ሰሞኑን “ቄሮ ቃር እንዳይሆን” በሚል ርዕስ አቶ ሽሽጉ በሚባሉ ግለሰብ የተጻፈ ማስታወሻ በአይጋ ፎረም ላይ ታትሞ በጥሞና አንብቤ ነበር።

አቶ ሽሽጉን በዚች ቀውጢ ሰዓት እንደዚህ ዓይነት ጽሁፍ ለማውጣት የገፋፋቸው አንዳች  ዓይነት  ምክንያት  ቢኖር  ነው ብዬ ስለገመትሁ፣ የግል አስተያየታቸውን የመሰንዘር ህገ መንግሥታዊ መብታቸው እንደተጠበቀ  ሆኖ፣  ከቅንነት ተነስተው የተሰማቸውን ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳወቅ ካላቸው በጎ ግምት ተነስተው ነው እንደዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የደረሱት  ብዬ  ለማለፍ  ሞከሬ  ነበር።  ግን  ደግሞ፣  በኔ ግምት ድምዳሜያቸው የተሳሳተ ስለሆነ፣ ይህንን የተሳሳተ ግምታቸውን በቅንነት ላይ የተመሰረተ ዕርምት ለማድረግና ለሌሎችም ጉዳዩን በደንብ ላልተረዱ  ዜጎች  ዕውኔታውን በትክክል ለማስቀመጥ  ወሰንሁ።  ይህ  እንግዲህ  አቶ  ሽሽጉ ስለቄሮ የጻፉትና አንዳች ዓይነት ድምዳሜ ላይ የደረሱት ስለዚህ ወጣት ትውልድ የጠለቀ ዕውቀት ስላልነበራቸው እንጂ የተደበቀ አጄንዳ ስላላቸው አይደለም ብዬ በማመን ነው። አለማወቅ በራሱ ጥፋት ባይሆንም፣ በደንብ ስለማያውቁት ነገር መጻፍና አሉታዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ ግን ከጥፋት በላይ ነው!

እንደማየው ከሆነ አቶ ሽሽጉ ስለ ኦሮሞ ህዝብ የቅድመ-ፊውዳሊዝምን የአስተዳደር ታሪክ ሳያውቁ ወይም ያንን የአስተዳደር ታሪክ ይዘት በተጣመመ መልኩ የተረዱት ይመስለኛል። ወይም ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ የአስተዳደር ታሪክና ይዘት በደንብ ያልገባው ሰው እሳቸውንም አሳስቷቸው  ይሆን እንደሁ እንጂ የኦሮሞ ህዝብን የገዳ  ሥርዓት  መግቢያ  እንኳ ያነበበ ሰው ስለ ቄሮ እንደዚህ ዓይነት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ይደርሳል ብዬ ለመገመት ያዳግተኛል። ከአቶ ሽሽጉ ጋር በአካል ተገናኝተን ስለ ገዳ ሥርዓትና በተለይም ስለ ቄሮ ጠለቅ ያለ ትምህርት ብሰጣቸው ደስ ባለኝ ነበር። ለጊዜው ግን ያ ዕውን ስለማይሆን፣ እዚሁ “በአይጋ ፎረም” በኩል ትምህርታዊ መልዕክቴን ላስተላልፍ። ኦሮሞ በመሆኔ ደግሞ  ከአቶ  ሽሽጉ የበለጠ የማህበረሰቤን ታሪክና አስተዳደራዊ ቅርጽ ይዘት ስለማውቅ፣ ስለቄሮ ማንነት አፌን ሞልቼ ለመናገር እችላለሁ ባይ ነኝ።

‹‹ ቄሮ ማለት ወጣት ማለት ነው” ለማ መገርሳ- ” አልሸባብ ማለትም ወጣት ማለት ነው” እኔ በሚል ርዕስ ሽሽጉ የጻፉትን ጽሁፍ እዚህ ላይ ያንብቡ ቄሮ ቃር እንዳይሆነ ጸሃፊው ” አልሸባብ በአንድ ወቅት ሶማሊያን የማስተዳደር ስልጣን በሃይል ይዞ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት የወጣቶች ክንፍ ነበር።ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ራስዋ ሶማሊያን በመተባበር ሊያጠፉት ቢሞክሩም እንደ እባብ አፈር ልሶ ልሶ እየተነሳ ሊነቅሉት የማይችል ሆኖ ዛሬ የወገኖቹን  …” ሲሉ ይጀምራሉ። ሃሳባቸው ቄሮን ወደ አልሸባብ ማጠጋጋት ሲሆን …..

ኦሮሞዎች ለብዙ ምዕተ ዓመታት ይተዳደሩበት በነበረው የገዳ ሥርዓት መሰረት ህብረተሰቡ በዕድሜ ክልል የተከፋፈለና እያንዳንዱ ግለሰብ የትውልዱን የሥራ ድርሻና ማህበረሰባዊ ግዴታ የሚወጣው በየስምንት ዓመት በሚደረገው የትውልድ ሽግሽግ የጊዜ ገደብ ነው። ከተወሰነው የስምንት ዓመት “የግዴታ የዕድሜ ገደብ” ውጭ የአንድን ግለሰብ ወይም ቡድን የሥራ ድርሻና  ግዴታ ማራዘም ስለማይቻል አስተዳደራዊ ሥልጣንን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስረከብ ምንም ዓይነት ችግር አይከሰትም። ይህም በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ አስተዳደራዊ ቀውስ ፈጽሞ አይታይም ነበር።

በዚህ የዕድሜ አንጓ ውስጥ ማለትም ከሃያ አራት እስከ ሰላሳ ሁለት ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች (በኦሮምኛ ቄሮ በመባል የሚታወቁት) ያለምንም ማሳሰቢያ ማህበረሰባዊ ግዴታቸውን የመወጣት ኃላፊነትን ይረከባሉ። በሰው ልጅ የዕድሜ ዘመን ደግሞ በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ግለሰቦች ተክለ ሰውነት የዳበረና የጠነከረ በመሆኑ ማህበረሰቡን ከውጭ ወራሪ ለመከላከልና ትላልቅ አውሬዎችንም ሳይቀር አድኖ የመግደል “የጀግንነት” ባህርይ በግልጽ የሚታይባቸው በመሆኑ ሁሌም የማህበረሰቡ ጋሻና መከታ ሆነው ያገለግላሉ። ማህበረሰቡም በጣም ስለሚታማመንባቸው ከቄሮ የዕድሜ ክልል ውጭ የሆኑ ማለትም ለጋ ወጣቶችና ጠና ያሉ የማህበረሰቡ አባላት ቄሮን ተክተውም ሆነ አብረውም ለውጊያ አይሰለፉም። ለቄሮ ዕድሜ ያልደረሱ ከቄሮዎች የውጊያና የትግል ሥልት ይለምዳሉ፣  ጠና  ያሉት  ደግሞ  ያለፉበትን  ጎዳናና  ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም የሕይወት መሰናክሎችን እንዴት እንዳለፉ ለቄሮዎች ያስረዷቸዋል። ላንድ ህብረተሰብ ጤነኛ ዕድገት በጣም ጠቃሚ የሆኑትን ሁለት ነገሮች ማለትም የጭንቅላት (ልምድ) እና የጡንቻ ውህደት የሚባለው መሆ ኑ ነው። ስለዚህ ነው እንግዲህ ቄሮ በተለምዶ ከምናውቃቸው የፖሊቲካ ድርጅት የወጣት ኮሙኒስቶች ወይም ካድሬዎች ዓይነት አወቃቀርና አደረጃጀት የሚለየው። ቄሮ ከታላላቆቹ እንዳስፈላጊነቱ ምክር ይቀበል እንደሁ እንጂ ለመደራጀትም ሆነ መፈጸም ስላለባቸው ህብረተሰባዊ ግዴታዎች ከማንም ግለሰብ ወይም ቡድን መመርያ አያስፈልገውም። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አቶ ሽሽጉ “ቄሮ ከኦነግ በተሰጠው መመርያ” መሰረት የሚንቀሳቀስና “ሌሎችን ብሄሮች እያጠቃ ያለ”፣ “ሁሉም ነገር ለኦሮሚያ   የሚል”፣ “በጠባብ የዘረኝነት አስተሳሰብ የታወረ ኃይል” ብለው በድፍረት ሲጽፉ፣ ስለዚህ ወጣት ትውልድ ያላቸው ግምት የተሳሳተ ነው ለማለት የደፈርኩት። አቶ ሽሽጉ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል እስቲ ሶስቱን ብቻ ባነሳ፣

ሀ) ቄሮ ማለት ከላይ ባስቀመጥኩት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም የኦሮሞ ወንድ ስለሚያጠቃልልና ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት ከአርባ ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ኦሮሞዎች መሃል ስድሳ በመቶው የሚሆነው በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ  ስለሚካተት፣  ይህን  የሚያክል  ቁጥር  ያለውን፣  በማንም  ያልተደራጀና በማንም የማይመራውን ወጣት ትውልድ፣ ኢህአዴግ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል እየጣሰባቸው ያለውን ህገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው  ደጋግመው ቢጠይቁም ሰሚ ጆሮ  ያለው  መንግሥት  በማጣታቸው ራሳቸውንና ህዝቡን ለሰላማዊ ዓመጽ በማነሳሳታቸው ብቻ፣ እንደጥፋተኛ ተቆጥረው “ምርመራ ይደረግባቸው” ማለት ካለማወቅ የተነሳ ድምዳሜ ነው እላለሁ።

ለ) በርግጥ ቄሮ በራሱ ብቻ ሳይሆን መላውን የኦሮሞ ህዝብ አስከትሎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለግላዊና ቡድናዊ መብቱ መከበር ሲል በኦሮምያ ክልል ውስጥ ሰላማዊ ህዝባዊ እንቢተኝነትን ብቸኛ የትግል ዘዴው አድርጎ መታገልና ማታገል ከጀመረ ዓመታት አስቆጥሮአል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አቶ ሽሽጉ እንዳሉት ሳይሆን፣ ቄሮዎች አንድም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ላይ አንዳችም ዓይነት እንኳን የጦር መሳርያ ቀርቶ ለወትሮው ከጁ የማይለየውን ዱላ እንኳ ሳይይዝና የሰላም ምልክት የሆነውን እጃቸውን አጣምረው ነበር ለሰልፍ የሚወጡት። በሌሎች አገራት፣ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የሚያደርሱትን ጥፋት በየቴሌቪዥኑ ስንመለከት፣ ቄሮ ምንኛ የነቃና፣ ህገ መንግስታዊ መብቱን ብቻ በሰላም ለመጠየቅና በሰላማዊ ዓመጽ መንግሥትን አንበርክኮ ተገቢውን መልስ ለማግኘትና ማህበረሰባዊ ግዴታውን ለመወጣት  በእንቢተኝነት  የወጣ፣  ግን  ደግሞ  ለሰላም፣  ለፍትህና ለዕኩልነት የቆመ የማህበረሰቡ አካል መሆኑን ስናስተውል እኔ በግሌ ልባዊ ኩራት ይሰማኛል።

ሐ) የኦሮሚያ ክልል ከሌሎቹ ስምንት የኢትዮጵያ ክልሎች በተለየ መልኩ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄር ተወላጆች ለዘመናት አቅፎና ደግፎ በመከባበርና በሰላም አብሮ ለማኖር የቻለ ብቸኛ ክልል ነው። የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥትም ከሌሎች የክልል መንግሥታት ህገ መንግሥቶች በተለየ መልኩ የሌሎች ኢትዮጵያ ብሄር ተወላጆችን የመኖርና የመስራትን ብቻ ሳይሆን የክልሉን መሥርያ ቋንቋ እስከቻሉ ድረስ በክልሉ መንግሥትና አስተዳደር ውስጥ ከማንኛውም የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ እኩል የመወዳደርና የሥልጣን ወንበር ላይ ሊቀመጡ ይችላሉ ብሎ የደነገገው። የዚህ የክልሉ ህገ መንግሥታዊ ዋስትናና የቄሮ ያለመታከት የሰራው የዜጎችን መብት ማክበር ድምር ነው እንግዲህ በሰላማዊ እምቢተኝነት የትግል ሂደት ውስጥ በክልሉ የሚኖር የሌላ ብሄር ተወላጅ ዜጋ ህገ መንግሥታዊ መብቱ ተጠብቆለት ሰላማዊ ኑሮውን የመግፋት ዋስትና ያገኘው። ለአቶ ሽሽጉ ግን ይህ ያልተገለጸላቸው ወይም በትክክል ያልተነገራቸው ይመስለኛል።

ይህ ማለት ግን፣ ቄሮም ሆነ የክልሉ ህዝብ፣ ወያኔን ከለላ በማድረግ፣ ለምሳሌ የክልሉን አርሶ አደር ህዝብ ያለምንም ካሳ ለዘመናት ይኖሩበት ከነበረው መሬታቸው አፈናቅለው  በልማት  ስም በህዝቡ ላይ እጅግ በጣም አስከፊ የሆነ ጥፋት ባደረሱት ሰዎች ንብረት ላይ አደጋ የማድረስ ሁናቴ አልነበረም ማለቴ አይደለም። ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለማስጠበቅ ግዴታ ያለበትና በራሱ በህዝቡ ተመርጬ ነው ሥልጣን የተረከብኩት ብሎ አራት ኪሎ የመሸገው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ “ጥፋተኛ ነኝ” ብሎ በአደባባይ ይቅርታ የጠየቀባቸውን የመብት ጥሰቶች ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆኖ ሳይገኝ ሲቀር፣ ለህዝቡ የቀረው ብቸኛው የትግል ዘዴ ሰላማዊውን ዓመጽ ለተወሰነ ዓላማና ጊዜም ቢሆን ወደ ዓመጽ መቀየር ተፈጥሮያዊ ክስተት ይመስለኛል። ሴት ልጅ ሊደፍራት የሚሞክረውን ወንጀለኛ፣ በመጀመርያ ድርጊቱ ወንጀልና ኢ-ሰባዓዊ መሆኑን እያስረዳችና መብቷን እንዲያከብርላት በሰላም እየጠየቀች፣ ወንጀለኛው ግን ጉልበቱን ተማምኖ ሰላማዊ ጥያቄዋን ወድያ ብሎ ሊደፍራት ከወሰነ፣ ልጅቷ ራሷን ከጥቃቱ ለማዳን በሰላሙ ጊዜ “ህገ ወጥ” የሆኑትን ዘዴዎች ተጠቅማ በደፈራት ግለሰብ ላይ ጉዳት ብታደርስ፣ ድርጊቷ ራሷን ከማዳንና የግል መብትን ከማስከበር ባሻገር ሌላ ስውር ዓላማ ስለሌለው፣ ማህበረስቡ ሊኮንናት አይገባም። ቄሮዎችም አልፎ አልፎ የወሰዱትን እርምጃ በዚሁ መንፈስ ከተመለክትነው፣ የግልን መብት ለማስከበር ሲባል የመብት ገፋፊውን ጥቅም በመንካት ትኩረትን  ለመሳብ  መሞከር ከወንጀል ሊቆጠር አይገባም ባይ ነኝ። የወያኔ መስራቾችም እኮ ወደ ደደቢት ያቀኑትና ለአስራ ሰባት ዓመትም ያለማቋረጥ ዜጎችን ሲገድሉና ባንክ ሲዘርፉ እንዲሁም የህዝብን ንብረት ያወድሙ የነበሩት “ተጥሶብናል” ያሉትን ህገ መንግሥታዊ የቡድን መብታቸውን የሚያስተካካል ሰሚ ጆሮ ያለው መንግሥት ባላመኖሩ ይመስለኛል። ድርጊቱ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚለውን ክርክር ለማንሳት ብዬ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው፣ የተጠቃ  መስሎ  ከታየው  ከጥቃቱ  ለመከላከል  ሲባል በሰላም ጊዜ “ሊደረግ የማይገቡ” ነገሮችን ማድረጉ ኢ-ተፈጥሮያዊ አይደለም ለማለት ያህል ነው። ከአቅሙ በላይ የሆነና ሊያቃልል የማይችል ክስተተ መስሎ ከታየው እኮ የሰው ልጅ፣ እንኳን የሰውን ንብረት ይቅርና፣ ውድ የሆነውንና ተለዋጭ የማይገኝለትን የራሱንም ነፍስ እኮ ያጠፋል!

ለመሆኑ ቄሮዎቹ ምንድን ነበር የጠየቁት?  ኢህአዴግስ ለምንድነው መልስ ለመስጠት ያልፈለገው?  ይህንን ጥያቄ ባጭሩም ቢሆን መዳሰሱ ለአቶ ሽሽጉ ጠቃሚ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ለንጽጽር ያህል ደግሞ ራቅ ብለን ከመሄድ፣ የወያኔ መስራቾችን ወደ ደደቢት የገፋው የያኔውን እውኔታ፣ ዛሬ ቄሮዎችን ወደ እንቢተኝነት ከገፋፋው ሁኔታ ጋር ማመላከት ምናልባት ቅን አእምሮ ኖሮት ነገሮችን በትክክል ለመረዳት ለሚፈልግ ሌላውም ሰው ይረዳልና እስኪ አብረን እንቃኛቸው።

የትግራይ ኤሊቶች ህዝባቸው በፊውዳሉ ሥርዓት የተበደለና ፍትህ የተነፈገ መሆኑን ደጋግመው ለማሰማት ሞክረው ሰሚ በማጣታቸው፣ የተደላደለ  ኑሮአቸውንና  የከፍተኛ  ትምህርት ዕድላቸውን እርግፍ አድርገው በመተው፣ በሰላም ጠይቀው ለማስከበር ያልቻሉትን መብት፣ በጠብመንጃ ብርታት ለማግኘትና ከጭቆናና ብዝበዛ ነጻ የሆነችዋን ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ለመመስረት ወስነው ወደ ደደቢት አመሩ። የትጥቅ ትግል በተፈጥሮው ሰላማዊ አለመሆኑን ጠንቅቀው ቢያውቁም፣ ራሳቸውንና ህዝባቸውን ከጥቃት ለማዳንና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሬፑብሊክን የመፍጠር ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ጠብመንጃ አንስተው “ጠላቶቻቸውን” የመግደል ተግባርን የትግላቸው ዋና አካል አድርገው ወሰኑ። ከላይ እንዳልኩት የተጣሰባቸውን መብት መልሶ ለማስከበር፣ በሰላሙ ጊዜ ኢ-ሰብዓዊ ተብለው የተፈረጁትን ነፍስን የማጥፋትና ንብረትን የማውደም ተግባር የቀን ተቀን ሥራቸው በማድረግ፣ ራሳቸውም እየተገደሉ፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ   የጭቆና   አገዛዝ “ነጻ ሊያወጡ” ቻሉ። ዓላማቸውን ከግቡ ያደረሱት ህገ መንግሥታዊ ባልሆነና ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ነበር ማለት ነው።

ቄሮዎችም ህገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበርልን ብለው በተደጋጋሚ ለመንግሥት ያቀረቡት ስሞታ ሰሚ ባለማግኘቱ፣ ለሰላማዊና ህዝባዊ ዓመጽ ጥሪ በማድረግና ህዝቡን አስተባብሮ በመምራት፣ የግል ምቾታቸውን ወደ ጎን በመተው ለህዝባቸው መብት መከበር ሲሉ የፈለገውን መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ሆነው ተነሱ። ይህንን የመብት ጥያቄ ያነሱትን ቄሮዎችን ነው እንግዲህ ኢህአዴግ፣  “የህዝቡን  ሰላም ለማደፍረስ  ተነሳስታችኋል”  ብሎ የጸረ  ሽብር ዓዋጅ ያወጀውና “የህዝባዊ  ዓመጹ አቀንቃኝ ናቸው” ብሎ ያሰባቸውን ኦሮሞዎችን ሰብስቦ ወደ ማዕከላዊና ቃሊቲ፣ ቅሊንጡና ዝዋይ፣ ወርውሮ የቁም ሥቃይ ያሳያቸው የነበረው። አቶ ሽሽጉም፣ እንደወንጀለኞች ቆጥሮአቸው “የወንጀል ክስ ይመሥርትባቸው” ብሎ በቁጭት የሚናገረው እነዚህን ወጣት ትውልድን ነው።

የወያኔ መስራቾችንና ቄሮን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ሁለቱም የየህዝባቸውን የተጣሰውን ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለማስከበር ያላቸው ቁርጠኝነት ነው። በመካከላቸው ያለው ልዩነት ግን ከሚያመሳስላቸው ባያሌው ይሰፋል። ወያኔ፣ በመሳርያ ኃይል ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዓላማውን ለማሳካት፣ የተቃወመውን ሁሉ፣ ለኢትዮጵያ የግዛትና የህዝቦች አንድነት ሲዋጉ የነበሩትን ሳይቀር እየገደለ፣ ለሥራ ማስኬጃው እንዲረዳ የመንግሥት ባንኮችን እየዘረፈና እሥር ቤቶችን ሰብሮ ያላግባብ ታስረዋል ብሎ ያላቸውን እስረኞች ሲያስፈታ እንደነበረ ራሳቸው ተጋዳሊቶቹ በአደባባይ ይናገሩና ይጽፉ ነበረ። ቄሮ ግን፣ ያላንዳች ጠብመንጃ ወይም ዱላ፣ በሰላማዊ መንገድ የተጣሱትን መብቶች  መልሶ  ለማስከበር  እጁን አጣምሮ የወጣ፣ ለጥያቄውም መልስ ማግኘት ደግሞ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላምና በመከባበር በአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ አብሮ ለመኖር የሚረዳ መሆኑን በማስተማር፣ የሌሎች ብሄሮች ተወላጆችን አብረውት እንዲሰለፉ ያደረገ፣ ማድረግ እየቻለ ግን ደግሞ አንድም ቦታ ላይ ባንክ ያልዘረፈ ወይም ያላስዘረፈ፣ የማድረግ አቅሙ እያለው ግን ደግሞ አንድም ቦታ ላይ የህግ ታሳሪ ኦሮሞዎችን ለማስፈታት ያልሞከረና ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ የግዛትና የህዝቦቿን አንድነት እንዲከበር፣ ለህግና ሥርዓት ተገዥ ሆኖ በህገ መንግሥቱ የተደነገገለትን የመሰብሰብና ለመረጣቸው ባለሥልጣናት ጥያቄ የማቅረብ መብቱን በመጠቀም የመንግሥትን ጆሮ ለመሳብ እየሞከረ ያለ ሰላማዊ ዜጎችን ብቻ ያቀፈ ትውልድ ነው። የጨለማና ብርሃን ዓይነት ልዩነት!

አቶ ሽሽጉ ግን ይህንን ዕውኔታ በቅጡ የተረዱት አይመስለኝም። ምናልባትም፣ ሳያድለን ቀርቶ ሚዲያው ሁሉ የመንግሥት በመሆኑና እውነትን ከቅጥፈት ለይቶ የማየት ዕድል ባለመኖሩ የመንግሥትን ፕሮፓጋናዳ ብቻ እንደ ጥሩ የመረጃ ምንጭ አድርጎ ከማየት የተነሳ ይመስለኛል ቄሮን እንደ አጥፊ ድርጅት ለመፈረጅ የደፈሩት። አለበለዚያማ፣ በቄሮዎች አነሳሽነት ለደረሰው አለመረጋጋት ዋናው ምክንያት ኢህአዴግ ራሱ የፈጠረው የመልካም አስተዳደር ጉድለት መሆኑን አምኖበት ባለፈው ወር በአደባባይ ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ የጠየቀበት በመሆኑ፣ ለደረሰው ማናቸውም ዓይነት ጥፋትና አለመረጋጋት ተጠያቂው ኢህአዴግ እንጂ ቄሮ አለመሆኑን አቶ ሽሽጉ በተረዱት ነበር። ይህንን አለመረዳትማ ከላይ የጠቀስስኩት ሴት ልጅን የመድፈር ትዕይንት ላይ ሴቲቷን ለምን አርፈሽ አልተደፈርሽም ብሎ የመፍረድ ያህል ስለሆነ፣ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ህግ የልጅቷን ራስን የመከላከል መብት እንደሚደግፍ አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም።

በኔ ግምት አቶ ሽሽጉ ለቄሮ አስበው ያሰፉት ሱሪ በኢህአዴግ ልክ የተሰፋ ይመስለኛል። ሰላማዊ ዜጎችን ከሱ የተለየ የፖሊቲካ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ አስሮ የሚያሰቃይ፣ ሴት ልጆችን በማዕከላዊው እሥር ቤት ያለአግባብ የሚያስርና የሚደፍር የገራፊ ቡድን አሰልጥኖ ያሰማራ፣ ወንድ እስረኞችን የሚያኮላሹና አካል ስንኩል የሚያደርጉ የአሰቃይ ቡድንን ያቋቋመና የሚመራ፣ አግዓዚ የሚባል ያለምንም ርህራሄ በጠራራ ጸሃይ ሰላማዊ ቄሮዎችን አነጣጥሮ  የሚገድል አሸባሪ ቡድንን ያቋቋመና የሚመራ የኢህአዴግ መንግሥት እንጂ፣ ቄሮ በምንም ተዓምር አጥፊ ሊባል አይገባም።

ለመደምደም ያህል፣ እያንዳንዳችን የየራሳችን የሆነ ወገናዊነትን ስለምናስተናግድ፣  የክስተቶችን  ይዘት  በትክክል  ሳናውቅ ከምንሰማውና ከተነገረን ብቻ በመነሳት “የኛ ያልሆነውን” ሁሉ በጠላትነት ከመፈረጅ ተቆጥበን፣ በመጀመርያ ደረጃ፣ ስለ “ሌላኛው ወገን” ስሞታ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረንና ድምዳሜያችን በመረጃ እንዲደረግ መጣር፣ ነገሮችን በጥሞና ለመስማት ዝግጁ መሆንና አብሮ መፍትሄ ለመፈለግ በጎ  ፈቃደኝነትን  ማሳየት  ዝግጁ መሆን አለብን እላለሁ። አለበለዚያ ሁላችንም የየራሳችንን የተንሸዋረረ ግምት ታቅፈንና አንዳችን ስለሌላው የተሳሳተ ግምት እያስተናገድን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ባንድ ላይ ሆነን እንገነባለን ማለት ወንዝ የማያሻግር የይስሙላ “አብሮነት” ይመስለኛል። ትክክለኛ  ድምዳሜ  ላይ  ለመድረስ  ደግሞ አስቀድሞ ትክክል የሆነ መረጃ መሰብሰብ ወሳኝ መሆኑን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።

****

ጄኔቫ፣ ፈብርዋሪ 20, 2018  wakwoya2016@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *