በሀገራችንም ኾነ በብዙ ታዳጊ ሀገራት ለዘመናት ያጣነው ነገር ሙሉ አካል ያለው የሰው መንግሥት ነው፡፡ እንደሰው ስብስብነቱ በነጠላ ያለውን በጋራ የሚይዝ፡ ከነጠላ በላይ የጋራ ፍላጎትና ግብ (Autonomous Goals) ለማሳካት ቀን ከለሊት የሚተጋ መንግሥት፤ ይህም የኹሉ ኹለንተናዊ ማዕከል እንዲሁም የኹሉ ነገር መለኪያ (a standard for everything) ሊኾን የሚገባው ባጭሩ አካል ጉዳተኛ ያልኾነ መንግሥት ነው፡፡

(ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ) ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ

 

የሰው ልጅ የትላንት፣ ዛሬና ነገ ኹለንተናዊ – ፍላጎት/ቶች እና ኹለንተናዊ መስተሳስራዊ ግንኙነት/ቶች ውጤት በመኾኑ በጊዜ ሂደት ውስጥ በተለያየ ኹኔታ ውስጥ በኹኔታዎች አስገዳጅነት፣ በሂደት ውጤት፣ በፍላጎትም ኾነ በመወራረስ ውስጥ ኾኖ የመንግሥት ምስረታ ሂደትን የታሪኩና የአኗኗሩ ሂደት አካል አድርጓል፡፡

ይኸውም ትንታኔ በአለም አቀፍ ምሁራን ዘንድ በሰፊው የሚጠቀሰውን Max Weber: Essays In Sociology: (Translated and Edited by H.H. Gerth and C. Wright Mills – New York: Oxford University Press, 1958) ስራ ባለመዘንጋት ነው፡፡

ገለጻው ከትርጓሜ አንጻር “A State is a human community that (successfully) claims the monopoly of the legitimate use of physical force within a given territory.” (ገጽ 78) እንዲሁም ከተግባራዊ እንቅስቃሴ የውጤታማነት መለኪያ አንጻር “the modern state is a compulsory association which organizes domination.” (ገጽ 82) ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ከጽንሰ ሀሳባዊ ገለጻ ባሻገር መሬት ላይ በወረደ ኹለንተናዊ መስተሳስር መንግሥት በምስል (Image) እና በተግባር (Practice) ደግሞ ከተለያዩ ዕይታ/ዎች (Perspectives) በመነሣት እንደሚቀረጽና እንደሚቀርጽ በማስተዋል ይኾናል፡፡

አንድ ሰው ከእምነቱ፣ ከእውቀቱና ከተግባሩ በመነሣት ግልጽ – ድብቅ፣ ደግ – ክፉ፣ የሠለጠነ – የሰየጠነ፣ የዋህ – መሰሪ፣ ቅን – አስመሳይ፣ ታማኝ – ከሃዲ – – – ወዘተ ተብሎ ሰው በባሕሪው አንድ ኾኖ በጠባያት እጅጉን እንደሚለያይ ኹሉ የሰው ስብስብ የኾነው መንግሥትም ከእምነቱ፣ ከእውቀቱና ከድርጊቱ በመነሣት ነጻ – ባሪያ፣ ዲሞክራሲያዊ – ኢ-ዲሞክራሲያዊ፣ ግልጽ – ድብቅ፣ ተጠያቂነት ያለበት – ተጠያቂነት የሌለበት፣ የሠለጠነ – የሰየጠነ፣ ሕዝባዊ – ግላዊ (ቡድናዊ)፣ ፍትሃዊ – ኢ-ፍትሃዊ፣ የነጻ ፍቃድ አክባሪ/አስከባሪ – አፋኝ፣ ነጻነት አስከባሪ – አሳሪ፣ – – – ወዘተ ተብሎ መንግሥታት በባሕሪያቸው ተመሳሳይ ኾነው በጠባያት ግን እጅጉን ይለያያሉ፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚገኙ መንግሥታት መሐከል ባሕሪያዊ መመሳሰልን እውቁ የአለም አቀፍ የፖለቲካ ምሁር John Mearsheimer: ስለመንግሥታት በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ “there is no higher authority above state, their principle goal is to survive, they are rational actors and it is difficult to be certain about their intension especially their future intension.” በማለት ባሕሪያዊ መገለጫቸውን ከአለም አቀፍ ግንኙነት አንጻር ለመተንተን ያስቀምጣሉ፡፡

ከዚህ በመነሣት የመንግሥት ሕልውና ከሰው ስብስብ (ሕዝብ) ጋር የተሳሰረ በመኾኑ የማንኛውም መንግሥት መነሻና መዳረሻ የኾነው፣ እየኾነ ያለው፣ የሚኾነውና ሊኾን የሚገባው የሰው ስብስብ (ሕዝብ) ነው፡፡ ምክንያቱም ኹሉ ነገር ከሕልውና በኃላ ስለሚኾን ከግላዊና ቡድናዊ ወደ ሕዝባዊነት፤ ከርስ በራስ መባላት ወደ ገዥነት – ከገዥነት ወደ መሪያዊነት፤ ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ የሚያድግ መንግሥት ይኖረን ዘንድ ምን ያስፈልጋል?

ሰው አምስት የስሜት ህዋሳት (ማሽተት /በአፍንጫ/፣ መቅመስ /በምላስ/፣ ማየት /በዓይን/፣ መዳሰስ /በእጅ/፣ መስማት /በጆሮ/፣) እንዲሁም “ስድስተኛ” የስሜት ህዋስ ተብሎ የሚጠራ ፍቅር /በልብ/ የተሰኘ ኃያል ተፈጥሯዊ ባለቤት ከመኾኑም በላይ እነዚህን የተሸከመና መሸከም የሚችል ሕልውናቸውንና ሕልውናውን ከርሱ ጋር ያስተሳሰረ ሰባት ባሕሪያት (አራት ባሕሪያተ ስጋ (ከአፈር፣ ውሃ፣ ነፋስና እሳት) እና ሶስት ባሕሪያተ ነፍስ (ነባቢት /ተናጋሪነት/፣ ለባዊት /አሳቢነት/ና ህያውነት /ዘላለማዊነት/) ያሉት ታላቅ ፍጡር መኾኑ ይታወቃል፡፡

ስለኾነም የሰው መንግሥት – የሰው ስብስብና የሰው ስብስብን ማዕከል ማድረጉ የግድ ነውና በነጠላ ያለውን በስብስብ መያዙ ሂደትን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ነው፡፡ ብዙ ሀገራትና ሕዝቦች ግን በዚህ አውድ ይህን በእጅጉ ተርበው፣ ተጠምተው፣ ታርዘው፣ ታመውና ጠያቂ አጥተው ይገኛሉ፡፡

ሕዝባዊ መንግሥት ኹለንተናዊ የትላንት፣ የዛሬና የነገ ሕዝባዊ ጉዳዮችን እንደሰው አምስት ህዋሳት ያለው (የሚያሸትበት /አፍንጫ/፣ የሚቀምስበት /ምላስ/፣ የሚያይበት /ዓይን/፣ የሚዳስስበት /እጅ/፣ የሚሰማበት /ጆሮ/) እንዲሁም “ስድስተኛ” የስሜት ህዋስ ሕዝባዊ ፍቅርን በዕምነት፣ በዕውቀትና በድርጊት ደረጃ በኹለንተናዊ መንገድ የሚያሳይበት /ልብ/ በኃያል ሕዝባዊ ውግንና፣ መርህ፣ ዲሲፕሊኒን (discipline)ና ዕሴት (Values) ሊኖረው ግድ ይላል፡፡

ምድራዊ መንግሥት ያለ ሰው ፈጽሞ እንደማይመሰረት ኹሉ፤ ሕዝባዊ መንግሥት ያለ ሕዝባዊ ባሕሪያትና ጠባያት ሊመሰረት ከቶ አይችልም፡፡ ሕዝባዊነት በአንጻሩ የግለሰቦች ስብስብ እንደመኾኑ መጠን ግለሰቦች እንደግለሰብ ያላቸው ፍጹም ባሕሪያዊ ተመሳሳይነት (ባሕሪ/ያት የማይቀየር – ጠባይ/ያት በአንጻሩ የሚቀያየር የመኾኑን ዕሳቢያዊ ዐውድ በማስተዋል!) በስብስብ ሊቀየር እንደማይችልና እንደማይገባ ሊሰመርበት የሚገባ ታላቅ ቁም ነገር ነው፡፡

አንድ ሰው ከስሜት ህዋሳቱ አንዱ ቢጎድል እንደጉዳቱ አይነትና መጠን ተቀጽላው እንዳለ – አካል ጉዳተኛ ተብሎ ሲጠራ ተመሳሳይ ጉዳት ያለባቸው አካላት ደግሞ በብዛት – አካል ጉዳተኞች ተብለው ይጠራሉ፡፡ እንደዚሁም ያለ ልዩነት የሰው ስብስብ – መንግሥታት በዋና አካላቶቻቸው – ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ በኩል በነጠላ የስሜት ህዋሳቶች ያሏቸው ኾነው በስብስብ ሲያጎድሉና ሲያጠፉ፤ ሲበድሉና ሕዝብን ሲያጉላሉ – – – “የመልካም አስተዳደር ችግር ይባላል” እንጂ አካል ጉዳተኞች አይባሉም፡፡

ትልቁ ተቃርኖ ወዲህ አለ! 1. በነጠላ ጆሮ፣ ዐይን፣ አፍንጫ፣ ምላስና እጅ ብሎም ልብ ያላቸው በስብስብ የጋራን ጉዳይ በጋራ ለጋራ ስለጋራ የሚሰሙበት ጆሮ፣ ዐይን፣ አፍንጫ፣ ምላስና እጅ ብሎም ልብ ከሌላቸው “የሰው ስብስብ ናቸውን?” የሚለውን ትርጉም ያለው ጥያቄ እንድናነሣ ያስገድዳል፡፡

  1. በተፈጥሮም ይኹን ሰው ሰራሽ በኾነ፣ በመወለድ ይኹን በሂደት፣ በዘር ይኹን በእድገት፣ በማጣት ይኹን በመታጣት፣ በአቅም ማነስ ባለመታከም ይኹን ባለማወቅ፣ በህክምና ስህተት ይኹን በመድኃኒት ጎንዮሽ ጉዳት፣ ባለማየት ይኹን ባለማስተዋል፣ በእንክብካቤ ማጣት ይኹን በቸልተኝነት፣ – – – መስማት ሲገባው ያልሰማ – መስማት የተሳነው፣ ማየት ሲገባው ያላየ – ማየት የተሳነው፣ ማሽተት ሲገባው ያላሸተተ – ማሽተት የተሳነው፣ መዳሰስ ሲገባው ያልዳሰሰ – መዳሰስ የተሳነው፣ – – – ወዘተ እየተሰኘ በጥቅሉ ከአይነት ባሻገር አካል ጉዳተኛ ተብሎ ይጠራል፡፡

ታድያ ሕዝባዊነትን መነሻና መዳረሻ አድርጎ ሕግ ማውጣት፣ ሕግ መተርጎምና ሕግ ማስፈጸም ሲገባው ማውጣት፣ መተርጎምና ማስፈጸም ሲያቅተው፣ አካል ኖሮት አካል አልባ ሲኾን፣ በወረቀት ሰምሮ በተግባር ሳይሰምር ሲቀር፤ መግባባት ሲገባው ሳይግባባ ሲቀር፤ መናበብ ሲገባው ካልተናበበ፤ አርቆ ማሰብ ሲገባው ካላሰበ፤ መምራት ሲገባው ወደ መግዛት ከወረደ – ኸረ ይባስ ብሎ ከመግዛት ወደ እርስ በራስ መበላላት ከዘቀጠ – – – አንዲህ አይነት መንግሥት አካል ጉዳተኛ መንግሥት ያልተባለ ማን ሊባል ነው? በአንድ የትርጓሜ ዐውድ አካል ጉዳተኝነት አካልን በተለያየ ምክንያት ማጣት ከኾነ – አካል ጉዳተኝነት በነጠላና በቡድን ብቻ ሳይኾን በተቋም ደረጃ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡

በሀገራችንም ኾነ በብዙ ታዳጊ ሀገራት ለዘመናት ያጣነው ነገር ሙሉ አካል ያለው የሰው መንግሥት ነው፡፡ እንደሰው ስብስብነቱ በነጠላ ያለውን በጋራ የሚይዝ፡ ከነጠላ በላይ የጋራ ፍላጎትና ግብ (Autonomous Goals) ለማሳካት ቀን ከለሊት የሚተጋ መንግሥት፤ ይህም የኹሉ ኹለንተናዊ ማዕከል እንዲሁም የኹሉ ነገር መለኪያ (a standard for everything) ሊኾን የሚገባው ባጭሩ አካል ጉዳተኛ ያልኾነ መንግሥት ነው፡፡

መንግሥት – ለሰው ስብስብ፡ በሰው ስብስብ፡ ስለሰው ስብስብ የሚተጋና ሊተጋ የሚገባው እንደመኾኑ በጋራ ስለጋራ ለጋራ ኹለንተናዊ ጉዳዮች እንደሰው ኹሉ እንደመንግሥትነቱ አምስቱ የስሜት ህዋሳት ሕዝባዊነትን ትርጉም ባለው መንገድ በሶስቱ ዋነኛ አካላቱ (ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ ፈጻሚ):- የሚያይበት /ዓይን/፣ የሚሰማበት /ጆሮ/፣ የሚያሸትበት /አፍንጫ/፣ የሚዳስስበት /እጅ/፣ የሚቀምስበት /ምላስ/ ብሎም ኹሉን ማዕቀፍ የሚያደርግለት ሕዝባዊ ፍቅር /ልብ/ ከሰባቱ ባሕሪያት ጋር ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ሕዝባዊ መንግሥትነት ከቶ በሌላ መንገድ ሊመጣም ኾነ ሊስተናገድ አይችልም፡፡

ብዙ ታዳጊ ሀገራት ግን ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፣ ቢሰሙ እንኳ መስማት ሚፈልጉትን ብቻ የሚሰሙ፣ ሰሙ እንኳ ብንል የማያደምጡ፣ አይን እያላቸው የማያዩ፣ አዩ እንኳ ብንል ማየት ሚፈልጉትን ብቻ የሚያዩ – አይተው የማያስተውሉ፣ ማሽተት ሚፈልጉትን ብቻ የሚያሸቱ፣ መቅመስ ሚፈልጉትን ብቻ የሚቀምሱ፣ መዳሰስ የሚፈለጉትን ብቻ የሚዳስሱ፣ ከአርቆ ማሰብ ይልቅ በጊዜያዊ ነገሮች የተጠመዱ፣ ቀድመው ከመዘጋጀት ይልቅ በኹኔታዎች የሚመሩ፣ ከመምራት ይልቅ መግዛትን የሙጥኝ የሚሉ፣ አልፎ ተርፎ ከመግዛት ወርደው እርስ በራስ የሚበላሉ – – – ኾነው እንደተቸገርን ታሪካችን፣ ዕይታችንና አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

ስለኾነም ሰው እንዳለው 7 ባሕሪያት ያሉት መንግሥት፤ ሰው በባሕሪ ፍጹም አንድ ኾኖ በጠባያት እንደሚለያይ በጠባዩ ከሌሎች የሚለይ ብሎም ከጊዜ ጋር ዘመኑን የሚዋጅ፤ ጠባይ በእድሜ እንደሚቀየር የመንግሥቱ ጠባይም በጊዜ ሂደት የሚቀያየር፤ 5 የስሜት ህዋሳትን በውስጡ የያዘ – ስድስተኛ የስሜት ህዋስ የኾነውን ፍቅር – በውስጡ የያዘ ሰው-ሰው ጠረን ያለው መንግሥት መኾን ከተዘፈቅንበት እንደጣዖት ቢናገሩት/ቢያናግሩት ከማይሰማ፣ ቢያዩት ከማያይ፣ ቢያነ ከማይሰማው፣ ቢጠይቁት ምላሽ ከማይሰጥ፣ ፈራሽና በስባሽ ከኾነ የራቀና የላቀ – ስብዕና የተላበሰ መንግሥት ማሰብ ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡

በአንድ የተወሰነ የድንበር ክልል ውስጥ ያለ ሕዝብ መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ይሄ የመውደድና የመጥላት፣ የመፈለግና ያለመፈለግ፣ የማወቅና ያለማወቅ፣ የመሠልጠንና ያለመሠልጠን ጉዳይ ሳይኾን የሰው ልጅ በዘመናትና በትውልዶች ሂደት ውሰጥ የደረሰበት የእምነት፣ የእውቀትና የድርጊት ኹለንተናዊ የአስተሳሰብና አመለካከት ደረጃው መገለጫ ነው፡፡ በሁሉም ውሰጥ መንግሥት አለ፡፡ መንግሥት ያስፈልጋል፡፡ ልዩነት የሚፈጥረው ምን ዓይነት መንግሥት?ከቅርጽ፣ ከይዘት፣ ከመጠን፣ ከዓውድ፣ ከመገለጫ (ከእምነቱ፣ እውቀቱና ድርጊቱ መገለጫዎች)፣ ከአድማስ፣ ከውጤታማነት አንጻር ያሉ ኹለንተናዊ ነጥቦች ብቻ ናቸው፡፡

ዳዊት በዓለም እንደሱ ያለ ጠቢብና ባለጸጋ እንዳልነበረ፣ እንደሌለ ብሎም ሊኖር እንደማይችል ለተነገረለት ልጁ ሰለሞን “ልጄ ሆይ! ሰው ኹን!” (ልብ እንበል! – ልጅ ብሎ መቼስ ከሰው ውጪ እንደማይታሰብ የታወቀ ዕውነትም (Truth) እውነታም (Reality) ነው፡፡ ‘ሰው ኹን!’ ብሎ ስለመኾን አጽንዖት መስጠቱ ከመፈጠር፣ ከመወለድና ከመባል ባሻገር ስለአኗኗር መኾን ማንሣቱ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት ማለት የሰው ስብስብ መኾኑን መነሻና መዳረሻ አድርገን ከመመስረትና ከመባል አንጻር እኛም እንግዲህ ብዙ ጊዜ ለዘመናት ስለተጠማነው፣ ሰለተራብነው፣ ስለታረዝነው፣ ስለተሰደድንበት፣ ስለታሰርንበት፣ ስለታመምንበት፣ ስለናፈቅነው የአኗኗር ሰው የመኾን ስብስብ (የሰው መንግሥት) ብለን “ገዥያችን ሆይ! መንግሥት ኹን!”፤ “መንግሥታችን ሆይ! መንግሥት ኹን!”፤ “መንግሥታችን ሆይ! የሰው መንግሥት ኹን!” ብንል መልካም ይኾናል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

https://youtu.be/SaV7H9bV1kM

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *