ሪፖርተር – በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎትና ሒደት በኅብረተሰቡ፣ በተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ በዳያስፖራው፣ በውጭ መንግሥታትና በገዥው ፓርቲም ጭምር እየተስተዋለ ነው፡፡ ነገር ግን የሚፈለገው ለውጥ ምን ዓይነት ነው? ከዚህ ቀደም ዘውዳዊውን ሥርዓት በረሃብና ተያያዥነት ባላቸው ምክንያቶች በደርጋዊ ሥርዓት እንደተለወጠው ዓይነት ነው? በደርግ ሥርዓት በመጀመርያ እንደታየው ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም››

ዓይነት ለውጥ ነው? ወይስ በወቅቱ እጁን ወደ ዘረጋልን ዘለን እንደታቀፍነው ሁሉ አሁንም ፊቱን ፈገግ አድርጎ ወደሚያሳየን ሮጠን መጠምጠም ነው? ወይስ እንዲያው ዝም ብሎ የውስጥ ፍላጎት ነው? ወይስ በፍልስፍና ላይ የተመሠረተ የብሔራዊ መግባባት ለውጥ ነው? ብሐራዊ እርቅ ነው? ነፃዊነት የሊበራሊዝም ሥርዓትን ዕውን ማድረግ ነው? ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ነው? የጥገና ለውጥ ማካሄድ ነው? ሥር ነቀል ለውጥ ነው? የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት ናፍቆት ነው? ወይስ ሌላ ለውጥ ነው? ከሆነ ምን?

ጥያቄውን እንደገና በሌላ መልኩ እናንሳው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ የለውጥ ፍላጎት ቢኖርም፣ ይህን ፍላጎቱን በፍልስፍና በተመሠረተ ለውጥ ዕውን የሚያደርገው ማን ነው? በዚህ ጸሐፊ እምነት ከኢሕአዴግ በመቀጠል የሚጠሩ ብዙ አባላትና በሳል አመራር ከፍልስፍና ጋር ያላቸው አንድ ሁለት፣ ሦስት ፓርቲዎች አሉ፡፡ በፖለቲካ ሜዳ ላይ ተሠልፈው የጨዋታውን ሕግ የሚያውቁ የምሁራን ስብስብ ያላቸው ፓርቲዎችም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ሲውተረተሩ እንደነበረም አሌ አይባልም፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ጥቂቶቹ የኢሕአዴግ ጠንካራ ክንድ ተጭኗቸው ‹‹ኧረ ስለነፍስ›› እያሉ እስካሁን የቀጠሉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ፍላጎት ነው እንጂ አቅምም፣ ችሎታም የሌላቸው ቢሆኑም የትም እንደማይደርሱ ታውቆ የተሳሳተና አስቂኝ ሐሳብ እየሰነዘሩም እንደ ልብ የሚፈነጩ ናቸው፡፡

ይህን የመጨረሻ አገላለጽ በምሳሌ እንመልከተው፡፡ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ጋር በሚያካሂደው ውይይት ጋዜጠኛው፣ ‹‹ሥልጣን እንቁልጭልጭ በል›› ወይም በድመት አጠገብ ቋንጣ ያዝና ውሮ ትፈልጊያለሽ በላት?›› እንደተባለ፣ በትዝት ዓይንም እያየ፣ ‹‹አሁን ኢሕአዴግ ሥልጣን ቢለቅላችሁ ትቀበላላችሁ? ወይም ሥልጣኑን ቢለቅላችሁ እውነት አመራሩን ተቀብላችሁ ለመሥራት ትችላላችሁ?›› ዓይነት ይላቸዋል፡፡ እነሱም ልክ ድመቷ ቋንጣውን ዓይታ ‹‹ሚያው፣ ሚያው፣ . . . ›› እያለች ዘላ ለመውሰድ የምትፈልገውን ዓይነት ስሜት ተላብሰው ዓይናቸውን ፍጥጥ፣ ጥርሳቸውን ግጥጥ አድርገው፣ ‹‹አዎን እንችላለን፡፡ ብቻ እርሱ ያስረክበን እንጂ እኛ መምራት ሲያቅተን ታያለህ፤›› የሚል ዓይነት መልስ ይሰጣሉ፡፡ እና በእነዚህ በፖለቲካ በስለው፣ ከመብሰልም አልፈው አረው በሚያሳርሩ ፓርቲ መሪዎች ዕይታ ሥልጣን ሰጪው ኢሕአዴግ፣ ሥልጣን ተረካቢዎቹ እነሱ ሆነው እርፍ! በእነሱ ቤት ሕዝብ የለም! ፍልስፍና የለም! . . . ብቻ መስጠትና መቀበል የሚፈለገው ሥልጣን ነው፡፡ ለእነሱ ለውጥ ማለት ይኼው ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲያ ቢሉ የሚገርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሥልጣን ከአንዱ ወደ ሌላው በስጦታ ማስተላለፍ በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገሥት ሲሞት ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ልጅም በሞግዚት ሥልጣን ተቀብሎ ሕዝብን ይገዛ ነበር፡፡ በጥንት ግሪኮች፣ ሮማውያን፣ ግብፆችና አገራችንም ነበር፡፡ በአገራችን በዚህ ረገድ ንግሥት እሌኒና የጎንደሯ እቴጌ መነን የቅርብ ምሳሌዎች ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰፍኖ የነበረ ሥርዓት ካለፈ ደግሞ ገና 44 ዓመቱ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን፣ ‹‹አትልፉ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ሥርዓት ዘውዳዊ ነው፡፡ ዘውዳዊው ሥርዓት ተመልሶ ሥልጣኑን ካልያዘ ወንበሩ አይረጋም፣ ሰላምም አይሰፍንም፤›› የሚሉ ይኖራሉ፡፡ በመሠረቱ አመለካከታቸውን የሚቀበል ካለና ሕዝቡ በድምፅ ድጋፉን ከሰጣቸው ዙፋናዊ ሥርዓቱን መመለስ ይችላሉ፡፡ ይህም ሆኖ ሩቅ ስለሆነ ወደ አክሱማውያንም፣ ላስታዎችና ሸዋዎች ባንሄድ የአፄ ፋሲልም፣ የአፄ ቴዎድሮስም፣ የአፄ ዮሐንስም፣ የአፄ ምኒልክም፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴም የልጅ ልጆች የይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርምና በዘውዳዊው ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ፉክቻ አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ሕገ መንግሥታዊና ፈላጭ ቆራጭ ዘውዳዊ ሥርዓት የሚባል የአገዛዝ ሥርዓት ስላለ ዕድሉ ቀንቷቸው ቢያሸንፉ፣ ሕገ መንግሥቱን በዚያው በሚፈልጉት መንገድ መቅረፅና ማስፀደቅ ይኖርባቸዋል፡፡

አንዳንዱ ደግሞ በደመ ነፍስ የሚመራ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1987 ዓ.ም. የምክር ቤት ምርጫም ‹‹የምክር ቤት መቀመጫ ሻሞ!›› የተባሉ ወይም ‹‹የድርጅት ተሳትፎውን አብዙት›› የተባሉ የሚመስሉ ድርጅቶች ወደ ምርጫ መድረኩ ብቅ ብለው እንደነበር ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡ ይልቁንም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለምክር ቤት አባልነት ለሚወዳደሩ አንድ ዓምድ ከፍቶ ስለነበር ወደ ቢሮ መጥተው ዓላማቸውን የሚያስረዱት ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ በግልጽ እንደተናገሩት ዋና ዓላማቸው ቢመረጡ ጥሩ ደመወዝ ለማግኘት ነው፡፡ አንዳንዶቹም ዕድሉ ከተመቻቸላቸው በተቃዋሚነት ስም ገብተው ላሠለፏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ ነበሩ፡፡ ውጭ አገር የመሄድ ዕድል ቢገጥማቸው በዚያው ለመቅረትም የሚያስቡ ነበሩ፡፡

አንዳንዱ ደግሞ ኢሕአዴግ ማለት በቃ ምንም አቅም የሌለው ነገር ስለሆነ የሚያስፈራራው ከተገኘ እንደ ጢስ በኖ እንደ ውኃ ተኖ የሚጠፋ፣ የሆነ ከሸረሪት ድር የተሠራ መረብ ዓይነት ይመስላቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ተደምረውና በመቶ ተባዝተው ቢመጡም፣ ኢሕአዴግ እንዲያው በደፈናው ያሰባሰባውን ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና ተግባራዊ አቅም ሊደርሱበት እንደማይችሉ አያውቁም፡፡

የኢሕአዴግ የደርግን ሥርዓት የማፍረስ ሒደት ከዛሬ አንፃር

እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ ሥርዓት በመጣል ነበር፡፡ የደርግ መንግሥትም የወደቀው በኢሕአዴግ የፈረጠመ ክንድ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ሥርዓት መለወጥ ጭምር ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት አንድ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ የነበረውን ወታደራዊ አቅም ስንመለከት፣ የኢሕአዴግና የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ሻዕቢያ ወታደራዊ አቅም ከደርግ አቅም ጋር የሚመጣጠን አልነበረም፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ1917 ጀምሮ ሲገዘገዝ የነበረው የሶቪየት ኅብረት ኮሙዩኒስት ፓርቲ በ1980ዎቹ መጀመርያ ላይ እየተዳከመ መምጣቱ ታየ፡፡ እንኳንስ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በእስያ የነበሩትን የሶሻሊዝም ሥርዓት ይጠቅመናል ብለው መንገዱን ጀምረው የነበሩ አገሮችን ለመርዳት ቀርቶ ራሱን ለመርዳት አልቻለም፡፡

በፌዴራሊዝም ሥርዓት ተሳስረው የነበሩ እንደ ዩክሬይን፣ ቤላሩስ፣ ጆርጂያ፣ አዘርባጃን፣ ወዘተ ያሉት ክልሎች የመገንጠል ፍላጎት አሳዩ፡፡ ሩሲያም ድሮውንም እናንተን ተሸክመን በመኖራችን ተጎዳን እንጂ አልተጠቀምንም በሚል ስሜት ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ›› አለቻቸው፡፡ የምሥራቅ ጀርመን ከምዕራብ ጀርመን ጋር መቀላቀል፣ የደቡብ የመን ከሰሜን የመን ጋር መቀላቀል የአቅሙን መዳከም ያመለከተ እውነታ ነው፡፡ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችም የኮሙዩኒስት ሥርዓቱን ለማራመድና ለማስቀጠል አልቻሉም፡፡ በእነዚህ አገሮች ዕርዳታ ላይ ተመሥርቶ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቋም ተዳከመ፡፡ በተለይ ሚስተር ጎርባቾቭ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ወታደራዊ ድጋፍ ጥየቃ ሄደው በነበረበት ጊዜ ‹‹እኔ የምሰጥህ ድጋፍ የለም፣ ይልቅ ከተቃዋሚዎችህ ጋር ታረቅ፣ የፖለቲካ ሥርዓትህን ለውጥ፤›› በማለት እንደ ሸኟቸው ይታወሳል፡፡

ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ግዙፍ የኮሙዩኒስት ፓርቲ ወደነበራት ቻይና የኮሙዩኒስት ዓለም አቀፋዊነትን ባህርይ ተላብሰው ቢጠጓትም የምትበገር አልሆነችም፡፡ እንዲያውም ከኢሕአዴግና ከሻዕቢያ ጋር የወገነች መስላ ታየች፡፡ ኩባም ሆነች የመን ራሳቸው በለውጥ ማዕበል በመናጥ ላይ ስለነበሩ የተለመደውን ዕርዳታ ለማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም፡፡ በዚያ ክፉ ቀን የደርግ መንግሥት አጋር መስላ የተገኘችው ሰሜን ኮሪያ ነበረች፡፡ በዚህም ምክንያት የሶቪየቶች ፍልስፍና ተትቶ የኪም ኤል ሱንግ ፍልስፍና በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን መንፈስ ጀመረ፡፡ የሰሜን ኮሪያን የሚነቅፍ ሐሳብ በመገናኛ ብዙኃን እንዳይወጣ ከኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ርዕዮተ ዓለም መምርያ መመርያ ተሰጠ፡፡ እናም በሰሜን ኮሪያ ድጋፍ የጋፋት ጦር መሣሪያ ፋብሪካ በከፍተኛ ደረጃ ሥራውን መጀመሩን ወሬዎች ተናፈሱ፡፡ ወሬው ምን ያህል ተጨባጭ እንደነበረ የሚያውቀው ወታደራዊ ክፍሉ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫም ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆኗ ይነገር ነበር፡፡

እንዲህ ያለው አዝማሚያ ያላስደሰታቸው ምዕራባውያን አገሮች ‹‹እስከዚህም ተደርሷል እንዴ?›› በሚል ስሜት ኢሕአዴግና ሻዕቢያ የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ነገሮች ሁሉ የእንቧይ ካብ እየሆኑ መሄድ የዕለት ተዕለት ትዕይንት ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት የደርግ መንግሥት ዋነኛ አራማጅ የነበሩ የጦር መኮንኖች በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሙከራ አመራር ባለመደሰታቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አደረጉ፡፡ በዚህ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተሳተፉት አገሪቱ ያፈራቻቸው የጦር መሪዎች ነበሩ፡፡ የእነዚህ የጦር መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት ከሸፈና ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ነገሮችን በዝግታ ማየት ሲገባቸው፣ ጠላቶቻቸው ካዘጋጁላቸው የጥፋት መረብ ውስጥ ሰተት ብለው በመግባት ሁሉንም ጨረሷቸው፡፡ ሆኖም እነዚህን ጀኔራሎች በአዳዲስ ለመተካት ቢሞክሩም አልሆነም፡፡

የመፈንቅለ መንግሥቱን ቴአትር ያዘጋጁት ኃይሎች የደርግ መንግሥትን ያፍረከርኩት ጀመር፡፡ በአንፃሩም ለ15 ዓመታት ከትግራይ ክልልና ከደቡብ ትግራይ አጎራባች አውራጃዎች መውጣት ተስኖት የነበረው ሕውሓት ከኢሕፓ ያፈነገጠው ኢሕድንን በማቀፍና ከተማረከው ወታደር ያደራጀውን ኦሕዴድን በማቋቋም፣ በአንድ ዓመት ውስጥ  ወሎንና ትግራይን፣ ጎጃምና ሸዋን በመቆጣጠር ወደ ሸዋ ዘለቀ፡፡ በምዕራባውያን ባገኘው ድጋፍ በመኩራራትም ከደርግ ጋር የጀመረውን ሰላማዊ ውይይት ናቀው፡፡ የመታረቅ አዝማሚያ ያሳየውን ሻዕቢያንም ‹‹ለድል ተቃርበሃልና ድርድሩን ተወው፣ እኛም በአስተማማኝ ሁኔታ እንረዳሃለን፤›› በሚል ዓይነት ገፋፉት፡፡ በአንድ በኩል ማዕከላዊ አመራሩ ዳዋ የመታውን የደርግ ሠራዊት እያባረረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የነበሩትን የደርግ ተቃዋሚ ኃይሎችን ማስተባበር ጀመረ፡፡

ኢሕአዴግ የሽግግሩን መንግሥት ለማቋቋም ያሳየው ብልህነት

ከደርግ ሽንፈት በኋላ የሚመሠረተው የሽግግር መንግሥት በቅርፁ ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆንና አገሪቱን በጋራ የመምራት ፍላጎት እንዳለው ብልህነት በተሞላበት ሁኔታ አስረዳ፡፡ ደርግን በጦር መሣሪያ ጭምር በመውጋት ከነበሩት ኃይሎች ውስጥ ብዙዎቹም አዎንታዊ መልስ መስጠት ጀመሩ፡፡ በውጭ አገር ሆነው ፀረ ደርግ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከልም ጥቂቶቹ  ፈቃደኛነታቸውን መግለጽ ጀመሩ፡፡ ለአካባቢያችን ዕድገት መልካም አጋጣሚ ነው ብለው ያመኑ ብሔር ብሔረሰቦችን እንወክላለን የሚሉታም እሺታቸውን አስታወቁ፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥትን ድል ያደረገው ኢሕአዴግ አዎንታዊ መልስ የሰጡትን የፖለቲካ ድርጅቶች በማሰባሰብ፣ ከሰኔ 24 ቀን እስከ ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ባለው ጊዜ  አገር አቀፍ ጉባዔ በማካሄድ ቻርተሩን አፀደቀ፡፡

እነዚህም  የሽግግሩ መንግሥት የመሠረቱት የፖለቲካ ድርጅቶችም የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ፣ የአፋር ነፃነት ግንባር፣ የአገው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቡርጂ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የጉራጌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የሐዲያ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ሆሪያል፣ የኦሮሞ ነፃነት ኢስላማዊ ግንባር፣ የኢሳና ጉርጉራ ነፃነት ግንባር፣ የከንባታ ሕዝቦች ኮንግረስ፣ የከፋ አስተዳደር ክልል ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሞቲክ ሕዝቦች ዴሚክራሲያዊ ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የተባበረው ኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ግንባር፣ የሲዳማ ነፃነት ንቅናቄ፣ የላብ አደሮች ተወካይ፣ የወላይታ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የምዕራብ ሱማሌ ነፃነት ግንባር፣ የየም ብሔረሰቦች ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰላምና ማረጋጋት ዕርምጃ ተሸጋገረ፡፡ ሊፈነዳ ተቃርቦ የነበረው የመበታተን ችግር ቀስ በቀስ መተንፈስና ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ጀመረ፡፡ በምክር ቤቱ የነበረው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎም በመልካም አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ አንዳንድ ሁኔታዎች አመለከቱ፡፡

ኢሕአዴግ ከብልህነት ወደ ብልጥነት

ቀደም ሲል የተጠቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶች ከኢሕአዴግና ከኦነግ፣ ከኢድሕ፣ ከአፋር ነፃነት ግንባርና ከተቀሩት ጥቂት የነፃነት ንቅናቄዎች በስተቀር ይህ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ዝግጅት አልነበራቸውም፡፡ አንዳንዶቹም የዘውዳዊው ሥርዓት የፓርላማ አባላት የነበሩ ሲሆን፣ ለውጡ በዚያ ቅኝት እንዲጓዝ የሚፈልጉ ዓይነቶች ነበሩ፡፡ ይህም ሆኖ ልምድ በነበራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እየተደገፉ፣ እነሱም አንዳንድ ጊዜ ነፃ ሆነው፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ የኢሕአዴግን ፊት እያዩ የሚመክሩ ነበሩ፡፡ በተለይም ከሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 1984 ዓ.ም. ድረስ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብሔራዊ ጉዳዮች በምክር ቤቱ ውይይት እየተደረገባቸው ይፀድቁ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ክርክር በመገናኛ ብዙኃን ባለመቅረቡ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ባህርይን የሚያንፀባርቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ዳሩ ግን ከግንቦት 1983 ዓ.ም. በኋላ ማለትም በኅዳር ወር 1984 ዓ.ም. በወጣው የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችለው አዋጅ ቁጥር 9/1984 መሠረት የክልሎች ምርጫ ሲካሄድ፣ በየቦታው ቅሬታዎች በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰማት ጀመሩ፡፡ ድርጅቶቹ ለምክር ቤቱ ባሰሙት ቅሬታም የኢሕአዴግ ካድሬዎች አባሎቻቸውን በማሰር፣ በማንገላታት፣ ደጋፊዎቻቸውን በማስፈራራት፣ የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ስብሰባ በሚጠሩባቸው ቀናት በሌላ ቁጥጥር በሚደረግበት ሥራ በማሠማራት፣ የስብሰባ አዳራሽ በመንፈግ፣ . . . ወዘተ በምርጫው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደገቱባቸው ገለጹ፡፡ አንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅቶችም የኢሕአዴግን ሰላማዊ ጥሪ ተቀብለው የመጡ ቢሆኑም የድሮ ታሪካቸው እየተመዘዘ፣ የሚመዘዝ ባይኖራቸውም እየተለጠፈባቸው የማጥላላት ዘመቻ ተካሄደባቸው፡፡ በተለይም እንደ ኢዲዩ ያሉት በትግራይ፣ እንደ አፋር ነፃ አውጪ ያሉት በአፋር፣ እንደ ሲአን ያሉት በሲዳማ የደረሰባቸውን በደል አስታወቁ፡፡

አለመታደል ሆኖ ኢሕአዴግ ይህን ትክክል ያልሆነ አዝማሚያ በመቅጨት የዴሞክራሲ መድረኩን ማስፋት ሲገባው በቸልታ አለፈው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም እንደዚያ ያለውን ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ሒደቱን ሊያቀጭጨው እንደሚችል ማስተማር ሲገባቸው የስህተቱ ጠበቆች ሆኑ፡፡ ይልቁንም በምክር ቤቱ የወጣውን የአየር አጠቃቀም ድልድልን ዴሞክራሲውን ለማጎልበት መጠቀም ሲገባቸው እንደ መንግሥትም፣ እንደ ድርጅትም፣ እንደ ወገንም በማገልገል አብዛኛውን የአየር ጊዜ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ሲታይ ከሁሉም ለተሻለው ኢሕአዴግ ከፍተኛ ሽፋን ማድረግ ቀጠሉ፡፡ የተቀናቃኝ ድርጅቶች እንደ ኢሕአዴግ የኅትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ስለሌላቸው (የጥቂቶቹ ብቻ)፣ በመጠኑም ቢሆን ዕድላቸው በግሉ ፕሬስ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡  የግሉ ፕሬስም ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ሲገባው ጠባብነት፣ ዘረኛነትና ጥላቻ የሰፈነበትን የፕሬስ ውጤት ማውጣትን እንደ አማራጭ ወሰደው፡፡ ለአንዳንዱም የገንዘብ ማግኛ ምንጭ ሆነ፡፡ ያ ሆኖ የግሉ ፕሬስ ሽፋን ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ከአዲስ አበባ፣ በተለይም ከአራት ኪሎ፣ ከፒያሳና ከብሔራዊ ቴአትር አካባቢ የማያልፍ ስለነበረ ተፅዕኖ የማድረግ አቅሙ ደካማ ነበር፡፡

በወቅቱ ኤርትራ ከጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ነፃነት የምትሸጋገርበት ጊዜ ስለነበርም፣ የኤርትራን ነፃነት የማይደግፉ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኃይሎች አምስት ወራት ባልሞላው የሽግግር መንግሥት ላይ ችግሩን በማጎን አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ከዚህ ላይ በበዶኖና በወተር ላይ በተደረገው ግድያ የተጠያቂነት ጉዳይ በኢሕአዴግና በኦነግ መካከል የነበረውን ከስምንት ወራት እምብዛም ያልበለጠ ወዳጅነታቸውን ክፉኛ ጎድቶት ነበር፡፡ በኦሮሞ አቦ (የቀድሞ የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጪ) የተከሰተው ችግርም እንደዚሁ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ነበረው፡፡  

የኤርትራ ነፃነት ጉዳይ ምክር ቤቱን ችግር ላይ ጥሎት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በተለይም አንድነት፣ ፌዴሬሽን፣ ኮንፌዴሬሽን፣ ነፃነት የሚል ምርጫ እንዲኖረው የሽግግር መንግሥቱ ተፅዕኖ ማድረግ ሲገባው ‹‹ነፃነት›› ወይም ‹‹ባርነት›› የሚል አማራጭ ብቻ እንዲሆን፣ ይልቁንም ነፃነት የሚለው በአረንጓዴ ቀለም፣ ባርነት የሚለው ደግሞ በቀይ ቀለም ቅስቀሳ ሲደረግ እንደ በጎ ነገር በመታየቱ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አልቀረም፡፡ ይልቁንም በኤርትራ ነፃነት ላይ ኤርትራውያን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ባለመደረጉ፣ ከመጀመርያው ሪፈረንደም ጋር በመጠኑም ቢሆን ተመሳሳይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ይህም ሁሉ እየሆነ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ታማኝ ተቃዋሚዎች በመሆን ለመቀጠል ፈልገው ነበር፡፡ ዳሩ ግን በፓሪስ ጉባዔ የተሳተፋችሁ ተብለው በርካታ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች አንድም ውሳኔውን እንዲያስተባብሉ፣ ካለበለዚያ ምክር ቤቱን ለቀው እንዲወጡ ተደረጉ፡፡ ኦነግም ምክር ቤቱን ጥሎ ወጣ፡፡ ኢሕአዴግ ዝርዝር ነገር ቢኖረውም የዛሬውን ደኢሕዴን ዕውን በማድረግ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት አደረገው፡፡ በሱማሌና በአፋርም፡፡

ኢሕአዴግ ከብልጥነት ወደ ራስ ወዳድነት

ኢሕአዴግ ከሽግግሩ መንግሥት ቀጥሎ ታማኝ ተቃዋሚዎች እንዲመሠረቱና እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥረት አድርጎ እንደ ቅንጅት ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ብቅ ቢሉም አዝማሚያቸው ስላላማረው፣ በምርጫው በቂ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ተፅዕኖ ማድረጉ አልቀረም፡፡ በኦነግ፣ በሲአን፣ በደቡብ ሕዝብና በመሳሰሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የደረሰው ተፅዕኖ በእነሱም ላይ ደረሰ፡፡ ሐሳባቸውን በድምፅ ብልጫ ተቀባይነት እንዳይኖረው እያወቀ ‹‹በሉ እንደ ልባችሁ ተናገሩ›› ሲላቸው ከነበሩት ጋርም አብሮ መቀጠል አልፈለገም፡፡ በመጨረሻም ‹‹ከእነዚህ ጫጫታ ጋር መሥራት አልችልም›› በሚል ዓይነት ተቃዋሚዎችን ገፈተረና ብቸኛ አሸናፊ የሚሆንበትን ሁኔታ አመቻቸ፡፡ ምክር ቤቱንም ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር ያዘው፡፡

በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች በኢሕአዴግና በፖለቲካ ድርጅቶቹ መካከል ቅራኔው እየከረረ ሄደ፡፡ ይህም ቅራኔ ኢሕአዴግን ጋሻ መከታ አድርገው የተቀመጡ ባለሥልጣናት ሕዝቡን ሲበድሉት እየናረ መጣ፡፡ ሙሰኝነት ሥሩን ተክሎ ተስፋፋ፡፡ ሙሰኞች ራሳቸው በአደባባይ ሙሰኝነትን እያወገዙ በተግባር ግን በዚያው አፀያፊ ተግባር ተዘፍቀው የሚዳክሩ ሲሆኑ ሃይ የሚል ጠፋ፡፡ ኢሕአዴግም ችግሩን መፍታት ሲገባው በቸልታ አየው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ድርጅታቸው በልዩ ልዩ መንገዶች ግንባር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የፈቀደላቸው፣ ምናልባትም እንዲዘርፉ የተፈቀደላቸው እስኪመስሉ ድረስ ሁሉንም ማግበስበስ ጀመሩ፡፡ ጨረታ የሚያሸንፉት እነሱ፣ የሚገነቡት እነሱ፣ የሚገዙት እነሱ፣ የሚሸጡት እነሱ፣ ለመሆናቸው ግልጽ ምልክቶች ታዩ፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች በልዩ ልዩ ከተሞች ጉምጉምታ ተከሰተ፡፡

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በአብደራፊ፣ በወልቃይት፣ በቅማንት ወረዳዎችና በአንዳንድ ቦታዎች በዘረኝነት የተሞላ እንቅስቃሴ ታየ፡፡ ‹‹ትግሬዎች ከክልላችን ይውጡ›› እስከመባል ተደረሰ፡፡ በደቡብ ትግራይም ‹‹የራያ ራዩማ›› አመለካከት ቀስ በቀስ ሥሩን እየሰደደ አድጎ ወደ ትግራይ የሚወስደውን አውራ መንገድ እስከ መዝጋት ተደረሰ፡፡ በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሞና በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተካሄደ፡፡ በአፋርና በአማራ መካከል ግጭት ተፈጠረ፡፡ ሌሎችም ግጭቶች አሉ፡፡ የመንግሥት እርሻዎች ተቃጠሉ፡፡ የግል ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ደረሰባቸው፡፡ ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ወጣ፡፡ በመሠረቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (ስፋቱና ምክንያቱ ሊለያይ ቢችልም) ባደጉ አገሮችም የሚታወጅበት ሁኔታ አለና ሰላምና ሥርዓት ለማስፈን ቢታወጅ ችግር የለበትም፡፡

ነገር ግን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የሚከተለው ምዕራፍ ምንድነው? እንደሚታወቀው ሁሉ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ‹‹ብሔራዊ እርቅ ወይም ብሔራዊ ድርድር›› የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረትና ያም የሽግግር መንግሥት ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጣ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ የት ይሂድ ቢባሉ መልስ የሚኖራቸው አይመስልም እንጂ ‹‹ኢሕአዴግ የሚባል ድርጅት አንይ›› የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ በአብዛኛው በፌስቡክ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ የሚሹ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የኢሕአዴግ መንግሥት ከራስ ወዳድነት ራሱን አላቆ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንና ለዚህም የሚመች ሁኔታ ከአሁኑ እንዲፈጠር የሚሹ ናቸው፡፡

የኢሕአዴግ ሦስት መንታ መንገዶች

ኢሕአዴግ የሽግግሩ መንግሥትን ለማቋቋም ብልህትን አሳይቷል፡፡ እንደ ኦነግ፣ እንደ ሲአንና ኦነግ የመሳሰሉትን በምርጫ ሰበብ ተቃዋሚዎቹን በአጋሮቹ ለመተካት ባደረገው ጥረት ወደ ብልጥነት ተሸጋግሯል፡፡ ተቃዋሚ ድርጅት በሌለበት ብቻዬን ልግዛ ሲል ደግሞ ራስ ወዳድነትን አሳይቷል፡፡ ብቻዬን ልግዛ ማለቱም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ተቃውሞ ሲያስነሳበት በኃይል ፀጥ ረጭ ለማድረግ ሳይፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመቀየር ተዘጋጅቷል፡፡

ዳሩ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተካ በኋላስ? ሥር ተከል በሆነ ዘዴ ራሱን አጠናክሮ በነበረው ሁኔታ ይቀጥላል? የጥገና ለውጥ ለማምጣት ይሞክራል? ወይስ ሕዝባዊ ጥያቄውን መሠረት አድርጎ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣል? ለማንኛውም በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ካካሄደ በኋላ በእነዚህ ሦስት መንታ መንገዶች ላይ ቆሟል፡፡ ከሦስቱ ግን አንዱን መምረጥ አለበት፡፡ አንዱን ለመምረጥ ግን ከራስ ወዳድነት ወደ ብልጥነት፣ ከብልጥነት ወደ ብልህነት፣ ከብልህነት ወደ ጥበበኝነት መሸጋገር ይኖርበታል፡፡ ወደ ጥበበኛነት ለመሸጋገር ምን መደረግ አለበት? ሦስቱን መንገዶች አንድ በአንድ ጠለቅ ብለን እንፈትሻቸው፡፡

ሥር ተከል ለውጥ የምንለው ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት የነበሩትን ፖለቲካዊ ድክመቶች እምብዛም ጠንከር ባላለ መንገድ ቀንሶ ለሚቀጥለው ማለትም ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ራሱን በማዘጋጀት፣ እንደገና በአሸናፊነት በመውጣትና እስከ 2017 ዓ.ም. ድረስ የገዥነቱን ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ አሁን የሚታዩት የሙስና አሠራሮችን ለውጫለሁ በማለት ከፍተኛ ሹም ሽር ሊያካሂድ ይችላል፡፡ ይህንም ሥር ተከል ለውጥ ለማምጣት ለተቃዋሚ ድርጅቶች መጠነኛ የፖለቲካ መብት በመልቀቅ እርሱ ግን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ በራሱ የመገናኛ ብዙኃን፣ በውጭ የመገናኛ ብዙኃን እየተጠቀመ ስላደረገው የጥገና ለውጥ ብሩክ ወቅዱስነት መስበክ ይጀምራል፡፡ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳይለሙም፣ እንዳይጠፉም ከመኮርኮም ባሻገር አሥጊ የሚመስለውን ድክመታቸውን እየፈለፈለ በማውጣት አመኔታ እንዳያገኙ ለማድረግ ሊሞክር ይችላል፡፡

ሌላው መላምት አስፈላጊ መስሎ ከታየውም ‹‹እውነታችሁን ነው፣ ብሔራዊ እርቅ መካሄድ አለበት›› ብሎ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት፣ የሽግግር መንግሥቱም ሕዝባዊ መንግሥት እንዲያቋቁም በመፍቀድ እርሱ ከውድድሩ ይወጣና ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኃይሎቹን በመጠቀም በሚመሠረተው መንግሥት ላይ እረፍት የለሽ ተቃውሞ ያደርጋል፡፡ በኢኮኖሚ አውታሮቹ ተጠቅሞ ልዩ ልዩ መሰናክሎችን ይፈጥራል፡፡ ሰው ሠራሽ ችግሮች እንዲፈጠሩና እንዲባባሱ ያደርጋል፡፡ በደርግ ጊዜ የተፈጠሩት የቅንቢቢት፣ የቂርቆስ፣ የቄራ፣ ወዘተ ማጅራት መቺ ቡድኖች ይፈጠሩና በሕዝቡ ዘንድ ፍርኃትና ሽብር ይነግሣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ‹‹ኢሕአዴግ ማረን›› ብሎ ወደ አደባባይ ይወጣል፡፡ አዲሱ መንግሥትም ከሥልጣኑ ይወርድና ኢሕአዴግ ወደ ነበረበት መንበር ይመለሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ሥር ተከል ለውጡን በበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ እንደዚህ ያለው ሁኔታ በምዕራባውያን አገሮች የተለመደ ሲሆን፣ በብዛትም እንደ ኢጣሊያና ግሪክ ባሉ አገሮች ይስተዋላል፡፡

ሁለተኛው መላምት ሕወሓት ከኦሕዴድ፣ ከብአዴንና ከደኢሕዴን በተጨማሪ እንደ ሱማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ያሉ አጋር ድርጅቶችን በማቀፍ ሚዛኑን እንዲጠብቅ በማድረግ አመራሩን አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ ሦስተኛው መላምት እስካሁን ድረስ ሲከተለው የነበረውን ግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር በመቀየር የጥገና ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ አራተኛው መላምት ከራስ ወዳድነት ወደ ብልጥነት፣ ከብልጥነት ወደ ብልህነት፣ ከብልህነት ወደ ጥበበኛነት ፈጥኖ ራሱን ማሸጋገር ነው፡፡

ኢሕአዴግ ከብልህነት ወደ ጥበበኛነት ራሱን እንዴት ያሸጋግራል?

በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመጥቀስ እንደተሞከረው ኢሕአዴግ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አንፃር ሲታይ በብዙ ነገሩ የተሻለ ነው፡፡ ስለሆነም ከብልህነት ወደ ጥበበኛነት መሸጋገር መቻል አለበት፡፡ ጥበበኛነት ደግሞ ከፖለቲካ ፍልስፍና ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካም እንዲህ ያለው ቀውስ ሲፈጠር በፍልስፍና የታገዘ ለውጥ በማድረግ ነገሮችን ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን እንደ እነርሱ በሀቅ ላይ ተመሥርቶ፣ የፖለቲካ መስኩን ሰፋ በማድረግ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ የሚካፈሉበትን፣ ተካፍለውም እንዳገኙት ድምፅ የምክር ቤት መቀመጫ የሚይዙበት፣ ይዘውም አስተሳሰባቸውን ያለገደብ የሚገልጹበት ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የደረሰበትን መጠነኛ ሽንፈት የሚመስል ነገር ቢገጥመውም፣ በሚቀጥለው ምርጫ የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ራሱን ማዘጋጀቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚችለው ደግሞ ሊበራል ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ካደረገ ወይም አስተሳሰቡን ይዘው የሚነሱትን ያገዘ እንደሆነ ነው፡፡

ኢሕአዴግ የጠባብነትና የዘረኝነት ፖለቲካ ተወግዶ ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍንም በሕዝቡ  እየተጠየቀ ነው፡፡ ይህን የሚጠይቁ ኃይሎችን በሌለ ጠላትነት፣ አሸባሪነት፣ አክራሪነት ወይም በሌላ ከመፈረጅ ይልቅ የሚጠየቀውን የእኩልነት ጥያቄ መመለስ፣ ክንዱን ተማምኖ ‹‹የታባታችሁ እንዳትደርሱ›› ብሎ ችግሮችን ከማዳፈን ይልቅ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመፍታት፣ በተቃዋሚዎች ላይ አሉባልታ እንዲነዛ ከማድረግ ተቆጥቦ ጥረታቸው በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት እስከሆነ ድረስ አብሬያቸው እሠለፋለሁ ብሎ በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርበታል፡፡

ከተቃዋሚዎች ምን ይጠበቃል?

ተቃዋሚዎችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ብለን የምንከፍላቸው እንደሆኑ ሁሉ፣ ፖለቲካዊ ሒደቱን በሚመለከትም በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ተቃዋሚዎች የሚሳተፉበት የብሔራዊ እርቅ ጉባዔ እንዲጠራና ይኼው ብሔራዊ እርቅ ጉባዔ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ፣ የሽግግር መንግሥቱም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዶ ሕዝባዊ ሥርዓት ማስፈን የሚፈልግ ነው፡፡ በመሠረቱ እንደዚህ ያለው ጥያቄ አሁን የተነሳ አይደለም፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የውጭ አገሮች ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፣ በሽግግር መንግሥቱ መቀመጫ አግኝተው የነበሩትን የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲባረሩ ያደረገ፣ አንዳንዶቹንም በፈቃዳቸው እንዲለቁ ያደረገ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ከ1997 ዓ.ም.  ምርጫው ጋር በተያያዘ በሌለበት የሞት ፍርድ እንዲፈረድባቸው ያስቻለ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የብሔራዊ እርቅ ጉባዔውን የመጥራት አስፈላጊነት እስካሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

መልካም ኢሕአዴግ ድርቅ ካለ አቋሙ ለዘብ ይበልና ሐሳቡን ይቀበለው እንበል፡፡ ለመቀበል ከሁሉ አስቀድሞ በጉዳዩ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ተቀርፆ መወያየት አለበት፡፡ በውይይቱም ዓለም አቀፍና ብሔራዊ አደራዳሪዎች ተካፋዮች ይሆናሉ፡፡ የውይይቱ ቦታም በተመረጠ ውጭ አገርና በአገር ውስጥ ይሆናል፡፡ በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ በጉባዔው ለሚሳተፉ አስፈላጊው የገንዘብና የጊዜ በጀት ይመደብለታል፡፡  ውይይቱ ላይ መግባባት ይደረስና የሽግግር መንግሥቱን ለመመሥረት የሚረዳ ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችል አዋጅ ይረቀቃል፡፡ የተረቀቀው አዋጅ በውሳኔ ሕዝብ ይፀድቃል፡፡ ለዚህም የገንዘብና የጊዜ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ የብሔራዊ እርቅ ጉባዔ ኮሚሽኑ ብሔራዊ የሽግግር መንግሥቱን ለማቋቋም የሚያስችል ቻርተር ማርቀቅና ይህንንም ቻርተር በብሔራዊ ሸንጎ አባላቱ ማስፀደቅ አለበት፡፡ ጉባዔተኞችና ታዛቢዎችን ከመላው ዓለም ለማንቀሳቀስ የገንዘብና የጊዜ በጀት መመደብ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ አለመግባባቶችና መጥመሞችን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ስንት ጊዜና ገንዘብ ይበቃዋል? በተለይ ገንዘቡ ከየት ይገኛል? ከመንግሥት በጀት፣ ከተባበሩት መንግሥታት? ወይስ ከማን?

የብሔራዊ እርቅ ጉባዔውን በገንዘብና በጊዜ ተመን አንፃር ስናየው ከሁለት ዓመት በላይ የሚጨርስ ከሆነ፣ ይህን ሐሳብ የማይደግፉት አገር በቀል የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄ ኢሕአዴግ የፖለቲካ መስኩን ለውድድር ነፃና ዴሞክራሲያዊ ያድርገውና ሁላችንም ተወዳድረን ውጤታችን በሕዝብ ድምፅ ይለይ የሚል በመሆኑ የተሻለ ሚዛን ይደፋ ይሆን? እንደ እውነቱ ከሆነ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መወያየትን ይጠይቃል፡፡

ጸሐፊው በልዩ ልዩ ሥራዎቹ እንደሚያቀርበው ግን ብሔራዊ የእርቅ ጉባዔ ጠርቶ የሽግግር መንግሥትም ሆነ ዘላቂ መንግሥት ማቋቋም ነባር ችግራችንን ይፈታዋል ወይ? ሌላ ተቃዋሚ እንዳይነሳ ቃል ይገባል ወይ? በታሪክ መፋለስ ምክንያት የተመሰቃቀሉ ችግሮቻችንን ይፈታል ወይ? በየትኛው ወረዳ የተገኘ ሰው ወይም የትኛው ብቃት ያለው ሰው የመሪነቱን ሥልጣን ቢያዝ በታሪካችን ጠባሳ ምክንያት መሪዬ ነው ብለን እንወስደዋለን ወይ? ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በየጊዜው መንግሥት እያፈረሰ፣ የሽግግር ጉባዔ እየጠራና አዲስ መንግሥት እየመሠረተ መቀጠል አለበት ወይ? ይህ ከሆነስ እስከ መቼ? ለምንስ ነባር ልምዳችንን ትተን ከፈረሰ ይልቅ ከተገነባው መቀጠል አንጀምርም?

በጸሐፊው እምነት የሚራመደው ፖለቲካ በፍልስፍና የተመሠረተ መሆን ይችላል፡፡ እርግጥ ነው የፖለቲካ ድርጅቶች ፍልስፍና ነፃዊነት (ሊበራሊዝም)፣ ማኅበረሰባዊ (ሶሻል) ዴሞክራሲያዊነት፣ ማኅበራዊ ጥገናዊነት (ሶሻል ሪፎርም)፣ ሥር ነቀልነት (ራዲካል)፣ ሶሻሊስት፣ ኮሙዩኒስት፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን በሚያቀርቡት ተጨባጭ የልማት ፕሮግራም ላይ የተመሠረተና በሕዝብ ምርጫ የሚወሰን መሆን አለበት፡፡ እነዚህ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች ምንድን ናቸው? ዕድሜ ከሰጠን ወደፊት የምንመለከታቸው ይሆናሉ፡፡ በሰላም እንሰንብት፡፡

አንባቢ – በተሾመ ብርሃኑ ከማል ጸሃፊውን  bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *