የማያውቁት አገር አይናፍቅም ሲባል እሰማለሁ። እኔ ግን የማላውቃቸው የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ሀረር ከነምንጣፏ፣ድሬደዋ ከነአሮጌው ሰፈሯ፣አሰበ ተፈሪ ከነብርቱካኗ፣ በሰሜኑም ቢሆን ባህር ዳር ከነ ጣናዋ፣ ጎንደር ከነ ፋሲለደሷ፣ ደቡቡም ምእራቡም ሁሉም ….ጭራሽ እንደልጅነት ትዝታ ነው የሚናፍቁኝ።

አሁንም የማያውቁት አገር አይናፍቅም ሲባል እሰማለሁ። እኔ ግን መቼም እንደማላየው እያወቅሁም እንኳ ቀዩ ባህር ይናፍቀኛል። ዛሬም ፊያሜታ ያለች ይመስል የምፅዋ ማእበልና ንፋስ ይናፍቀኛል፤ ዳህላክ ደሴቶቹ፣ አዱሊስ ወደቡ፣ መርከቦቹም ሁሉ ባህሮችን ሲቀዝፉ በምናቤ እያየሁ ይናፍቁኛል፤ የማውቃት አዲስ አበባ ይልቁን እየናፈቀችኝ አይደለም!… እንደተናካሽ የቤት እንስሳ ሲመሽ የሚፈታው ልቤ የዛሬ ቅብጠቱ ይሄ ሆነ፡፡ በናፍቆት ማእበል መመታት፡፡

እየናፈቀችኝ ውቢቷ ባህር ዳር ላይ ከተምኩ ‹‹ ተቀበል እንግዲህ›› አዝማሪው ነው፡፡ ግለቱ ከተፋፋመበት አምሳል ምትኬ የባህል ምሽት ጉሸማ የተሞላበት ቅኔያዊ ግጥሞችን እየኮመኮምን ነው፡፡ ፊት ለፊቴ ከተቀመጡት ጥንዶች በቀር ሁሉም ከመጠጡ በላይ በግጥሞቹ ሰክሯል፡፡ ኮሚኒስታዊ  የሚመስል የማያቋርጥ ጭብጨባ ያስተጋባል፡፡ ሁሉም ለማሲንቆ ሰግዷል፡፡ ለከበሮም አጎብድዷል፡፡ እልም ያለ የጥበብ ዛር፡፡

የቤቱ ጩሀት ከጆሮ በላይ ነው፡፡ እንደውም ከዚህ ቀደም  አንድ ሰው የጎረቤቱን ትንሽ ልጅ ከበራፋቸው ላይ ያገኝና ‹‹ታዲያስ ማሙሽ ትላንት የተወለደው ህጻኑ ወንድምህ እንዴት ነው ?›› ቢለው ማሙሽ መልሶ ‹‹ እሱም ወዲያ ጥለው ቁራ ቢኖረን ይሻል ነበር፡፡ ካለ ጩኸት ስራ የለውም፡፡›› በማለት የመለሰለትን አስታወሰኝ፡፡ ከዘፈኑና ግጥሙ በላይ መልእክት አልባ ጩኸቶች አየሉብኝ፡፡

ዘመኑ የዘፈንና የጫት ምርት የበዛበት ሆኗል፡፡ በእርግጥ በዚህኛው ቤት ድብልቅ የአገር ባህል ዘፈንና ትውን ጥበብ ይታያል፡፡ ዳሩ ግን ባህሉ ዘመናዊነትን ተከናንቧል፡፡ በእኔ አገላለጽ ‹‹እየደረቁ መበስበስ›› ይባላል፡፡ ለምሳሌ ጸሀይ መሀል ዝናብ ሲጥል ዝናቡ ላይ የቆመ ሰው እየደረቀ ይበሰብስ የለ ልክ እንደዛ ማለት ነው፡፡ ወይ ባህላችንን ወይ መጤውን አልተቀበልን እንገርማለን እኮ፡፡ ምርጡን የጎጃም እንቅጥቅጥ ዘመናዊ በሆነው የአደናነስ ስልት ለመንቀሳቀስ ይቃጣናል፡፡

ብቻዬን እዝናናለሁ ብዬ ከገባሁበት ባህል ቤት ብቸኝነት ቁዘማ የመሰለው አዝማሪ ጠጋ ብሎ በግጥም ሊኮረኩመኝ ሲል ጠጋ ብዬ ገንዘብ እንደምሸልመው ስነግረው ወደ ሌሎቹ አቀና፡፡ ለካስ በአዝማሪ ቤትም ኪራይ ሰብሳቢነት ይሰራል፡፡ ወይ ጉድ፡፡ 

በነገራችን ላይ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት ሲነሳ ለመንግስት መስሪያ ቤት አዲስ የሆነ ሰው የመጀመሪያ ስብሰባውን ሲያደርግ በመድረኩ ‹‹ ሁላችንም በኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ ድረጊት ተጠምደናል!›› የሚል አስተያየት ሲሰነዘር ሰምቶ በተራው የመናገር እድል ሲሰጠው ‹‹ በነገራችን ላይ ቅድም የተነሳው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተያየት እኔን አይመለከተኝም፤ እኔ ያለችኝ አንዲት ጠባብ ክፍል ቤት ናት ለእኔም አልበቃችኝም እንዴት ብዬ ነው እሷን አከራይቼ ኪራይ የምበላው?›› ሲል ቤቱ በሳቅ አውካካ፡፡

‹‹የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀው›› የሚል አገርኛ ምሳሌ አውቃለሁ፡፡ ድብልቅልቅ ያለው የዝላዩና ሁካታ ድባብ አትኩሮቴን ጨመረልኝ፡፡ ከባህል ቤቱ ከመውጣቴ በፊት ብዙ ነገሮችን ለመታዘብ ሞከርኩ ነገር ግን ስሜት ነውና እኔም ለሙከራ ያክል ትከሻዬን ማንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡ ደግነቱ ጨለማ ሆነ እንጂ የእኔን አጨፋፈር ላየ ሰው ለሳምንት የወሬ አጀንዳ ሳልሆን አልቀርም ነበር፡፡ አጠገቤ የነበረው አንድ ሰው በስካር መንፈስ እግሩ ከእጁ ጋር ተሳስሮ እስኪጠፋበት ድረስ መሬት ላይ እየወደቀ እየተነሳ ይጨፍራል፡፡ አዝማሪዎቹ እንደጨረሱ  የጥላሁን ዘፈን ካልተከፈተልኝ ብሎ ቀወጠው ዲጄውም ተሳስቶ ይሁን አውቆ…. በማይታወቅ ምክንያት የነዋይን ዘፈን ከፈተ በስካር የጦዘው ሰውም ዘፈኑ የጥላሁን መስሎታል መሰለኝ… በነዋይ የጥቅምት አበባ ዘፈን… አይ ጥልሽ አይ ጥልሽ… እያለ ይደንስበት ጀመር፡፡ ራሱን እስኪስት ድረስ ጥለሁንንና ነዋይን መለየት አቃተው፡፡

ባህር ዳርን በቀን እንደማየት የሚያስደስተኝ ነገር የለም፡፡ ንጋትን እየናፈቅኩኝ ስገላበጥ አደርኩኝ፡፡ የጸሀይ ብርሀን ካረፍኩበት ክፍል ውስጥ በመስኮት ብቅ አለች፡፡ ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ ልብሴን ለባብሼ ቁርስ ቢጤ ቀምሼ ሞቅ ሲል ወደ ገበያው መሀል አቀናሁ፡፡ 

ቆይታዬን ለሌላው ጊዜ ተወት ላድርግና በዚህ መሀል ያየሁትን አንድ ነገር ብቻ ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡ በሄድኩባቸው ገበያዎች ሁሌም ሰዎች ሲከራከሩ ማየት ደስታዬ ነው፡፡ ክርክራቸው እየናረ ሲመጣ በጥሩ ደራሲ የተጻፈ ድራማ ይመስላል፡፡ ቴአትር ቤት ገብቼ ከማየው ተውኔት አይተናነስም፡፡ እናም የገና በአል እየደረሰ በመሆኑ በግ መግዛት አቅሙ ባይኖረኝም ለገዢዎች ዋጋውን ለመናገር የበግ ገበያ ውስጥ ተሰየምኩ፡፡ በገጠር አደግኩኝ ባይ አንድ ሰው ለገና በአል ጓደኛውን በግ ሊያጋዛ ወደ ገበያ ተያይዘው መጡ፡፡  በብዙ በጎች ላይ አቃቂር እያወጣ ሲያማርጥ አየሁት፡፡ ኋላም የአንዱን በግ አፍ አላቆ አየና ይሄስ የሸረፈ ነው! ቢለው በትችቱ ያልተደሰተው በግ ሻጭ ‹‹ ይተውት ጌታው ወርቅ ይተከልለታል ›› ብሎ መለሰለት፡፡

የገበያ አሰሳዬን ጨርሼ በመውጫው አካባቢ ስደርስ ያላሰብኩት ነገር ገጠመኝ፡፡ ከእኔው መኖሪያ መንደር ሸፍታ ወደ ቀድሞ አድባሯ የተመለሰች ጉብል መንደር ዳር ቆማ አገኘኋት፡፡

ልጅት ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ባህረ ገብ ከሆነችዋ ውቢቷ የጣና ዳር ፈርጥ ዘጌ በአንድ አዲስ አበቤ የፍቅር ቋንቋ ተወትውታ አብራው ኪሎ ሜትሮችን ተጉዛ ከሰፈሬ ከተመች፡፡  በባዶ እጅ በሙሉ ልብና የዋህነት፡፡ የቀዬዋ ዘዬና ልማድ አለቀቃትም፡፡ በሶፋ መቀመጫ መደብ ያምራታል፣ ለመዋቢያዋ ከቅባት ይልቅ ቅቤ ያሻታል፣ ከኤሌክትሪኩ ምጣድ ይልቅ ኩበት አንድዶ መጋገር ይቀናታል፡፡ ግን ግን ስልጣኔን ያለመረዳት አይደለም ማንነት እዚህ ድረስ ዘልቆባታ እንጂ፡፡ አርባ ሽንሽን ያልተለያት ልጅት አርባ ጊዜ ትሳቀቃለች፡፡ በራሷ ሳይሆን እሷን በሰፈሯት ዘመነኛ መሳይ ዘማዊያን፡፡

የፍቅር ዳርቻው ብዙ ሳይጓዝ ከእለታት በአንዱ ቀን አርባ ሽንሽኗን እንደለበሰች ኢዲስ አበቤው አዲስ ወዳጅ ከስራ ውሎ ሲመጣ ‹‹ ጌታዬ እግርዎን ይለአለኡ! ዘርጉና ልጠቦት›› አለች፡፡ ከመንደሬው ኪስ አጣቢ ሌላ እግር አጠቢ ተገኘ፡፡ ‹‹ለዘመናት ኪሴን እንጂ እግሬን የሚያጸዳልኝ አልነበረም፤ እነሆ የሰከነች አክባሪ ወዳጅ ስጦታ በማግኘቴ ፈጣሪ ይመስገን፡፡›› አለ፡፡ ከማስመሰል ተቆጥቦ ውስጡን ሀሴት ሞልቶት፡፡

ይህንን ያዩ እነ ‹‹እንብላውና እንጋጠው›› ጥጋ ጥግ መሄዱ ቢያስጨንቃቸው ከማታለል ይልቅ ማማለልን ተያያዙት፡፡ ከንፈርን የጦም በየአይነት የተበላበት ትሪ ማስመሰል፣ ህጻን ልጅ ዘሎ የማይደርስበትን ቀሚስ ቢጤ መልበስ፣ ሰባት ሰው ጎትቶ ማውለቅ የማይችል ጥብቅብቅ ያለ ሱሪ መልበስ ወዘተ… የማማለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ስርአት አክባሪውን ማስቀናት ስራቸው ሆነ፡፡ ልብን ንቆ ለውስጣዊ ውበት ያደላው አቶዬም አስኮብልሎ ያመጣትን ልጅት ፈትቶ ሌላ አገባ፡፡ በዚህ የተጎዳች ልጅት የት እንደገባች ሳይታወቅ ከረመች፡፡ ፈርጥጣ የገባችበት ባህር ዳር ግን ርቀቱን አቅርቦ ስውሩን አርቅቆ እንዳያት አደረገኝ፡፡  ከገበያው ጫፍ ላይ… ሳምንት ይቀጥላል፡፡

አዲሱ ገረመው – አዲስ ዘመን

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *