ዶ/ር አብይ አህመድ ኢህአዴግ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆኖ መምረጡን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ጮቤ ሲረግጡ ለመገንዘብ ችያለሁ። ለኢትዮጵያ ለውጥ ያመጣል ብላችሁ ተደስታችሁ ከሆነ ሃሳባችሁ እንዲሰምር ምኞቴ ነው። እኔ ግን ዶ/ር አብይ የመጡበት ወቅት ሳየው ኢህአዴግ አጣብቂኝ ውስጥ ስለገባ የማዕበሉ ማብረጃ ሊያደርጋቸው በመሳብ የሾማቸው ይመስለኛል። የኢህአዴግ መዋቅርና የፓርቲው አሰራር በቡድን በመሆኑ ዶ/ር አብይ የለውጥ ፈር ቀዳጅ ለመሆን ቢፈልጉም የሚሆንላቸው አይመስለኝም። ግምቴ የተሳሳተ ሆኖ እርሳቸው ለአገራቸው ለውጥ ማምጣት ከቻሉ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ዶ/ር አብይ አህመድ ውጤታማ እንዳይሆኑ ደንቃራ የሚሆነው ተቃዋሚው ኃይል ወይንም የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ህወሃት/ኢህአዴግ ነው። ህወሃት ዶ/ር አብይ እንዲመረጥ እንደማይፈልግ ግልፅ ነው። የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባውን በጊዜ መጨረስ ያልቻለው ለዚህ ነበር። ዶ/ር ደብረፂዮን ለግንባሩ ሊቀመንበር ለመሆን ተወዳድረው 2 ሰው ብቻ መረጣቸው የምትለዋ በራሷ ትልቅ መልዕክት ያላት ትመስላለች። ህወሃት የበላይ አይደለም የሚለው ለኢትዮጵያና ለአለም ማህበረሰብ ለማስረጃነት ለማቅረብ ይመስለኛል። ዶ/ር አብይ አህመድ መመረጡም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማደረጋቸውን ለምዕራባውያን ማታለያ ነች።

ዶ/ር አብይ አህመድ ለውጥ አራማጅ የሚሆን ከሆነ እኔ ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ ሊሰለፍ ይገባል። የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ግን የለውጥ ቃብድ በትረ-ስልጣኑ እንጨበጠ መጀመሪያ መውሰድ የሚገባው ተቀዳሚ እርምጃዋች አሉ።

1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአስቸኳይ ማንሳት
2. የፖለቲከኛ እስረኞች ሁሉም ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ መፍታት
3. ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የብሔራዊ እርቅ ጉባዔ እንዲዘጋጅ ሁኔታዎችን ማመቻቸት
4. የመከላከያ ሰራዊት አባላት ማህበረሰባችን ከሚኖርባቸው ቀዬ ለቆ በመውጣት ወደ ካምፓቸው እንዲመለሱ ማድረግ

ከላይ ከ1 እስከ 4 የዘረዘርኳቸው ሂደቶች በቀላሉ ማድረግ የሚቻሉትን በአስቸኳይ እየተገበሩና ለሌሎቹ ዝግጅት እየተደረገ ለቀጣይ እርምጃ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ዶ/ር አብይ አህመድ የህዝቡ ጥያቄ የስርዓት ጥገና ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት የሚወዳደርበት  ምሄራዊ ምርጫ እንዲካሄድ አስፈላጊ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል። በተግባር የሚታይ ለውጥ ማሳየት ካልቻሉ ህዝቡን ማረጋጋት ትልቅ ፈተና ነው የሚሆንባቸው። ስለዚህ ህዝቡን ለማረጋጋት ይረዳ ዘንድ የሚከተሉት ቀጣይ እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

1. ከተዋሚና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ገለልተኛ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም
2. በውስጥም በውጭም የሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ መድረኩ ክፍት በማድረግ ብሄራዊ ምርጫ በአስቸኳይ ማድረግ
3. ቀጣይ በሚደረጉ የለውጥ ሂደቶች የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጡ አካል እንዲሆን ለማስቻል ማወያየት፤ ከማህበረሰቡ የሚመጡ ጥያቄዎች አንጥሮ ማውጣት
4. ላለፉት 27 ዓመታት በስርዓቱ የተገደሉት ዝርዝራቸውን በመልቀም ለቤተሰቦቻቸው ይቅርታ መጠየቅ፤ ተገቢውን ካሳ መክፈል፤ ነፈሰ ገዳዮቹን ለፍርድ ማቅረብ
5. ለ27 ዓመታት በዚህ ስርዓት በግፍ የታሰሩትና ታስረው ለተፈቱት የፖለቲካ/ህሊና እስረኞች ይቅርታ መጠየቅ፤ ተገቢውን ካሳ መክፈል
6. ስርዓቱ በሚያደርሳቸው የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ችግሮች ምክንያት በተነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በማሳበብ ደህንነቱ በላካቸው ቡድኖች ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ፤ ካሳ መክፈል፤ የደህንነት ነውጠኞች ለፍርድ ማቅረብ
7. በኦሮሚያና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የውርስ መሬታቸው በግፍ ለተነጠቁ ሰዎች ተገቢውን ካሳ መክፈል፤ መሬታቸው መመለስ የሚቻለውን መመለስ
8. በሙስና ሃብታቸውን ያካበቱ ግለሰቦችና ባለስልጣናት ሀብታቸውን በመቀማት ለአገሪቷ ገቢ ማድረግ፤ ለፍርድ ማቅረብ
9. ህግ-አውጪው፣ ህግ-አስፈፃሚውና ህግ-ተርጓሚው አካል ነፃና ገለልተኛ ማድረግ
10. ህገ-መንግስቱን ማሻሻል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወያይቶበት ከምርጫ በኋላ በሚመሰረት ስርዓት እንዲፀድቅ ማድረግ። ለምርጫው የሚሆን ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጠቅላላ ሂደቱን ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ ጊዜያዊ ሰነድ ማዘጋጀት።
11. እስከዛሬ በስርዓቱ በመጠለል በኢትዮጵያ ህዝብ በደል ሲፈፅሙ የነበሩ አካላት አማራሮችና የበላይ መሪዎች ለፍርድ ማቅረብ።

ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ መሪ በሚያስፈልጋት ወቅት እድሉ ገጥሟቸው ስልጡ በእጃቸው ገብቷል። ወጥ ለራስህ ስትል ጣፍጥ ካልሆነ… እንደሚባለው ሆነው ከመጣላቸው በፊት ህዝብ የማረጋጋትና በለውጥ ጎዳና የመምራቱ ሂደቱ በአስቸኳይ መጀመር ይኖርባቸዋል። ከህወሃት ለሚደርስባቸው ጫናዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ድምፅ የተመረጡ ባይሆኑም የተግባር ስራ መስራት ከቻሉ ለውጥ ፈላጊ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።

በመጨረሻም፦

በእኔ እምነት የዶ/ር አብይ መመረጥ ምንም ሊያዘናጋን አይገባም፤ ትግላችን የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ወንበር በሌላ ግለሰብ መተካት ሳይሆን የስርዓት ለውጥ መሆን አለበት ባይ ነኝ። የስርዓት ጥገና ሳይሆን የስርዓት ለውጥ… የስርዓት ለውጥ… ልድገመው የስርዓት ለውጥ መሆን አለበት ባይብነኝ።

(ሥዩም ወርቅነህ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *