” ዋጋ ተከፍሎበታል” የሚል ግራ የሚያጋባ ጉዳይ በተደጋጋሚ ይሰማል። ሕዝብ በቃ ሲል፣ ሕዝብ ሲያምጽ፣ ሕዝብ ሲነሳ ” ዋጋ ተከፍሎበታል” የሚል ተረት ከህወሃት ደጋፊዎችና አፍቃሪዎች ይሰማል? የምን ዋጋ? ሌላው ጥይት ተኩሶ እንደማያውቅ፣ ሌላው ጨካኝ መሆን እንደማይችል፣ ሌላው አልሞ መምታት እንደማይችል፣ ሁሉም ጋር ብሶት ጀግኖችን እንደምይፈጥር፣ ብሶት ትግራይ ብቻ ተወልዶ በሌሎች አካባቢዎች የመከነ እስኪመስል መመጻደቅ… 

አሁን አሁን ነገሮች ሁሉ መስመር ስተዋል። ልጓሙ የተበጠሰ መኪና ገደል አፋፍ ላይ የመንዳት ያህል የአገራችን ሁኔታ እቋፍ ላይ ነው። መሪዎች ይሰበሰባሉ መፍትሄ የለም። ድርጅቶች ይገማገማሉ አይደማመጡም፣ ህዝብ ይናገራል የሚሰማ የለም። በአብዛኛው ሚዲያዎች በዚህ አሳሳቢ ወቅት በተራ ድጋፍና አሸርጋጅነት የታወረ ዘገባ ላይ ተተክለዋል። የገባቸው ያስጠነቅቃሉ፣ የመፍትሄው አካል መሆን ይፈልጋሉ፣ በሩ ግን ዝግ ነው። ከዚህ በላይ ምን ይምጣ? ምን ይፈጠር? ለዓመታት የሚንቀለቀል የቀውስ ፍም በጉያ ይዞ እስከመቼ?

 

ከተወለደ ቀናት የሆነው ህጻን እንደ አሞራ ተሰዶ ሜዳ ላይ ወድቋል። በሺህ የሚቆጠሩ ለጋ ታዳጊዎች አውላላ በረሃ ላይ አገር አላባ ሆነው ተበትነዋል። መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ በአገሩ መኖር እንደማይችል ተነገሮት እንደ ከብት በዚታዎ እየተጫነ ሜዳ ላይ ተዘርግፏል። ከየ አይነቱ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ታዳጊዎች፣አዛውንቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ቤተሰብ … ሞተዋል። ይህ ላለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ የሆነ፣ እየባሰ የመጣ፣ መቆሚያ የሌለው፣ ሁሉንም ዜጎች ያሳሰበ ችግር እንዴት ለመሪዎች አይታይም? እንዴት ይህ ችግር አያስደነግጣቸውም? አስገራሚ፣ አሳዛኝ፣ አሳፋሪ፣ ሲያስቡት ውለው ቢያድሩ መልስ የሌለው ጉዳይ!!

አንድ አገር በዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለቴ አስቸኳይ አዋጅ ስታውጅ ” ሰበር ዜና” የሚሉ የመንግስት ሚዲያዎችና አለቆቻቸው እንዴት ይሰፈራሉ? እንደው ለመሆኑ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መግባት ለአንድ የድርጅት ባሪያ፣ ለአንድ የድርጅት ጌታ፣ ለአንድ የድርጅት ሎሌ፣ ለአንድ የድርጅት… በምን መስፈርት ነው ድል ሆኖ ሰበር ዜና የሚሆነው? ለነገሩ መሰበርና ” ሰበር” በሁሉም የሚዲያዎች ሰፈር ሃፍረት የሌለው ርዕስ ሆኗል።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ሁሉንም ባይመለከትም በሚዲያው ዙሪያ እገሌ ከእገሌ ሳይባል ገብተን የምንቦራጨቅበት ሃፍረት ለሌላ ጊዜ ይቆይና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ። እንደው ኢህአዴግ ለሚባለው ድርጅት ” ሃፍረት” ምንድን ነው? ለካድሬዎቹስ ቢሆን ሃፍረት እንዴት ነው የሚገለጸው? አትደነግጡም? ህዝብ ውስጥ ስትገቡ ስትወጡ የምታዩት አያስጨንቃችሁም? አገሪቱ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አይታያችሁም? ለናንተ አስደንጋጭ፣ አሳሳቢ፣ እረፍት የሚሰጥ ጉዳይ ምንድን ነው?

ሕዝብ፣ ከሕዝብም ውስጥ ሃጻናት / ልክ እንደ እናንተ ልጅ/ በማያውቁት በረሃ ደጅ አልባ፣ ቤት አልባ፣ ቀዬ አልባ ሆነው ሲበተኑ፣ 600 ነበሰጡሮች ተሰደው ሜዳ ላይ ሲወድቁ አትደነግጡም? አይቆጠቁጥም? ከምንድን ነው የተሰራችሁት? በሰበስን፣ ገማን፣ ሸተትን እያላችሁ እርስ በርስ ስትነታረኩና የተሳዳጅ፣ አስዳጅ ድራማ ስትሰሩ ህዝብ ጠበቀ። በመታደስና በመበስበስ ሰበብ ሶስት አስር ዓመታት ሊያልፉ ነው። አይበቃም?

” ዋጋ ተከፍሎበታል” የሚል ግራ የሚያጋባ ጉዳይ በተደጋጋሚ ይሰማል። ሕዝብ በቃ ሲል፣ ሕዝብ ሲያምጽ፣ ሕዝብ ሲነሳ ” ዋጋ ተከፍሎበታል” የሚል ተረት ከህወሃት ደጋፊዎችና አፍቃሪዎች ይሰማል? የምን ዋጋ? ሌላው ጥይት ተኩሶ እንደማያውቅ፣ ሌላው ጨካኝ መሆን እንደማይችል፣ ሌላው አልሞ መምታት እንደማይችል፣ ሁሉም ጋር ብሶት ጀግኖችን እንደምይፈጥር፣ ብሶት ትግራይ ብቻ ተወልዶ በሌሎች አካባቢዎች የመከነ እስኪመስል መመጻደቅ…

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የደርግ ስርዓት ወደቀ። አወዳደቁ ላይ ብዙ ዓይነት እጆች እንዳሉ ቢታመንም ” እኔ ነኝ የጣልኩት” በሚል ተወራርዶ የማያልቅ ሂሳብ የሚጠየቀው እስከምቼ ነው? ይህንን ሂሳብ ለማወራረድ ሌሎች ለምን ይሰደዳሉ? ለምን ይሞታሉ? ለምን ይታሰራሉ? ” ዋጋ” ማለት ይህ ነው? አንድን ጨቋኝ ስርዓት ለመጣል የተደረገ ተጋድሎ መቼ ነው ግብሩ የሚያልቀው? እንዴት ነው የሚታሰበው? አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጊው፣ አፋሩ… ሁሉም ክልሎች በፈለጉት ድርጅትና ሰዎች ለመመራት የሚያቀርቡት ጥያቄና ” ዋጋ”ን ምን ያገናኛቸዋል። በምን አይነት ቋንቋ ህዝብ ይናገር?

ይህ ” ዋጋ” የሚባለው ነገር የሞያሌ ነዋሪዎችን ማፈናቀል ነው? አማራዎችን እየፈረጁ፣ መሬታቸውን መቀማት ነው? አገሪቱን ሁሉ እስር ቤት ማድረግ ነው? ኦርሚያን ወደ ማያቆም ቀውስ ማምራት ነው? ምንድን ነው? በተለያዩ አጋጣሚዎች ” ነጻ አወጣናችሁ” የሚባል ዲስኩርም አለ። የኢትዮጵያ ህዝብ በማን ቅኝ ግዢ ስር ነበር? ደርግ እኮ አገሩን የሚወድ፣ በባህሪው አምባገነን የሆነ ድርጅት እንጂ ቅኝ ገዢ አልነበረም። ጠለቅ ብለን ካየነው አሁን ይልቁኑ የቅኝ መገዛት ስሜት ጎልቶ የሚታይበት ጊዜ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ” እኩል ተጠቃሚነት” የምትለዋን አባባል ማድመጥና ማብላላቱ ጠቃሚ ይሆናል።

ሰሞኑንን የሚወጡ በረጃዎች ይዞታቸው አህጉር አቀፍ እየሆነ ነው። አስር ሺህ የሚጠጉ ዜጎቹን በረሃ በሰው አገር ያፈሰሰው ኢህአዴግ ስብሰባ የሚያቆም አይመስልም። የኬኒያ ሰዎች ጉዳዩ አሳሳቢ ነው እያሉ ነው። ተፈናቃዮቹም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። ይህ ችግር ኬንያን በተፈናቃዮች እንዳያጥለቀልቃት አስግቷል። አስር ሺህ የሚጠጉ ወገኖች በምግብ፣ መጠለያ፣ በመኝታ፣ በጤና፣ በመጸዳጃ ችግር ላይ ናቸው። ቢቢሲ እንዳለው 600 የሚጠጉ ነፍሰጡሮች አሉ። ከሰማንያ በመቶ በላይ ሴቶችና ህጻናት ናቸው። ይህንን ሁሉ ጉድ ተሸክመን ስብሰባ!! መፍትሄ የሌለው ስብሰባ!!

Related stories   አስከሬን እንዲለቀም ታዘዘ - ትህነግ የአጽም ፖለትካ ድራማ ይፋ ሆነ

ድፍን ህዝብ የሚጠይቀው ያለው የፓለቲካ ውሳኔ እንዲሰጥ ነው። ይህንን ራሱም ኢህአዴግም ያውቀዋል። ችግሩ ወንበር ነው። ወንበር!! ”አገር” አሉ አቶ አለማ መገርሳ ” የእኛ ስልጣን ከአገር አይበልጥም፣ ሲፈልግ ጥንቅር ይበል” ውድ ታጋዮች፣ መሪዎች፣ ጀግኖች፣ ሂሳብ አወራርጆች … በሁሉም ስፍራ ጩኽት አለ። በሁሉም ስፍር ችግር አለ። በሁሉም ስፍራ አድማ አለ። በሁሉም ስፍራ ” በቃኝ” የሚሉ አሉ። ይህንን ስሜትና ጥልቅ ፍላጎት በመሳሪያ ለማስቆም መሞከር በደም መዋኘት እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም። ህዝብ በቃኝ ካለ አለ ነውና።

ኢኮኖሚው ጣጣ ውስጥ ነው። በቤት ውስጥ መቀመጥ የተጀመረው አድማ መልኩን እየቀየረ ነው። የጦርነት ወሬም እየተሰማ ነው። ምሬቱ የሚታጀብባቸው የለውጥ ሂደቶች ወደፊት የሚወሳሰቡ ይመስላሉ። መፍትሄውን አሁን በ”ወርቃማው” ጊዜ ላይ ማፈላለጉ ግድ ነው። አለያ ኪሳራው ከባድ ነው። ጠበን እንበጣጠስም ይሆናል። የዛኔ ደረት ቢደቃ ዋጋ የለውም። ወደየትም መሸሽ አይቻልም። ስማችን፣ ሰላማችን፣ ኑሯችን፣ ማንነታችን፣ እየጎደፈ ነው።

መደማመጥ ግድ የሚሆነበት ግዜ ላይ ነን። ለማን ይነገራል? ማንስ ይሰማል፣ መፍትሄውስ ወዴት ነው? የሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢኖርም፣ አማራጩ መስማት ብቻ ነውና ስሙ!!አስር ሚሊዮን የሚጠጋ ረሃብተኛም አለን!! ለሚያስቡ ሁሉ ሃፍረታችን ብዙ ነው። የሚሳዝነው ግን ከሃፍረታችን ከምንወጣበት መንገድ ይልቅ ወደ ባሰ ቀውስ ለሚወስደን መንገድ ትኩረት መስጠታቸን ነው። እኔ ካልመራሁ ኢትዮጵያ ትደፋ!!

 
 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *