት ማለት ነው። የኣካባቢ ኣውራ ነን ወይንም ኣውራ እንሆናለን የሚሉ ኣገሮች፡ ኣብዛኛውን ግዜ በራሳቸው የውስጥ ዓቅም ኣይደሉም የሚሄዱት። ኣስቀድሜ እንዳልኩት ካርታዎችን ይዘው፡ ሃያላን ከሚባሉት የዓለም ሃይሎች ጋር ተስማምተው ተጽእኖዎቻቸውን ለማስፋት ከሚሞክሩት ኣገሮች ኣንዷ ቱርክ ናት። ይህ የሶማልያው ሁኔታ  በእጅጉ መጠኑን የጣሰ ነው ልንለው እንችላለን። ምክንያቱም የመልክኣ-ምድራዊውን ርቀት ግምት ውስጥ ካስገባኸው፡ የሶማልያ ጉዳይ ቱርክን በምን ሊመለከታት ወይ ተጽእኖ ሊያደርግባት ይችላል?  ምናልባት በዒራቅና በሶርያ ያለው ሁኔታ በቀጥታ የኩርዲስታን ጉዳይ ስላለ፡ የቱርክን ኣገራዊ ደህንነት ሊነካ ይችላልና እዚህ ልትገባ ትችላለች ሊባል ይቻላል። ሆኖም ግን ቱርክ ሶማልያ ውስጥ ምን የሚያስገባ ምክንያት ኣላት? ሶማልያ ውስጥ ኩርድ ኣሉ እንዴ? ለምንድን ነውስ በሱዳን፡ በሊብያ፡ በኢትዮጵያ ጣልቃ መግባት የምትፈልገው? እኔ እዚያ ውስጥ ለመግባት ኣልፈልግም። ግን ምንድን ነው ዓላማው? ብዙ ፈላስፎች ኣሉ። የቱርክን ግዛት ወይንም የኦቶማንን ኢምፓየር ለማስመለስ ነው የሚሉ። ይህ የህጻናት ትንታኔ ነው የምለው እኔ። ኣሁን ባለንበት የ 21ኛው ክፍለዘመን፡ ለምንድንነው በሶማልያ በሱዳንና በተለያዩ ኣካባቢዎች ወታደራዊ ህልውናዋን ለማስፋፋት የምትፈልገው? በዜና ከተስተጋባው ሌላ በእርግጠኝነት በስዋኪን ወታደራዊ ካምፕ የማቋቋም ዓላማ ስላለ ነውን? የቀይበህር ተነቃፊነትንና ሌሎች የተለያዩ ለውጦችን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲህ ዓይነቱን ህላዌ እንዴት ኣድርገህ ልታያይዘው ትችላለህ? ትንታኔን ወደ ጎን በመተው በጭብጦች ላይ ለመነጋገር እንድትችል፡ የስምምነቱ ይዘት ከግዜ ጋር የምናየው ስለሆነ፡ ኣሁን ባለኝ ግንዛቤ ግን፡ ከህዝባዊ ግኑኝነት ፍጆታ የሚወጣ ነው ኣልልም። ከዚያ ባሻገር የሚሄድ ከሆነ ግን፡ በእውነት ታላልቅ የጥያቄ ምልክቶችን የሚያነሳሳ ነው። ግብጽና ሱዳን ስላልተስማሙ፡ ቱርክ ከሱዳን ጎን ሆና ወደ ግብጽ ምን ዓይነት መልእክት ለማስተላለፍ እየፈለገች ነው? ብዙ የተንታኞች ንግግር ልትሰማ ትችላለህ። ኣንድ ሴናርዮ ወስደህ፡ ቱርክ በስዋኪን ግዙፍ ወታደራዊ ካምፕ ኣቋቋመች በሚባልበት ግዜ፡ የዚያ በስፍራው የሚሰፍረው ሰራዊት ተልእኮ ምንድን ነው? ቀይባህርንና የቀይባህርን መረጋጋት ለማረጋገጥ፡ የኣካባቢው ህዝቦች ተስማምተው በህብረት ለጋራ ደህንነታቸው እንዲተጋገዙ ለማስቻል ኣስተዋጽኦ ታደርጋለችን? ዓላማዎቹ ኣንድ በኣንድ መታወቅ ኣለባቸው። ኣሁን ግዜውን ቀድመህ በጥድፊያ ልትናገርበት የሚቻል ኣይደለም።  ደግሞም ተቀባይነት የለውም። ለህዝባዊ ግኑኝነት ዓላማዎች ተብሎ ቢደረግም፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ህላዌ ማማኻኛ የሚሆን ኣይደለም።

ምንልባት ስለ ቱርክ ብቻ ነው እየተናገርን ያለነው። ከማን ጋር በየትኛው ኣካባቢ ምን እያደረገች ነው ብዙ ጭብጦችና መረጃዎች ኣሉ። ኣዛምደህ ከተመለከተከው፡ በእውነት ይህ የእንደዚህ ዓይነቱ ውሳኔዎች ጠባሳ ለዘለቄታው ምን ሊሆን እንደሚችል ብዙ መናገር ይቻላል። በኛ ተሞክሮ ዓሰብ፡ ምጽዋ፡ ዳህላክና በተለያዩ ኣካባቢዎች እንዲሁም በቀይባህር ያሉት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች፡ ለጋራ ጥቅሞች የጋራ ስጋት ስለሆነ በዋናነት ደግሞ የዚህ ኣካባቢ የተለያዩ ሃይሎች ተባብረው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተስማሙበትን ነገር፡ በማንኛውም ሁኔታ ስር የጥያቄ ምልክት ኣታስቀምጥበትም። በተደጋጋሚ በዳህላክ እስራኤልና ኢራን ኣሉ፡ የእስራኤል ግዙፍ የሳይቬርላንስ ጣቢያ ኣለ፡ ለእንዲህ ዓይነት ዓላማ የተቋቋመ ነው…የሚሉና እንዲህ የመሳሰሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታዎች የሚለቀቁ ፊኛዎች ወዴት ለመድረስ ነው? እነዚህን ትማርባቸዋለህ ግን የተፈበረኩ ናቸው። ይህንን ባዮቹ ወይም ይህን ተናጋሪዎቹ ምን ዓይነት መልእክት ነው ለማስተላለፍ የሚፈልጉት? ባብ-ኣልመንደብ፡ ስዊስ፡ ቀይባህር  እንደ የዓለምኣቀፍ የውሃ መተላለፍያ መስመሮች ወይም መንገዶች መጠን ኣስፈላጊነታቸው ምንድንነው? እዝያ በመምጣት ማተራመስ የሚፈለገው ለምንድንነው? የዚህን ኣካባቢ ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ መፈለግስ? በእንዲህ ዓይነቱ ግዙፍ ገጽታ፡ በእርግጥ ቱርክ ተስማምታ በስዋኪን ለመስፈር ፈልጋ ከሆነ፡ ተንታኞች፡ ሊቃውንት፡ ኣዋቂዎች፡ ተመራማሪዎች የሚባሉት የሚናገሩት ንግግር ብዙ ነው።

ስለዚህ፡ ከሁሉም ኣስቀድመን ማስረጃዎችን መሰብሰብ ኣለብን። ማስረጃዎች ብቻም ሳይሆን፡ በተጨባጭ የነዚህ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወስዱት ሃይሎች ቱርክም ጭምር፡ ዓላማቸው መታወቅ ኣለበት። የገዛ ራሳችንን ብሄራዊ ደህንነትና ሉኣላዊነት ብቻ ሳይሆን የዛሬውን የነገውንና የከነገ ወዲያው የጋራ ጥቅሞቻችን ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ይኖረዋል? ባለፉት 25 ዓመታት ብዙ ነገሮች ነው የተማርነው። የኤርትራ ህዝብ ሊቀበለው ኣይችልም። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹን ሁኔታዎች ስንመለከት ተጣድፈን ወደ ድምዳሜ ከመዝለላችን በፊት በደንብ ልንከታተላቸው ይገባናል። ይህ ስለ ሳዋ ጉዳይ ሲነገር የሰነበተው ፡ የቱርክ ፕረዚደንት ወደ ሱዳን መጥተው ስዋኪንን ተመልከቱት። እዚያ ወታደራዊ ካምፕ ሊያቋቋሙ ነው፡ የሚሉት ዜናዎች፡ ለህዝባዊ ግኑኝነት ፍጆታ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ብንገነዘበው ይሻላል። ምክንያቱም ልናገዝፈው ከሞከርን ባልተጨበጠ ነገር ላይ ልንናገርና ልናርገበግበው ነው ማለት ነው። ኣሉባልታ በሚያሰራጩ ወገኖች ገበታ ተጋብዘን ማጨብጨብ ስለማይገባን ቆጠብ ብለን መከታተል ብቻ ነው የሚያስፈልገን። ባጠቃላይ ግን፡ የዚህ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ተጨባጭ ኣብነት ማጣቀስ ከተፈለገ የሶማልያ ሁኔታ ኣለልን። ከወያኔ ጋር የሚሰሩ ሌሎች ተዋናዮችም ኣሉ። ባለፉት 25 ዓመታት የደለበ በውጭ ፖሊሲዎቻችን ላይ፡ ያሳለፍናቸው ተሞክሮዎች ያሳዩን ብዙ ጭብጦች ኣሉ። ከዚያ እንማራለን። በቀዝቃዛው ጦርነት ግዜ የነበሩት ሁኔታዎችን ኣንድ በኣንድ በመገምገም ማንበብ መቻል ኣለብን። እነዚያ ዓለምኣቀፋዊ ይሁኑ ቀጠናዊ የኣገር ውስጥ ተዋናዮች ፡ የነዚህ ሶስቱ መስፈርቶች የተዋናይነት ሂደት በቀጠናችን ውስጥ ምን ይመስላል? የመጨረሻው ዓላማችን ከጎረቤቶቻችንና ኣዋሳኞቻችን ጋር መረጋጋት፡ ሰላም ጸጥታና ትብብር ከሆነ፡ ከባለፈው በተማርነው ተሞክሮ፡ ለወደፊት መደገም የለበትም፡ ወደ ተሻለ  የሚወስደን መንገድና ሁኔታ ብቻ  መምጣት ስላለበት በዚያው መጠን ይህንን በዚህ ኣካባቢ የሚደረገውን የቱርክና የሌሎች እንቅስቃሴን እየተከታተልን ልንመዝነው ይገባል። ለመፈተሻ ለማደናገርያ፡ ለማወኪያ የሚነግሩ ወሬዎችና ለህዝባዊ ግኑኝነት ፍጆታ ሲባል የሚደረጉ ንግግሮችን ጠንቀቅ ብለን ለናስተውላቸው የሚገባን ጉዳዮች ናቸው። የምናናንቀው ኣልያም ‘ኣይደለም’ ብለን ወደ ጎን የምንገፋው ሳይሆን በግዙፍ የውጭ ፖሊሲ ውስጥ ከኣዋሳኞቻችን ጋር ኣዛምደን ልናየው የሚገባ ጥያቄ ነው። ቱርክን ምን ልታደርጉ ነው ወደዚያ እየመጣችሁ ያላችሁት? ብለን ልንጠይቃቸውም ይገባናል። ትንሽ እንዲገባን ብትነግሩብም ጥሩ ነው። የለም ኣንነግርም የምትሉ ከሆነ ደግሞ የራሳችሁ ጉዳይ ነው ግን ፍቃዳችሁ ከሆነ ንገሩን እንላቸዋለን።

እሺ ክቡር ፕረዚደንት፡ ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ እንሻገር። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ ኣዘቅት ውስጥ ነው ያለው። በክልሎች መካከል በቀጣይ የሚከሰቱ ግጭቶች ኣሉ። በመንግስት ላይ ያነጣጠሩ ታላላቅ ህዝባዊ ተቃውሞዎችም ኣሉ። የኢህኣዴግ ኣባል በሚባሉት ድርጅቶች መካከልም ኣለመግባባት ኣለ። የኢትዮጵያ ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው?

እንዴት እንገመግመዋለን ? ለወደፊቱስ በእንዴት አይነት መልኩ እንመለከተዋለን የሚለው ነገር በእጅጉ አስፈላጊ ነው ። በዚህ ቀጠና ወይም አዋሳኛችን በምንለው አካባቢ ከማንኛዉም አገርና ህዝብ በላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ እኛን ይመለከተናል ። ግልጽ በሆነ ምክንያት ። ለዚህ ሰፊ ትንታኔ አያስፈልገዉም ። እንዲሁ በግምገማ 25  ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ዓመታት አልፈዋል ብለን ለመናገር እንችላለን ። ምንድን ነው የመጣው ነገር  ። ሁልግዜም ቢሆን ቀልድ ወይም ጆክ ነው ። አሁን በቅርቡ ለምሳሌ በአንድ የዜና ትንታኔ ላይ አንድ ቀልድ አንብቤ ነበር ። እነሱ የኢትዮጵያ ፓርላማ በሚሉት የወያኔ ፓርላማ ዉስጥ ፡ በክልሎች ወይም በጎሳ ቡድኖች መካከል ያለዉን ግጭት የሚመረምር ተቋም ተመሰረት ተባለ ። የኢፌድሪ ህገመንግስት ዓንቀጽ 39 ምን እንደሚል ማየት ይቻላል ።ይህ ምን ያመለክተናል ከተባለ ፡ የወያኔ ቁጥር አንድ አጀንዳ ኢትዮጵያ በጎሳና በብሄር እንድትከፋፈልና እንድትበታተን ነው ። ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን ተከሰተ ? ክስተቱስ እንዴት ሊመጣ ቻለ ? የሚል የፖለቲካ ግምገማ የምናደርግ ከሆነ  ፡ እኔ የኢትዮጵያውን ውድመት የወያኔ ጤናማ ያልሆነ አእምሮ የወለደው ነው ‘ ነው የምለው ። በመካከላችን ያለው ግንኙነት ደህና በነበረበት የ1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ወቅት ፡ እንዴት ቢሆን ይሻላል እንባባልና እንመካከር ነበር ። ምክንያቱም የሁለቱን ህዝቦችና ትዉልዶች የወደፊት እድል ልታራርቀው አትችልም ። በጋራ መስዋእትነት ከፍለንበታል ። ከወያኔ ታሪክን ከመጠምዘዝ ባህሪ ዉጭ ፡ የወደፊቱን በመመልከት ተነጋግረንበታል ። የኢፌድሪ  ህገ – መንግስት ረቂቅ ከመዉጣቱ በፊት ፡ ከዚያም በፊት ፡ ከ1991 ና ከ1990 በፊት ፡ በ1970ዎቹና በ1980 ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ከወያኔ ጋር ያነጋግረን የነበረው ጉዳይ ፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ   ወያኔ ያራምድ የነበረዉን የተዛባ አካሄድ  ለማረም ነበር እንታገል የነበረው ። የመጀመርያው የወያኔ ፕሮግራም ሲወጣ “ እንደዚህ አይደለም ። ኤርትራ አገር ናት ። ስለ አገሮች ስንናገር ፡ የቅኝ ግዛት ታሪክን ነው አስታከን  የምንናገረው ። ከሽዎች ዓመታት በፊት ህዝቦች የት ነበሩ ብለን አንናገርም ። እንዲህ መሰሉ የፍልስፍና ፕሮግራም አያስፈልጋችሁም ። አይሆንም – እንገነጠላለን  ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የሚያገናኘን ነገር የለም ። ከአማራ ጋር ተግባብተን በአንድ ላይ ለመኖር አንችልም እየተባለ ይነገር ነበር ። ይህ አልፎ አንድ መድረክ ላይ ደረስን ። በመጨረሻ ላይ ደግሞ ከዚህ በእጅጉ አክራሪነት የተንጸባረቀበትና ምክንያት አልባ የሆነ ሌላ የኢትዮጵያ አጀንዳ መጣ ። ስነአእምሮው ግን ገና አልተቀየረም ።” እኛ ጥቂቶች ወይም ደግሞ አናሳዎች ስለሆንን ፡ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር አልያም ደግሞ ለመግዛት ፡ የግድ መበታተን አለብን ‘’የሚለው ነው ዋነኛ ነገረ ስራቸው የነበረው ።

ቀጥሎ የኢትዩጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት ተራማጅ ነው ተብሎ ተነገረ። ከዛ በኋላ በወያኔ ኣእምሮ ውስጥ የሰፈረው ኣጀንዳ ኢትዮጵያን በታትነህ እንዴት ታስተዳድራታለህ ነው። ኣሁን ወደ ኋላ ተመልሰን ፖለቲካዊ ኣጀንዳውን ከተመለከትንነው ፍጹም ኣልሰራም። ኢህኣዲግ ከመመስረቱ በፊት ብሄር ከብሄር ነውጥና፥ ህውከት ማነሳሳት ኣያስፈልግም የምንላቸው ጉዳዮች ነበሩ። ከ 1991 ዓ/ም በኋላ የኢትዩጵያ ህዝብ ወዴት ኣቅጣጫ ሊጓዝ እንደሚችል እንዲወስን የሽግግር ሕገ- መንግስት መኖር ኣለበት ኣልን። በዚያን ጊዜ ጉዳያችን ስላልሆነ ኣይደለም የገባነው ሸሪኮች ስለነበርን  እንጂ። ቢያንስ የ10 ዓመት የሽግግር ወቅት ይኑርና ከዚያ በኋላ ወደ ሌላ መድረክ ያመራል ኣልን። ይህንን ትተህ ሌላ ምንም ነገር ልታመጣ ኣትችልም። ያለውን የብሄሮች እንቅስቃሴ ማንኛውም ሰው ሊክደው ኣይችልም። ለወደፊት  ከኣዲሱ የኢትዩጵያ ሁኔታ ጋር እንዲሁም  ከኣካባቢው ጋር የሚስማማ የሽግግር ወቅት መኖር ኣለበት። እንዲህ ኣይነት ሁኔታ ኣያስፈልግም ተባለ። ወያኔ ኢትዮጵያን በፖለቲካ ከፋፍለህ ለመቆጣጠር  ኣንድ የኣስተዳደር ጥላ መፈጠር ኣለበት ኣለ ። ይህም በኢህኣዲግ ስር ማለት ነው። ኢህኣዲግን መቶ በመቶ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ህወሃት ብቻውን የሚቆጣጠረው እንዲሆን ሁኔታውን ኣመቻቹት። ሌሎቹ ድርጅቶች ተቀጥያ ናቸው ማለት ነው። ወይም መገልገያ ናቸው። ይህ ከውስጥ የሚሰጠው ምስል ብዙዎች ብሄሮችን ያካተተ ድርጀት እንደተመሰረተ የሚያስመስል ነው። ነገርግን በድርጅቶቹ መካከል መተማመንም ኣልነበረም። ይህ ኣሁን በኢትዮጵያ የምንመለከተው ሁኔታ የዚያ ኣጀንዳ ውጤት ነው። በዚያን ወቅት ስንሰጥ ለነበረው ምክር በተቃራኒው ይሰሩ እንደነበር ግልጽ ቢሆንም እንኳን ወያኔ የነደፈው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ተራማጅ ህገ መንግስት መተግበሩ፡ በኢትዮጵያ ከተፈጠሩ ከፍተኛ በደሎች ዋነኛውና ለዚህ  ኣሁን ለምንመልከተው ፖለቲካዊ ቀውስ ጠንቅ ሆነ። ይህ ደግሞ ከሰማይ የወረደ ችግር ኣይደለም። ወያኔ የቀየሰው ችግር ነው። ለጉራ ወይም የኔን ድርሻ ለማጉላት ሳይሆን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ረቂቅ ሕገ- መግስትን ከተመለከቱት ሰዎች ኣንዱ ነኝ። በነበረን መልካም ግንኙነት የማንወያይበት ኣርእስት ኣልነበረም። ሁሉንም ነገር ኣንስተን እንመካከርበት ነበር። ብሄሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ኣንቀጽ 39 ምን ማለት ነው? ከተሳካልን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ኣብረን እንዘልቃለን፡ ካልተሳካ ደግሞ እንገነጠላለን ማለት ነውን? ይህ የብሄረሰቦች ኣመሰራረት የሚባለው ቀስ በቀስ በኣገር ግንባታ እየተቀናጀ ወደ ኣንድነት እንዲያመራ ማድረግ እንጂ እንዳለ እስኪደህ ተቋማዊ ቅርጽ ለማስያዝ መሞከር ኣደገኛነቱ ማለቂያ የለውም። በማንኛውም ኣገርም ይሁን ኣካባቢ ኣይሰራም። ብዙሃነትን ተገንዝበህና ኣምነህ ወደ ኣስተማማኝ ውህደት እንዲያመራ መስራት ኣለብህ። ካልሆነ ግን የነበረው ክፍፍል እንዲቀጥል ኣድርገህ በህብረተሰብ መካከል  የጎጥ፥ የጎሳና፥ የብሄር፥ ልዩነት በመፍጠር  በጎሪጥ የመተያየት ሁኔታ እንዲከሰት ማድረግ በእጅጉ ኣደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ይህንኑ ኣደገኛ ጨዋታ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገው ወያኔ ነው። ይህ ብቻ ግን ኣይደለም። ወያኔ የፈጸማቸው ኣራት ከፍተኛ ስህተቶች ኣሉ። ይህ በኣሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ህዝብ እያተራመሰ ያለው  የወያኔ የፖለቲካ ኣጀንዳ መጨናገፍ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ከፋፍለህ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተዳደር መሞከር ኣንዱ ኣጀንዳ ነው። ከሱ ጋር በተያያዘ ደግሞ ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር መወሰኑ ነው። ይህ ሁኔታ የሚያስከትለውን መዘዝ ግን ወያኔ ኣልተገነዘበውም። በኣንዲት ኣገር ውስጥ ኣንድ ኣናሳ ቡድን ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠር ማድረግ ማለት ሌሎችን ማግለል  መዘዙ በጣም ኣደገኛ ነው። ከዚህ የከፋ ኣደገኛ ጨዋታ ኣልነበረም። በተለያዩ የኣውሮፓና የኣሜሪካ ኣካባቢዎች ጉዳይ-ኣስፈጻሚዎች እየቀጠርክ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ኣገር ናት። ባለሁለት ኣሃዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ነው እያልክ የሆነ ያልሆነ ወሬ በመንዛት መኖርና  በመጨረሻ የኣገርህን መሬት እየሸጥክ የኣንድ ጠባብ ቡድን የኢኮኖሚ የበላይነትን መፍጠር ያስከተለው መዘዝ ኣሁን ኣየተመለከትነው ያለነውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ነው። በኣጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ውድመት – የወያኔ ፕሮፖጋንዳ ከግምት ውስጥ ሳይገባ – በኣሁኑ ወቅት የታየውን የኢኮኖሚ ቀውስ ኣስከትሏል። ወያኔ ከፈጠረው የፖለቲካ ችግር በተጨማሪ ህዝቡ የኢኮኖሚ መብቱን ለማስከበር ባለመቻሉ ምሬቱን እየገለጸ ነው። በኣሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ካልን፥ የኣለም የገንዘብ ድርጅትና የኣለም ባንክ በሰጡት ማሳሰቢያና ምክር የብርን የምንዛሬ መጠን በማጉደል ኢኮኖሚውን ማስተዳደር ኣይቻልም። ባለሁለት ኣሃዝ  እድገት ኣስመዘገቧል እየተባለ ሲነገርለት የነበረ ኢኮኖሚ እንዴት ወደ እንዲህ ኣይነቱ ሁኔታ ሊገባ ይችላል?  ይህ ደግሞ የወያኔ ሁለተኛው ከፍተኛ ስህተት ነው። ሶስተኛው ኣጀንዳ ደግሞ ወታደራዊና ጸጥታዊ ቁጥጥር ነው። በኣሁኑ ወቅት በኣገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዴት ተከሰተ? በሶማሊያ ድረስ ሄዳ የምትዋጋ ወደ ሌሎችም ኣገሮች የሰላም ኣስከባሪ ሰራዊት የምታሰማራ ከኤርትራ ጋርም በተደጋጋሚ ጦርነት የገጠመች  ይህች የቀጠናው ሃያል ነኝ የምትል ኣገር ፡ ይህ ሃያል  የሚሉት ተጫባጭነት የሌለው ጉራ ለምን ኣስፈለገ?. . . .ከኤርትራ ጋር በሰላም ለመኖር ሰራዊትም ሆነ የጸጥታ ሃይል ባላስፈለገ። በጋራ የምትኖር ከሆነ የጋራ የጸጥታ ሃይል ታቋቁማለህ ። ወደ ሶማሊያ የሚያስኬድ ምክንያት የለም። በተለያዩ ኣካባቢዎች የኣንድን ጠባብ ቡድን የበላይነት በወታደራዊ ሃይል ልታረጋግጥ ኣትችልም። መጀመሪያ ላይ በርግጥ ሊመስል ይችላል። በእንዲህ ኣይነት የወታደር ሃይል ህዝብን ኣንበርክኬ እገዛለሁ ብለህ ታስብ ይሆናል ።  ይሁን እንጂ ይህ ኣስተሳሰብ እሩቅ ሊያስኬድ ኣይችልም። ያለ ከፍተኛ ወታደራዊና የጸጥታ ሃይል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማረጋጋጥ መቻል ኣለብህ።  ገና ከመጀመሪያውም ለዚህ የሚሆን ምቹ መድረክ መፈጠር ኣለበት።

አራተኛው የወያኔ አጀንዳ ወይንም ችግር ከዉጭ ሃይሎች ጋር ተጎዳኝትህ ወይም ተስማምተህ ቁጥጥርህን ለማጠናከር መሞከር ነው ። ስለሆነም ደግሞ ለዉጭ ሃይሎች ትገዛለህ ማለት ነው ። የወያኔ ፈላስፋዎች በተደጋጋሚ ይሉን የነበረውና ፡ ይህ ነገር አያዋጣችሁም ይባል በነበረበት ወቅት የነርሱ ፍልስፍና “ ከሃያላን ጋር ተስማምተህ እደር” ነው  ። ከሃያላን ጋር ተስማምተህ እደር ማለት ፡ ከነርሱ ጋር በምንም ዓይነት አቋምም ቢሆን ተስማምተህ ተጓዝ እንደ ማለት ነው ። ከዚህ የባሰው ነገር ደግሞ ፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የመቆጣጠርና የአካባቢው አንኳር የመሆን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ፡ የትግላቸው አጋር የሆነዉን የኤርትራን ህዝብ በመካድና ጭዳ በማድረግ ፡ ከዉጭ ሃይሎች ጋር ተስማምተው የኢትዮጵያን ህዝብ እየበደሉ የመቀጠል ፍላጎታቸው ነው ። ይህ የፍልስፍና ምርምር ምናልባት መጀመርያ ላይ ለወያኔ እንደ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትርፍ ወይም እንደ ታላቅ የስትራቴጂ ድል መስሎት ሊሆን ይችላል። መጨረሻ ላይ ግን ሁሉንም የመቆጣጠሩ ጉጉት አልሰራም ። የኤርትራን ህዝብ ክደህ ፡ ሻእቢያ አጋርህና የትግል ጓድህ እንዳልነበረ ሁሉ እንደ ቀዳሚ ጠላትህ ቆጥረህ ፡ ከዉጭ የሚመጣዉን ሁሉንም ዓይነት ጠብ አጫሪነት ስታስተናግድ ፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጋር የጎሪጥ እንዲተያይ ልታደርገው ፡ ያዉም ደግሞ የትግራይን ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ልታራርቀውና ልታጋጨው መሞከር በምን ኣመክንዮ ሊገለጽ ይችላል ? በ25 ዓመታት ዉስጥ የተመለከትነውን የወያኔ ፖለቲካዊ ፡ ኢኮኖሚያዊ ፡ ደህንነታዊና የዉጭ ጉዳይ ግንኙነቱንና አጀንዳዎቹን አንድ ባንድ ካየነው ፡ የጎላ ስህተቱን መገንዘብ እንችላለን ። አሁን እየተባለ እንዳለው ፡ “ ግብጽ በዚህ በኩል መጣች ፥ ከሱዳን ጋር ተወዳጅተናል ፥ በኤርትራ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር እየሰራን ነው ወ.ዘ.ተ የሚባለው ነገር ባላስፈለገ ። በዋነኝነት ግን ወያኔ የተጓዘበት የፖለቲካ ፥ የኢኮኖሚ ፥ የጸጥታም ሆነ የዉጭ ጉዳይ ፕሮግራሞች ይህን ያህል ሊቀጥል መቻሉ በተናጠል ሊታይ የሚችል አይደለም ። ወደ ኋላ መለስ ብለን ፡ የክሊንተን ፥ የቡሽና የኦባማ ሶስቱም አስተዳደሮች የነበራቸዉን አስተዋጽኦ መመልከት እንችላለን ። እንዲህ አይነቱ ስህተት እየተፈጸመ እያለ ፡ ለምን ይሆን “ አይዞህ በርታ “ ይሉ የነበረው ? በአዉሮፓ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ለምን ይሆን ይህንን አካሄድ ሲያበረታቱ የነበረው ? ለምን ይሆን የቀውሱ ግዜ የተራዘመው ? ከተባለ በራሱ በወያኔ የዉስጥ ፕሮግራም ወይም በራሱ በወያኔ የዉስጥ አጀንዳ ብቻ እንደሆነ አድርገን የምንመለከተው አይደለም ። ወያኔ ይህንን የማድረግ ሃይል የለዉም ። ጉዳዩም ይበልጥ እየተወሳሰበ ባልሄደ ነበር ። በራሱ በወያኔ የዉስጥ አቅምና በኢትዮጵያ ፕሮግራም ብቻ ቢሆን ኖሮ ፡ ይህን ያህል ግዜ ባልተራዘመ ነበር ። ለተፈጠረው የተወሳሰበ ሁኔታ ከፍተኛዉን አስተዋጽኦ ያበረከተው ፡ ከዉጭ የሚደረገው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ድጎማ ነው ። ኢነቨስተሮች ነን ሃብታሞች ነን በማለት መዋእለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ላይ የሚያፈሱና ሌሎችም  ቢሆኑም ፡ ይህንን ሁኔታ እያመቻቹ እድሜው እንዲራዘም አድርገዋል ።  ይህ  ከፍተኛ እንክብካቤ የሚባለው በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ዘላቂነት የለዉም ። ሊቀጥል አይችልም ። ይህን ነገር ደግሞ ፡ እኛ ስለተካድን ወይም ደግሞ ሰለባ ስለተደረግን የምንናገረው ነገር አይደለም ። የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ገምግሞ ፡ ከዚህ ዉጭ የተለየ ሁኔታ ነው ያለው የሚል ካለ ፡ ባለፉት 25 ዓመታት ወስጥ ሲቀጥል የቆየው የፖለቲካ ፡ የኢኮኖሚ ፥ የጸጥታና የዉጭ ግንኙነት እንዴት አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደቻለ ነቂስ በነቂስ ተንትኖ ይመልከተው ። ወያኔን ያሳሳቱት ከዋሽንግተን ጀምሮ እስከ አዉሮፓ ርዕሰ መዲናዎች ድረስ ያሉት መንግስታት ሲከተሉት የቆዩት ፖሊሲ ነው፡፡  ወያኔን ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ፡ በኤርትራ ህዝብና መንግስት ላይ ያራመዱት የጠብ አጫሪነት አካሄድን አንድባንድ ከተመለከትከው ፡ ምስሉ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ባለበት ሊቀጥል አይችልም ። የእዉነቱን ለመናገር እኛ ፡ የእጃችንን አይደለም ያገኘነው ። ታሪካችንን ደምስሶ ለማደብዘዝና ለማጥፋት ያልተደረገና የማይደረግ ሙከራ የለም ። ያልተሞከረ ማናቆር አልነበረም ። በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ፡ መጨረሻ የሌለው ጥላቻ ለመዝራት  የተደረጉ ሙከራዎችን በሙሉ ፡ በነቃ ህሊና ስነከታተለው የቆየነው ነገር ነው ። ያለፉት 25 ዓመታት የኪሳራ ዓመታት ናቸው  ። ያለፉን እድሎች ቀላል አይደሉም ። ይሁን እንጂ ባለፈው ነገር የምንቆጭበት ምክንያት የለንም ። ባለፈው ነገር ተደናግጠን እጅና እግራችን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ምክንያትም የለም ። የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን የወደፊት ግንኙነት  በተመለከተ ፡ በጋራ እስከታገልነበት 1991 ድረስ ከነበረው ማለትም ከበፊቱ የተለየ አዲስ ፍልስፍና የለንም ። ከ25 ዓመታቱ ዉድመት በቂ እዉቀት ቀስመናል ። የሁለቱም አገራት ህዝቦች ካለፈው ነገር ብዙ ተምረዋል ።  የትግራይ ህዝብም ቢሆን በዋነኝነት ካለፈው ነገር ትምህርት አግኝቶበታል ።  ምናልባት በአሁኑ ወቅት ፡  ግዜ ለመግዛትና እድሜ ለመቀጠል  ፡ “ጥገናዊ ለውጥ አድርገናል ፥ እስረኞችን እንፈታለን ፥ የጎሳ ችግሮችን እንፈታለን ፥ የኢኮኖሚ ማሰተካከያ እናደርጋለን ፥ እንዲህ እንሰራለን. . . ወዘተ” የሚሉ የተለያዩ ማማለያዎችና ማዘናጊያዎችን በየእለቱ የምንከታተለው ነገር ነው ። ነገር ግን ጉዳዩ አብቅቷል ። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ቢሆን የወደፊት እድሉን የሚወስንለትን ማወቅ አለበት ። በህዝቦች እድሜ 25 ዓመታት ማለት ፡ አጭር ግዜ አይደለም ። ረጅም ግዜ ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ መንገዱን ማወቅ አለበት ።

በአሁኑ ወቅት የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለማራራቅ ፡ “ኤርትራ እንዲህ እየፈጸመች ነው ፥ ሻዕቢያ እንዲህ አደረገ ፥ በኢትዮጵያ በእከሌ ክልል እንዲህ ፈጸመ ፥ እየተባለ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ  ማንንም የዋህ ሊያታልል ወይም ሊያደናግር አይችልም ።  በፊትም ቢሆን’ኮ ታንክና መድፋችን ይዘን አዲስ አበባ ድረስ የዘለቅነው ለሁለቱም ህዝቦች የወደፊት እድል ስንል እንጅ ለጉራ አይደለም ።እኛ ጎበዝን እናንተ ግን ሰነፋችሁ ብለን የምንናገርበት ጉዳይም አይደለም ። አሁን ላይ የተከሰተ አዲስ ፍልስፍና የለንም ። የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን አዲስ ፍልስፍና የለዉም ። በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል በሚኖረው ግንኙነት ላይ አዲስ የሚባል ፍልስፍና የለም ። የወደፊት እድሎቻችንን እንዴት እንወስናለን ፥እንዴት አድረግን እንተባበራለን ፡ ከማንኛውም ሰው የተሰወረ አይደለም ።

ስለዚህ ይህ ኣሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ኣለ የሚባለው ሁኔታ ፡ በተጨባጭ መነበብ መቻል ኣለበት። እንደየስሜትህ የሚነገር ኣይደለም። እነዚህ ኣንድ በኣንድ ስገልጻቸው የቆየሁት ሁሉ የተሰነዱ ናቸው። ትንታኔ ኣይደሉም፡ የተመዘገቡ ጭብጦች ናቸው። ከዚያ የበለጠ የትምህርት መጽሃፍ ደግሞ የለም። በዚያ ላይ ግዜ ለማጥፋት ሳይሆን፡ የሚበቃንን ተምረናል። ብዙ ስለከሰርን ደግሞ ካሁን በኋላ በእንደዚያ ሁኔታ መቀጠል ኣንችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፈው ዓመት ያሳያቸው ተቃውሞዎች፡ ያለመርካቱና  የተሳሳተ የወያኔ ስትራቴጂ ገሃድ መግለጫ ነው። ስለዚህ ረጋ ብለን፡ ኣዲስ ፈጠራ ሳናመጣ ፡ ድሮ በተጓዝንበት መስመር መጓዝ ብቻ ነው ያለብን። ይህ ኣሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሌለ ገጽታ ለመስጠት፡ ኤርትራ እገሌን ደገፈች፡ እንዲህ ኣደረገች እያላችሁ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክርቤት የምትከሱን ታድያ እኛስ ከናንተ ጋር ኣይደለም እንዴ ኣዲስኣበባ የገባነው?  ለምን ያኔ በጉዳያችን እጃችሁን እያስገባችሁ ነው ኣልተባለም? ብዙ ሊባል ይችላል።

ታሪኩን በሚገባ የሚያውቁ ብዙዎች፡ ‘ ያ ሁሉ ኣብረን በልተን፡ ኣብረን ሰርተን፡ ኣብረን ተሰውተንና፡ ኣብረን ታግለን ኣሁን ያን እንዳልነበረ ለመደምሰስ የሚደረገው ሙከራ ሚስጢሩ ምንድንነው? ይላሉ። ነገር ግን ኣዲስ ታሪክ የለም፡ ሁሉም በሰነድ የተያዘ ነው። በኣካሄዳችን በርግጥ ድሮ ከነበረን እምነት ዛሬ ያለን እምነት ይበልጥ ይጠነክራል። ለወያኔ ብቻ ሳይሆን፡ ለወያኔ ኣሰሪዎችም ቢሆን የምናፍርበት ወይም የምንፈራበት ጉዳይ ኣይደለም።

ይህ በኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችለው የፖለቲካ ለውጥ፡ በኤርትራ ባጠቃላይ ደግሞ በኣፍሪካው ቀንድ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊያሳርፍበት ይችላል? ሁለቱም ህዝቦች የከሰሯቸውን ዕድሎች ዳግም ለማንሰራራት የሚያስችል ምን ተክእሎ ኣለ ወይንም እንዴት ዓይነት ሁኔታ ይጠይቃል? 

የጀርባ ታሪኩ ያው ኣስቀድሜ የገለጽኩት ስለሆነ፡ በሁለቱም ህዝቦች መካከል ያለውን ግኑኝነት ብቻ መመልከት የለብንም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፡ ይህ የኢትዮጵያ ተረት-ተረት ተፈጠረ። ኢትዮጵያ ገዛችን ፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ኣደረገችን ሲባል ለኔ በእውነቱ ሁልግዜ ቅር የሚለኝ ነገር ነው። በኢትዮጵያ የነበረውን ስርዓት ለማንኳሰስ ሳይሆን፡ የኢትዮጵያ ውሳኔ ኣልነበረም። የኤርትራ ህዝብ እንደ ሁሉም ህዝቦች፡ እንደ ሌሎች የቅኝ ግዛት ድንበሮቻቸውን እንዳመላከቱላቸው ህዝቦች ነጻነቱን መጎናጸፍ መብቱ ነው የነበረው።ግን ኣልተቻለም። ለምን ቢባል ያኔ የመጣው ዓለማዊ ስርዓት የፈጠረው ሁኔታ ነው። ዕድላችንንና መብታችንን ከተከለከልን በኋላ መጨረሻ ላይ ታገልን፡ ደግሞም ከባድ ዋጋ ከፈልበት።

ይህ ፍልስፍና ማለት ይህ ኣንዲት የኣካባቢው ሃያል ኢትዮጵያን ፈጥረህ የመስራት ፍልስፍና ባለፉት 25 ዓመታትም ከተመለከትነው ኣልተቀየረም። ከ 1991 በኋላም ኣብረን ተጉዘንና ኣብረን ታግለን ከምንፈልገው ግብ ደርሰናል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ መፈጠር የነበረበትን ሁኔታንም መልሰንዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፡ ኤርትራ ነጻነቷን ኣግኝታ ቢሆን ኖሮና፡ ኢትዮጵያም ነጻና ሉኣላዊት ኣገር ሁና ሁለቱም ኣገሮችና ሁለቱም ህዝቦች ጀምረውት በነበረው የመተጋገዝ ጎዳና ቢቀጥሉ ኖሮ ያ ሁሉ የከፈለነው መስዋእትነት፡ የደረሱብን ችግሮች፡ የባከኑት ዕድሎች ለነሱም ጭምር ባላጋጠመ ነበር። ምናልበት ያኔ የነበሩት የኢትዮጵያ ገዢዎች ፍጻሜው ጥሩ መስሏቸው የነበረ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ህዝቦቹ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩትን ዕድሎች ከስረዋቸዋል። ኣብረን ነው የከሰርነው። ኣብረን የታገልንበት ምክንያት ደግሞ ይህን በደል ኣስተካክለን ወይ ኣርመን በዚህ ኣካባቢ እየተባበርን ኣዎንታዊና ገንቢ ሚና ለመጫወት እንድንችል ነው። በተለይ የደርግ ስርዓት በ 1970ዎቹ ኣጋማሽ ወደ ስልጣን ሲመጣ ፡ ከዚያ በኋላ ያካሄድነው ትግል በታላላቅ የኣፍሪካ መዛግብት የሰፈረ ሃቀኛና ተጨባጭ ታሪክ ነው። ኣብረን ነው የሰራነው። ይህንኑ እንደ የጀርባ ታሪክ ወስደን ደግሞ በዚህ ኣካባቢ ገንቢ ኣስተዋጽኦ ለማበርከት ተነሳሳን። በሶማልያ የሃገሪቱ ሁኔታ ከደፈረሰ በኋላም ቢሆን ኣብረን እንስራ ተባለ። ይህ የተመዘገበና በታሪክ ያለ ነው። ሰዓቱንና ዕለቱን እየነቀስን ልንናገርበት የምንችል ነው። ‘ኣብረን እንስራ፡ የሶማልያ ህዝብም ወንድማችን ነው፡ ከሶማልያ ህዝብ ጋር ሆነን በዚህ ኣካባቢ ኣንድ ጠንካራ ውህደት መገንባት እንችላለን’ እንል ነበር። ጂቡቲም እንዲሁ ፕረዚደንት ጉሌድ በነበሩበት ግዜ ስንነጋገርበት የነበረ ኣርእስት ነው። ያ የተባለው የዚህ ኣካባቢ ጠንካራ ውህደት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ያኔ የነበረው የነ ቢንላደን ካርሎስና ሌሎች የተለያዩ ወንጀለኞች በሱዳን መታየት ባልተከሰተ ነበር። በ 1993ም ቢሆን እኛ ኢራንን እንጠላት ወይንም እንወዳት ነበር ብለን መናገር ኣንችልም። ነገር ግን መጀመርያ የኣካባቢያችንን ወዳጅነት ሳናጠናክር ሌሎችን የምናስቀድምበት ምክንያት የለም። ‘እኛና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ እናደርጋለን ሲባል ቀላል ነገር ኣይደለም። ሁለት የፖለቲካ ሃይሎች ማለት ሻዕቢያና ወያኔ ሃሳቡን ስላመጡት ኣይደለም ጉዳዩ። በታሪካዊ ኣመጣጡ ከተመለከትነው የሁለቱም ህዝቦች ወዳጅነትና ትብብር ስትራቴጂካዊና በበርካታ መስፈርቶች የሚያያዝ  ሃቅ ነው። የፖለቲካ ሃይሎች ፈጠራ ኣይደለም። በቀጣይ ትውልዶችም ሊቀየር የሚችል ነገር ኣይደለም።

እንዲህ ስለሆነ ኣስቀድሜ እንደጠቀስኩት ይህ ወያኔ የፈጸመው ኣደጋ ወይም የታሪክ ዲስቶሽርን ወደ ነባራዊ ሁኔታው መመለስ መቻል ኣለበት።

በህዝቦች መካከል ጥላቻ ፈጥረን ምን የምንጠቀመው ኣለ? ምንም። ኣብረን ሰርተን ልናመጣው የምንችል ለውጥ ግን፡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬው፡ የጸጥታ መረጋጋቱ፡ ከኣካባቢያችን ጋር ልንመሰርትረው የምንችል የተለያየ ወዳጅነት ሌላ በሆነ ነበር። ስለዚህ ኦፕሽን ወይንም ምርጫ ኣይደለም። ይህ ወዳጅነት መመስረት መቻል ኣለበት። እንዴት ኣድርጎ ነው የሚመሰረተው ለሚለው እኛ ልንመካከርና ልንተጋገዝ እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የተለያየ ሁኔታ ጋር ለመስራት እንችላለን። ነገር ግን ስልታዊና ለኣጭር ግዜ ያነጣጠረ መሆን ኣይገብውም። ይህ  በ 1990 ዎቹ መጀመርያ ላይ ያቀረብነው ነው ኣሁን ኣዲስ ነገር የለውም። ከዚህ ሁሉ የወያኔ ኣደፍራሽ ተግባር በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ኣሁንም ቁጭ ብሎ ‘ወዴት ነው እየሄድን ያለነው ብሎ ዕድሉን ራሱ መወሰን መቻል ኣለበት። በርግጥ የሽግግር መድረክ የሚጠይቅ ነው። በእህኣዴግ ውስጥ የቆዩና ከዚያ ውጭ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ኣሉ።

በተለያዩ መንገዶች ሊገለጹ የሚችሉ ኣደረጃጀቶች ኣሉ፥ ከነእንትና ጋር ኣብረን  እንሁን ወይ በተቃራኒው ከሌሎች ጋር እንሰለፍ ሳይሆን መጭውን ሁኔታችንን በጋራ ለመንደፍ ኣንድንችል በኢትዩጵያ ያለው ሁኔታ መስመሩን መያዝ መቻል ኣለበት። በኤርትራና በኢትዩጵያ ህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት በዚሁ ኣምሳያ መያዝ መቻል ኣለበት። በዚህ ኣካባቢ ያሉ ህዝቦችና ኣገሮች በዓለም ደረጃም ቢሆን የዋሽንግተን ስርዓት ይህም ማለት  የኣሜሪካ ፕሬዝደንቶች የኪሊንተን የቡሽና የኦባማ የተዛባ ኣመለካከት ወይም ኣቅጣጫውን የሳተ ሚስጋይዲድ የምንላቸው ፖሊሲዎች በኢትዩጵያ ላይ ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን በሶማሊያ፡ በደቡብ ሱዳን፥ በኣጠቃላይ በዚህ ቀጠና የፈጠሯቸው ችግሮች መስመሩን መያዝ መቻል ኣለበት። የውጭ ሃይል ኣፍራሽ ሚና ማክተም ኣለበት። በኣውሮፓ ያሉት ኣገሮች ይሁኑ ወይም በኣሁኑ ጊዜ ወደ እነሱ ጎራ ኣየተቀላቀሉ ያሉት ሃይሎች በቀጠናችን  ገንቢ ሚና የማይጫወቱበት ምክንያት የለም። ሩሲያ፡ ቻይና፡ ኣንዲሁም የተለያዩ ኣገሮች ማለት ነው። ስለዚህ ያለፉት የ25 ዓመታት ተመኩሮ ይህ ስለሆነ የወደፊት የነዚህ ኣዋሳኝ ኣገሮች እድል የሚመለከት ሃሳብ  ከዚህ ከምናቀርበው የተሻለ ኣስተያየት  ኣለን የሚሉ ከሆነ ኣዲስ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ።  ሲጓዙበት በነበረው መንገድ ግን ሊራመዱ ኣይችሉም። ለሁላችንም የሚመች ሁኔታ እንድንፈጥርና የራሳችን  ተነሳሽነት ኣንድንወስድ የራሳችንን  ስራ መስራት ኣለብን ። የቀረው ቢቀር ሁሉም ሰው  ኣውንታዊ ኣስተዋጽኦ እንዲኖረው  የሚጠበቅ ነው።   ባለፉት 25 ዓመታት በዚህ ቀጠና ወያኔ የፈጠራቸው ሁኔታዎች መቀጠል የለባቸውም። የዚህ መተኪያው ምንድን ነው? መተኪያ ኣለው ወይንስ የለውም? በኢትዩጵያ ሊመጣ የሚችል ኣዲስ ነገር ኣለ ወይንስ የለም። እዚህ ጉዳይ ላይ የምንለው የለንም። ነገር ግን ያለውን ሁኔታ ጠጋግነን ከተጓዝን ይሻላል ኣንላለን።  በምን ሁኔታ ነው የምትጠግነው? መጠገንስ ይቻላል ወይ? ዘላቂ መፍትሄው ምን መሆን ኣለበት የሚሉ ሰፋፊ ኣርእስቶች ኣሉ። ኣዲስ ፈጠራ የለንም ። ወዴት ነው የምናመራው፥ ያና ይህ የምንላቸው መርሃ ግብሮች ኣሉን  ለማለት በኣሁኑ ወቅት ኣስፈላጊነት የለውም።  እንዴት ኣድርገን ነው የሁለቱን ኣገር ህዝቦች ግንኑኙነት ምቹ የሚያደርግ ሁኔታ መፍጠር  የሚቻለው የሚለው ግን ኣማራጭ የለውም። ዝርዝር ሁኔታው ምን ይመስላል፥ በእንዴት ኣይነት ሁኔታ ተባብረን እንሰራለን ለሚለው ሁሉም የሚገነዘበውና የሚከታተለው ሁኔታ ስለሆነ በሚመጡት ዓመታት ምን እናደርጋለን?  ለወደፊት ምን እቅዶች ይዘናል? የኛ የብቻችን ነው ወይስ በዚህ ቀጠና ካሉት ህዝቦች ጋር የተቀናጀ መርሃግብር ነው? በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ያሉትን ሁኔታዎች ኣንስተን ለመነጋገር እንችላለን። ጅቡቲም ትንሽ ኣገር ናት ለማለት ኣንችልም፥፡ ትልቁ ችግር በጅቡቲ የነበሩት ስርዓቶች ናቸው። ጅቡቲ ለሽያጭ የቀረበች  ኣገር ናት ቢባል ማጋነን ኣይደለም በጅቡቲ የነበረው ስርዓትና ከፕሬዝደንት ጉሌድ በኋላ እየተባባሰ የመጣው መጥፎ ኣስተሳሰብ ደግሞ ጅቡቲ የዚህ ኣካባቢ ትልቅ ወደብ ተደርጋ እንድትታይ ኤርትራና ኢትዩጵያ ግጭት ውስጥ መግባት ኣለባቸው የሚል ነው። ኤርትራና ኢትዮጵያ ተግባብተው መስራት ከጀመሩ የዓሰብና የምጽዋ ወደቦች ኣገልግሎት ላይ ስለሚውሉ የጅቡቲ ካገልግሎት ይስተጎጎላል። ስለዚህ ጅቡቲ ለወያኔ ይሁን ኢትዮጵያ ህዝብ ተቆርቁራ ወይንም ወዳ ኣይደለም እንዲህ ኣይነት ሁኔታ እያደረገች ያለችው። የጅቡቲ ጥቅም እንዲጠበቅ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭት ውስጥ መግባት ኣለባቸው ከሚል እሳቤ ነው። ይህ  ኣይነት ኣስተሳሰብ ደግሞ ጠባብነት ነው። ለዘላቄታም የሚያሰራ ኣይደለም።  በዚህ ቀጠና ላሉት ኣገሮችና በተለያዩ ኣገሮች ለሚገኙ ልዩ ጥቅመኞች ፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ሲገቡ ብቻ ነው ተረጋግተን መኖር የምንችለው ወይም ደግሞ ጥቅም የምናገኘው የሚለው ኣስተሳሰብ እርባና የለውም ነው የምንላቸው።

ሁላችንም በዚህ ኣዋሳኝ ያለን ኣገሮች በትብብር እንስራ ነው የምንለው፥ ግብጽ፥ ሳውዲ፥ የባህር ሰላጤ ኣገሮች ሁሉም ኣዋሳኞቻችን   የዚህ ቀጠና የኣሁኑ በጋራ የመስራት እድል የመጭው ትውልድ መልካም እድል ስለሆነ የማንመካከርበት ምክንያት ኣይኖርም። እያንዳንዱ ህዝብ የራሱ ሉዓላዊነትና ነጻነት ኣለው። በመጨረሻ የጋራ ጥቅሞች ስላሉን እኛ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንሰራለን እያልን ባለንበት ወቅት ሌሎችም በዚህ ጉዳይ የማይሳተፉበት ምክንያት የለም።

ክቡር ፐሬዝደንት ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በመላው ኣድማጮች ስም ኣያመሰገንን በመጨረሻም ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልእክት ካለ፥-

በመጨረሻ ለኤርትራ ህዝብ መልካም ኣዲስ ኣመት ይሁንልህ እላለሁ። ኣዲስ ኣመት በመሆኑም ብቻ ሳይሆን ኣሁን የደረስንበት ረዥም ጊዜ የወሰደ ተሞክሮ ለቀጣዩ ጉዞ መሰረት በመሆኑ ወደ ተሻለና የተመቻቸ ኣቅጣጫ እንድንጓዝ ያለፈውን ሁሉን ነገር በጽናት ችለን ተቋቁመን በትእግስት ሰርተን ያለፍነውን በተመሳሳይ ሁኔታ መጭውን ጉዞ ኣንድንገነባበት ብቻችንን ሳንሆን በዚህ ቀጠና ካሉ ህዝቦች ጋር እንዴት ኣድርገን በጋር እንደምንሰራ ምክር ወይም ማሳሰቢያ የሚያስፈልገው ኣይደለም። ከገባንበት ኣዲስ ዓመት ጀምረን ለወደፊት ሳንታክት ለመራመድ ከመልካም ምኞት ጋር ግስጋሴያችን እንዲቀጥል ለመላው ኤርትራውያን መልካሙን እመኝላችኋለሁ።

ከሳተናው የተወሰደ እርዕሰ የተቀየረ

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *