ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደሚለቁ ካስታወቁ እነሆ እሑድ ሲመጣ (ይህን ጽሑፍ የምታነቡት እሑድ ነው ብዬ ነው) 18ኛ ቀን ሆነ፣ በዚህ ምክንያትም ባይሆን፣ ከዚህ ጋር ግንኙነት ይኑረውም አይኑረውም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የታወጀው በማግሥቱ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ከፀናበት ቀን ጀምሮ ሲቆጠር ደግሞ አሥራ አምስት ቀን የሚሞላው (የሞላው ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው)፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው የካቲት ወር ውስጥ በመሆኑና የካቲት ደግሞ በየዓመቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእረፍት ጊዜ ስለሆነ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመስተዳደሩ ለራሱ የሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ለፓርላማው በ48 ሰዓት ውስጥ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምክር ቤቱ መቅረብ ያለበት በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ቢሆንም፣ እስካሁን በምንሰማው ይፋ ያልሆነ ወሬ መሠረት ፓርላማው የሚሰበሰበው ባለቀ፣ ምናልባትም በተቃጠለ፣ ለዚያውም የሕዝብ በዓል በሆነ ቀን የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 እና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 15 መሠረት፣ ምክር ቤቱ በእረፍት ላይ እያለ የምክር ቤቱን ውሳኔ የሚሹ አስቸኳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል ይላል፡፡ የሚጠራውም አፈ ጉባዔው ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆኑ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ሲጠይቁ እንደሆነና አጠራሩም አፈ ጉባዔው የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው በማለት ይደነግጋል፡፡

በጠቅላላው ይህን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት እስከማውቀው ድረስ የምንገኘው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ድንጋጌው የመጀመርያ ዙር የአሥራ አምስት ቀን ዕድሜ (በተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ በስተቀር) በመጠናቀቅ ላይ ባለበት ወቅት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ተተኪ የሚመረጥበት፣ ወይም የሚመድብበት፣ ወይም የሚሰየምበት ሥርዓትና አሠራር ‹‹የአገር ጉዳይ›› የሆነውን ያህል ይፋና የአደባባይ የሁሉም ሰው አጀንዳ ሳይሆን ነው፡፡

ካለፈው ድንገተኛ ተሞክሯችን አኳያ በእርግጥ ጊዜው ገና ነው፡፡ ያለፈው ልምዳችን ማለት በአቶ መለስ ምትክ አቶ ደሳለኝ የተመደቡበት ወይም የተመረጡበት ነው፡፡ ለማስታወስ ያህል አቶ መለስ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ሞቱ ይኼው ነሐሴ 15 ቀን በማግሥቱ ተነገረን፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ነሐሴ 27 ቀን ተፈጸመ፡፡ የኢሕአዴግ ምክር ቤት መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን መረጠ፡፡ መስከረም 7 ቀን 2005 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስከረም 11 ቀንን አስቸኳይ ስብሰባ በይፈ ጠራ፡፡ መስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰበሰበው አስቸኳይ ስብሰባ የአገሪቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ሰየመ፡፡ በዚህ መሠረት የ‹‹መተካካቱ››፣ ምትክ የመሰየሙ፣ ወይም የምደባው ሥራ የተከናወነው በአንድ ወር ከሳምንት (32 ቀናት) ባልበለጠ ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ሥሌት ገና እኮ ነው ይባል ይሆናል፡፡ አረማመዳችን መለካት ያለበት ግን በተቋቋመ የተዘረጋ አሠራር መሠረት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዛሬም ከስድስት ዓመታት በኋላ ከዚህ በፊት ከተነሱት ጥያቄዎችና ውዥንብሮች ያወጣ ዕድገት አላሳየንም፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት የኢሕአዴግ ጉባዔ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም. የድርጅቱን ሊመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ከመረጠ በኋላ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫው፣ ከሌሎች መካከል በ‹‹አመራር ግንባታ›› ላይ መነጋገሩንና ውሳኔ መስጠቱን ነግሮናል፡፡ ‹‹የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ተሞክሮዎችንና ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመር የአመራር ግንባታና የህዳሴው ጉዞ በሚል ርዕስ ቀደም ሲል በታላቁ መሪ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ›› መወያየቱንና ውሳኔ መስጠቱን ገልጾልን ነበር፡፡ ከአመራር ግንባታ መካከከል የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ልዩ ልዩ ዝርዝር ጉዳዮች አፍታትቶ፣ ይዘት፣ ልክና መልክ ሰጥቶ ቁርጥና ቁልጭ አድርጎ መወሰንን፣ በተለይም የፓርቲውን መሪዎችና ለሕዝብ ለምርጫ የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች ምርጫ ሥርዓትን የሚመለከቱ ጉዳዮች መሠረታዊና ወሳኝ ናቸው፡፡ እነዚህንም ከአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ከሌሎች ሕጎች ጋር ማጣጣምን፣ እንደ መንግሥት ደግሞ የአገሪቱን ልዩ ልዩ ሕጎች ከዚህ አንፃር መፈተሸን፣ ማሻሻልንና ማጣጣምን ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለንበት ተጨባጭና በምንገኝበት ልዩ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የሌለንና የጎደለን ይኼው ነው፡፡ ከተፈጠረው ለየት ያለ (በአቶ መለስ ሞት ጊዜ ያልነበረ) ነገር ጋር ቃጭል የተጨመረበትን ድንብርብራችንን ያወጣውም እሱ ነው፡፡

ልክ እንደ 2010 ዓ.ም. 2005 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት ነበር፡፡ የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ የሚካሄድበት ዓመት፡፡ በዚያ የ2005 ዓ.ም. የካሌንደርና የምርጫ ዓመት መጀመርያ ላይ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ከኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባና ውሳኔ በኋላ አቶ ኃይለ ማርያም ባደረጉት ንግግር (ኢሕአዴግ ምክር ቤት ውስጥ)፣ ‹‹ስለተደረገው ምደባ እናመሰግናለን፡፡ ምደባው ለመስዋዕትነት፣ ምደባው የጓዳችንን ሌጋሲ ለማስቀጠል፣ ምደባው ሕዝቡ ከኢሕአዴግ የሚጠብቀውን ሁሉ በሙሉ መስዋዕትነት ለመፈጸም፣ ምደባው በሙሉ የምክር ቤት አባላት ድጋፍና በእናንተ ሙሉ ምክርና ከኋላችንና ከፊትም በምታደርጉት አስተዋጽኦ የተሳካ ውጤት ለማምጣት የተደረገ ነው ብዬ ነው የማምነው በግሌ፤›› ብለው ነበር፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም በትልቁ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ የ‹‹ምደባ››ው ጊዜ ሳይደርስ (ከ2012 ዓ.ም. ምርጫ በፊት) ኢሕአዴግ በተሃድሶ የደገሰው ‹‹የመፍትሔ አካል ለመሆን›› ሥልጣን ለቀዋል፡፡ ከምደባው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን የሚያስተናግድ፣ መስተንግዶውንም ከፓርቲው የውስጥ አስተዳደርና መተዳደሪያ ደንብ፣ ከመንግሥት ሕግና ከመረጣቸው ሕዝብ ጥቅም ጋር የሚያጣጥምና የሚያቆላልፍ ሕግና መረማመጃ አለን ወይ? የመደባቸው ፓርቲ የሚያነሳበት አሠራር፣ ደግሞም እንደገና ሌላ ተተኪ የሚመድብብት አካሄድ፣ እንኳንስ የመላው ሕዝብ የራሱ የፓርቲው አባላት ከምክር ቤቱ በታች ያለ የፓርቲው አመራር ንቃትና ግንዛቤ ሆኗል ወይ? ‹‹ምደባውን›› እንዲሁም ከምደባ የማንሳቱን ተግባር በሕጋዊና በሰላማዊ ዴሞክራሲዊ መንገድ ‹‹እንቢ››ና አቤት የሚሉበት፣ የሚሰሙበት፣ ለሕዝብ የሚነግሩበት ብሎም በሰላም የሚሰነባበቱበት መድረክ ገዥው ፓርቲ፣ መንግሥትና አገር ያውቃሉ ወይ? እነዚህን ሁሉ ሕዝብ በተለይም ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ ሆ ብሎ የተነሳባቸው የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል ናቸው፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ‹‹ከድርጅት ሊቀመንበርነትና ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒትርነት በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ›› ባቀረቡበት ኦፊሲያል ንግግር እንደነገሩን፣ ‹‹ . . . በቀጣይ ጊዜም የመጨረሻው የሥልጣን ሽግግር በተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚከናወንበት ጊዜ በበኩሌ ያለኝን መልዕክት የማስተላልፍ … ›› መሆኑን እገልጻለሁ ብለው ለአሁኑ ግን ‹‹ሕዝቡ የመፍትሔው አካል እንዲሆንና በአገራችን ዋስትና ያለው ሰላም እንዲረጋገጥ ዘላቂነት ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ የሆነውን የሕዝቡን ሚና ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከፍ ሲል ካነሳሁት ጥያቄ ማዕዘንም ‹‹መላው የኢሕአዴግ አባላትና የኢሕአዴግ መዋቅር በሚቀጥለው ጊዜ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፍፁም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተካኝን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ይመርጣል ብዬ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የሚለቅቁ መሆኑን ካስታወቁበት ንግግር በላይ ለምን እንደለቀቁ፣ ምን ሆነው እንደሚለቁ ይበልጥ ዘርዘር አድርገው የልባቸውን ቢነግሩን ደስ ይለናል፡፡ ከተቻላቸው ይህንን ዝርዝር ቀጠሮ በያዙለት ‹‹ . . . በቀጣዩ ጊዜ›› የሥልጣን ሽግግሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት በሚከናወንበት ጊዜ ቢነግሩን ደስታውን አንችለውም፡፡ ጥያቄው ግን ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በተባለው መድረክ ማለትም የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሰያየም ሥርዓት በሚፈጸምበት የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደ ሕግ፣ እንደ ተቋቋመ ደንብ፣ እንደማይገሰስ አሠራርና ሥርዓት፣ እንደ መብትም፣ እንደ ግዴታም ይገኛሉ ወይ? ወይስ የሚገኙት በቦሎሶ ሶሬ ቁጥር 2 (አረካ) ተመራጭነታቸው ነው? የሚለው ነው፡፡ ይህንን አበጃጅተን፣ አደራጅተንና ሥርዓት አድርገን ያቋቋምንበት ዋስተና ያለው አሠራር የለንም፡፡ አሠራራችን ሁሉ የቢሻኝ አካሄድ ሆኖ በማረፉ ይህን የማድረግም ያለማድረግም የቢሻኝ ውሳኔያችን ‹‹የተጠበቀ›› ነው፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ያቀረቡት ጥያቄ ላይ የመጨረሻው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በሥራቸው ላይ እንደሚቆዩ ገልጸው፣ ‹‹መላው የኢሕአዴግ አባላትና የኢሕአዴግ መዋቅር በሙሉ በሚቀጥለው ጊዜ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፍፁም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተካኝን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ይመርጣል ብዬ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ፤›› በማለት ምኞታቸውንና እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ የንግግራቸው ክፍልም ውስጥ ተፈልቅቀው የሚወጡ መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የመጀመርያው ጉዳዩ በተነሳበት ቅደም ተከተል መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ኃላፊነት ላይ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እስኪያገኝና ከሁሉም በላይ ደግሞ ተተኪያቸው እስኪሰየም ድረስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትርንት የሚቆዩ መሆኑን የሚመለከተው ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው? የኢሕአዴግን ሊቀመንበር የመምረጥና ሊቀመንበሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የመሰየም ሚና የሚጫወቱት አካላት በዚህ ረገድ የተጣለባቸውና ‹‹አፍጥን›› የሚላቸው የጊዜ ገደብ አለ ወይ? ከዚህ በላይ ደግሞ ይበልጥ የሚያሳስበው ሥራውን የመልቀቅ ጥያቄ ያቀረበ የመንግሥት መሪ በሥልጣን ላይ በ‹‹ጊዜያዊነት›› በሚቆይበት ጊዜ የባሰ ሊተኮርበት የሚገባው የሥልጣኑ ዳር ድንበርና ገደብ ነው፡፡

ለዚህ ጉዳይ መስጠት ያለብንን ትኩረት ስንመዝንና ስናስተነትን ስለመፍትሔውና ስለሚበጅለት መላ (እስከ ዛሬም ስላልተበጀለት መላ) ስንነጋገር አንድ ወይም ሌላ ሰው እያሰብን፣ ወይም አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን እያየን አይደለም፡፡ አንዳንዱ አለዚያም ብዙ ሰው እንደሚያስበው ሰውየው ጥሩ ሰውና ሃይማኖተኛ መሆናቸው፣ ወይም በምሪት ይሠሩ የነበሩ፣ ጠባቂ ያለባቸውና መፈናፈኛ የሌላቸው ባለሥልጣን መሆናቸው በሕግና በድንብ መጠበቂያ ከማቋቋም የሚያዘናጋ ምክንያት አይደለም፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሥርዓተ መንግሥታችን ፓርላሜንታዊ ነው ይለናል፡፡ እንዲህ ያለ ሥርዓት ባላቸው አገሮች በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ወይም ተከታዩ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ፓርላማው ይበተናል፡፡ ፓርላማው ከተበተነ በኋላ ከመሠረታዊው ዓውደ መንግሥት (የመንግሥት አውታር) በቀር የሌላው ፖለቲከኛና ባለሥልጣን ሥራ ከሞላ ጎደል ‹‹ይታገዳል›› ወይም ዕድሜ ለአንድ የፖለቲካ ቡድን ታማኝ ወይም ደባል አገልጋይ ሆኖ ለማይሠራው/ገለልተኛ ሆኖ ለተቀረፀውና ለተገራው የሲቪል ሰርቪሱ መዋቅር የባለሥልጣናት ሥራ በዓይነ ቁራኛ ውስጥ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ይጠረጣራል፡፡ እንዲህ ያለ መቆጣጠርያ የለንም፡፡ እኛ አገር ይኑር ቢባልም አምባገነንነትና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀናበሩ አውታራት ባሉበት (ሕመማችንም ይህ በሆነበት) አገር ስለፓርቲ ዴሞክራሲ ስለሥልጣን ገደብ ማውራት አስቂኝ ይሆናል፡፡

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ በመታሸት፣ በማውጣትና በማውረድ ላይ እያለሁ ከረፈደና ከመሸ በኋላ (ማክሰኞ የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ከምሸቱ ሦስት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ አካባቢ) በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አፈ ጉባዔ የአስቸኳይ ስብሰባ አፊሴል የጥሪ ማስታወቂያ ሰማን፡፡ አስቸኳይ ስብሰባው የተጠራውም ልክ በ15ኛው ቀን አናቱ ላይ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የካቲት 23 ቀን የሕዝብ በዓል ጭምር ነው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በሕግ ዝግ ሆነው በሚውሉበት ዕለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ ለምን ያደርጋል ባልልም፣ በእነዚያ አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ስብሰባው ያልተጠራበት ምክንያትን መጠየቅና ተጠየቅ ማለት ግን እንደ መጀመርያው በጭራሽ አጉል መሞላቀቅ አይደለም፡፡ ሕግ መጣስ የለመድነው፣ ሕግ መጣስ ልማዳችን የሆነው እንዲህ እንዲህ እያልን ነው፡፡

ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የየካቲት 23 ቀን 2010 ስብሰባ የሚያስተናግደው ‹‹የሹመትና የአሰያየም ሥነ ሥርዓት›› ስለመኖሩ ስላለመኖሩም/በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ ከዚህ የአሰያየም ሥነ ሥርዓት አኳያ የሚነሳ ሌላም ተከታይ ጥያቄ አለ፡፡ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰይመው (ምናልባትም እስከ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ጭምር) በአስቸኳይ ስብሰባም ሆነ፣ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ባለው መደበኛ ስብሰባ እዚህም ላይ የቢሻኝ ውሳኔ ሰለባ የሆነ ሌላ ጉዳይ አለ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ነው፡፡ በአንቀጽ 73 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል ይላል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አሰያየም፣ በአንፃራዊነት ትንሽ ሰፋ አድርጎ የሚዘረዝረው የተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ደግሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብላጫ መቀመጫ ካገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች ከምክር ቤት አባላት መካከል በምክር ቤቱ ይሰየማል፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቱ የተወከለው አባል ማለትም እንደራሴ የሚሰየመውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለምክር ቤቱ ያስተዋውቃል፡፡ የቀረበውን ጠቅላይ ሚኒስትር (ሕጉ ሌላው ቀርቶ ዕጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር እንኳን አይለውም) ‹‹ምክር ቤቱ በቀጥታ ተቀብሎ ያፀድቀዋል›› በማለት ይደነግጋል፡፡

ይህ እንግዲህ ሌሎች በየቦታው የተበታተኑ በፓርላሜንታዊ ሥርዓተ መንግሥት የተቋቋሙ ዝርዝር ደንቦች ወግና ልምድን የመሳሰሉ ጓዝና ጉዝጓዞች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለመመረጥ (ለመሰየም) ለመመደብ መጀመርያ የግድ የአገራዊው የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሆኖ መመረጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህን የግድ የሚያደርገው የፓርላማዎች አገሮች ወግና ልምድ ብቻ ሳይሆን፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 እና 73 ተፈልፍሎ የሚወጣው ግዴታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድ የፓርላማ አባል ማለትም እንደራሴ መሆን ያለበት መሆኑ ደግሞ  ወለም ዘለም የማይሉበት የሕጉ ቃል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆንና ፓርላማው እንዲሰይመው (በቀጥታ እንዲሰይመው) የሚቀርበው ሰው መጀመርያ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠ መሆን አለበት፡፡ ማንም የፓርቲ መሪ ሆኖ መመረጥ አይችልም፡፡ መጀመርያ የፓርቲ አባል፣ የፓርቲው የሆነ ደረጃ መዋቅር አባል መሆን አለበት፡፡ መራጩም በሕግ የተወሰነው ቢያንስ ቢያንስ የሕግ ድጋፍ ባለው የፓርቲው መተዳደርያ ደንብ የተወሰነው የመራጭ ቡድን ወይም “Electorate” መሆን አለበት ማለት ተራ የሀ፣ ሁ. . .  ዕውቀት ነው፡፡ የዚህንም አጠቃላይ ማዕቀፍ ከሞላ ጎደል የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ይደነግጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ የፓርቲ የመመሥረቻ ጽሑፍ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም፣ እንደሁም የፓርቲ መተዳደርያ ደንብ ሊኖረው እንደሚገባና የእነዚህንም መንዕስ ይዘትና ልክ ይወስናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲው ሰነዶች ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸውም ይላል፡፡ የእኛው የፓርቲ ምዝገባ ሕግማ ከዚያም በላይ በአንቀጽ 8(2) ለመመዝገብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊዎች በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ መቅረብ አለበት ይላል፡፡

ይኼንንና የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት፣ ሕጋዊነት የሚመለከቱ አለመግባቶችና ፀቦች እየተፈጠሩ ስንትና ስንት (የተቃውሞው ጎራ) ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተናቆሩ፣ እንደተሰነጣጠቁ፣ የአመራር መከፋፈል እንደተፈጠረባቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የእንዲህ ዓይነቱ የአገር ሕመም የቅርብ ጊዜው ተጠቂና ገና ቁርጡ ያልታወቀው ‹‹በሽተኛ›› ኢዴፓ ነው፡፡ ተመርጫለሁ፣ አልተመረጥክም የሚባባሉ ተወዛጋቢዎች አፍርቷል፡፡

በገዥው ፓርቲ፣ በግንባሩ አባል ድርጅቶች፣ በአጋሮቹ ውስጥ እንዲህ ያለ ምርጫ ቦርድ የሚያመላልስ፣ ምርጫ ቦርድን የሚወቅስ፣ የሚከስና የሚጠቅስ ጉዳይ ሰምተን የማናውቀው ፓርቲዎቹ መሠረታዊ ሰነዶችና ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያቸው እንከን የለሽ ሆኖ ሳይሆን ሁሉም‹‹ስምም›› በመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡ ዛሬ ይህ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ በኢሕአዴግ አባልና አጋር (በተለይም አባል) ድርጅቶች ውስጥ በግልጽ የሚታይ ከመፈነካከር በላይ የሆነ አደባባይ የወጣ ልዩነት አለ፡፡ ልዩነታቸው የ‹‹ግንባር እስከ መቃብር›› የእስከ ዛሬውን ጉዞ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ የፓርላማ ወንበር መቋጠር ድረስ ፉክክር ያለበት ነው፡፡ ያ ሁሉ ‹‹እኛም ወደናል›› አሠራር ድራሹ ጠፍቶ በመጠማመድ ፖለቲካ የተተካበት አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡  ተስብስቦና ተኮልኩሎ እጅ የመስቀል ወግ ከማሟላት የተሻለ ሥራ ኖሮት የማያውቀው ፓርላማ እንኳን ማስፈራሪያ እየሆነ ነው፡፡

በኢሕአዴግ 27 ዓመታት የሥልጣን ዘመን በኢሕአዴግ አሥር ያህል ጉባዔዎች ጊዜ እንኳን መነሳት ታልሞም ታስቦም የማያውቀው የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የምርጫ ጉዳይና ሒደት ዛሬ መጠየቅ የጀመረውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡    

ኢሕአዴግ መረጠም፣ መደበም፣ ሾመም ለዚህ ሥልጣን የሚያበቃው የራሱን ድርጅት ሊቀመንበር ቢሆንም የዚህ ሰው ‹‹ተልዕኮ›› ወይም ‹‹አገልግሎት›› ግን የአንድ ድርጅት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፡፡ በሰፊው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ የሕዝብ ፈቃድና ምርጫ ባልተገጣጠመበት አገር፣ ኢሕአዴግ በገዛ ራሱ አንድ መቶ ሰማንያ ሰዎች ክበብ ብቻ የአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ መሪ መወሰን ሌላው ቢቀር ለስምንት ሚሊዮን የፓርቲ አባላቱ እንኳን ደስ አይልም፡፡ ለዚህ ነው ቢዘገይም የእናንተ ሊቀመንበር ጉዳይ የብቻችሁ አይደለም ያገባናል የምንለው፡፡

ከአዘጋጁ  reporter ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *