በነቀምቴ እና በደንቢ ዶል የተከሰተውን የህዝብ ተቃውሞ መነሻ በማድረግ የኮማንድ ፓስት ሰክሬታሪያት ዛሬ ለጸጥታ ሃይሎች መመሪያ አስተላለፈ። በዚሁ መግለጫ መሰረት አዋጁን በሚጥሱ ላይ አስፈላጊ የተባለውን ርምጃ ሁሉ እንዲወሰዱ አዟል። በነቀምቴ ሰዎች መጥይት መመታታቸውና ቁጥሩ በውል ያልተገለጸ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

ፋና ይህንን ዘግቧል – የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አዋጁ ከወጣ ወዲህ የፀጥታ ሀይሎች ባደረጉት ፈጣን እንቅስቃሴ እና ሰላሙ ታውኮ በቆየው ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እና ትብብር ከሞላ ጎደል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተረጋጋ እና ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ የመጣ ቢሆንም ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በነቀምትና ደምቢዶሎ ከተሞች ህገወጥ ሀይሎች የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ጥረት ከማድረግ ባሻገር በፀጥታ ሀይሎች ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አደጋ ለማድረስ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ነው የገለፀው።

የፀጥታ ሀይሎች ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን የሰው ህይወት እንዳይጠፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን የገለፀው መግለጫው፥ በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት እየተቸገሩ እና አልፎ ተርፎም ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ትእግስት በተሞላበት ሁኔታ አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ብሏል።

እነዚህ ሀይሎች ከዚህ የጥፋት ድርጊታቸው በአፋጣኝ የማይቆጠቡ ከሆነ በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ እና በመመሪያው መሰረት በእነዚህ አካላት ላይ አስፈላጊ የተባለውን እርምጃ ሁሉ እንዲወስዱ ለፀጥታ ሀይሎች ትእዛዝ መሰጠቱን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት ፅህፈት ቤት በመግለጫው አስታውቋል።

ከዚህ ሌላ በኦሮሚያ ክልል የህዝብ ተወካዮች አባላት የመኖሪያ ቤት እና አድራሻ በተለያዩ የማህብራዊ ሚዲያዎች በማሰራጨት ፀረ ሰላም ሀይሎች በአካል እቤታቸው ድረስ በመሄድ እና ስልክ በመደወል እያስፈራሯቸው መሆኑን የህዝብ ተመራጮቹ ራሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው ለኮማንድ ፖስቱ ተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

ይህ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ እና ፍላጎትን በሀይል ለመጫን የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ ነው ያለው ኮማንድ ፖስቱ ድርጊቱን በቸልታ እንደማይመለከተው አስታውቋል።

በዚህ ተግብር ላይ በተሰማሩ ሀይሎች ላይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አመልክቷል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኘው ህዝቡ የራሱን ህይወት እና ንብረት ከፀረ ሰላም ሀይሎች ጥቃት ለመጠበቅ ከፀጥታ ሀይሎች ጎን ተሰልፎ መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ለኮማንድ ፖስቱና ለፀጥታ ሀይሎች እየሰጠ ላለው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል።

የሀገሪቱን ሰላም ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ መንግስት እና የፀጥታ ሀይሎች የሚያደርጉት ጥረት እንዲሳካ ህዝቡ የጀመረውን ሁለገብ ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ፅህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

ፋና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *