ሐይሉ አባይ ተገኝ – 

ሀ) ህወሃት-ወያኔ በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት ነው!

ህወሃት-ወያኔ በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት ነው (State within a State/”Deep State” or Imperium Imperio)። ‘በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት’ ስንል በመንግስት መዋቅር ውስጥ በሚስጥር የተደራጀና ጭንብል ያጠለቀ መንግስታዊ የውስጥ አካልና ዋና አንቀሳቃሽ (Internal Organ) ሃይል ሲሆን፤

ይህም አካል የጦር ሃይሉን፣ የደህንነት ኤጀንሲውን፣ የውጪ ጉዳይ፣የሚስጥር ፖሊስን (Secret Service) የአስተዳደር አባላትን የሚቆጣጠረው ህወሃትን ለማመልከት ነው። ህወሃት እነኚህን የመንግስት አካላትን መቆጣጠሩ ኢኮኖሚውንና ፖለቲካዊን በብቸኝነት መቆጠጠር አስችሎታል። በፌበርዋሪ 26/2018 ፖስት ላይ ይህን አስፍሬ ነበር።

“ወታደራዊና የደህንነት መቃቅሩን፣ ፖለቲካዊ ስልጣንንና አኮኖሚያዊ የበላይነቱን ለራሱና በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ የያዘን አፓርታይዳዊ ወያኔን የስልጣን ዘመኑ እስካላከተመ በስሩ ለሚቆጣጠራቸው እነዚህ መንግስታዊ መዋቅሮች ፍፁም ታማኝነት (pledge allegiance) ለሌለው ወይም ለማይኖረው ግለሰብን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ከሾመ ስልጣኑን በፈቃዱ ለመልቀቅ ወስኗል ማለት ነው። ይህንን ካደረገም ህወሃት አምባገነን ሣይሆን ዲሞክራት ነበር ማለት ነው።

በህወሃት መዳፍ ስር ያሉት መንግስታዊ መዋቅሮች ሳይነኩና አፓርታይዳዊው ስርዐትና “የጎሣ ፌደራሊዝም’ ርዕዮቱ ሣይፈርስ፤ እንኳን እነ አቶ ለማ ወይም አቢይ ይቅርና፤ ክርስቶስ፣ ነብዩ መሃመድና ቡድሃ በጥምር (coalition) በህወሃት ስር በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢሾሙ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ ቀርቶ አይሞክሩትም። የሚኖራቸው ሚናም ህወሃት-ወያኔን በታማኝነት ማገልገል ብቻ ነው።

ፓለቲካው የዘነጋው ዋነኛ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የታጩት እነዚህ ግለሰቦች በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ሣይሆኑ፤ ህወሃት ከራሱ ጋር ተወዳድሮ 99.6% በማግኘት “ያሸነፈው” ምርጫ ማግስት የሾማቸው ናቸው። ህወሃት ከአምስት ሚሊዮን ያነሰ ህዝብ ከሚኖርበት ትግራይ መጥቶ ፓለቲካውን የሚዘውረው አብላጫ ህዝብ ቁጥር ካላቸው ጎሣዎች እኩል 45 ድምፅ ይዞ ነው። ወያኔ ፓርላማው፤ ፓርላማውም ወያኔ ነው!”

ለ). የተቃዋሚዎችና የህወሃት-ወያኔ የጋራ ዕጩ ጠቅላይ ሚኒስቴርና ዶ/ር አቢይ አህመድ በህወሃት-ወያኔ ‘በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት ውስጥ የሚኖራቸው ሚና

ሀወሃትና ተቃዋሚዎች ድጋፋቸውን ለዶ/ር አቢይ አህመድ ሲሰጡ የራሳቸው ፖለቲካዊ ቀመር አላቸው። ህወሃት በቅድሚያ ታማኝነት “ለኢህእዴግ መርሆዎች” ታማኝነት ያለው ሰው ብቻ በጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን በማያሻማ መንገድ ገልጿል። የህወሃት ምርጫ ዶ/ር አቢይ ናቸውና የታማኝነት ማረጋገጫ (pledge allegiance) ከርሳቸው አግኝቷል ማለት ነው። የዶ/ር አቢይን እጩነት ከግምት በላይ የህወሃት ሣይበር አርሚ ሲያራግብም ይስተዋላል። የተቃዋሚውም ጎራ ዶ/ር አቢይ “የተጀመረውን የጥገና ለውጥ” ከግብ ያደርሳሉ፤ ፍላጎታችን በዶክተሩ ሰር በማስረፅ ፖለቲካዊ ትርፍ እናገኛለን ሲሉ ፖለቲካዊ ስሌት በመስራት ስለዚህም “የኛን ሠው በቦታው ማስቀመጥ” ያስፈልጋል ሲሉ ድጋፍ ችረዋቸዋል። “አንድ ክብሪት አንድ ሚሊዮን ዛፍ ታቃጥላለች(ካርማ)” የሚለውን ብሂል ያለቦታው ሲደነቅሩ ይስተዋላል። አቶ ሃይለማርያም የህወሃት ሎሌ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ከህወሃት ሠዎች በዕውቀት አንሰው አይደለም። ለህወሃት በሠጡት የታማኝነት ማረጋገጫ (pledge allegiance) ሣቢያ ነው። የዶ/ር አቢይ አህመድ ከአቶ ሃይለማርያም የተለየ ተግባር ሊሰሩ ወይም ተዐምር ሊያሳዩን የማይችሉ መሆኑ የሚገባን እነዚህ እውነቶችን ስናጤን ነው።

1. ህወሃት የፈጠረውና የሚያሽከረክረው ፓርላማ 547 አባላትን ይዟል። ሁሉም አባላት የህዝብ ተወካዮች ሣይሆኑ የህወሃት ሹመኞች (appointee) ናቸው። የፓርላማውም ህግ ‘ማንኛውንም ውሳኔ ላማሳለፍ የ2/3ኛ ድምፅ ወይም 364 ድጋፍ ነው’ ይላል።

2. እነዚህ የፓርላማ አባላት ተብዬዎቹ ባለፉት 27 ዓመታት የህወሃትን የጭፍጨፋና የዘረፋ ወንጀል ሲደግፉና ሲያስፈፅሙ የኖሩ ከህወሃት ጋር ስልጣንን እና ጥቅምን ‘በእከክልኝ ልከክልህ (ኪዊክ ፕሮ ኮ’ የተጋቡና አስከፊውን የየካቲቱን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተጋድሎ ላይ ያፀደቁና ያወጁም ናቸው። በህዝብ ላይ የጦርነት አዋጅ ያስከተቱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የድምፅ አሰጣጥ እንመልከት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲፀድቅ በስብሰባው የተገኙት አባላት 441 ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ 345 አዋጁን የደገፉ፤88 የተቃወሙ፤7 ድምፅ ተዐቅቦ ያደረጉና ተደምረው ቁጥራቸው 441 ነው። በስብሰባው ቀን ያልተገኙ አባላት (absentee)106 ናቸው። ባጭሩ ለህወሃት ‘’የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ’’ ድጋፍ የሰጡ አባላት ቁጥር 346 ነው። ህወሃት የ2/3ኛ ድምፅ ድጋፍ የሚያስፈልገው በስብሰባው ካልተገኙት 106 አባላት ውስጥ 18 ብቻ ነው። ዶ/ር አቢይ ለውጥ ያመጣሉ የሚሉን በዚህ ፓርላማ አባላት ውስጥ ነው። ይደንቃል። ሌላው እንቆቅልሽ ዶ/ር አቢይ በሚኒስተርነት ወይም ለከፍተኛ ሥልጣን እንዲሾሙላቸው የሚያቀርቡትን እጩዎች የሚያፀድቀውም ይህ የህወሃት ፓርላማ መሆኑ ነው።

3. ብዙ ሠው የዘነጋው ነገር ይህ “ፓርላማና” ህወሃት-ወያኔ ያለመለያየታቸውን ይመስለኛል። ህወሃት-ወያኔፓርላማው፤ ፓርላማውም የህወሃት-ወያኔ ነው። ከህወሃት-ወያኔ ወደ “ፓርላማ አባላቱ”፤ “ከፓርላማ አባላቱ” ወደ ህወሃት-ወያኔ ተመለከትን። ልንገነዘብ የቻልነው ህወሃት-ወያኔ “ፓርላማ አባላቱን”፤ “ፓርላማ አባላቱም” ህወሃት-ወያኔ መሆናቸውን ብቻ ነው። እኛ ብንዘነጋም እነርሱ እራሣቸው በድጋሜ አስታወሡን። እንደገናም በሃገራችን ፖለቲካዊ ከባቢ ዓየር ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ህወሃት-ወያኔ፤ ከህወሃት-ወያኔ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብንመለከት የምንረዳው ጉዳይ ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህወሃት-ወያኔ በታማኝነት ከማገልገል ውጪ ሌላ ምርጫም ሆነ አማራጭ የሌለው መሆኑን ብቻ ነው።

ለማጠቃለልም እንኳን ዶ/ር አቢይ ወይም ሌላ ሰው ይቅርና፤ክርስቶስ፣ ነብዩ መሃመድና ቡድሃ በጥምር በህወሃት ሥር በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢሾሙ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ ቀርቶ አይሞክሩትም። የሚኖራቸው ሚናም ህወሃት-ወያኔን በታማኝነት ማገልገል ብቻ ነው።

በጥገናዊ ለውጥ ፍርፋሪ ከህወሃት ጠብ ይላል በማለት መጠበቅና በህዝብ ትግል፣ ደምና ሞት ላይ ከመቀለድና ውሃ ከማፍሰስ ወገብን አስሮ ለመሠረታዊ ለውጥ መታገልና ነፃነት፣ዲሞክራሲያዊና ሠብዓዊ መብቶች ተከብረው የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበትን አዲስ ህዝባዊ ሥርዐት ማለሙና ለዚሁም መፋለሙ የወቅቱ ጥያቄ ነው።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *