በላሊበላ ስኮትላንዳዊቷ ወይዘሮ ነግሰዋል። ሱዛን ኤይቸሰን ይባላሉ። የቀድሞዋ የኤኮኖሚክስ መምህርት ከትውልድ አገራቸው ስኮትላንድ ወደ ላሊበላ ዘልቀው ለወጣቶች ሥልጠና ይሰጣሉ፤ ታዳጊዎችም በትምህርት ቤቱ እንዲቆዩ በገንዘብ ይደግፋሉ። ከኢትዮጵያዊው የሥራ አጋራቸው ጋር ቤን አበባ የተሰኘ ምግብ ቤትም ከፍተዋል።

 
አውዲዮውን ያዳምጡ።10:05

ሱዛን ወጣቶች ያሰለጥናሉ፣ ችግረኞች እንዲማሩ ይደግፋሉ

ላሊበላ ብቅ ያሉ አገር ጎብኚዎች ከድንቅ የአብያተ-ክርስቲያናት ኪነ-ሕንፃ እና ውብ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ባሻገር ቀልባቸውን የሚስብ ቦታ አግኝተዋል። በትንሿ ከተማ ሰሜናዊ አቅጣጫ ከቹል አምባ ኮረብታ ጉብ ያለው ቤን አበባ አገር ጎብኚዎች መረጃ በሚሰበስቡባቸው ትሪፕ አድቫይዘር የመሳሰሉ ድረ-ገፆች በአገልግሎት አሰጣጡ እና ኪነ-ሕንፃው አድናቆት ይጎርፍለታል። ቤን አበባ ምግብ ቤት ነው። አነስተኛ ምግብ ቤት። ምግብ ቤቱ ካረፈበት ቹል አምባ ላይ ሆኖ የላስታን ተራሮች ውብ አቀማመጥ ማየት፣ የጸሐይ ግባት የሚፈጥረውን አስደናቂ ብርሐን መመልከት ወደ ቦታው ላቀኑ አገር ጎብኚዎች ፍሰሐን ይሰጣል። ደርሰው የተመለሱ በድረ-ገፆች እንዲያ ፅፈዋል።

ምግብ ቤቱ ስያሜውን ያገኘው እንደ የባለቤቶቹ ማንነት ከስኮትላንድ እና የኢትዮጵያ ቃላት ጥምር ነው። ቤን በስኮቲሽ ቋንቋ ኮረብታ የሚል ትርጓሜ ሲኖረው አበባ ደግ ያው አበባ ነው። ቤን አበባ የኢትዮጵያዊው ሐብታሙ ባዬ እና ስኮትላንዳዊቷ ሱዛን ኤይቸሰን ጥምረት ውጤት ነው። ሱዛን ጡረታ የወጡ መምህር ናቸው። ከአመታት በፊት ወደ ላሊበላ ያቀኑት በጎረቤታቸው ግብዣ ድንገት ነበር።

“ለጉብኝት ላሊበላ ደርሶ የተመለሰ ጎረቤት ነበረኝ። ሲመለስ የላሊበላን ማሕበረሰብ ለመርዳት አንዳች ነገር ማድረግ አለብኝ ብሎ ነበር። በስተመጨረሻ ትምህርት ቤት ለመገንባት ወሰነ። ትምህርት ቤቱ ከላሊበላ 35 ኪ.ሜ. በሚርቅ መንደር ይገኛል። የዚያ መንደር ነዋሪዎች ትምህርት ቤት የላቸውም።  ወይን እየጠጣን ስለትምህርት ቤቱ አጫወተኝ። ፎቶግራፎችም አሳየኝ። እኔም እርዳታዬን ትሻለህ ወይ ስል ጠየኩት። እንዲህ ድንገት ወደ ላሊበላ ለመምጣት ወሰንኩ። አይኖቼን ጨፍኜ ስገልጥ ራሴን ላሊበላ አገኘሁት። የመጣሁት ትምህርት ቤቱን ሥራ ለማስጀመር ነበር። ሐሳቤ ለሁለት አመታት ብቻ ለመቆየት ቢሆንም ከዚያ በኋላ አልተመለስኩም”

Bet Giyorgi Felsenkirche von Lalibela in Äthiopien (picture alliance/Robert Harding World Imagery)

ሱዛን በመጀመሪያዎቹ 3 አመታት ወደ ትውልድ አገራቸው አልተመለሱም። ሕይወት በስኮትላንድ እና በኢትዮጵያ የሰማይ እና የምድር ያክል ልዩነት ቢኖራትም ላሊበላ ቀልባቸውን ገዝታለች። ሱዛን እጅግ የተራራቀውን የኑሮ ሁኔታ ለማየት በመታደሌ “እድለኛ ወይዘሮ ነኝ” ሲሉ ይናገራሉ። ትምህርት ቤቱ በተሰራበት አካባቢ መንገድ፣ መብራት፣ ውሐ ስልክ የለም። እርሳቸው የለመዱት የመጸዳጃ አገልግሎትም አይገኝም። ለሱዛን ግን በጋባዥ ጎረቤታቸው የተገነባውን ትምህርት ቤት ሥራ አስጀምሮ ለመንግሥት ከማስረከብ የሚገታቸው አልተገኘም።

“አብዛኛው ሥራዬ በላሊበላ ከሚገኘው የትምህርት ፅ/ቤት ጋር የተገናኘ ነበር። ስለዚህ እንግሊዘኛ በሚነገርበት ላሊበላ ብዙ ቆየሁ። በዚያ ለማኞቹ ጭምር እንግሊዘኛ ይናገራሉ። ከትምህርት ቤቱ ወደ ላሊበላ የሚያመላልሰኝ የህዝብ ማጓጓዣ ሥራ የሚሰራ ወጣት ነበር። ወደ ትምህርት ቤቱ ስንሔድ አብሮን ይቆያል። ሥራ ካለ ያግዘናል። አንድ ቀን በእሱ መኪና ውስጥ ሳለን ወደ ፊት በላሊበላ ጥሩ ምግብ የሚያቀርብ ምግብ ቤት መክፈት እፈልጋለሁ ሲል ሕልሙን አጫወተኝ። በዚያን ጊዜ እድሜዬ 60 ደርሷል። ከስኮትላንድ መንግሥት ጡረታ የማገኝበት ጊዜ እየቀረበ ነበር። ሥራ ለማቆም ተዘጋጅቻለሁ። ስለዚህ ፈቃደኛ ከሆንክ እኔም ፈቃደኛ ነኝ። ምን ማድረግ እንደምንችል እንይ አልኩት”

ሐብታሙ እና ሱዛን ለእቅዳቸው የሚሆን ቦታ በላሊበላ ፈለጉ። በስተመጨረሻ ግን ከቹል አምባ ቀልባቸው እረጋ። ቤን አበባ ሥራ ከጀመረ ሰባት አመታት ተቆጠሩ። ብቅ ብለው የኢትዮጵያ እና የስኮትላንድ ምግቦችን ያጣጣሙ አገር ጎብኚዎች በአገሪቱ ቆንጆ ምግብ አስደማሚ መልክዓ ምድር በሚታይበት ቦታ የሚያቀርብ ምግብ ቤት ቢሸለም ኖሮ ቤን አበባ ወርቅ ባገኘ ነበር ሲሉ ፅፈዋል። አቅማቸው የፈቀደ የአገሬው ሰዎች ጭምር ቤቱን ወደውታል።

በላሊበላ ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር ሙያዊ ስልጠናዎች ማግኘት ፈታኝ ነው። ከተማዋ ከድንጋይ ተፈልፍለው በተሰሩት አስራ አንድ አብያተ-ክርስቲያናት የአገር ጎብኚዎችን ቀልብ ትግዛ እንጂ ኤኮኖሚዋ ፈቅ አላለም። በላሊበላ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ሕይወታቸውን የሚገፉት ዛሬም ዝናብ ጠብቀው ነው። ለላሊበላም ይሁን ለአካባቢው ወጣቶች አማራጭ የሥራ መስክ ማግኘት ይፈትናል።

ለሚቀጥሯቸው ሰራተኞች የምግብ አሰራር፣ የእንግዳ አቀባበል የአገልግሎት አሰጣጥ ስልጠና ይሰጣሉ። ወይዘሮ ሱዛን የመጦሪያ ገንዘባቸውን በላሊበላ ላይ ሲያውሉ እንዴት ያሏቸው አልጠፉም። እርሳቸው ግን ለወደዱት አንዳች ትርጉም ያለው ሥራ በመስራታቸው ኩራት ይሰማቸዋል። “አንዳች ልዩ ነገር ለላሊበላ አበርክቻለሁ። ያ ለእኔ እጅግ ጠቃሚ ነው። ምንም አይነት ደሞዝ አልቀበልም። ደሞዝ አያሻኝም። የሚገኘው ሁሉ ተመልሶ ወደ ማኅበረሰቡ ይሔዳል።” ሲሉ ይናገራሉ።

ቤን አበባ የማስፋፊያ ሕንፃዎች ሰርቷል። በሒደት ወደ ሆቴል ሊያሳድጉት እቅድ ይዘዋል። አብረዋቸው የሚሰሩ ከትርፉ በፊት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታሉ።

ዕድሜያቸውን ሙሉ በመምህርነት ያገለገሉት ወይዘሮ ሱዛን ታዳጊ ልጆች የትምህርት እድል እንዲያገኙ የስኮላርሺፕ እድል ይሰጣሉ። ከተጀመረ ዘጠኝ አመታት ሆኖታል። “የጀመርንው በመስከረም 2009 ዓ.ም. በ10 ታዳጊዎች ነው። የትምህርት እድል ያላገኙ ልጆች የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን” ሲሉ ያክላሉ። 

ወይዘሮ ሱዛን ታዳጊዎች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ ማገዝ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። “የእኔ እዚህ ግባ የማይባል ትንሽ ድርጅት ነው” ይበሉ እንጂ እስከ ዛሬ ድረስ ለ76  ተማሪዎች ይኸንንው የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

Source – እሸቴ በቀለ, ኂሩት መለሰ

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *