ወ/ሮ ነበቡ ደሳለኝ የሶስት ሴት ልጆች እናት ነች። ጥር 22/2009 ዓ.ም መንገድ ላይ ነበር ድንገት የደህንነት አባላት የያዟት። ሲይዟት ለጥያቄ ‘እንፈልግሻለን፣ ትመለሻለሽ’ ቢሏትም እሷ ግን አላመነቻቸውም። ስለዚህ መኪና ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። ይህ ግን የደህንነት አባላቱን አላስደሰተም። ስለዚህ መኪና ውስጥ አንስተው ወረወሯት።

በዚህ ምክንያትም የመኪናው ወንበር ሆዷ ላይ መቷት ጉዳት እንደደረሰባት ትናገራለች፤ ጀርባዋንም ያማታል። ማዕከላዊ ከገባች በኋላ ሕክምና ለማግኘት የጠየቀች ቢሆንም ለሁለት ወር ያህል ተከልክላ እንደቆየች ለቢቢሲ ተናግራለች።

መጀመሪያ የተወሰደችው ወደ ማዕከላዊ እንደነበር የምትናገረው ነበቡ ስልኳን ከተቀበሏት በኋላ ስልኳ ላይ የሰፈሩ ሰዎችን ማንነት እንድትናገር ምርመራው እንደጀመረ ታስታውሳለች።

ቤተሰቦቿ መታሰሯን ያወቁት መርማሪዎች ቤቷን ለመበርበር በሄዱበት ወቅት እንደሆነ የምትናገረው ነበቡ “ቤተሰቦቼ ጠፍታለች በሚል ፍለጋ ላይ ተሰማርተው ነበር” ብላለች።

በብርበራው ወቅት ቤት ውስጥ የተገኙ ማንኛውም ሰነዶች ብርን ጨምሮ መወሰዳቸውን ታስታውሳለች።

”ማዕከላዊ ሰቆቃ የበዛበት ቦታ ነው” የምትለው ነበቡ በተለይ ደግሞ በምርመራው ሂደት ሴትነቷንና እናትነቷን የሚመለከቱ ዘለፋዎች እንደደረሰባት ትናገራለች።

በምርመራ ወቅት በተለያዩ ንግግሮች አእምሮዋን ለመጉዳት ደጋግመው እንደሞከሩ የምትናገረዋ ነበቡ “ሌባ፣ ቅጥረኛ፣ ሽብርተኛ የምታደራጂ” እያሉ ይሰድቧት ነበር ትናገራለች።

ከዚህ የከፋው ደግሞ “ልጆችሽ በረንዳ ነው የሚወጡት፣ ለወደፊቱ ሴተኛ አዳሪዎች ነው የሚሆኑት፣ ልጆችሽን ቁጭ አድርገን ስለሰራሽው እንነግራቸዋለን፣ ስለዚህ አንቺ ደግሞ እዚሁ ነው የምትበሰብሽው” የሚሉና ሌሎች አፀያፊ ስድቦች ይሰነዘሩባት እንደነበር ታስታውሳለች።

በማዕከላዊ የሥነ-ልቦና ቀውስ ደርሶብኛል የምትለው ነበቡ በምርመራ ወቅት ብቻ ሳይሆን በኑሮም ጉዳት ይደርሳል ትላለች። በእስር ቤት እሷን ለመጠየቅ የሚሄዱ ቤተሰቦቿ ሳይቀሩ ተንገላተው እንደሚገቡም ታስታውሳለች።

“ሲፈልጉ ምግብ፣ ሲፈልጉ ቤተሰቤን የሚፈልጉትን ነገር ብለው ይመልሳሉ” ይህ ሁሉ ሥነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ጉዳት አለው ትላለች ነበቡ። ኦዲዮውን እዚህ ላይ ያድምጡ  

ለሊሴ ባህሩ ክሳቸው ተቋርጡ በፌደራል መንግሥት ከተለቀቁ አምስት ሴት እስረኞች መካከል አንዷናት። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ለሊሴ ሰኔ ስምንት 2008 ዓም ከምትኖርበት ሸጎሌ አካባቢ ሦስት ማንነታቸውን የማታውቃቸው ሰዎች በኃይል አስገድደው ወደ ማዕከላዊ በመኪና እንደተወሰደች ታስታውሳለች።

”አሞኝ ስለነበር ከሐኪም ቤት ወደቤት ተመልሼ ብዙም ሳይቆይ ቤቴ ተከበበ። ከዚህ በፊትም ይመጡ ስለነበር ልጆቼ ፊት እንዳይዙኝ በማለት ከቤት ወጣሁ፤ ከዛ በመኪና ተከተሉኝ። በኋላም በኃይል ወደ መኪና አስገቡኝ።” ብላ የተያዘችበትን ሁኔታ ታስታውሳለች።

ለሊሴ በተያዘችበት ቀን አይኗን ታስራ ከተማ ውስጥ ሲያሽከረክሯት ከቆዩ በኋላ ማታ ላይ ወደ ማዕከላዊ እንደወሰዷትና ለሶስት ቀን ከቤተሰቦቿ ደብቀው እንዳቆይዋት ትናገራለች።

ሕይወት በእስር ቤት

ነበቡ ስለታሰረችበት ስፍራ ስትናገር “የሴቶች ክፍል ያለው ሁለት ነው። አራት በአራት ወይም ሶስት በሁለት ይሆናሉ ክፍሎቹ። 20 እና 30 እስረኛ ተፋፍገን ነው የምንኖረው” ብላለች።

እስር ቤት ሳለች እፈታለሁ ብላ አስባ እንደማታውቅ የምትናገረው ነበቡ “እዚሁ በስብሰሽ ትቀሪያለሽ’ የሚለው ንግግር ስለነበር የሚመጣውን ነገር ሁሉ ለመቀበል ከመወሰን ውጭ ሌላ የማስበው ነገር አልነበረም” ትላለች።

ነበቡ በደህንነቶች በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ለተከታታይ አምስት ወራት በየወሩ ፍርድ ቤት እየሄዱ የ28 ቀን ቀጠሮ ተቀብሎ ከመምጣት ውጪ ጉዳይዋ ታይቶ ፍትህ አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንዳልነበራት ታስታውሳለች።

“እኔ ንፁህ ነኝ ብልም በንፅህናዬ አላምንበትም ነበር” የምትለው ነበቡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቷ ከሌሎች እህቶቼ እንዳየሁት እስከፈለጉት ድረስ በእስር ቤት ስለሚያቆዩ እኔም ለዚህ ራሴን አዘጋጅቼ ነበር ትላለች።

ነበቡ እንደምትለው ለመፈታታቸው ምክንያት በሃገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች የተነሱት ተቃውሞዎች መንግሥት አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነ እንዲረዳ ስላደረገው ነው ትላለች።

ለአራት ወር በማዕከላዊ እንደቆየች የምትናገረው ለሊሴ የማዕከላዊ ቆይታዋ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ትናገራለች።

የእስረኞች ካቴናImage copyrightGETTY IMAGES

እንደ ነበቡ ሁሉ ለሊሴም በማዕከላዊ ስቃይ ተፈፅሞባታል ”የሚፈልጉትን እንዳምን ድብደባ፣ የተለያዩ ማስፈራሪያዎችን ያደርሱብኝ ነበር።”

በኋላም ከኦነግ ገንዘብ በእርሷ በኩል ይደርሰው እንደነበር ድሪብሳ በተባለ ግለሰብ ላይ መስክሪ ተብላ በተደጋጋሚ ተጠይቃ እንቢ በማለቷ ክፉኛ መደብደቧን ትናገራለች።

”ከግራና ከቀኝ በጥፊ ያጣድፉኝ ነበር። ጣቶቼ መካከል ማስመሪያ አስገብተው ይጨምቋቸዋል። በእስክርቢቶ አይኔን ለመውጋት በተደጋጋሚ ሞክረዋል” ትላለች። የማታውቀውን ነገር ወረቀት ላይ በመፃፍ ፈርሚ በማለት እንደተደበደበች እንዲሁ ትናገራለች።

በማዕከላዊ መረገጥ፣ በጥፊ መመታት፣ አስተኝተው ጀርባ ላይ መሄድ፣ ስፖርት ማሰራት እና እርቃን በወንድ መርማሪዎች ፊት እንዲቆሙ በማድረግ የተለያዩ እንግልቶች ይደርስባቸው እንደነበር ታስታውሳለች።

ከአራት ወር የማዕከላዊ ቆይታ በኋላ ወደ ቃሊቲ መዛወሯን የምትናገረው ለሊሴ፤ እዚያ ድብደባ ባይኖርም በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ ሰው ከሌሎች እስረኞች እኩል መብት የላቸውም ትላለች።

እርሷን ጨምሮ ሦስት ሰዎች የቀረበባቸው ምስክርም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ስላልተገኘ፤ ስታወሩ የተቀዳ ነው ተብሎ ከቴሌ በመጣ የድምፅ ቅጂ በአሸባሪነት መከሰሷን ትናገራለች።

የልጆች እናት የሆኑት ነበቡ ደሳለኝ እና ለሊሴ ባህሩ በማዕከላዊ የምርማራ ማዕከልና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ መንግሥት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ክሳቸው ተቋርጦ ከተለቀቁ እስረኞች መካከል በመሆን ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

ወ/ሮ ነበቡ ደሳለኝ የሶስት ሴት ልጆች እናት ነች። ጥር 22/2009 ዓ.ም መንገድ ላይ ነበር ድንገት የደህንነት አባላት የያዟት። ሲይዟት ለጥያቄ ‘እንፈልግሻለን፣ ትመለሻለሽ’ ቢሏትም እሷ ግን አላመነቻቸውም።

ስለዚህ መኪና ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። ይህ ግን የደህንነት አባላቱን አላስደሰተም። ስለዚህ መኪና ውስጥ አንስተው ወረወሯት።

በዚህ ምክንያትም የመኪናው ወንበር ሆዷ ላይ መቷት ጉዳት እንደደረሰባት ትናገራለች፤ ጀርባዋንም ያማታል። ማዕከላዊ ከገባች በኋላ ሕክምና ለማግኘት የጠየቀች ቢሆንም ለሁለት ወር ያህል ተከልክላ እንደቆየች ለቢቢሲ ተናግራለች።

መጀመሪያ የተወሰደችው ወደ ማዕከላዊ እንደነበር የምትናገረው ነበቡ ስልኳን ከተቀበሏት በኋላ ስልኳ ላይ የሰፈሩ ሰዎችን ማንነት እንድትናገር ምርመራው እንደጀመረ ታስታውሳለች።

ቢቢሲ አማርኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *