“…እስክንድር ዕድለኛ አይመስለኝም። የመረጠው መንገድ ለእርሱም ሆነ ለቤተሰቦቹ አደገኛ ነው፤ እነዚህ ሁሉ እስሮች ወቅት እየጠበቁ እንደሚመጡበት ጠንቅቆ ያውቃል …. በእኔ እምነት እስክንድር ያላወቀውና የተታለለበት ጊዜ የሚመስለኝ፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ ተከብሯል ሲባል፤ የተማረባትንና በምቾት የኖረባትን አሜሪካን ትቶ ወደ ሚወዳት አገሩ ተመልሶ ኢትኦጲስጋዜጣን ሲጀምር  ነበር  ” ባለቤቱ ሰርካለም ከተናገረችው የተወሰደ

Eskinder-Nega-and-family

ምን እንደምል አላውቅም ተዘበራርቆብኛል። ስልክና መልዕክት በብዛት ይላካል። መመለስ አልቻልኩም። ብዥታ ውስጥ ነኝ። እኔ እራሴን አይደለሁም። መልዕት ልከው ላልመለስኩ ይቅርታ። ስልክ የመመለስ አቅም አልነበረኝም። 2004 መስከረም ረቡዕ ከቀኑ 9-30 ናፍቆትን ከትምህርት ቤት ሲያመጣ ነው የታሰረው። ናፍቆት አልሰማም ዛሬ የአስራ አንድ ዓመት ከአራት ወር ጎረምሳ ነው ። …. አሁን መናገር አልችልም። እስክንድርን ድምጹን ሰምቼ ብናገር ደስ ይለኛል። ለልጃችን ትልቅ ነገር ነው። በአጠቃላይ ግን በአመለካከትና በአምነታቸው የታሰሩ የህሊና እስረኞች በሙሉ ተፈተው ደስታችን ሙሉ ቢሆን … ሰርካለም ለጀርመን ድምጽ ይህንን አለች።

ሰርካለም ፋሲል የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ነች። ምርጫ 97ትን ተከትሎ ወደ ወህኒ ቤት ወርዳለች ። 18 ወራት ግድም በእስር አሳልፋለች። እዛው ወህኒ ቤት ሆና ልጅ አግኝታለች። ሕፃኑ ሲወለድ ክብደቱ አነስተኛ በመሆኑ የፖሊስ ሆስፒታል ወሰነ። ይሁን እንጂ የእስር ቤት ኃላፊዎች ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። ናፍቆት እስክንድር ማሞቂያ ውስጥ እንዳይገባ ተደረገ። ታጣቂና ካድሬ ከሃኪም በላይ ሆኖ ምንም በማያውቅ እርጥብ አራስ ላይ ይህንን መወሰናቸውን እናት በአንድ ወቅት ተናግራለች። ያም ሆኖ ናፍቆት አደገ።
ሰኔ 12 ወህኒ የተወለደው ናፍቆት ስድስት ዓመት ሳይሞላው መስከረም 3 ቀን 2004 አባቱ እስክንድር ነጋ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ዋለ። ናፍቆት እያያ እና እያለቀሰ ታጣቂዎቹ እስክንድርን ወሰዱት። እስክንድር ለስምንተኛ ግዜ ወህኒ ወረደ። ይህ ጨቅላ ህጻን አባቱ የት እንዳለ ይጠይቃል። ይወተውታል። እናቱ ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ትመልሳለች ሙሉውን የሰርካለምን ቃል እዚህ ላይ እዚህ ላይ ያንብቡ ሰርካለም ስለ እስክንድር ነጋ

ሰባት ጊዜ ክስ ክስ ተመስርቶበት መረጃ ያልቀረበበት እስክንድር ለስምንተኛ ጊዜ እንዲታሰር ከተደረገ በሁዋላ አስራ ስምንት ዓመት ተፈርዶበታል። አቶ ግርማ ሰይፉ ለጀርመን ድምጽ ሲናገሩ ” እስክንድር እንኳን አስራ ስምንት ዓመት ሊፈረድበት፣ ምክር እንኳን የማያስፈልገው ጥፋት አልሰራም ” ሲሉ የመፈታቱ ዜና ይፋ በሆነ ማግስት ተናግረዋል።

አንድ አስተያየት ሰጪ ፟ ቀሪ ዘመንህን አምላክ ይካስህ። ልጅህ ርቦሃል። አንተም እሱን ተርበሃል። የአገራችን ፖለቲካና የሚወሰደው እርምጃ እዚህ ድረስ የከፋ ነው። ስቃይህ ያማል። የልጅህ በቃላት የማይገለጽ ሰቀቀን እንደ እናት ልቤን አድምቶታል። ምን ለበል? ደስታዬ ሰፊ ነው።” ብሏል። 

የእስክንድር ልጅ ስለ ወህኒ ቤት ምን ግንዛቤ ሊኖረው ይችላል? እስር ቤት ተወልዶ፣ አባቱ እንደ አባት ሳያሳድገው ቆየ። ይህ ታሪክ የሚረሳና የሚፋቅ አይሆንም። አገራችን በተለያዩ ወቅቶች ሊረሱ የማይችሉ ጥፋቶች የተከናውኑባት ነች። አንድ ምሁር እንዳሉት የሚረሳውንና የሚጥቅመንን፣ የማይረሳውንና የማይጠቅመንን ለይተን ካልሄድን ከባድ ነው። እኚሁ በኢ ኤን ኤን ቲቪ ቀርበው የተናገሩት ምሁር ይህንን ያሉት ወደው አይደለም።

ሊረሱና ሊታተምባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል እያንጠለጠልን ኪሳራ ደርሶብናል። አዲሱ ትውልድ በማያውቀው ጉዳይ ዋጋ ይከፍላል። ለመጪውም ትውልድ ተመሳሳይ ችግር ይተላለፋል። እንደ እስክንድር ነጋ ልጅ ሁሉ በርካታ የአዲሱ ትውልድ አባላት ተጎድተዋል። ይህንን ማስተካከል ግድ ነው። 

አንዷለም አራጌም የአመለካከቱና የፖለቲካ እምነቱ ሰለባ ነው። እሱም ቤተሰቦች አሉት። ልጆች አሉት። ዘመኑ ሁሉም ነገር አየር ላይ የሚውልበት ነው። የሚባለውን ሁሉ ልጆች፣ ትውልዶች፣ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ ደጋፊዎች ያዩታል። ይመዘግቡታል። ልክ ሌሎች ሲነገራቸው እንደነበር ሁሉ ነጋሪም አላቸው። በመጥፎ ሪኮርድ የት ዘመን ድረስ እንዘልቅ ይሆን? ከታሰሩ ተፈቱ የማያልቅ አዙሪት ይልቅ መሰረታዊ ለውጥ አድርጎ የአገሪቱን ጉዳይ በእርቅ መደምደሙ ለሁሉም ወገኖች እንደሚበጅ ገለልተኞች እየወተወቱ ነው።

ዶክተር በረራ ጉዲና መፈታታቸውን ተከቶል የኦህዴድ ካድሪዎች፣ ፖሊሶች፣ ታጣቂዎች ሳይቀሩ እንደ ጎርፍ ወጥተው ነው አቀባበል ያደረጉት። በአንድ አምቦ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ስፍራ። በሁሉም ክልል። እናም መረራ ሲታሰሩ ያ ሁሉ ህዝብ ነበር የታሰረው። ያ ሁሉ ህዝብ ነበር የተቀየመው። ከዚ አንጻር ሲታይ እስር ፖለቲካዊ ኪሳራ እንጂ ጥቅም አይደለም። ዛሬ አንድም የኢህአዴግ ካድሬ የመረራ አይነት አቀባበልና ክብር ሊኖረው አይችልም። ይህንን ማደስ አዋቂነት ነው። አቶ ሃይለማሪያም እንዳሉት ” ዛሬ ህዝብ ፊት ቆም የሚናገር አመራር የለንም” በዚህ መነሻ ነው እርቅ አስፈላጊነቱ የሚጎላው። ምክንያቱም አስሮ ከመልቀቅ በላይ የሆኑ በርካታ ጉድሳዮች ስላሉ።

አብዛኞች የኢትዮጵያ ጉዳይ ብሄራዊ እርቅ እንደሚያሻው ያምናሉ። ራሳቸው የኢህአዴግ አባላትም ይህንኑ ያምናሉ። እናም ሁሉ አቀፍ የሆነ እርቅ አውርዶ ፣ ሁሉን የሚያሳትፍ ስርዓት እንዲፈጠር በማድረግ ምርጫውን ለህዝብ መተው ምን ያስቸግራል? የስልጣን ጥማት ካልሆነ በስተቀር። 

የእስር አዙሪት፣ ታሰረ፣ ተፈታ ጣጣ ያከትም ዘንድ ይህንን ማሪና ይቅር ባይ ህዝብ ወደ ምህረትና ይቅርታ ደጆች የሚያመሩ ጥርጊያዎች ቢከፈቱ ለአገሪቱ ብሎም ይህንን ላደረጉ ሁሉ ታላቅ ታሪክ በሆነ ነበር። በአንደኛው በር እስረኛ ይወታል፣ በሌላኛው በር ይገባል። ልክ እንደ ዩኒቨርስቲ እስር ቤት የኖሩ ሲወጢ፣ አዳዲስ ይገባሉ። እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል? በየችሎቱስ ግፍና የሃዘን ታሪክ ሪፖርት እየሰማን እንኖራለን? እናም መፍትሄው ” እኔ ካልገዛሁ” ከሚል ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ መውጣትና የዘመኑ ሰው መሆን ግድ ነው። አለያ ህዝብ ያስገድዳል። ያኔ ለአገርም ፣ ለህዝብም፣ ለግለሰቦችም፣ ለሁሉም ኪሳራ ነው። አሁን ያለንበት ወቅት ይህንን አመላካች ነው። እስርና ሃይል ብዙም የሚያስኬዱ አይመስልም። 

አቶ ጌታቸው ረዳ አቶ ፋኑኤል በሚያዘጋጁት የውይይት ፐሮግራም ላይ እንዳሉት አሁን ባለው አዙሪት ተጠቃሚ የለም። አንዱ ጋር ያለው ችግር ሌላውን ከቶውንም ሰላም አያደርገውም። ከላይ እስክንድርና አንዷለም ለምሳሌ አነሳን እንጂ ጉዳዩ የሁሉም ነው።

 

Related stories   Ethiopia’s transition misrepresented. Reply to Obang Metho

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *