የአማራ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ምድብ ችሎት በኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መዝገብ ላይ የካቲት 22/2010 ዓም ብይን ለመስጠት የመጨረሻ ቀጠሮ ይዟል። ፍርድ ቤቱ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መዝገብ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ መርምሮ “ይከላከሉ፣ አይከላከሉ” የሚለውን ለመበየን ለዛሬ የካቲት 9/2010 ዓም ቀጠሮ ይዞ የነበር ቢሆንም “ከጉዳዩ ስፋት አንፃር እያንዳንዱ ዳኛ ማየት ስላለበት” በሚል ለየካቲት 22/2010 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ መዝገቡን እንዳየው የገለፀ ሲሆን ተለዋጭ ቀጠሮው ብይኑን ለማጠቃለል ነው ብሏል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግን ወክለው የተከራከሩት አንተነህ አያሌው በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በርካታ መዝገቦች ስላለባቸው ለመጋቢት አጋማሽ እንዲቀጠርላቸው ቢያመለክቱም ፍርድ ቤቱ “ቀጠሮ በተራዘመ ቁጥር ሌላ ጊዜ ማባከን ነው።” ሲል ረዥም ቀጠሮ እንደማይሰጥ ገልፆአል።

27858148_1970516602977329_3534019090153178644_n

የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጠበቃ አቶ አለለኝ ምህረቱ “ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ብይን የሚሰጠው በመዝገቡ ላይ ነው? ወይንስ በመዝገቡ ላይ ባቀረብናቸው መቃወሚያዎች ነው?” ብለው ለፍርድ ቤቱ ላቀረቡት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ “በመዝገቡ ላይ ግራ ቀኛችሁ የምትሰጡት አስተያየት አብቅቶልታል። የብይኑ አንድ አካል ነው። በመዝገቡ ላይ ብይን እንሰጣለን” ብሏል።

ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳልተያዙ በመግለፅ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተያዙ የተባሉበት መዝገብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ እንዲልክ የአማራ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያዝዝም መዝገቡ ሳይላክ ቀርቷል። የመዝገብ ቁጥሩም የሌላ ሰውና ከተዘጋ ቆይቷል በሚል የሀሰት ሰነድ ቀርቦብኛል ብለው አመልክተዋል።

በተመሳሳይ የደሕንነት መስርያ ቤቱ ክሱ ላይ የኮ/ል ደመቀ የስልክ ንግግር ነው ተብሎ በፅሑፍ የተያያዘው ማስረጃ የድምፅ ማስረጃን እንዲልክ ቢታዘዝም አላቀረበም። እነዚህ ማስረጃዎች ለኮ/ል ደመቀ መዝገብ ላይ በሚሰጠው ብይን ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሎ ተገምቷል።

(ፎቶዎቹ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ከፍርድ ቤት ሲመለሱ የማረሚያ ቤት ፖሊስ በሁለት መኪኖች ላይ በተጠመደ መትረየስ አጅቧቸው የሚያሳይ ነው)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *