Skip to content

የበርበራ ወደብ ጉዳይ የዓረብ ሊግ እንዲገባበት ጥሪ ቀረበ

ሶማሊያ ቅሬታዋን ኢትዮጵያ ማስተባበያዋን ያስተጋቡበት የበርበራ ወደብ የዓረብ ሊግ እንዲገባበት ጥሪ ቀረበሪፖርተር – የግዛቴ አካል ከሆነውና ራሱን ነፃ መንግሥት ብሎ ከሚጠራ አካል ጋር የተደረገ ስምምነት ሉዓላዊነቴን ተጋፍቷል በማለት ቅሬታውን ያሰማው የሶማሊያ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ከዱባዩ ዲፒ ወርልድ ኩባንያና ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የበርበራ ወደብ የባለድርሻነት ስምምነት ውድቅ እንዲደረግ ለዓረብ ሊግ ጥሪ አቀረበ፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊነትን የሚዳፈርም ሆነ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ስምምነት ሳይሆን፣ ሙሉ በሙሉ በኢኮኖሚና በንግድ ላይ ያተኮረ የወደብ ልማትና ተጠቃሚነት ስምምነት ማደረጉን ደጋግሞ ሲያስታውቅ ቢቆይም፣ የሞቃዲሾ መንግሥት ግን በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን ማብራርያም ሆነ ማስተባበያ ካለመቀበሉም በላይ፣ በፓርላማ ጭምር ስምምነቱን ውድቅ እንዳደረገው ይፋ አድርጓል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የዲፒ ወርልድ ግሩፕ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት ሚስተር ሱልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም፣ እንዲሁም ከሶማሌላንድ መንግሥት የውጭ ጉዳይና ከዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ከሳዓድ አል ሺሬ (ዶ/ር) ጋር ከሁለት ሳምንት በፊት በዱባይ ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ እንደያዘች ታውቋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት ኢትዮጵያ የ19 በመቶውን ድርሻ ለማስከበር ለአንድ ዓመት የዘለቀ ድርድር ማድረጓንና ድርድሩ በመሳካቱም ወጪና ገቢ ንግዷን የምታስናግድበት ተጨማሪ ወደብ ማግኘቷን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የዲፒ ወርልድ የቀድሞ ድርሻ 65 በመቶ የነበረ ስለሆነ ከዚህ ተቀንሶ ለኢትዮጵያ መሸጡን፣ የሶማሌላንድ መንግሥት በበኩሉ የ30 በመቶ ከወደቡ ድርሻ መያዙ ታውቋል፡፡

ወደቡን ዲፒ ወርልድ የሚያስተዳድረው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከባለድርሻነትና የወደብ ተጠቃሚነት በተጨማሪ፣ በበርበራ ኮሪዶር የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እንደሚያከናውን ታውቋል፡፡ ይህም የአገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያቀላጥፈው ሦስቱ አካላት በስምምነታቸው ወቅት አስታውቀዋል፡፡ ዲፒ ወርልድ ከወዲሁ ተጨማሪ የመርከብ መልህቅ መጣያ ግንባታ ሥራ መጀመሩም በስምምነቱ ወቅት ይፋ ተደርጓል፡፡

በሶማሊያ መንግሥት የቀረበበትን ተቃውሞ በማስመልከት የኢትዮጵያ መንግሥት በትራንስፖርት ሚኒስትሩ በኩል በሰጠው ምላሽ እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ፖለቲካዊ አጀንዳ ውስጥ የመግባት አካሄድ እንዳልተከተለ አብራርቷል፡፡ አቶ አህመድ ሰሞኑን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የሶማሊያ መንግሥትና ሕዝብ ወንድም ነው፡፡ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መስዋዕትነት በመክፈል፣ ደሙን በማፍሰስ አብሮ የታገለ ነው፤›› በማለት በሞቃዲሾ በኩል የቀረበው ቅሬታ አግባብ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም፣ መንግሥት በበርበራ ወደብ ባለድርሻነት የያዘው ለፖለቲካ ጥቅም ሳይሆን ለንግድና ለኢኮኖሚ ነው በማለት የመንግሥትን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡  

አቶ አህመድም ሆኑ አቶ መለስ ይህን ይበሉ እንጂ የግዛቴ አካል ከሆነው ሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ተገቢ ስላልሆነ ውድቅ ተደርጓል በማለት የመንግሥትን ማስተባበያ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተጨማሪም በሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ) የተመራ ልዑክ ወደ ኳታር ማቅናቱም ተሰምቷል፡፡

እንዲህ እየተካረረ የመጣው የሁለቱ አገሮች ፍጥጫ ምናልባትም የሞቃዲሾ መንግሥት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊወስደው ይችላል የሚሉ ሥጋቶችን ማጫር ጀምሯል፡፡ ስለዚህ ጉዳይም ሆነ የሶማሊያ መንግሥት ያሰማውን ቅሬታ እንዲያብራሩ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የጂኦ ፖሊቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ አበበ ዓይነቴ፣ ማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት ላለፉት 21 ዓመታት ራሱን የቻለ ነፃ መንግሥት ሆኖ ከቆየው የሶማሌላንድ መንግሥት ጋር በርካታ አገሮች ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ወታደራዊ ስምምነቶችና ግንኙነቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በርበራ ወደብ መግባቱን መቃወሙ ከፖለቲካ ቁጣ የዘለለ ነገር እንደማያስከትል የሚናገሩት አቶ አበበ፣ ይልቁንም ይህንን ያህል ጊዜ በዝምታ የቆየው የሞቃዲሾ መንግሥት አሁን ቅሬታ ማሰማቱ ምናልባትም ከጀርባው ውትወታ የሚያደርጉበት መንግሥታት ጫና ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ካበረከተችው አስተዋጽኦና አሁን ያለው መንግሥትም በኢትዮጵያ አማካይነት ሥልጣኑን እንደያዘ በመግለጽ፣ በወደቡ ሳቢያ የታየው መካረር ብዙም እንደማይዘልቅ አቶ አበበ አብራርተዋል፡፡

ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥበት በኢትዮጵያ ለሚገኘው የሶማሊያ ኤምባሲ ሪፖርተር ጥያቄ ቢያቀርብም፣ አምባሳደሩን ጨምሮ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ሞቃዲሾ በመሆናቸው ለጊዜው ምላሽ የሚሰጥ እንደሌለ ተገልጿል፡፡

የበርበራ ወደብን ለማልማት 442 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚደረግ ሲታወቅ፣ የሶማሌላንድ መንግሥትም ለ30 ዓመታት የሚቆይ ውል መፈራረሙም ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ምዕራፍ የግንባታ ሒደት ስምምነቱ ከተደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚጀመር፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም እንደሚጠናቀቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይሁንና የሶማሊያ መንግሥት የተቃወመውና የሶማሊያ የታችኛው ምክር ቤትም ውድቅ ያደረገው የሦስቱ ወገኖች ስምምነት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ፎርማጆን ውሳኔ እንደሚጠባበቅ እየተነገረ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥትንም ሆነ የፓርላማውን ሐሳብ በመቀበል ስምምነቱን ውድቅ ካደረጉት፣ ዲፒ ወርልድ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚደርስበት ጫና ምክንያት በርበራን ለቆ እንዲወጣ የሚያስገድደው ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡

ምስል መግለጫ – ከግራ ወደቀኝ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከዲፒ ወርልድ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሡልጣን አህመድ ቢን ሱላዬም፣ እንዲሁም ከሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሳዓድ አል ሺሬ (ዶ/ር) ጋር ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ መግዛቷን በማስመልከት በዱባይ ስምምነት ባደረጉበት ወቅት

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   Sisi warns Ethiopia against continuing to fill Nile Dam during visit to Sudan

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
ሶማሊያና ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ኩርፊያ ላይ ናቸው

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ የዐረብ ኤምሬትሱ ዱባይ ፖርትስ (Dubai Ports) ና ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብን በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም የደረሱበት ስምምነት ሞቃዲሾን አስቆጥቷል።...

Close