በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙት የቡራዩ፣ የለገጣፎ እና የሰበታ ነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎትም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን እና ወደ አዲስ አበባ መሄድ የሚፈልጉ ሰዎች በእግር እየተጓዙ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናሩ።

ሻሸመኔ እንዲሁም አምቦ የገበያ ማቆም አድማውን ሙሉ በሙሉ የተቀላቀሉ ከተሞች መሆናቸውን በአካባቢው የሚኖሩ ግለሰቦች ለበቢሲ ተናግረዋል።

የቡራዩ አሸዋ ሜዳ ኗሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው፤ ከአዲስ አበባ ምዕራባዊ መውጫ የአምቦ መስመር ከፀጥታ ኃይሎች መኪኖች ውጭ ምንም ዓይነት ተሽከርካሪዎች ወደ መዲናዋ ሲወጡም ሆነ ሲገቡ እንደማይታዩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ጅማ ዞን የሰቃ ጨቆርሳ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሌሊት ጀምሮ መንገዶች በድንጋይ ተዘግተዋል።

ጠዋት ላይ የተወሰኑ የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች ወደሚዛን፣ ቴፒ እና ቦንጋ የሚወስዱ በመሆናቸው በመከላከያ ታጅበው የመጡ ሲሆን፤ መንገዱ በድንጋይ ስለተዘጋ ተሳፋሪዎች ወርደው ድንጋዮቹን በማንሳት መኪኖቹ እንዲያልፉ ተደርገዋል።

መከላከያ ሠራዊት አባላት አውቶቡሶቹን ሸኝተው ሲመለሱ ዋናው መንገድ ላይ ጎማ እየተቃጠሉ እንዳገኙና በዚህም የተነሳ ከመከላካያ ሠራዊት ጋር በተፈጠረ ግጭት አራት ሰዎች ቆስለው በህክምና ተቋም ህክምና እያገኙ እንደሆነ ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።

በአካባቢው ጠዋት ላይ ኮማንድ ፖስቱን የሚቃወሙ መፈክሮች ይሰሙ እንደነበርም ነግረውናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የኮማንድ ፖስቱ ህብረተሰቡ ለሚነዙ ውዥንብሮችና ቅስቀሳዎች ትኩረት ሳይሰጥ መደበኛ ህይወቱን እንዲመራና የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያለስጋት እንዲያከናውን አሳስቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ባወጣው መመሪያ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማስተጓጎልና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብትን የሚገድቡ እንቅስቃሴዎች፣ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን፣ የንግድ ሥራዎች ወይም ሱቆችን፣ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማትን መዝጋት ወይም ምርትና አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረግ ተከልክሏል።

ከስራ ቦታ ያለ በቂ ምክንያት መጥፋት ወይም ስራ ማቆምና ስራን መበደል፣ በህዝብና በመንግስት ተቋማት እንዲሁም በግል ንብረት ላይ በማንኛውም መንገድ ጉዳት ማድረስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን በኮማንድ ፖስቱ ዝርዝር መመሪያ ላይ መስፈሩም የሚታወስ ነው።

BBC AMHARIC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *