በእስር ላይ የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት በማረሚያ ቤት ዉስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምብናል ሲሉ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ ዛሬ የጽሑፍ መልስ አቀረበ።ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤቱ የደረሰዉን ደብዳቤ መርምሮ ዉሳኔ ለመስጠት ለፊታችን ረቡዕ መጋቢት 5 ቀጥሯል። መነኮሳቱ የምንኩስና ልብሳቸዉን እንዲያወልቁ ጫና እንደተደረገባቸዉ፤ እና ሌሎች ይፈፀምብናል ያሉትን በደል ለፍርድ ቤቱ ከተናገሩ በኋላ ወደ እስር ቤቱ ሲመለሱ ስድብ እና መንገላታት እንደሚደርስባቸዉ አመልክተዋል።
ከታሳሪዎቹ አንዱ ከባልደረባቸዉ ተነጥለዉ ዞን አምስት የሚባለዉ ዉስጥ መታሰራቸዉን ለችሎቱ መግለፃቸዉን ጉዳዩን ከሚከታተሉ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነዉ ሀብታሙ ምናለ ለዶቼ ቬለ ገልጿል።«የመጀመሪያዉ እዚያ እያለን ልብሳችን እንድናወልቅ ተገደናል ነው። ይኼኛዉን አቤቱታ ነበር እስካሁን ሲያቀርቡት የነበረዉ በጽሑፍ መልክ። በዛሬዉ ደግሞ ያቀረቡት ተጨማሪ ነገር፤ በፊት ዞን ሦስት ዉስጥ አብረዉ ነበረ ሁለቱም የታሠሩት አባቶች። ነገር ግን አንደኛዉን አባ ገብረ ኢየሱስ የሚባሉትን ለብቻ ዞን አምስት ወይም ደግሞ እኛ አሁን በተለምዶ የምንለዉ ቅጣት ቤት ወይም ጨለማ ቤት የሚባል ነው። እዚያ ዉስጥ ወስደዋቸዋል። እዚያ የሚወሰደዉ ደግሞ ማረሚያ ቤት ዉስጥ እያለ ከፖሊስ ጋር የሚጣላ፤ በስነምግባር ጉድለት ያለዉ፤ ወይም የተለያዩ ችግሮችን ፈጥሮ እንደቅጣት የሚሄድበት ነው። እና፤ መነኮሳቱ ደግሞ ምንም ጥፋት አላጠፋሁም ነገር ግን አንደኛዉን ዕቃዎትን ይዘዉ ዉጡ ተብለዉ እዚያ ወስደዉ ብዙ ጊዜ ሆናቸዉ እዚያ ከሁለት ወር በላይ ሆኗቸዋል እና ካለምንም ጥፋቴ ነው እዚያ የሄድኩት ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ደግሞ ሊያይልኝ ሊመለከተዉ ይገባል፤ አሁን የኦርቶዶክስ እምነት ብቻ ሳይሆን የእስልምና እምነት ተከታዮች ሕዝቦች ወጣቶች፣ እናቶች ተሰብስበዉ ሄደዉ እየጠየቋቸዉ ነው።»የተለያየ ዞን ሁለቱም ስላሉ ለመጠየቅ አመቺ አይደለም፤ ዞን ሦስት ከተገባ ዞን አምስት አይገባም። ዞን አምስት ከተገባም ዞን ሦስት አይገባም ብለዉ ኅብረተሰቡም እየተስተጓጎለ ነው እና ወደቦታቸዉ ይመለሱ የሚል ጠቅለል ይዘት ነዉ ሲል ሀብታሙ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ልብስ መቀየር ያልቻሉት መነኮሳት በሚጠይቋቸዉ ወገኖች አማካኝነት በቅርቡ አንደኛዉ ቅያሪ የመነኩሴ ልብስ ቢያገኙም ሌላኛዉ እንዳልተፈቀደላቸዉ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። ችሎቱን ለመከታተል ከታደሙ ወጣቶች መካከል ልብስ መያዛቸዉን በመግለጻቸዉ ጠባቂዎቻቸዉ ቢያንገራግሩም በዳኞቹ ትዕዛዝ ቅያሪዉን ልብስ መቀበል እንደተፈቀደላቸዉም ጋዜጠኛ ሀብታሙ ዘርዝሯል።