የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ /ኦ ኤም ኤን/ በቆቦ ግጭት “ኢህአዴግ በሄሊኮፕተር የተደገፈ ጥቃት አላካሄደም, እንደውም ሄሊኮፕተር የሚባል ነገር የለም ” ሲል መንግስትን ቀድሞ ማስተባበያ ሰጠ።”ከቆቦ የደረሰን የድምጽ መረጃ አለን” በሚል ነው ማስተባበያው የተሰጠው። ዜናው አነጋጋሪ ሆኗል። የመንግስትን ሚና መወሰዱና እማኞችን ጠቀሰው የዘገቡትን ቪኦኤ፣ጀርመን ራዲዮ፣ ኢሳትና በርካታ ሚዲያዎችን የሃሰት ዜና እንደሰሩ አድርጎ ማቅረቡ ከዜናው በላይ ቀልብ የሳበ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል። 


“እማኝ” ወይም “መረጃ” የተባሉት ግለሰብ በቆቦ ” የከፋ ሃይል ተጠቅሟል” የተባለው የአጋዚ ሰራዊት ከትግራይ መነሳቱን አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ጦሩየመጣበትን ተሽከርካሪ እንኳን ወደ ከተማ ይዞ አለመግባቱን መክረዋል። ጦሩ የወሰደውን እርምጃ ዓይነትና መጠን አላብራሩም።
በጥያቄና መልስ ወይም ሌሎች ሚዲያዎች “እማኝ” ያሉዋቸውን በርካታ የቆቦ ነዋሪዎች ምስክርነትን ጠቅሶ በግጭቱ ሰራዊቱ ሄሊኮፕተር ስለመጠቀሙ መዘገባቸውን እንደ መከራከሪያ ያላቀረበው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ዜና፣ ቪኦኤ፣የጀርመን ድምጽ፣ኢሳት በድምጽ የተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎችን በማነጋገር ያቀናበሩትን ዜና ለምን ማስተባበል እንደፈለገ አላብራራም። ፍንጭም አልሰጠም። እማኙ ንግግራቸውን ሲጨረሱ ዜናው ” ወልቂጤ ህዝባዊ አመጹን ተቀላቀለች” ሲል ነው ወደ ቀጣዩ ጉዳይ የገባው።

OMN: ዕለታዊ ዜና (LIVE) Jan 25, 2018

OMN: ዕለታዊ ዜና (LIVE) Jan 25, 2018

Публикувахте от Oromia Media Network в Четвъртък, 25 януари 2018 г.

ዜናውን የሰሙና ለዛጎል አስተያየት የሰጡ ” ሁሉም ሚዲያዎች የሃሰት ዜና አቅርበው ከሆነ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ትክክለኛ መረጃ በማቀበሉ ሊመሰገን ይገባል” ብለዋል። አክለውም ” ሚዲያው በዜናው ያናገራቸው ሰው ግጭቱን ከተራ ዝርፊያ ጋር በማዛመድ ማቅረባቸው ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል ነው”
አስተያየት ሰጪዎቹ ቪኦኤ፣የጀርመን ድምጽ፣ኢሳት ” የሃሰት ዜና አቅርበዋል” በሚል በተዛዋሪ በመዘለፋቸው ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከሁሉም በላይ ግን የጉዳዩ ባለቤት መንግስ ምንም ባላለበት፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ዜናውን ለማስተባበል መክነፉ በራሱ ከጀርባው ጥያቄ እንደሚያስነሳ ያምናሉ።

ቪኦኤ — ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተል እንደነበር የገለፀለን ወጣት እንደተናገረው፤ “እስካሁን እነርሱ ሰባት ገድለዋል። አንድ መከላከያም ሞቷል። እስካሁን በሄሊኮፕተር ነው ሲያሸብሩን የዋሉት።” በማለት ከተማው ውስጥ የመንግሥት ታጣቂ ሰራዊት መስፈሩን ይናገራል።

የንብረት ውድመቱ ላይ አተኩረው መረጃ የሰጡት ሰው ” ሄሊኮፕተር የሚባል ነገር የለም” እንዳሉት ሁሉ የጀርመን ድምጽ ያቀረባቸው የቆቦ ከተማ ነዋሪ ” ከእኛ የተወለዱ አይመስሉም” ሲሉ ሰራዊቱ የወሰደውንና እየወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ የተናገሩት ነገር የለም።

የጀርመን ሬዲዮ – “ዛሬ 3ኛ ቀኑ ነው:: ትላንት 8 ስዓት አካባቢ ነው ህዝቡ ሆ ብሎ የወጣው።የስርዓቱ ደጋፊዎችን ባለቡቲኮች፣ ባለህንጻዎች፣ ባለቦቴ መኪናዎች፣ ባለማደያዎች ነበሩ:: የእነርሱን አቃጥለዋል:: [ዛሬ] ማዘጋጃ ቤቱን፣ ፍርድ ቤቱንና ገቢዎች ቢሮን በማቃጠል ተጀመረ:። እስካሁን 7 ልጆች ሞተዋል። አጋዚው ህፃን ሲመታ አርሶ አደሮች አይተውት ገድለውታል። ሌሎቹ በተቃውሞ ወቅት ነው:።”

በተቃዉሞ አመፁ የታሰሩ 13 ያህል ወጣቶች በሀገር ሽማግሌወችና በሀይማኖት አባቶች ሽምግልና ተፈተዉ በአካባቢዉ አንፃራዊ መረጋጋት ታይቶ እንደነበር የገለፁት ነዋሪዉ መንግስትን ይደግፋሉ ያሉትንና ወጣቶቹን ” ጠቁመዉ አሳስረዋል” ያላቸዉን የትግራይ ተወላጆች ንብረት ማዉደም መቀጠሉ ግን ዉጥረቱን እንዳባባሰዉ ገልፀዋል።እናም በአሁኑ ስዓት በከተማዋ ከተኩስ ድምፅ በስተቀር ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ነዉ ያሉት።
“ጠዋት ከ11 ሰዓት ጀምሮ የሂሊኮፕተር ድምጾች ነበሩ፣ መከላከያ የሚያወርዱ።ጥይትም እየተኮሱ ነበር።በጣም የተኩስ ድምፅ አለ።ከተማው የጦር አውድማ መስሏል።ስራ የሚባል የለም። ሙሉ ለሙሉ ከተማዋ ውስጥ እንቅስቃሴ የለም።”

” አሁንም ከበውናል፤ ምን እንደሚያደርጉን አናውቅም” በሚል ሳግ ባነቀው ድምጽ ሲናገሩ የተደመጡት አስተያየት ሰጪን ጨምሮ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ እማኝ በቀር ሄሊኮፕተር ስለመኖሩ አስረድተዋል። እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ መሳሪያ ባልያዘ ህዝብ ላይ እንዲህ ያለው ከበባና ወረራ ዜጎች በራሳቸው ዜጋ ላይ ማካሄዳቸው በዚህ ዘመንና ከአገሪቱ የቀድሞ የአብሮነት ታሪክ ጋር ሲነጻጸር ለማመን የሚያዳግት ነው።
ለጥንቃቄ በሚል በአብዛኛው የኦሮሚያን ዜናዎች ሲያትት ድምጽ የማይጠቀመውና ” ምንጮቻችን” በሚል የሚዘግበው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ለዚህ ዜና ድምጽ መጠቀሙም ግራ የሚያጋባ እንደሆነ የጠቆሙም አሉ። ሚዲያው እውነት ካለው በዚህ ዜና ገፍቶበት እውነተኛነቱን ሊያረጋግጥ እንደሚገባና እንደ ሚዲያ ከማስተባበያው በስተጀርባ ያለውን ጉዳይ ሊያጠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በሕዝብ ድጋፍና በቦርድ የሚተዳደር ሚዲያ እንደመሆኑ የሚመለክታቸው አካላትም ” ሚዲያው አግባብነት ያለው ተጨባጭ ዜና ካሰራጨ በማድነቅ፣ ካልሆነም ማስተካከያ በማድረግ የቆቦን ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ ሊያስገድዱ ይገባል” ብለዋል።

በተለይም አንድ የሰብአዊ መብት ተጓደለ፣ ፍትህ ተዛባ፣ የዴሞክራሲ ያለህ …. በሚል ለሰፊ ሕዝብ ድምጽ ለመሆን ተነሳሁ የሚል ሚዲያ፣ ከድርጅትም ሆነ ከግለሰቦች ጋር ያለውን ልዩነትና በሁሉም ወገን በሚስተዋለው ውሉ የማይታወቅ አለመግባባት ተነስቶ ይህንን ካደረገ፣ አሁንም የቆቦን ህዝብ ሊያስብ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ሌሎችም ሚዲያዎች ተመሳሳይ የመቧደንና መረጃን ወደ ግልና ድርጅታዊ ፍላጎት የማንጋደድ ባህሪ እንደሚታይባቸው አብዛኞች ይስማማሉ። በዚሁ ችግር የተነሳም ሚዲያዎች ከጀርባቸው ስም እንዳላቸውና ሁሉንም ወገኖች እኩል ሳያስተናግዱ ” መዋጮ አምጡ” ማለታቸውን የሚቃወሙ ጥቂት አይደሉም። ያም ሆኖ ግን ባላቸው ውስን አቅምና ሎጅስቲክ ለሕዝብ መረጃ ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት የሚመሰገን እንደሆነ መሳማማት አለ። በዚሁ መነጽር የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክንም የሚመለከቱት ክፍሎች የሚከተለውን ይላሉ።
“መከላከያ ጣልቃ መግባቱን፣ መንገድ በመዘጋቱና በፍጥነት ተጨማሪ ሃይል ለማቅረብ በሚል ሄሊኮፕተር ጥቅም ላይ ውሏል” ሲሉ የስርዓቱ ደጋፊ የሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ ተከራክረዋል። እንዲህ ያለው አሰራርም የተለመደ መሆኑንን አመልክተዋል” እናም “የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ምን እያለ ነው?” 
በሁሉም የዜና ምንጮች እንደተረጋገጠው ንብረት ወድሟል። የግለሰቦች መኖሪያና ድርጅቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የንግድ ቤቶች፣ የመንግስት መዋቅር ማስፈጸሚያ ተቋማት ነደዋል። የንብረት ቃጠሎው ብሄርን የለየ ሲሆን አሁን ግጭቱ ጋብ ማለቱን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አስታውቀዋል።
በወልድያ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ ለሶስት ቀናት በተካሄደው ተቃውሞ የትግራይ ተወላጆች መሳተፋቸውን፣ ይህንን የሚፈጽሙት እኛን አይወክሉም” ማለታቸውን የቆቦ ነዋሪዎች ሲመሰከሩ፣ ለኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ መረጃ ያቀበሉት ግን ይህንን አላሉም። ሚዲያውም አልጠየቀም። 
ግጭቱ እንዴት ተነሳ
ያነጋገርናቸው ሌላኛው የቆቦ ነዋሪ የግጭቱን መነሻ ሲያስረዱ፤ ”በወልዲያ ከተማ የተፈጸመው ግድያ ቆቦ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሮ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ ንብረታችን ሊዘረፍ ወይም ሊወድምብን ይችላል ብለው የሰጉ ሰዎች ንግድ ቤቶቻቸውን በመዝጋት ንብረት ለማሸሽ ሞክረው ነበር። አንዳንድ ወጣቶችም ‘እዚህ ምንም ሳይፈጠር እንዴት ይህን ታደርጋላችሁ’ ብለው መጠየቃቸውን ተከትሎ ግርግር ተፈጠረ ከዚያም ወደ ግጭት አመራ” ሲሉ ያስረዳሉ። ቢቢሲ

እንደ አካባቢዉ ነዋሪወች በቆቦ ከተማ ሰኞ እለት የተቀሰቀሰዉ ይህ ህዝባዊ ተቃዉሞ ከጅምሩ ሰላማዊና ሰሞኑን በወልደያ ከተማ የተፈፀመዉን ግድያ የሚያወግዝ ብቻ ነበር ።ያም ሆኖ ግን የፀጥታ ሀይሎች የተቃዉሞዉን ሰልፍ ለመበተን ጥይት መተኮሳቸዉንና ቆይቶም በሰልፉ የተሳተፉ ወጣቶችን ማሰር መጀመራቸዉን ይናገራሉ። በዚሁ ሳቢያ በቆቦ ከተማ ነዋሪና በአካባቢዉ ገጠር ቀበሌዎችም ጭምር ተቃዉሞዉ እየጠነከረ መጥቶ በዛሬዉ እለት አንድ የፀጥታ ሀይልን ጨምሮ የ 7 ሰወች ህይወት መጥፋቱንና በርካታ ንብረት መዉደሙን ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢዉ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግጭቱ የተቀሰቀሰው፤ “በወልዲያ ከተማ ንጹኃንን የገደሉ የመንግሥት ታጣቂዎች ለፍርድ ይቅረቡ” እንዲሁም “በቆቦ ከተማ የታሰሩ ወጣቶች ይፈቱ” የሚሉ መፈክሮችን የሚያሰሙ የከተማው ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣታቸው ነው ብለውናል።

ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተል እንደነበር የገለፀለን ወጣት እንደተናገረው፤ “እስካሁን እነርሱ ሰባት ገድለዋል። አንድ መከላከያም ሞቷል። እስካሁን በሄሊኮፕተር ነው ሲያሸብሩን የዋሉት።” በማለት ከተማው ውስጥ የመንግሥት ታጣቂ ሰራዊት መስፈሩን ይናገራል።

አያይዞም የከተማው ሕዝብ ከወልድያው ግድያ በተጨማሪ በከተማው ከኮማንድ ፖስቱ ጊዜ ጀምሮ የታሰሩ ወጣቶችን ጉዳይ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማቅናቱን ይናገራል። “እነሱ ይፈቱልኝ ብሎ ጥያቄ አቀረበ። ይባስ ብለው የከተማውን ሕዝብ ይደበድቡ ነበር። በዚህ ግዜ ሕዝቡ በነቂስ ወጣ የታሰሩትን ካስፈታ በኋላ መረጃ እየሰጡ ሲያስደበድቡን ነበር ያሉትን ሰዎች ቤት ንብረትና የመንግሥት ተቋማትን ማቃተል ጀመረ” ሲል የቆቦ ከተማውን ውሎ ይናገራል። ቪኦኤ

ዝግጅት ክፍሉ


የዘገገብነው የሄሊኮፕተር መኖር አለመኖር አሳስቦን ሳይሆን ከአንባቢ በተላከልን አጭር ጥያቄ መሰረት ነው። ጥያቄውም ” ማንን እንመን” በሚል መነሻ ሲሆን እንዲህ ያለው አካሄድ ጥፋት የሰራው ክፍል እኛን ጨምሮ እንድንማርበትና ለወደፊቱ ጥንቃቄ እንድንወስድ በማሰብ ነው። የትግል መስመርና የሕዝብ ጉዳይ ልዩ በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ” ወኪልህ ነን” ሲባል እንጂ ” ወኪሎቼ” ለማለት ታድሎ ስለማያውቅ፣ አሁንም በዚህ ዘመን በተመሳሳይ መንገድ ስለምንገኝ፣ ሕዝብንና የትግል መስመርን ለሚሞተው ሕዝብ ሲባል ማቆም ቢቻል በሚል ምኞት ነው። ሪፖርቱ ክፍተት ካለውና እርማት የሚያሻው ከሆነ፣ ተጨማሪ አስተያየትም ካለ ክፍት ነው

 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *