ከዚህ በፊት በአሜሪካ ምክርቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በረቂቅ ሕግነት ከቀረቡት መካከል ህወሓት/ኢህአዴግ HR 128 እጅግ ፈርቶታል። ይህንን ረቂቅ ሕግ ለማክሸፍም የውትወታ (ሎቢ) ሥራ ከመሥራት ጀምሮ የአሜሪካ ባለሥልጣናትንና የፖለቲካ መሪዎችን በ“አልሻባብ ምስራቅ አፍሪካን ይወራል” ድራማ ለማስፈራራት ተደጋጋሚ በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርግም አልተሳካለትም። ላለፉት በርካታ ወራትም (በቅርቡ ወደ አሜሪካ የመጡትን እነ ወርቅነህን ጨምሮ) ሊያሳምኑ ይችላሉ የሚላቸውን ሹሞቹን በመላክ ረቂቅ ሕጉ በተግባር እንዳይውል የአሜሪካ ባለሥልጣናትንን – ጊዜ ስጡን፣ ሁሉን እናስተካክላለን፣ … የመሳሰሉ ተማጽንዖዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በግምባር ቀደምትነትም የህወሓት ወዳጅ የሆኑት ሴናተር ኢንሆፍ ህወሓት/ኢህአዴግን ለመታደግ ኢትዮጵያ ድረስ እስኪሄዱ ያደረሰ የውትወታ ሥራ ተካሄዷል።

ይህንን ረቂቅ ህግ ገና ከጅምሩ የፈራው ህወሓት ለወትዋቾች (ሎቢይስቶች) በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል። በዋሽንግቶን ዲሲ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ተጠሪ የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ SGR Government Relations ከተባለ የወትዋቾች ድርጅት ጋር በተፈራረሙት ሰነድ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ለዚህ የውትወታ ሥራ ድርጅቱ (SGR) በወር 150ሺህ ዶላር፤ በጥቅሉ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎት ረቂቅ ሕጉን የማክሸፍ ዘመቻ እንዲሠራ ስምምነት ተደርጓል።

ይህንን ሁሉ አድርጎ ረቂቅ ሕጉ ፀሐይ እንድትጠልቅበት በሥፋት ሲንቀሳቀስ የነበረው ህወሓት ድርጎ ሰፋሪዎቹን “ያሁኑን ብቻ ማሩኝ ሁሉን አስተካክላለሁ፤ እስረኞችን እፈታለሁ፤” … በማለት ተማጽንዖ በማቅረቡ እስከ ፌብሩዋሪ 28 ድረስ ገደብ ተሰጥቶታል። በማንም በምንም አንደፈርም እያለ ምስኪኖች ላይ ሲደነፋ የነበረው ህወሓት ይህ ረቂቅ ሕግ ለምንድነው ይህንን ያህል ያስፈራው? ለሚለው ጥያቄ ብዙ ምላሾች ቢኖሩም ዋንኛው ግን በረቂቅ ሕጉ ውስጥ የተጨመረው የማግኒትስኪ ሕግ ነው።

የHR 128 ረቂቅ ሕግ ተራ ቁጥር 8 እንዲህ ይላል፤ “(ዜጎችን) ያለ ፍርድ በመግደል፣ በማሰቃየት (ቶርቸር በማድረግ)፣ ወይም ሌሎች በዓለምአቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸውን የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በማንኛውም ዜጋ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የፈጸሙ “በዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ የሰብዓዊ መብቶች ተጠያቂነት ሕግ” መሠረት ማዕቀብ እንዲጣልባቸው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር (ስቴት ዲፓርትመንት) ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዲተገብር (የአሜሪካ) እንደራሴዎች ምክርቤት ጥሪ ያደርጋል”።

ለመሆኑ ይህ ዓለምአቀፉ የአሜሪካ የማግኒትስኪ የሰብዓዊ መብቶች ተጠያቂነት ሕግ ምንድነው? ህወሓትስ የፈራው ለምንድነው? ከHR 128 ጋር ተዳብሎ በረቂቅ ሕጉ ውስጥ መካተቱ ለምን አስፈለገ? የሚያስከትለውስ ተጽዕኖ ምንድነው? ይህንን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ ጥበቃ ድርጅት (Human Rights Watch) በድረገጹ ላይ በጥያቄና መልስ ያቀረበውን ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ በዚህ መልኩ ተርጉሞታል።

አጭር መግቢያ

ሕጉ የተሰየመው ሩሲያዊው የንግድ ሒሳብ ሠራተኛ በነበረው ሰርጊዬ ማግኒትሰኪ ነው። ሰርጊዬ በሩሲያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሳተፉበትን ግዙፍ የግብር ማጭበርበር ዕቅድ በማጋለጥ ውስጥ በተጫወተው ሚና ባለሥልጣናቱ እርሱን ዒላማ በማድረግ ካሳሰሩት በኋላ እኤአ በ2009 ዓም በሞስኮ በሚገኝ እስርቤት ማሰቃየት ደርሶበት (ቶርቸር ተደርጎ) እና የህክምና ዕርዳታ እንዳያገኝ ተከልክሎ እዚያው ሞቶ ተገኘ።

በሰርጊዬ ማግኒትስኪ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ ተሳትፎ በነበራቸው የሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ በ2012 ዓም በስሙ ሕግ አወጀ። ሕጉም እነዚህ ወንጀለኞች በአሜሪካ ያላቸው ማንኛውም ንብረታቸው እንዲታገድ እነርሱም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ በጥብቅ የሚያግድ ሆኖ የታወጀ ነው።

በቀጣይ ጉዳዩን ዓለምአቀፋዊ ተጠያቂነት በሚያስከትል መልኩ ለመተግበር ኮንግረስ በሩሲያ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ያጸደቀውን ሕግ በ2016 ዓም ዓለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማሰብ አሳደገው። በዚህም መሠረት ሕጉ የሥራ አስፈጻሚውን ቅርንጫፍ በተለይ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት የፈጸሙና በሙስና የተዘፈቁ የተወሰኑ ግለሰቦችን ቪዛ ለመከልከልና በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ቢገኙ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፈቃድ እንዲኖረው በሚያደርግ መልኩ የሰፋ ሆነ። ይህ በሁለቱም የአሜሪካ ፓርቲዎች ድጋፍ ያገኘ ሲሆን ረቂቅ ሕጉን ዓለምአቀፋዊ ይዘት በመጨመር አስተካክለው የሜሪላንዱ ጠቅላይ ግዛት ዴሞክራት ሴናተር ቤን ካርዲን አምስት ሪፓብሊካን እና አምስት ዴምክራት ሴናተሮችን በማስፈረም የረቂቁ ተባባሪ ስፖንሰሮች እንዲሆኑ በማድረግ በሕግ እንዲጸድቅ አደረጉ። በቀጣይም ፕሬዚዳንት ኦባማ ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው አንድ ወር በፊት ፊርማቸውን በማኖር ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ አደረጉ።

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ የሚያደርገው ምንድነው?

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ የሰብዓዊ መብቶች የተጠያቂነት ሕግ (Global Magnitsky Human Rights Accountability Act) የተወሰኑ “የውጭ ሰዎችን” (ግለሰብ ወይም ድርጅት ሊሆን ይችላል) ቪዛ እንዳያገኙ ለመከልከል፣ ለመሻር፣ ለመዘረዝ፣ ለመንጠቅ እንዲችል ወይም ንብረታቸው ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለፕሬዚዳንቱ ሙሉ ሥልጣን ይሰጣል። ሰዎች ማዕቀብ የሚጣልባቸው፤

  1. “ፍትህ ሳይበየን ግድያ፣ ስቅየት (ቶርቸር ማድረግ) ወይም በዓለምአቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን” በሌሎች ሰዎች ላይ ከፈጸሙ፤ ወይም
  2. የመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከፍተኛ ተባባሪዎች በመሆን “መጠነ ሰፊ የሙስና ተግባር” ከፈጸሙ ነው

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ ለምንድነው ጠቃሚ መሳሪያ የሆነው?

ሕጉ የሰብዓዊ መብቶች በሁሉም የመንግሥት የሥልጣን ዕርከኖች እንዲከበሩ የሚያበረታታ ሲሆን የሰብዓዊ መብቶችን በጣሱ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ እስከ ዝቅተኛ ግለሰቦች ድረስ ይህም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተባባሪዎቻቸውን ጨምሮ በእነርሱ ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ የአሜሪካ የሥራአስፈጻሚው አካል እንዲጥል የሚያስችል ነው። ይህ ማዕቀብ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ንብረት ሆነ ገንዘብ ከማገድ ጀምሮ ግለሰቦቹ ወደ አሜሪካ እንዳገቡ ቪዛ እስከመከልከለ የዘለቀ ነው። … ይህንን ሕግ በማስከበር አገራት ከአሜሪካ ጋር በሚያብሩበት ጊዜ በአገራቸው ለሚገኙ የሰብዓዊ መብቶችን ለሚጥሱ ግፈኞች ትዕግስት እንደሌላቸው ያሳያሉ።

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ የሚጥለው ማዕቀብ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

የሚጣለው ማዕቀብ ግለሰቦችን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማገድ፣ በዚህ አገር ውስጥ ያላቸውን ንብረት መቆጣጠር እና ከበርካታ ባንኮች እና ኩባንዎች ጋር ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ እንዳያደርጉ መከልከልን ያካተተ ነው። ከእነዚህ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ግለሰቦች ጋር ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ የአሜሪካ ድርጅቶች እና/ወይም አሜሪካ ቅርንጫፍ ያላቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ይህንን ሕግ እንደጣሱ ተቆጥሮ በሕግ ይጠየቃሉ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዚህ ሕግ ላይ ያላቸው አቋም ምንድነው?

ባፈው ዓመት ሚያዚያ ወር (ኤፕሪል 20፣2017) ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለኮንግሬስ አባላት በላኩት ደብዳቤ የእርሳቸው አስተዳደር ይህንን “አስፈላጊ ሕግ እንደሚደግፍ” እና “ለተግባራዊነቱ ያለንን ቁርጠኝነት” እንገልጻለን ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤያቸው እንደገለጹት አስተዳደራቸው ሕጉ ተግባራዊ ሊደረግባቸው የሚገቡ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በመለየት ሂደት መሆኑን በመጠቆም “በተግባር ለመፈጸም አስፈላጊውን ማስረጃ እየተሰበሰበ” እንደሆነ ገልጸዋል። እስካሁን በሥልጣን በቆዩባቸው ወራት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል ተግባር ባይፈጽሙም፤ ፕሬዚዳንቱ ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ ተግባራዊ በማድረግ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥበቃ ማድረግ አሁንም የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መሠረታዊ ዓላማ መሆኑን የማሳየት ዕድሉ አላቸው።

ግለሰቦች ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ለፕሬዚዳንቱ ሐሳብ የሚያቀርበው ማነው?

ሕጉ እንደሚለው ከሆነ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር (ስቴት ዲፓርትመንት) የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና የሠራተኞች ረዳት ሚኒስትር (ጸሃፊ) ከሌሎች የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ባለሥልጣናት ጋር በመመካከር ለሚኒስትሩ ማዕቀብ ሊጣልባቸው የሚገቡ ሰዎች ስም ዝርዝር ያቀርባል። በሕግ መወሰኛው ም/ቤት (ሴኔት) የባንክ፣ የቤቶች እና ከተማ ጉዳዮች ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ እንዲሁም በእንደራሴዎች ም/ቤት የፋይናንስ አገልግሎቶች ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ለፕሬዚዳንቱ ስም ዝርዝር ሊያቀርቡ ይችላሉ።  ማዕቀቡን መጣል ተገቢ መሆኑን ለመወሰን ፕሬዚዳንቱ ሌሎች አገራትና የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰቶች በሚከታተሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያወጧቸውን ተዓማኒነት ያላቸውን መረጃዎች በድጋሚ ሊመለከቱ ይችላሉ። ይህም ሆኖ የተግባር አሠራሩ በአብዛኛው የሚከናወነውና ማዕቀቡ የሚጣለው የውጭ ጉዳይ እና የገንዘብ ሚ/ር መ/ቤቶች በጥምረት በሚያደርጉት ውሳኔ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ በተመለከተ ምን እየተደረገ ነው?

በሕግ መወሰኛው ም/ቤት የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ ካሉት አባላት የላቀ ደረጃ ያላቸው ሴናተር ካርዲን እና የውትድርና አገልግሎቶች ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ሴናተር ጆን ማኬይን ባለፈው ነሐሴ ወር ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በጻፉት ደብዳቤ በዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግ መሠረት ማዕቀብ ሊጣልባቸው የሚገቡ የ20 ግለሰቦችን ስም ዝርዝር ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንቱም ደብዳቤውን ከተቀበሉ በኋላ መስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ በሕጉ መሠረት የገንዘብ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማዕቀብ እንዲጥሉ በይፋ ሥልጣን ሰጥተዋቸዋል።

ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግን የሚመስል ሕግ ሌሎች አገራት አሏቸው?

በርካታ የአውሮጳ አገራት፣ ካናዳ እና የአውሮጳ ፓርላማ ከሰርጊዬ ማግኒትስኪ ሞት ጋር ግንኙነት ባላቸው የሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ ሕግ አውጥተዋል። በቅርቡ በርካታ አገራት የሚጥሉትን ማዕቀብ ሰፋ በማድረግ የሰብዓዊ መብቶችን የጣሰ የየትኛውም አገር አገዛዝ ማዕቀብ እንዲጣልበት ወስነዋል። በያዝነው የካቲት ወር (ፌብሩዋሪ 21) ታላቋ ብሪታኒያ የአሜሪካው ዓለምአቀፍ የማግኒትስኪ ሕግን የሚመስል የራሷን ሕግ አጽድቃለች። ኢስቶኒያ እኤአ በ2016 ተመሳሳይ ሕግ አውጥታለች። የካናዳ ፓርላማ እና የአውሮጳ ፓርላማ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የጣሱ ሁሉ ላይ ያነጣጠሩ ረቂቅ ህጎችን እያወጡ ነው።

ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ከዚህ ሕግ ጋር በተያያዘ እስካሁን ተግባራዊ የሆነባቸው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች እንዳሉ ባደረገው ፍለጋ ይህንን አግኝቷል፤

የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባለፈው ታህሳስ ወር ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ15 የውጭ አገር ዜጎችና 37 ድርጅቶች ላይ ዓለምአቀፉ የማግኒትስኪ ሕግን ተግባራዊ በማድረግ ማዕቀብ ጥለውባቸዋል። ማዕቀቡ የተጣለባቸው ከ12 በላይ በሚሆኑ አገራት የሚገኙ ኃያላን ፖለቲከኞች የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፤ በፖሊስና መሰል የሕግ አስፈጻሚ አካላት ውስጥ የሚገኙ፣ የመከላከያ አመራሮች፣ ሌሎችም ይገኙበታል። በውሳኔው መሠረት ግለሰቦቹ የንብረት እና የቪዛ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል። ከእነዚህም መካከል የአባቱን ሥልጣን ሽፋን በማድረግ ጠቀም ያለ ትርፍ የሚያስገኙ የመንግሥት ጨረታዎችንና ኮንትራቶችን ተፎካካሪ ነጋዴዎች ላይ ጫና በማድረግ ሲያሸነፍ የነበረው የሩሲያው ጠቅላይ ዓቃቤሕግ ዩሪ ቻይካ ልጅ አርቴም ቻይካ፤ በበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂ የሆነውየቼችኒያ መሪ ራምዛን ካዲሮቭ፣ በበርማ የሮሂንጋ ሕዝብ ላይ የሰብዓዊ መብቶች በመጣስ በኃላፊነት የሚጠየቀው ወታደራዊ ኮማንደር ማውንግ ማውንግ ሶዪ፣ እንዲሁም በቻይና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆነውን ካዎ ሹንሊ ለእስር፣ ለስቅየትና ለሞት የዳረገው የቻይና ከፍተኛ የፖሊስ ሹም ጋዖ ያን ይገኙበታል።

ህወሓት HR 128ን ለምንድነው የፈራው የሚለውን ጥያቄ በፍሪደም ሃውስ የአፍሪካ ከፍተኛ የፕሮግራም ኦፊሰር የሆኑት ዮሴፍ ባድዋዛ በቅርቡ ባወጡት መጣጥፍ ላይ እንዲህ በማለት መልሰውታል፤ “ኢትዮጵያ የምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ዋንኛ ትኩረቱን ያደረገው የተሳካ የልማት ተግባር አከናውኛለሁ፤ የሰላም ሻምፒዮን ነኝ፤ ውጥረት በነገሠበት የአፍሪካ ቀንድ የመረጋጋት ተምሳሌት ነኝ በማለት ነው። ይህ የስኬት ትርከት መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ሲሆን ደጓሚዎቹም አሜሪካ ብቻዋን ሳትሆን ሌሎች በዓለም የሚገኙ ለጋሽ መንግሥታትና ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ናቸው።

አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ፣ በቅርቡ የዓለም ባንክ እስከ 5ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የአምስት ዓመት የጋራ ወዳጅነት ስምምነት ተፈራርመዋል። ከዚህ አንጻር ይህ ረቂቅ ሕግ ከፀደቀ ይህ ሁሉ የስኬት ትርከት ገደል ይገባል፤ ይህም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ በአገሪቱ ሊያስከትል ይችላል።”

የዚህ ረቂቅ ሕግ ዋንኛ አዘጋጅና አቅራቢ የሆኑት ሪፓብሊካኑ ክሪስ ስሚዝ ይህ ሕግ እንዲፀድቅ አሜሪካ ለምን አቋም መውሰድ እንዳለባት ሲገልጹ “ሕጉ የኢትዮጵያ መንግሥት (ህወሓት/ኢህአዴግ) የሰራውን ሥራ ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ መስታወት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራውን በመስታወት ማየቱ ብዙም የሚያስፈራው አይደለም፤ ሆኖም ዋናኛ ፍርሃቻው ለረጅም ጊዜ ቸልታን የመረጠችው አሜሪካ (በኢትዮጵያ) ስለሚካሄደው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ድምጽዋን ለማሰማት ፈቃደኝነት ማሳየቷን (በመጥቀስ) ለለጋስ ድርጅቶችና መንግሥታት በማሳየቱ ላይ ነው” ብለው ነበር። የአሜሪካ ድምፅ የዓለም ድምፅ የመሆን ስፋት ስላለው HR 128 በአሜሪካ የመጽደቁን ሁኔታ ተከትለው ሌሎችም አገራት ተመሳሳይ እርምጃ በህወሓት ላይ መውሰዳቸው አይቀሬ ይሆናል።

ህወሓት ይህንን ሕግ ለማኮላሸት በርካታ ስልቶች ቢጠቀምም፣ እስረኞችን ቢፈፈታም፣ የውስጥ ማንነቷ ግን ለውጥን እንድትቀበል የሚያደርጋት አይደለም። በመሆኑም ይህ ረቂቅ ሕግ ከማግኒትስኪ ሕግ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በርትተው በመሥራት ለውሳኔ እንዲቀርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በHR 128 ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ካለው የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የሲቪክ ምክርቤት – Ethiopian Americans Civic Council in Colorado (EACC) ጋር ሊተባበሩ ይገባቸዋል። ምክርቤቱን ለማግኘት የሚከተሉትን አድራሻ በመጠቀም ምን ማድረግ እንዳለባቸው በቂ መረጃ ለማግኘትና በግፍ ለተገደሉትና ለተሰቃዩት ወገኖች ሲሉ የበኩላቸውን ለመፈጸም ይችላሉ። Email: Info@hr128.org, Facebook: H.Res. 128 Respect Human rights in Ethiopia, Twitter: @Ethio-American Civic Council, phone: 720 477 5711. HR 128 በሕግ መጽደቅ ይገባዋል።

ይህ ዘገባ  ሙሉ በሙሉ ከጎልጉል የድረ ገጽ ጋዜጣ የተወሰደ ነው። ርዕሱና የፊት ምስሉ ለዛጎል እንዲመች ተደርጎ ተቀይሯል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *