“Our true nationality is mankind.”H.G.

በ ” ሰበር ዜና” የታወጀው የሃፍረት አዋጅ መዘዝ…

“ሰበር ዜና” ሲሉ የኢህአዴግ መገናኛዎች ያበሰሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መዘዝ አገሪቱን ወዴት ያመራታል? የሚለው ጭንቀት አይሏል። ይህ አገርን ” ያረጋጋል” የተባለው አዋጅ ከመታወጁ በፊትም ሆነ በሁዋላ ዜጎች እየሞቱ ነው። የተጎዱ ቤተሰቦችን ምስክር በማድረግ የሚወጡ ዘገባዎች እንዳረጋገጡት ግድያው የሚፈጸምበት መንገድ እስከወዲያኛው የሚረሳ አይመስልም። በሄደበት ሁሉ ደም የሚቀባ አገር አስተዳዳሪ አካል ካሁን በሁዋላ እንዴት የህዝብ ልብና ቀልብ ያገኛል የሚለው ደግሞ የፍርሃቱ አብይ ጉዳይ ሆኗል።
አስቸኳይ ጊዜ ለማወጅ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው በቆራቆዝና የሃሳብ ልዩነት ገሃድ ወጥቶ ስለሰነበተ ፓርላማው አዋጁን ማጽደቁ ኩራት ሆኖ ” ሰበር ዜና” ሲሆን ነበር ዜጎች ሃረት ላይ የወደቁት። ያዘኑት።


አገር በመሰረታዊ የ”ህግ” አፈጻጸም መመራት ባለመቻሏ ወደ አስቸኳይ አዋጅ ስትዛወር ማቅ የመልበስ ያህል መሆኑ ያልታያቸው ክፍሎች፣ በአዋጁ ” ጸደቀ” በመባል የፈነደቁት ለምን ይሆን? የሚል ሰፊ መከራከሪያ አሁን ድረስ የማህበራዊ ገጾች፣ የተለያዩ ሚዲያዎች፣ የውጪ አገር ተቋማት፣ መንግስታት፣ ድርጅቶችን ጨምሮ እያነታረከ ነው። ከንትርክም በላይ የአዋጁ ጦስ ንጹሃንን እየጠበሰ፣ በሃዘን ለባቸውን እየሰበረ፣ በቂም ላብቸውን እያደነደነ፣ ይገኛል።
አንድ አገር የሚመራ ድርጅት የአስቸኳይ አዋጅ ለማወጅ የ ” ቀለጠው መንደር” አይነት ድራማ ሲሰራ፣ የቁጥር ሰርከት ትዕይንት ሲተውን ከማዘን ይልቅ አሽቃባጭ ለመሆን መምረጥ በምን መለኪያ ስኬትና ድል እንደሚሆን ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ግራ ነው።
አስቸኳይ አዋጅ ማለት፣ አገር ሰክራላች፣ አገር ቀውስ ውስጥ ነች፣ ስጋት አለ፣ መውጣት መግባት አልተቻለም፣ ሰላም የለም፣ የህጋዊ ጨዋታ ፈርሷል፣ ለማት ተስተጓጉሏል፣ ኢንቨስት አታድርጉ፣ ለቱሪዝም ተግባር አትምጡ፣ … በማለት ለዓለም ሁሉ ማስጠንቀቂያ የማሰራጨት ያህል ነው። እንዲህ ያለው አዋጅ ሲታወጅ ቢቻል አዋጁ ሳይታወጅ፣ ካልሆነም ከአዋጁ በሁዋላም ቢሆን አግባብ ያለው የመፍትሄ አፈላለግ ዘዴ በመጠቀም በአስቸኳይ ከቀውስ ለመውጣት መስራትና ሃፍረትን ማጠብ በተገባ ነበር።

eprdf 3
የሆነው ግን በተቃራኒ ቀውስን በአዋጅ ተደግፎ ማባባስ፣ ማጠናከር፣ ማስፋፋት፣ ቂምን ማጎልመስ፣ ጥላቻን ማንገስ፣ በጥቅሉ እየተንደረደሩ የደም ገንዳ ውስጥ መዋኘት ነው። ሞት ብርቃችን ባይሆንም፣ ስንሞት መኖራችን መለያችን ተደርጎ ቢወሰደም፣ ይህ ማፈሪያ የሆነብን አዋጅ ከታወጀ ወዲህ በአጭር ጊዜ ያጣናቸው ልጆች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ ጎላማሶች ቤት ይቁጠራቸው።
በዚህ ሁለት ቀን በሞያሌ የሆነው ደግሞ ሃፍረትን የሚያባብስ አረመኔነት እያየለ መሄዱን ወለል አድርጎ የሚያሳይ ለመሆኑ አልጠራጠርም። ሰራዊት ከተማ ገብቶ ” ሳያናግረን ጨረሰን” ሲሉ ምስክሮች እንዳሉት፣ በደርዘን አቁስሎ፣ በደርዘን ጨፍጭፎ ” በስህተት ነው” በሚል ህዝብ ፊት ወጥቶ መናገር ከጭፍጨፋው በላይ የሚያም ሃዘን ይሆናል።
ጎበዝ አስቡት። አንድ “የግዳጅ አፈጻጸም ካርድ” በኪሱ ይዞእ የሚዞር ” አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰራዊት ” ተሳስቶ ቦንብ ነው የወረወረው? ከብዙ ኪሎሜትር ርቀት ከባድ መሳሪያ ተኩሶ ነው የተሳሳተ ቦታ/ ከተማ የወደቀበት? በአየር ሲያጠቃ ነው ስህተት የፈጸመው? በታጠቀው ባለመንጽር መሳሪያ እያሳደደ ሲቀነድብ ህዝብ እያየ በስህተት ተደረገ ብሎ ለማስተባበል መሞከር፣ የጥልቅ ተሃድሶውን ጥልቀት፣ የተሃድሶውን መሪዎች ” ምጥቀት” የሚያሳይ መነጽር ከመሆን አያልፍል። እናም ሁሉም ዜሮ ማለት ነው።
ከሁሉም በላይ ይህን ጭፍጨፋ ያካሄዱት “አንቺ” የምትባል ” ሻለቃ” ውስጥ ለሌላ ግዳጅ ከኦነግ ሸማቂዎች ጋር ሊዋጉ የተመደቡ እንጂ የኮማንድ ፖስቱ አካላት አይደሉም መባሉ ደግሞ ያጥወለውላል። ይህንኑ ሲያብራሩ ለነበሩት ” ጀነራል” ጥያቄ ሲያቅርብ የነበረው ጋዜጠኛ ” ስለወደፊቱ ጥንቃቄ ምን የሚሉት አለ” ሲል የተሰጠው መልስም እንዲሁ ቲቪ ባይኖረኝ፣ ባላያቸው፣ ባልስማቸው የሚያሰኝ የታወረ ህሊና ኑዛዜ ስብከት ነው።
ለሶስት ቀን ተካሂዶ በነበረው ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ የደረሰውን ኪሳራ እያሰላን ባለንበት ወቅት በኦሮሚያና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የነዳጅ አቅርቦትን ማስተጓጎልን ያካተተ የትግል ጥሪ በድምጽና በጽሁፍ ተበትኗል። ላለፉት ሶስት ዓመታት አገሪቱ የገባችበት ጣጣ ኢኮኖሚዋን እየበላው፣ ማህበራዊ ቀውስ እያፋፋመ፣ የፖለቲካውን ጠረን እያከረፋው ባለበት ሰዓት መሆኑ ነገሮች እየተካረሩ እንደሚሄዱ አመላክች መሆኑንን የማይቀበሉ እነ ቃታ በእጃቸው ብቻ እንጂ ሌሎች ሊሆኑ አይችሉም።
በድፍን ወለጋ፣ በአምቦ፣ በባሌ፣ በጊንጪ፣ ዛሬ በሞያሌ የሚት ቢፌ እየደረደሩ ያሉት ክፍሎች አንድ ሚሊዮን ሰዎች ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀሉ የት ነበሩ? የሞያሌ ነዋሪዎች ምንም ከማያውቁ ህጻናት ጋር በስደት ወደ ኬንያ እንዲፈልሱ ማስበርገግና በጅምላ ማሳደድ ዓላማውና ግቡ ምን ይሆን?
ደርግ ወያኔና ሻዕቢያ ከውጭ ሃሎች ጋር አብረው መከራ ሲያበሉት ነዳጅ በኮንቦይ፣ ቀለብ በኮንቦይ፣ ሬሽን በኮንቦይ፣ ከወደብ ወደ ከተማ በኮንቦይ፣ ከከተማ ወደ ወደብ በኮንቦይ፣ በሰዓት እላፊ፣ በአሰሳና በልዩ ጥበቃ ስራ ተወጥሮ ነበር። ሟርት ሳይሆን እንደው ለማስታወስ ያህል ነው። እናም አሁን ታሪክ ራሱን ደግሞ ከመተማ ወደ መሃል የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ማጀብ ከተጀመረ ቆይቷል። አሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ሊሆን ነው። ይህ ኩራት ከሆነ ” ሰበር ዜና ቦቴዎች በኮንቦይ ታጅበው እንዲሄዱ ተደረገ” በሉ።
በግሌ እየተባባሰ የሄደውን ችግር በጥሞና አስቦ ምላሽ ለመስጠት አሁንም በህዝብ አቆጣጠር ጊዜ አለ። ከዚህ ውጭ ባለው አቆጣጠር በከፋቸው ዜጎች አቆጣጠር ጊዜው አልቋል። የከፋቸው ይበዛሉ? ከበዙ ስሌቱን ማስላት ነው። አንድ የሚያስማማን ነገር ቢኖር እንደቀድሞው የሚቀጥል ነገር የለም። ለነገሩ ደም ሞንስተር ነውና ይህ ለማያሳስባችሁ ….. ግፉበት። መቶ ሚሊዮን ህዝብ ግን በጥይት አያልቅም!!

አንድ ያሳቀኝ ጉዳይ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች የሞያሌን ነዋሪች ለማጽናናት፣ ለማነጋገርና ለማረጋጋት በሄሊኮፕተር ወደዛው ማምራታቸው ይፋ መሆኑንን ነው። ውድ ጀነራሎቻችን ንፍሮ እየቃሙ / ካላ ነው/ ሲያጽናኑ። 
ሰለሞን ተከለ ሃዋሪያት –

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች
0Shares
0