የቀጠና ስድስት ኮማንድ ፖስት የሚገኘው በአፋር ክልል ነው። እያደር የሚወጡ ዜናዎች ኮማንድ ፖስቱ አስተዳደራዊ ስራዎችን ሁሉ ጠቅልሎ መያዙን ነው። በቀጠና ተከፋፍሎ ኮማንድ ፖስት በወታደራዊ መኮንኖች እያስተዳደረ ይገኛል። ከስር ያለው የአዲስ ዘመን ዜናም ይህንኑ የሚያረጋገጥ ነው ። ሙሉ ዜናውን ከስር ያንብቡ

የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢና ወጪ ንግድ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሰላማዊነት ለማጠናከር በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ በአፋር ክልል የቀጠና 6 ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።  ኮማንድ ፖስቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕቅድ ላይ ከዞንና ከወረዳ የጸጥታ አካላት ጋር ትናንት በሰመራ ከተማ መክሯል።

በዕቅዱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የሰሜን ምስራቅ እዝ  የሕብረት ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ሀጎስ ገብረእግዚአብሔር የውጭና የውስጥ ጸረ ሰላም ኃይሎች የሕረተሰቡን ጥያቄ ለራሳቸው መጠቀሚያ እያደረጉት ነው።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ህገ-መንግስታዊ የፌዴራል ስርአቱን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው ፤ ይህን አፍራሽ ሴራቸውን ለማክሸፍና የሀገርና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ መውጣቱን ገልጸዋል።

አዋጁን ለማስፈጸም ዕቅድ ወጥቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የተናገሩት ኮሎኔል ሀጎስ፣ የሀገሪቱን ዋነኛ የገቢና ወጪ ንግድ የትራንስፖርት መስመር ሰላማዊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የዕቅዱ አንድ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚህም የሀገሪቱ እድገትና የተጀመሩ ልማቶች እንዳይደናቀፉ ከማገዝ ባለፈ አካባቢውን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም ከኤርትራና ጅቡቲ ህገወጥ የጦር መሳሪያና አሸባሪዎችን በማስገባት ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶችን የማክሸፍ ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከአጎራባች ክልሎች ጋር አልፍ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶችን የማጠናከር ሥራ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

“ለእዚህ ይረዳ ዘንድ በቀጠናው ስር አምስት ንዑስ ቀጠናዎች በተመረጡና ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ አካባቢዎች ይደራጃሉ”ብለዋል።

የጸጥታ ሥራውንም የሚመለከታቸው የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች፣ የሀገር ሽማግሌች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን ባሳተፈ አግባብ ለመስራት መታቀዱን አመልክተዋል።

የአፋር ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን አኒሳ በበኩላቸው የአፋር ህዝብ በፌዴራል ስርአቱ የተረጋገጠለትን እኩል የመልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በክልሉ አሁን ባለው ሰላም መዘናጋት ሳይፈጠር አስቸኳይ ግዜ አዋጁ ውጤታማ እንዲሆን የኮማንድ ፖስቱን ዕቅድ መነሻ አድርገው ለአካባቢው ሰላም ቀጣይነት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

” በጸረ ሰላም ኃይሎች የገቢና ወጪ ንግድ መስመር የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል በትኩረት ይሰራል” ብለዋል።

በተለይ ከአዋሽ እስከጋላፊ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች የጸጥታ ሥራውን ሕብረተሰቡን ባሳተፉ ሁኔታ ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ከዳሉል ወረዳ የመጣው የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡመር መሀመድ ወረዳቸው ከኤርትራ ጋር ድንበር የሚዋሰን በመሆኑ የአካባቢውን ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድርስ ህብረተሰቡን በማነቃነቅና የሕብረተሰቡን ባህላዊ መረጃ ልውውጥ በመጠቀም በአካባቢው የጸጉረ-ልውጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሃሪረሱ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳውድ መሃመድ በበኩላቸው “ገዳማይቱን አቋርጦ ወዴሃሪ-ረሱና አማራ ክልል ሊሸጋጋር የሚችለውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ለመቆጣጠር በአካባቢው ከኮማንድ ፖስት አካላት ጋር ተባብረን እንሰራለን” ብለዋል።

የፈንቲ ረሱ ዞን ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አረብ ዱፍና በበኩላቸው፣ ከአማራ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታትና  በሰላም የመኖር እሴት አንዲጠናከር የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መደረክ ላይ የፌዴራል ፖሊስና የሰሜን ምስራቅ እዝ መካላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ የክልሉ ፖሊስና ልዩ ኃይል እንዲሁም የዞንና የወረዳ አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በእነ ጃዋር የህክምና ጥያቄ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሁሉንም ተከራካሪዎች ጥያቄ ውድቅ አደረገ፤ ቃሊቲ ሆነው ይታከማሉ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *