የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ስራ ለመልቀቅ የወሰኑት ውሳኔ ከአንድ ሀላፊነት ከሚሰማው አመራር የሚጠበቅ መሆኑን የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር ገለፁ።

ሀላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ በሀገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሉትን ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገርን እየመራ ያለው ኢህአዴግ ጥልቅ ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

አራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጣቸውን እንዲፈትሹ አቅጣጫ መቀመጡን እና በዚህም መሰረት ጥልቅ ግምገማቸውን አንዳንዶቹ አካሂደው መጨረሳቸውን ሌሎች ደግሞ እንዳልጨረሱም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት፣ ህይወት እንዳይጠፋ ህዝብ እንዳይፈናቀል እና ንብረት እንዳይወድም ለማድረግ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ዶክተር ነገሪ አንስተዋል።

እነዚህ ችግሮች በተወሰነ ደረጃ እንዳሉ ይታወቃል ያሉት ሀላፊ ሚኒስትሩ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሲወስኑ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለመሆን ወስነው በራሳቸው ያደረጉት ነው ብለዋል።

መሪው ፓርቲ ኢህአዴግ በአሰራሩ መሰረትም የግንባሩ ምክር ቤት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስብሰባውን ጠርቶ ሊቀመንበር እንደሚመርጥ የተናገሩት ዶክተር ነገሪ፥ በሀገሪቱ ህገመንግስት መሰረትም ፓርላማው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሾም ይሆናል ነው ያሉት።

አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተሾመ የሚቀጥለው ካቢኔ ጉዳይም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚወሰን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ መልቀቂያ አስገቡ ማለት ስራ አቆሙ ማለት አይደለም ያሉት ዶክተር ነገሪ ፥ አጋጣሚው በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ በመሆኑ ሰዎች ግር ሊላቸው እንደሚችል አስታውቀዋል።

ይህ የዴሞክራሲ ሂደት እንደሆነና የስራ መልቀቂያ ቢያስገቡም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሚሾም ድረስ ሙሉ ስራቸውን እንደሚቀጥሉና አሁንም ስራ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *