ሩሲያ ውስጥ ተሰርቶ በሃገሯ ውስጥ በነበረ የቀድሞ ሰላይ ላይ ጥቃት ስለተፈፀመበት የነርቭ ጋዝ ሞስኮ ማብራሪያ አልሰጥም በማለቷ፤ ዩናይትድ ኪንግደም 23 የሩሲያ ዲፕሎማቶች ሃገሯን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟን ጠቅላይ ሚኒስትሯ አሳወቁ።

ቴሬሳ ሜይ እንደተናገሩትበሳምንት ውስጥ እንግሊዝን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት ዲፕሎማቶች “በግልፅ ያልወጡ የደህንነት መኮንኖች” ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የቅረበ የጉብኝት ግብዣ መሰረዙን እንዲሁም የእንግሊዝ ንጉሳዊያን ቤተሰቦች በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ሩሲያ በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ላይ እንደማይታደሙ ገልፀዋል።

ሩሲያ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቀድሞው ሰላይና ልጁ ላይ የነርቭ ጋዝን በመጠቀም በተደረገው የግድያ ሙከራ ውስጥ ተሳትፎ እንደሌላት አስተባብላ ነበር።

የሩሲያ መንግሥት እስከ ትላንት እኩለ ሌሊት ድረስ በጉዳዩ ላይ ለመተባበር ያለውን ፍላጎት እንዲገልፅ የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ “ግልፅ መልዕክት” የሚያስተላልፉ ያሏቸውን ተከታታይ እርምጃዎችን ይፋ አድርገዋል።

እርምጃዎቹም ዲፕሎማቶችን ማባረር፣ በግል በረራዎች ላይ፣ጭነቶችና የጉምሩክ አገልግሎት ላይ ፍተሻውን ማጥበቅ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ደህንነት ላይ ስጋት ይሆናሉ በተባሉ የሩሲያ መንግሥት ንብረቶች ላይ እገዳ መጣል፣ ከሩሲያ ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን ማገድንና ሌሎችም ይጨምራል።

የሩሲያ መንግሥት ሀገረቸውን የሚቃረን እርምጃ ሲወስድ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፤ ይህ ከ30 ዓመታት ወዲህ የተወሰደ በርካታ ዲፕሎማቶችን የማባረር ከፍተኛው እርምጃ ነው ብለዋል።

“በዚህ ዲፕሎማቶችን የማባረር እርምጃችን ሩሲያ በሃገራችን በቀጣይ ዓመታት የምታደርገውን የስለላ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ለማዳከም እንችላለን። መልሰው ለማንሰራራት የሚሞክሩ ከሆነም ያ እንዳይሆን እንከላከላለን”

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለፓርላማ አባላት እንደተናገሩት የሩሲያ ባለስልጣናት የነርቭ ጋዙ እንዴት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብቶ ጥቅም ላይ ሊውል እንደቻለ ምንም ማብራሪያ አልሰጡም። የተገኘውም ምላሽ “ንቀት፣ ምፀትና እምቢተኝነትን የተላበሰ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣኖቻቸው ተጨማሪ ማብራሪያ የተሰጣቸው ቴሬሳ ሜይ ለግድያ ሙከራው “ሩሲያን ተጠያቂ ከሚያደርገው መረጃ ውጪ አማራጭ መደምደሚያ አልተገኘም” ብለዋል።

የመርዝ ጋዙ ጥቃት የተፈፀመባቸው አባትና ሴት ልጁ አሁንም ድረስ በአስጊ ሁኔታ ላይ ሆነው በሆስፒታል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ። ቢቢሲ እንደዘገበው

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በትግራይ 3.5 ሚሊዮን ተረጂዎች የዕለት ቀለብና ተመሳሳይ እርዳታ እየተደረገላቸው ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *