Adiss Zemen– መገናኛ አካባቢ የሚገኘው ሾላ ገበያ እንደወትሮው በተገበያይ ተጨናንቋል፡፡ በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያው ደርቷል፡፡ እንደ ቲማቲምና ጎመን የመሳሰለው ምርት በየጎዳናው ላይ ተዘርግቶ ለሸማቹ ቀርቧል፡፡ በዚህ አካባቢ ሸማቹ የሚፈልገውን ምርት ሲገበያይ ቢታይም፤ በአንፃሩ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን በሚያከፋፍሉ መደብሮች አካባቢ ያለው ድባብ ተቀዛቅዟል፡፡

ከተገበያዮች መካከል በአንዱ ሥፍራ ሻጭና ገዥ የሞቀ ክርክር ይዘዋል፡፡ የዘይትና የፈሳሽ ሳሙና ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአራት እስከ ስምንት ብር ድረስ መጨመር ያሳሰባት ሸማች፤ «በአገር ውስጥ ምርት ላይ ምን ተአምር ስለተፈጠረ ነው በአንድ ሳምንት በዚህ መጠን የሚጨምረው?» ስትል ነጋዴውን ብስጭት በቀላቀለው አንደበት ትጠይቃለች፡፡ እሱም «እኛ ምን እናድርግ ከመርካቶ ያመጣነው በውድ ነው?» በማለት ለማግባባት ይሞክራል፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት በለጠ ትባላለች፡፡ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን እርሷና ባለቤቷ የሚተዳደሩት በጎዳና ንግድ ላይ ነው፡፡ ከአከፋፋዮች አንዳንድ አልባሳትን ገዝተው በመሸጥ በሚያገኟት አነስተኛ ትርፍ ቤት ተከራይተው ይኖራሉ፡፡ ይሁንና ከወራት በፊት መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ ከቤት አከራይ ጀምሮ ሁሉም የንግድ ማህበረሰብ ከፍተኛ ዋጋ በመጨመሩ የእለት ጉርስ ለመሸፈን እንኳ ፈተና እንደሆነባት ነው የምታስረዳው፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት «በአሁኑ ወቅት ያልጨመረ ነገር የለም፤ በተለይ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚታየው ጭማሪ እስከዛሬ ታይቶ ከሚታወቀው በላይ ነው» ትላለች፡፡ የበርበሬና የሽሮ እህሎች ዋጋ ከሚጠበቀው በላይ መጨመሩን ትጠቅሳለች፡፡ «በኪሎ 70 ብር ይሸጥ የነበረው በርበሬ አሁን 130 ብር ሆኗል፤ በተመሳሳይ በባቄላና አተር ላይ ከ20 ብር ያላነስ ጭማሪ ታይቷል» በማለት ትናገራለች፡፡ በመሆኑም መንግሥት በህብረተሰቡ ላይ ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ገበያውን ማረጋጋት ይገባዋል፡፡
በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ የተሰማራው አቶ ፀጋዬ ብርሃኑ፤ በሸቀጣሸቀጥ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ጭማሪ ከወትሮ የተለየና የተጋነነ ነው፡፡ «ከሁለት ሳምንት በፊት 32 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና አሁን 38 ብር ገብቷል፤ ከዚህ ቀደም 10 ብር የነበረው ሳሙና አሁን 13 ብር ነው፤ በፓስታ ምርት ላይ እጥፍ ጭማሪ ታይቷል» ይላል፡፡
ምክንያቱን ሲያብራራ በዋናነት መርካቶ ውስጥ ያሉ አከፋፋዮችን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ «ግብር እና የውጭ ምንዛሪ ጨምሮብናል» በሚል በእያንዳንዱ ምርት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማድረጋቸውን ይጠቅሳል፡፡ በሌላ በኩል ግን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ‹‹መንገድ ተዘጋብን›› በሚል የሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል፡፡ ይሄም በሸማቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በእነርሱም ላይ ጭምር ጫና እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በገበያው ላይ የሚስተዋለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት በአፋጣኝ እልባት ሊሰጠው ይገባል ባይ ነው፡፡
አቶ ክንፈ አድማሱ የአትክልትና የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች አሏቸው፡፡ እርሳቸውም አንዳንድ አትክልት በገበያው ላይ በሚፈለገው መጠን ያለመገኘታቸው ምክንያት በአገሪቱ የተፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ከአከፋፋዮቹ የሚሰጣቸውም ምክንያት የመንገድ መዘጋትና የመጫኛ ተሽከርካሪ አለመኖር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ሆኖም ግን በአትክልት ምርቶች ላይ የሚታየው ጭማሪ ከሸቀጣሸቀጥ ምርቶች ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ እርሳቸውም ይሰማማሉ፡፡ «ከሳምንት በፊት 20 ፍሬ የሚይዘው አንዱ እሽግ ፓስታ 205 ብር ነበር ከአከፋፋዮቹ የገዛሁት፤ ዛሬ ግን 305 ብር መድረሱን ስሰማ መግዛቴን ትቼ ተመልሻለሁ» በማለት ይጠቅሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ነጋዴው የቤት ኪራይ መክፈል እስከሚያቅተው ድረስ መቸገሩን የሚጠቅሱት አቶ ክንፈ፤ በሰዓታት ልዩነት ያለገደብ በሸቀጣሸቀጥ ላይ የሚደረገው ጭማሬ ስላስፈራቸው እቃ ከማምጣት መቆጠባቸውን ይገልጻሉ፡፡ «የዋጋ ጭማሪው ስላማረረኝ እቃ ማምጣት አቁሜያለው፤ ሱቄም ባዶ እየሆነ ነው» ይላሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት በሸማቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በነጋዴውም ላይ እየተፈጠረ ያለውን ጫና ተገንዝቦ ገበያውን እንዲታደገው ነው የጠየቁት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ በሸቀጣሸቀጥ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ አራት ሺ 22 የንግድ ድርጅቶችን ማሸጉን የከተማዋ ንግድ ቢሮ ሰሞኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም የጠየቅናቸው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ፤ መንግሥት በጥቅምት ወር የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ በገበያው ላይ በፀረ ውድድር የንግድ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን የመከታተል ሥራ በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ምርትን በመገደብና በማከማቸት በመደበኛው የንግድ መስመር እንዳይሸጥ በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠርና ፍትሃዊ ያልሆነ ከፍተኛ ዋጋ በመወሰን ላይ የተሰማሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል፡፡ «በዋናነትም በአንድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋደዎች በስምምነት፣ በህብረት አቋም በመያዝ ፍትሃዊ ያልሆነ ዋጋ ወስነው ሸማቹን እያማረሩ ስለመሆናቸው ከህብረተሰቡ በደረሱን ተደጋጋሚ ቅሬታዎች 65 በላይ ድርጅቶች ላይ ክስ መስርተናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በባለስልጣኑ አስተዳደር ችሎት ላይ በክርክር ላይ የሚገኙ አሉ» ይላሉ፡፡ 
ህገወጥ ነጋዴዎች በፈፀሙት ፀረ ውድድር ተግባርና ፍትሃዊ ያልሆነ ተግባር ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከዓመታዊ ሽያጫቸው እስከ 10 በመቶ ቅጣት የሚጣልባቸው መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የንግድ ፍቃድ ከማገድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እንዲሁም እንደየጥፋታቸው መጠን ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ድረስ በእስራት እንደሚቀጡ ጠቁመዋል፡፡ 
በአሁኑ ወቅትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚከለክለውን በገበያው ላይ ጫና የመፍጠር ዝንባሌ እንደሚስተዋል ለባለስልጣኑ ጥቆማ እየደረሱት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተሰጠው ስልጣን መሰረትም በአገሪቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ተገን አድርገው ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው፤ ሸማቹ ህብረተሰብም እንደዚህ ያሉ ነጋዴዎችን በማጋለጥ ከባለስልጣኑ ጋር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ማህሌት አብዱል

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የኮቪድ ጽኑ ታማሚዎች ቁጥር መብዛቱ በዲላ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና አስከትሏል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *